>

በየሳምንቱ በጉራፈርዳ፣ በወለጋ በገፍ ለተፈጁ ወገኖቻችን ማነው ሃላፊነቱን የሚወስደው?  (ያሬድ ሀይለማርያም)

በየሳምንቱ በጉራፈርዳ፣ በወለጋ በገፍ ለተፈጁ ወገኖቻችን ማነው ሃላፊነቱን የሚወስደው? 

ያሬድ ሀይለማርያም

ይህ በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መቆሚያውስ የትና መቼ ነው?
የዛሬ ሁለት አመት በወርሃ ጥቅምት መንግስት ከኦነግ ጋር የጀመረው እሽኮለሌ አላምር ቢለኝ “ኦነግን እንደ ስለት ልጅ ማቅበጡ ይቁም” በሚል ርዕስ አጭር ስጋቴን ያዘለ መልክት ጽፌ ነበር። ከዚህ በታች ታገኙታላችሁ። ባለፉት ሁለት አመታት ትጥቁን ባልፈታው የኦነግ ሰራዊት እና በሚመራው መንጋ የተጨፈጨፈውን ሰው ብዛት ቤት ይቁጠረው። ለዚህ ጥፋት እና ሰብአዊ ቀውስ ከኦነግ ጀርባ ያለው ህውሃት ብቻ ሳይሆን ኦነግን አቀማጥላለሁ ብሎ ለሕዝብ እልቂት ምክንያት የሆነው የአብይ አስተዳደርም እኩል ተጠያቂ መሆን አለበት። አላባራ ያላለውን የሕዝብ እልቂት ማስቆም ያቃተው የአገዛዙ ስርዓት ለሚደርሰው ሰብአዊ ቀውስ እና የከፋ የመብት ጥሰት ተጠያቂ ነው። መሀል አገር ላይ ኮማንዶ እያስመረቁ ዳርዳሩን ቆሞ ማስፈጀት ምን ይሉታል?
ኦነግን እንደ ስለት ልጅ ማንቀራበጡ ይብቃ!
 ——————
መንግስት ከኦነግ ጋር ያደረገውን ስምምነት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለበት!
የኦነግ መሪ የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዋልታ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ድርጅታቸው ትጥቅ አለመፍታቱን፣ መፍታትም እንደማይፈልግ፣ ፈታ መባልም እንደማይፈልግ እና በዚህ ደረጃ ከመንግስት ጋርም ስምምነት ያደረጉ የሚመስል መግለጫ ሰጥተዋል። ቃል በቃል ለመጥቀስም “ትጥቅ መፍታት የሚባል ነገር በጣም ሴንሲቲቭ ጥያቄ ነው፤ ኦነግ ትጥቅ አልፈታም፣ መፍታትም አይፈልግም፣ ፈታም መባል አንፈልግም … ማን ትጥቅ ፈቺ፣ ማንስ ትጥቅ አስፈቺ ሊበል ነው”። በእርግጥም መንግስት በዚህ መልኩ ከሆነ ከኦነግ ጋር ስምምነት ያደረገው በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ እየተፈጸሙ ላሉት ዘር ተኮር ግጭቶች በድርጅቱ ላይ እየቀረቡበት ያሉት ውንጀላዎች በአግባቡ ሊመረመር ይገባል። በዚህ እረገድ መንግስትም ተጠያቂ ከመሆን አይድንም።
በመጀመሪያ ሌሎቹን የትጥቅ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈተው እና እዛው አስመራ አስቀምጠው እንዲገቡ ያደረገ መንግስ ለኦነግ እንዲህ ያለ የተለየ ፈቃድ እና መብት መስጠቱ እጅግ የሚያስገርም እና የመንግስትን አካሄድም መርህ አልባ ያደርገዋል።  እንዲህ ያለው ወጥ ያልሆነ አሰራር ከምን የመነጨ ነው? ኦነግን ከመፍራት? ወይስ ኦነግ ከጀርባው ያሰለፈውን እና መስቀል አደባባይን ያጥለቀለቁትን ደጋፊዎቹን በመፍራት? ለነገሩ የኦነግ ሰራዊት ወደ አገር የገባው ገና የአስመራዊ ድርድር ሳይካሄድ በፊት ነበር። ሰራዊቱ ቀድሞ ገብቶ በተወሰኑ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ ቦታ ይዞ ሲዘዋወር እና አንዳንድ ቦታዎችም ዝርፊያ ይፈጽም እንደነበር በመንግስት ሚዲያ ጭምር ተገልጿል። ሰራዊቱ በየከተማው ገብቶ ከተቀመጠም በኋላ ነው በአቶ ለማ የሚመራ የመንግስት ለዑክ አስመራ ሄዲ ከድርጅቱ መሪዎች ጋር ድርድር ያደረገው። ሠራዊቱ በአንዳንድ ስፍራዎች ላደረሳቸው ጥቃቶች ዛሬ ሰራዊታችን በየስፍራው አለ የሚሉን የድርጅቱ መሪዎች የኛ ሰራዊት አይደለም ብለውም እንደነበር አስታውሳለሁ።
መንግስት ኦነግን ጨምሮ ከሌሎቹ የትጥቅ ድርጅቶች ጋር ያደረገውን ስምምነት በተመለከተ ሕዝብ የማወቅ መብት ስላለው ዝርዝር የድርድር ሃሳባቸውን ይፋ ማድረግ አለበት። በተለይም ኦነግ ሰራዊቱን ብቻ ከነትጥቁ ማስገባቱ ሳያንሰው በአንድ ካምፕ ውስት ተወስኖ እንዲቀመጥ አለመደረጉ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ እና አዋሳኝ ክልሎች እየታየ ላላው ግጭት እና መፈናቀል እጁ ሊኖርበት እንደሚችል በረካታ ማስረጃዎች እና ጥቆማዎችም ለመንግስትም እየቀረቡለት ቆይተዋል። ከቡራዩም ጥቃት ጀርባ ይህ በየሜዳው የተበተነ የድርጅቱ ሰራዊት እጅ እንዳለበት አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ነው።
የመንግስት ባለስልጣናት ዶ/ር አብይን ጨምሮ ድርጅቱን እና ባለስልጣናቱን በስም መጥራት ትተው በገደምዳሞሽ አንዳንድ ቡድኖች እያሉ የሚያቀርቡትን ዛቻ እና ማስፈራሪያ አቁመው ባፋጣኝ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እና በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ማድረግ አለባቸው።
በአንድ አገር ውስጥ በምን ሂሳብ ነው ሁለት የተለያየ ጦር ሊንቀሳቀስ የሚችለው። አቶ ዳውድ ኢብሳ እንደተናገሩት ከሆነ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ሰራዊታችን ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል። ይች አባባላቸው የአቶ ጃዋርን ሁለት መንግስት ነው ያለው የምትለዋን የምታጠናክር መሆኗ ነው። ይህ አይነቱ አካሄድ
– አሁነም በቡራዩ የተፈጸመው እልቂት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ መጠየቃችንን አናቆምም፤ ከዚህ እልቂት ጀርባ መንግስት ስማቸውን ሊገልጻቸው ያልፈለገው የተደራጁ የተባሉት ኃይሎች በየሜዳው የፈሰሱት የኦነግ ሰራዊት አባላት ላለመሆናቸው ምንም ማስተማመኛ የለም። በማህበረ ድረ ገጾች የተለቀቁ አንዳንድ ቪዲዮዎች በግልጽ የሚያሳዩት በአንዳንድ ሥፍራዎች የኦነግ ታጣቂዎች የሰዎችን ቤት እየሰበሩ እየገቡ ንብረት ሲዘርፉ ያሳያል። ታጣቂዎቹ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች እና የድርጅቱን ምልክቶች የያዙ መሆናቸው ተስተውላል።
– በቤኒሻንጉል ጉምዝ በቅርቡ በተቀሰቀሰው እልቂትም ጀርባ ይህ ድርጅት እጁ እንዳለበት የክልሉ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ለቪኦኤ ገልጸዋል።
– የመንግስት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩም ቀን ወቶላቸው ትላንት በሰጡት መግለጫ መንግስት ግጭቶቹን ለማብረድ ተገቢውን ሥራ እየሰራ እንዳልሆነ በመግለጽ ስጋታቸው ገልጸዋል።
– ኦነግን ለምን ፈራችሁት? ኦነግስ ለምን እንደሌሎቹ የትጥቅ ድርጅቶች በለውጡ እና በመንግስት ላይ እምነት አጣ?
– ከኦነግ ጋር በቂ የሆነ መተማመ ላይ እስኪደረስ ድረስ ለምን ድርጅቱ እዛው አስመራው አይቆይ አይደረግም ነበር? እንዴት በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚወቀስ የኦነግ አይነት ድርጅት ከነ ትጥቁ ወደ አገር ገብቶ ከሕዝብ ጋር እንዲቀላቀል ተደረገ?
መንግስት ከኦነግ ጋር ያለውን እንዲህ ያለ መርህ አልባ እና ቅጥ አንባሩ የጠፋ ግንኙነት ባፋጣኝ ሊያቆም ይገባል። የኦነግ ሰራዊት ትጥቁን እንዲያስረክብ እና ወደ ካምፕም እንዲገባ ደጋግመን ስናሳስብ ቆይተናል። ዛሬም ‘ይቺ ባቄላ ካደረች …’ ማለታችንን አናቆምም።
Filed in: Amharic