>

እነ እስክንድር ነጋ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለአለም ለማሳየት የርሀብ አድማ ጀመሩ ...!!! (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ)

እነ እስክንድር ነጋ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለአለም ለማሳየት የርሀብ አድማ ጀመሩ …!!!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች ማለትም አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወይዘሮ አስቴር ስዩም እና ወይዘሪት አስካለ ደምሌ ከዛሬ ሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የርሃብ አድማ ያደርጋሉ። አመራሮቹ አድማውን እያደረጉ ያሉት ፍርድ ቤቱ ሆን ብሎ እጅግ የተራዘመ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን በመቃወምና በአጠቃላይ ፍትህ ስላጡ ነው። ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት ይሰጣቸው የበሩ የቀጠሮ ጊዜያት በቀናት ወይም በሳምንት ጊዜ ውስጥ የተገደበ ሲሆን ሰሞኑን የሰጠው ቀጠሮ ግን ለአንድ ወር ከ20 ቀናት ወደ ፊት የተራዘመ ነው፡፡
እነእስክንድር ለመጭው ሀገራዊ ምርጫ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቅሰው ሂደቱ እንዲፋጠንላቸው አመራሮቹና ጠበቆቻቸው ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ አልቀበልም ማለቱ ይታወሳል፡፡
በጊዜያዊነት ከቆዩበት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ከተወሰዱ በኋላ መፅሐፍት፣ ጋዜጦችና መፅሔቶች እንዳይገቡላቸውም ተከልክለዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ቤተሰቦቻቸው ያነጋገሯቸው የወህኒ ቤቱ የሥራ ሓላፊ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳልተቀበሉ ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ቆየት ብሎ ደግሞ መፅሐፍትም ሆኑ ሌሎች የሕትመት ውጤቶች ሳንሱር ተደርገው እንደሚገቡላቸው ጠቅሰው መፅሐፍት፣ ጋዜጦችና መፅሔቶችን ቢቀበሉም ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከእስረኞች አልደረሰም፡፡ ከሦስት ሳምንታት በላይ በዚያው ሲቆይ ሳንሱር ሳያልፍ ቀርቶ የተመለሰም የለም፡፡ እነኝህና መሰል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በሕግ የተፈቀደ ቢሆንም ከሌሎች እስረኞች ተለይተው እነእስክንድር በደል ይፈጸምባቸዋል፡፡
እነ እስክንድር ነጋ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ እና በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩ መደረጉንም በጥብቅ እየተቃወሙ ነው።
 ጋዜጠኞች በሌላ ክፍል ተቀምጠው የምስክሮችን ቃልና የቀረበላቸውን መስቀለኛ ጥያቄ እንዳይከታተሉም ተገደዋል፡፡ በደፈናው ከመዘገብ ባለፈ ዝርዝር ነገሮችን እንዳይዘግቡ ማዕቀብ መጣሉም አግባብ አለመሆኑን የባለደራስ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ ገልፀዋል፡፡
ክሱ ብሔርና ሃይማኖትን መሰረት አድርገው ከተፈፀሙ ጥቃቶች በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ የክርክሩ ሂደት ሙሉ በሙሉ በግልፅ ችሎት እንዲካሄድም ጠይቀዋል፡፡ በአጠቃላይ በእነእስክንድር ላይ የተመሠረተው ክስ ፖለቲካዊ  በመሆኑ የሀሰት ውንጀላ በመሆኑና ፍትህ ስለጎደለባቸው ከዛሬ ጀምሮ ረሀብ አድማ እንዲያደርጉ ተገደዋል።

መላው ኢትዮጵያዊ የነዚህን ንፁሀን ትግል ሊደግፍ ይገባል ።

Filed in: Amharic