>
5:13 pm - Tuesday April 18, 0045

ለአገራችንና ለሕዝባችን ኅልውና በአንድነት እንቁም!!!! (የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) 

ለአገራችንና ለሕዝባችን ኅልውና በአንድነት እንቁም!!!!

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) 

ሕወኃት በአማራ ሕዝብ ላይ ያለው ጠላትነት ከውልደት እስከ ሞት ድረስ ነው። በዚህ መካከል በሕወኃትና ጀሌዎቹ አማካኝነት የአማራ ሕዝብ የከፈለው ዋጋ ዘግናኝ ነው፤ አሁንም ቀጥሏል። ሕወኃት በሕዝባችን ትግል ተሸንፎ ከማዕከል ቢገፋም የትግራይን ሕዝብ ሰብአዊ ጋሻ በማድረግ የሽብር ስራውን ዛሬም ቀጥሏል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) ሕወሀት የሽብር ድርጅት ተብሎ እንዲፈረጅ ጥያቄዉን ከ2 አመታት በፊት በይፋ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል። አብን በምርጫ መራዘም ጉዳይ መንግስት መር ሽግግርን የመረጠው በዋናነት ሕወኃትና ጀሌዎቹ ቅንጅት ፈጥረው አገራችንን ለዳግም የጥፋትና የአፈና ዘመን እንዳይዳርጓት በሚል ነበር። በሂደት መንግስት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥያቄ ባግባቡ ሳይመለስ በመቆየቱ ሕዝባችን በቋሚነት ተለይቶ እንዲጠቃ ሆኗል፡፡ ይህ በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ጥቃትም የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን የኢፌዲሪ የተወካዬች ምክር ቤት ዘግይቶም ቢሆን አረጋግጧል።
ይህ በሕዝባችን ላይ ለተፈፀመውና እየተፈፀመ ለሚገኘው የዘር ማጥፋት ወንጀል መነሻና አሁንም ግንባር ቀደም ተዋናዩ ሕውኃት ዛሬም አማራውን ግንባር ቀደም ጠላት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው ኃቅ ነው።
ትሕነግ/ሕውኃት ትላንት ለሊት በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ካምፕ ላይ እና በአማራ ክልል ዳንሻና ሶሮቃ በኩል ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ መንግሥት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል። ሕውኃት ዛሬም የአማራ ጥላቻ ያልበረደለት ለመሆኑ አብይ ማሳያው ትላንት በጀመረው ጥቃት መጀመሪያ የተኮሰው በአማራ ሕዝብ ላይ በዳንሻ/ቅራቅር/ አካባቢ ነው።
ስለሆነም አሁን በመንግስት በኩል በሕውኃት ላይ የሚወሰደው የሕግ ማስከበር ስራ ፍፃሜ እንዲያገኝ ሕዝባችንን ማስተባበር ያስፈልጋል። የአማራ የጸጥታ ኃይል የሕዝባችንን አጠቃላይ ደኅንነት እንዲጠብቅ፣ በትግራይ አዋሳኝ የምትገኙ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የራያ አካባቢ አማራዎች ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆምና በፀጥታ ኃይሉና በመንግስት የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመቀበል ራሳችሁንና አካባቢያችሁን እንድትጠብቁ አብን ያሳስባል።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችና ከክልሉ ውጭ በሚገኙ አማራዎች ላይ ትሕነግ/ሕውኃት የሽብር ጥቃት ሊፈፅም ስለሚችል አማራዊ አንድነታችሁን በማጠናከርና መረጃ በመለዋወጥ ብሎም ከየአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ራሳችሁንና አካባቢያችሁን እንድትጠብቁ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
የአማራ ወጣቶች፣ ሲቪክ አደረጃጀቶች፣ አክቲቪስቶችና የአማራ ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ወገኖቻችን በተለያዩ አካላት ከሚለቀቁ ሕዝባችንን ከሚያሸብሩ የሐሰት መረጃዎች በመቆጠብ በተለይም የእምነት ተቋማቶችን በልዩ ንቃት በመጠበቅ፣ አጠራጣሪ ነገሮች ሲታዩ ለጸጥታ ኃይሉ በፍጥነት ሪፖርት በማድረግ ለሕዝባችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ እንጠይቃለን።
ሁሉም የክልል መስተዳድሮች በክልሎቻቸው የሚገኙ ዜጎችን ደኅንነት ከመቸውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንዲጠብቁ ጥሪ እናቀርባለን።
መላዉ የኢትዬጵያ ሕዝብ የሕወኃትን የሽብር ቡድን በሕግ ጥላ ስር ለማዋል በሚደረገው እንቅስቀሴ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪያችንን ለማቅረብ እንወዳለን።
በሕዝባችን ላይ የተዘራው የጥላቻ ትርክት ከአገራችን ላይ ድባቡ የሚገፈፍበት ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ በአገራችን ላይ ለዘመናት ያጠላው ችግር ተገፍፎ ዜጎች በአገራቸው ውስጥ በሰላም፣ በእኩልነትና በፍትኃዊነት መኖር የሚችሉበት ምእራፍ እንዲከፈት ሁሉም አካል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የሕውኃት የአፈና አገዘዛ ሰለባ ሆኖ የቆየው ወንድም የሆነው የትግራይ ሕዝብም ነፃ ወጥቶ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በሰላምና በፍቅር በየእለቱ የሚገናኝበት በር እንዲከፈትለት ከመከላክያ ኃይሉ ጎን በመቆም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት የሕወኃትን የሽብር ቡድን በሕግ የበላይነት ስር ለማዋል በሚያደርገው እንቅስቃሴ መላው ኢትዬጵያውያን ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
Filed in: Amharic