>
5:18 pm - Sunday June 16, 7252

እነዚያ አብይን በሠይፍ የሚጠብቁት ስውር እጆች የማን ናቸው? (አሰፋ ሀይሉ)

እነዚያ አብይን በሠይፍ የሚጠብቁት ስውር እጆች የማን ናቸው?

አሰፋ ሀይሉ


‹‹ምክንያቱን ምን እንደሆነ ለይቼ መናገር አልቻልኩም፣ ግን አብይን የተጠጉ ሁሉ ተቀስፈው ነው የሚቀሩት፣ እርሱን ካገኙ በኋላ የቀድሞው እነሱ አይሆኑም፣ ወይ ይለውጣቸዋል፣ ወይ ይሞታሉ!›› 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሥርዓቱን ከማወደስ ወጥተው ሥርዓቱን ወደ መንቆርና ወደ ማጋለጥ ሀቀኛ ተግባራቸው በተመለሱ በቀናትና ሳምንታት ልዩነት – ዝርዝሩ ባልተገለጸ እንግዳ አኳኋን በቤታቸው ካለ ሰው እርሳቸው ብቻ በ‹‹ኮሮና›› ወረርሽኝ ተይዘው ሞቱ ተባለ፡፡ ዕድሜያቸው ስለገፋ ሞታቸውን ‹‹ለምን?›› ብሎ የጠየቀ አልነበረም፡፡ በቁማቸው የዘለፏቸው ሁሉ አጋፋሪ በሆኑበት ሽኝት፣ ከፍ ባለ ክብር ተቀበሩ፡፡

ከእርሳቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ደሞ የኦሮሞን ታሪክ አጥንተው ዶክትሬታቸውን የሠሩት የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው ‹‹ስለ አኖሌ የሚነገረው ታሪክ ውሸት ነው!›› ብለው የአኖሌን የተቆረጠ ጡት ሐውልት የሐሰት ሸፍጥ ባጋለጡ በቀናት ልዩነት ውስጥ ጀርመን ሀገር ድንገት መሞታቸው ተሰማ፡፡ ቤተሰባቸው ሲጠየቅ

‹‹ዶክተሩ ለሞት የሚያበቃ ህመም አልነበራቸውም፣ አሟሟታቸው ግራ ገብቶናል!›› 

ነበረ መልሳቸው፡፡ የእርሳቸውም አሟሟታቸው ሳይሆን ሞታቸው ትልቅ ዜና ሆኖ ተገኘና – ከፍ ባለ ክብር አስከሬናቸው እንዲያርፍ ተደረገ፡፡

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ – እርሳቸው ደግሞ ጠ/ሚው አብይ አህመድ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ሂደት በሙሉ ‹‹የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው፣ እንኳን 65 ፐርሰንት 35 ፐርሰንትም አልደረሰም፣ የዛሬ 35 ዓመትም አያልቅም፣ ተዘርፎ ተበልቶ ያለቀ ጉዳይ ነው!›› ብሎ በተናገረ በቀናት ልዩነት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ፡-

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ነገር አልገባኝም፣ የተናገሩት ነገር እውነት አይደለም፣ ግን የተሳሳተ መረጃ ደርሷቸው ሊሆን ይችላል፣ ከእርሳቸው ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ተይዞልኛል፣ አሁን ምንም ልል አልችልም፣ ከተነጋገርን በኋላ የደረስንበትን ባሳውቅ ይሻላል›› 

ብሎ ለጋዜጠኛ በተናገረ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ – በማያሳምን ሁኔታ፣ እና ብዙ የተዛቡ አጠራጣሪ ማስረጃዎች በሞሉበት የመኪና የፊት መቀመጫ ላይ በጥይት ጭንቅላቱ ተበርቅሶ ተገኘ፡፡ የኢንጂነሩን ሞት ‹‹ራሱን ማጥፋት›› መሆኑን ያረጋገጠው በአብይ አህመድ የተሾመው የፖሊስ ኮሚሽነር አህመድ ዘይኑ ከጥቂት ወራት የሥልጣን ቆይታ በኋላ በአምባሳደርነት ማዕረግ ከአገር እንዲርቅ ተደረገ፡፡

የብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ጽጌም አሟሟት ተመሳሳይ አስገራሚነት ነበረው፡፡ ‹‹በአማራ ክልል በአብይ አህመድ ሚሽን ተሰጥቷቸው የገቡትና የቅማንትንና የከሚሴን ጭፍጨፋ እናጣራለን ብለው በክልሉ በተለያየ አቅጣጫ የተሰማሩ ኃይሎች መኖራቸውን፣ ዓላማቸው ምን እንደሆነ እየተከታተለ እንደሆነ፣ እና ያለ ክልሉ የፀጥታ ክፍል ፈቃድ አንዲትም ወረቀት ከክልሉ ይዘው መውጣት እንደማይችሉ›› በተናገረ በቀናት ልዩነት ውስጥ – እነ ጄነራል ተፈራ ማሞን ሳይቀር አብይ አህመድና ደመቀ መኮንን አዲስ አበባ ድረስ ጠርተው አሳምነው ፅጌን እንዲገመግሙ ተደረጉ፡፡

ወደ ባህር ዳር በተመለሱ በቀናት ልዩነት ውስጥ ግን ጄኔራል አሳምነውን ከነህይወቱ አስሮ ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት በተደረገ በአብይና በደመቀ ቡድኖች የተቀነባበረ የኃይል ሙከራ – ጄኔራሉ ቀድሞ ሴራውን በመንቃቱ – ከፍተኛ የእርስ በርስ እልቂት ባስከተለ መልኩ – ጄኔራሉ አሴሩብኝ ባላቸው ላይ እርምጃ ወስዶ እርሱም በጠራራ ፀሐይ በመንገድ ዳር እንደ ውሻ ተገድሎ ሬሳው ለእናቱ ተወስዶ ተወረወረላቸው፡፡

እነዚህ ሁሉ ለኢትዮጵያውያን ያልተለመዱ ለሥርዓቱ እና ለሥርዓቱ ትርክት – እና በተለይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ አህመድና ኦሮሙማው ኃይል ሥልጣን መደላደል – አደጋ መስለው የታዩ ታዋቂ ሰዎችን በግድያ የማስወገድ ተግባሮች – ብዙ ሊመረመሩ የሚገባቸው ፍጹም እንግዳና አነጋጋሪ ነገሮችን ያዘሉ ግድያዎች ናቸው፡፡ ያለምንም ይሉኝታና ህዝብ ምን ይለኛል የተካሄዱ እንግዳ አደጋን የማፅዳት እርምጃዎችም ናቸው፡፡

ለወትሮው እንዲህ ዓይነት የተቀነባበሩ ‹‹አሳሲኔሽኖችን›› በመፈፀም የሚታወቁት የሲ አይ ኤና የሞሳድን የመሳሰሉ የሥለላ ተቋማት እንጂ – በሀገራችን የተለመዱ አይደሉም፡፡ ስላልሆኑም ነው ለምሳሌ በወታደራዊው መንግሥት ዘመን በድንገት የተሰወረው የደራሲ በዓሉ ግርማ ሞት እስከዛሬም እየተጋጋለ በቁጭት የሚነገር ትልቅ ታሪክ ሆኖ የቀረው፡፡

አንድ ነገር ልጨምር፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ – አብይ አህመድና ኢሣያስ አፈወርቂ በተገኙበት ለኢሳያስ አቀባበል በተካሄደው  የሙዚቃ ድግስ ላይ – የተገኙ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ድምፃውያን እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በዝግጅቱ ላይ እነ ፀጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ስለሺ ደምሴ፣ እና ማሀሙድ አህመድን የመሳሰሉት ድምፃውያን ጠብ እርግፍ ብለው አብይ አህመድንና ኢሣያስ አፈወርቂን የሚያስደስትና – እርቀ-ሠላሙን የሚያዳንቅ ዜማ መወድስ ሲያቀርቡ – ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ እና በአዘጋጆቹ መድረኩን ተከልክሎም፣ ራሱምም ሳይፈልገው፣ በህዝብ ጩኸት ወደ መድረኩ እንዲወጣ የተደረገው ቴዲ አፍሮ ግን እነ አብይ አህመድን ያላስደሰተ – ብዙ ተቃውሞና ሾርኔ ያለው የዜማና የቃል መልዕክት አሰምተው ከመድረኩ ወረዱ፡፡

በተከታዩ ቀን ጠ/ሚ አብይ አህመድ የሚሊኒየም አዳራሽ የኢሳያስ አቀባበል ዝግጅቱን ተሳታፊዎች በስም እየጠራ ሲያመሰግን – ሌሎቹን ድምጻውያን (እነ ማህሙድን፣ ጋሽ አበራ ሞላን፣ አረጋኸኝን፣ ወዘተ) እያንዳንዳቸውን በስም ጠርቶ አመሰገነ፡፡ ቴዲ አፍሮንና ሀጫሉ ሁንዴሳንስ? የእነሱን ስም ግን ከነመፈጠራቸውም ሳይጠቅስ በዝምታ አለፋቸው፡፡ በጊዜው ልብ ላልነው የሚገርም በቀልና፣ የሚገርምም የማያዳግም የአደባባይ መልዕክት ነበረው! ይህ በሆነ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሀጫሉ ሁንዴሳ በተቀናበረ መልኩ፣ እና አፄ ምኒልክን ዘልፎ የተናገረባት ፐርፌክት ጊዜ ተጠብቃ – ድንገት ተገድሎ ተገኘ፡፡ ብዙዎች ይህን የድምጻዊውን ሞት ማመን አቅቷቸው ነበር፡፡ ግን የሆነ ነገር ነው፡፡ ተገድሏል፡፡

ይሄም የሀጫሉ አነጋጋሪ ግድያ ራሱን የቻለ ትልቅ ምርመራና ማጣራት የሚጠይቅ – እና ለጊዜው አብይ አህመድ በሾማቸው ባለሥልጣናት – ኦሮምኛ የሚነጋገሩ ሰዎች ናቸው ጠርተው የገደሉት ተብሎ ተደምድሞ አለፈ፡፡ ከዚያ በቀብሩ ‹ሬሳ አስመለሳችሁ› በሚል – እነ ጃዋር አህመድን ጨምሮ አሰራቸው፡፡

እና በጃዋር መታሰር የተነሳ የተቀጣጠለ ቁጣ ይሁን፣ ወይስ በሀጫሉ ሞት የተነሳ የተፈጠረ ቁጣ – ወይስ በሁለቱም – ሳይታወቅ – ሁሉም ነገር በየሚዲያው ‹‹በድምፃዊ ሀጫሉ ሞት የተነሳ የተቀሰቀሰው ቁጣ›› እየተባለ ሁሉም ነገር በሀጫሉ የሞት ዜና ተሸፋፍኖ እንዲታለፍ ተደረገ፡፡ ሀጫሉን የገደለው ማነው? ሀጫሉን ያስገደለው ማነው? ሀጫሉ ለምን ተገደለ? – የዚህን ፈታኝ ጥያቄ መልስ የሚያውቁት – አንድዬ ፈጣሪ፣ አንድዬ አብይ፣ እና ከአብይ ጀርባ የሞት ጥላቸውን አጥልተው አብይንና ሥርዓቱን የሚጠብቁት ምስጢራዊ ገዳይ እጆች ብቻ ናቸው!

እና እነዚህንና ሌሎችን ቁጥራቸው የበዙ አስደንጋጭና አነጋጋሪ ነገሮችን አያይዞ የሚያስተውል አዕምሮ ያለው ሰው ሁሉ – ማን ነው እነዚህን ግድያዎች በብቃትና በህቡዕ በተመሳሳይ መልኩና ለተመሳሳይ ዓላማ እየፈፀማቸው ያለው? ማን ነው ከአብይ አህመድ ጀርባ የሞት ጥላውን በተቃረኑት ላይ እያጠላ አብይንና ሥርዓቱን ድምፅ በሌለው ሴራና ገዳይ መሳሪያ እየጠበቃቸው ያለው? የሚል አስደንጋጭና አስጊ ጥያቄ ይመላለስበታል፡፡

‹‹ኬኔዲን ማን ገደላቸው?›› እንዲል ደራሲው፣ እኛም በአደባባይ ወጥተው አብይን የሚቃወሙትን፣ ሥርዓቱን የሚያጋልጡትን፣ ከአብይ በላይ ተሰሚነትና ተቀባይነት ይኖራቸዋል ተብሎ የሚታሰቡን፣ የአብይንና በ‹‹ለውጥ›› ስም የተከለውን ሥርዓት  የተቃወሙትን በሚገርም ብቃትና ፍጥነት ማን ገደላቸው? – ብዙ ምርምር ያሻዋል፡፡ ብዙ አስተውሎት ያሻዋል፡፡ ምናልባትም ይሄ ዓይነቱም የተለባበሰውን ጉድ ማነፍነፍ ራሱ በራስ ላይ ያልታሰበ አደጋን ይጋብዝም ይሆናል፡፡ አደገኛም ጥያቄ ነው፡፡

ለጊዜው አንድ ነገር ብቻ አስታውሼ ልለፍ፡፡ የወያኔ ኢህአዴግ ሥርዓት ከራሱ ከውስጡ በሚንተከተክ እሳተ ገሞራ በሬክተር ስኬል በሚለካ ድንጋጤ በተንቀጠቀጠበት – እና ደኢህዴንን ከጀርባቸው አሰልፈው በህቡዕ በተነሱበት የኦህዴድና የብአዴን ህቡዕ አንጃዎች የመጨረሻውን አጣብቂኝ ስብሰባ በሚያደርጉበት ወቅት – ለማ መገርሳ ‹‹በበኩሌ ለህዝባችን ያልሆነ ስልጣን፣ ባፍንጫዬ ይውጣ! እደግመዋለሁ፣ ሥልጣናችን ባፍንጫችን ይውጣ!›› ብሎ በሙሉ ልብ ተናገረ፡፡ ይህን ዓይነቱ ቁርጠኝነት ሥርዓቱን ተቃውሞና ተላትሞ ሞትም ከመጣ፣ መከራም ከመጣ፣ ሥልጣንም መነሳት ከመጣ፣ በጸጋ ለመቀበል ከቆረጠ የኦሮሞ መሪ የመጣ ቁርጠኝነት ነበረ፡፡ አስደንጋጭ ነበረ፡፡ ስብሰባው በይደር፣ ጉዳዩና ቃላቶቹም በክውታ ታለፉ፡፡

ከዚያ በኋላ የመጨረሻው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ከመካሄዱ በፊት – በአሜሪካው የሲ አይ ኤ ሰላይና የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቁልፍ ባልደረባ – ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመገንጠሉ ሂደት የአሜሪካን መንግሥት ወክሎ ቁልፍ የአደራዳሪነት ሚናን በተጫወተው – በሄርማን ኮህን አማካይነት – ትዕዛዝ የሚመስል የትዊተር መልዕክት ተላለፈ፡- ‹‹ለማ መገርሳ የኦህዴድን ምክትል ሊቀመንበርነት እንዲይዝ ሆኖ፣ አብይን ወደፊት አምጡት! እና ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጉት! ለቦታው የሚመጥነው ትክክለኛው ሰው እርሱ ነው!›› የሚል አጭር ምክር የመሰለ ከባድ መልዕክት፡፡ አብይ አህመድ ማነው?

አብይ አህመድን ገና ብዙ ሰው አያውቀውም ነበርና አብይ አህመድ እንዲህ ተደርጎ ነበር የተሳለው፡- አብይ አህመድ እነ ለማ መገርሳ ወያኔን ፊት ለፊት ሲፋለሙ – ወሳኝ ድምፅ ከሚሰጥበት ጉባዔ በህመም አሳቦ ሳይመጣ የቀረ ዓይናፋር ነው፡፡ ንግግሩ ኃይለቃል ያልተሞላበት፣ ሥልጣንን ያህል ነገር በአፍንጫዬ ይውጣ የማለት ወኔው የሌለው፣ ከእስልምና ቤተሰብና አካባቢ ወጥቶ ራሱን ወደ ፕሮቴስታንት ወንጌላዊነት ያሸጋገረ፣ ክፉ የማይወጣው፣ የወያኔ ታማኝ የሥለላ ድርጅት የኢንሳ ኃላፊ፣ ሩህሩህና ምስኪን የኦህዴድ ታማኝ የልጅነት ካድሬ (መንጁስ) ነው፡፡ ጄኔራል አባዱላ ገመዳ – አብይን ለሚኒስትርነት ሲታጭ – በህቡዕ ለወያኔ ስለ አብይ በጽሑፍ ያስገባው አስተያየት በምሥጢራዊ መንገድ ሾልኮ ወጥቶ ነበረ፡፡ እንዲህ ይለዋል አባዱላ ገመዳ አብይ አህመድን፡-

‹‹ብሩህና አስተዋይ፣ ወደ ኋላ የማይመለከት፣ የፊቱን ብቻ የሚያይ፣

ተማሪ – በጣም ተማሪ፣ በየጊዜው ለመማርና ለማወቅ ራሱን

ለማጎልበት የሚተጋ፣ ለለውጥና ለመፍትሄ እንጂ ስላለፈው

ነገር በፍፁም የማይጨነቅ››

ሲል ነበር የገለጸው፡፡ ወይም በህቡዕ ሪኮመንዴሽን ያስገባለት፡፡ እና እንደ ለማ መገርሣ ያለውን የማያወላውል ቆራጥ ሰው – የመሪነት ሥልጣን ቢጨብጥ – ነገና ከነገ ወዲያ ምን ጉድ ያመጣብን ይሆን? ብለው የፈሩት – እና አማራ ሥልጣን ላይ ከወጣ ሥጋችንን በቁማችን ነው የሚዘለዝለው ብለው ሲባንኑ የኖሩት ወያኔዎች – በአሜሪካው ሠላይ በሄርማን ኮኸን በትዊተር መልዕክት የወረደላቸውን፣ በጉራውና እዩኝ ባይነቱ በቅፅል ስም ‹‹ማራገቢያ›› (‹‹መሽረፈት››) ብለው የሚጠሩትን፣ ታማኝ የኦሮሞ ጋሻጃግሬያቸውን (እና በእነርሱ እይታ በአንጸራዊነት ፍፁም ‹‹ሠላማዊውን››) አብይ አህመድ አሊን – ከልባቸው አመኑት፡፡ እና ከብዙ ሊያደርጉ ከሚችሉት የክፋት ተግባር ሁሉ ተቆጥበው – ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣነ መንበር ሲሸጋገር – አጨብጭበው ተቀበሉት፡፡ በአንድ ወቅት – ወደ መቀሌ ካፈገፈጉ በኋላ – ወያኔዎቹን፡-

‹‹እንዲህ የምትፎካከሩትና የምትጭንጨረጨሩት በአብይ አህመድ

ቀንታችሁ ነው፣ የእርሱ ስኬት እናንተን ያሳነሳችሁ መስሏችሁ ነው

ይባላል፣ ስለዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አላችሁ?››

ብሎ ሲጠይቅ፣ አንዱ የወያኔ ወፍራም ባለሥልጣን የሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡-

‹‹እናንተ (ከወያኔ ውጪ ያለውን ኢትዮጵያዊ ማለቱ መሰለኝ) – እናንተ

አብይ አህመድን እንዲህ የወደዳችሁት እኛ እርሱን ስለተቃወምነው

መሆኑን አትርሳ! ይሄኔ እኛ ከአብይ ጋር እፍፍ ብለን ብናሽቃብጥ ኖሮ

እናንተ በአብይ ላይ ትነሱበት ነበር! ስለዚህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ

የኢትዮጵያ ህዝብ አብይን እንዲወደው እያደረግን ያለነው እኛ መሆናችንን

አትርሳ!!››

ወቸጉድ! ማን ያውቃል? አብይ አህመድ ለወያኔዎች ያላቸው የመጨረሻው ታማኝ፣ የመጨረሻው የተሻለው ጥሩ ሰው ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ወይም ከብዙ የእዚያው-በዚያው ‹‹ዓይን ያወጣ ዓይኑ ይውጣ›› የሀሞራቢ በቀል አትርፏቸውም ይሆናል፡፡ እስከዛሬም የቆዩት ሰውየው እሱ በመሆኑ ሊሆንም ይችላል፡፡ ወደፊትም ከምን ጉድ እንደሚያወጣቸው የሚያውቁት እነሱና አንድዬ ብቻ ናቸው፡፡

የሆነው ሆኖ – አሁን ዓላማችን የአብይንና የህወኀትን እከክልኝ-ልከክልህ አንስተን መወያየት፣ አሊያም ጠብና ዝምድናቸውን፣ አሊያም ውላቸውንና መፋረሻቸውን እየዘከዘክን ለመመርመርም፣ ለመደርደርም አይደለም፡፡ ዓላማችን አብይ በሥልጣን ላይ የወጣው በእነ ማን ምሪት እና በእነማን ትዕዛዝ፣ በእነ ማንስ ስምምነትና በምን ዓይነት መስፈርቶች እንደሆነ አንዳንድ ነገሮችን ለማስታወስና – ምናልባትስ አሁን ከአብይ ጀርባ እያጠላ አብይን የተቃወሙትን ታዋቂዎች ሁሉ በተቀነባበረ ሁኔታ እስከ ወዲያኛው የሚሸኛቸው የሞት ጥላ የመሠለ ረዥምና አረመኔ ሥውር እጅ – የማን እጅ ሊሆን ይችላል? የሚለውን ፈታኝ ጥያቄያችንን ለመመለስ እንደ መንደርደሪያ ያግዘን ይሆናል ያልኩትን አንዳንድ ነገር ለመጠቃቀስ ነበር ሃሳቤ፡፡

በአንድ ወቅት የአሁኑ የኢትዮ-360 ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሠ ዋቅጅራ ስለ አብይ አህመድና ከእርሱ ጋር ስለተገናኙ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ሲናገር፡-

‹‹ምክንያቱን ምን እንደሆነ ለይቼ መናገር አልቻልኩም፣

ግን አብይን የተጠጉ ሁሉ ተቀስፈው ነው የሚቀሩት፣

እርሱን ካገኙ በኋላ የቀድሞው እነሱ አይሆኑም፣

ወይ ይለውጣቸዋል፣ ወይ ይሞታሉ!››

ነበር ያለው፡፡ የእኔም የቆየ ጥርጣሬ ይኸው ነው፡፡ እና – ብዙ ጊዜ የተደጋገመ ጥያቄዬ – እነዚያ አብይን በሠይፍ የሚጠብቁት ስውር እጆች የማን ናቸው? የሚል ሆኗል፡፡ ፈጣሪ ይግለጽልን፡፡ ሩስያኖች ሲተርቱ ‹‹ተኩላዎች በጨለማ ያፈሰሱትን ደም፣ ሲነጋ የቀን ብርሃን ያሳየዋል›› ይላሉ፡፡ እንግዲህ ጊዜ ብርሃን ነውና፣ ጊዜ መስታወት ነውና፣ ሁሉን በጊዜው ያሳየን፡፡ የውዶቻችንን የሞት ምስጢር ይግለጽልን፡፡ ብዬ ለዛሬ ተሰናበትኩ፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ!

ቸር እንሰንብት!

Filed in: Amharic