>

የህወሓት አገር የማፍረስ ሙከራ በተመለከተ ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

የህወሓት አገር የማፍረስ ሙከራ በተመለከተ ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

የሶማሌ ክልል መንግስት ካቢኔ ህወሓት በሰሜን ዕዝ በሚገኘው የኢፌዲሪ መከላኪያ ስራዊት ላይ ያደረሰውን አሳፋሪ ጥቃትና ከዚያ አልፎ በሌሎች አካባቢዎች ላይ የለኮሰው የጥፋት ወረራ በጥብቅ ያወግዛል፡፡
ይህ የአጥፍቶ መጥፋት ድርጊት ህወሓት ለ27 አመት በሶማሌ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲያካሂድ የነበረው ፋሽስታዊ የእኔ ብቻ ልግዛ ፖለቲካ  የመጨረሻ ምዕራፍ ነው ብለን እናምናለን፡፡
ምንም እንኳን የህወሓት ጭቆናና ግፍ የትግራይ ህዝብን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የቀመሱት ቢሆንም የሶማሌ ክልል  ህዝብ ያህል  በህወሓት ጨካኝ ቡድን የተገደለ፣ የተሰደደ፣ የተዘረፈ ህዝብ የለም፡፡
ህወሓት የሶማሌ ክልል ህዝብን ገድሏል፤ ሴቶችን ደፍሯል፣ ለማመን የሚከብዱ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን ፈፅሟል፡፡
ይህ ሳይበቃው የሶማሌ ህዝብ ከኦሮሞ ጎረቤት ወንድም ህዝብ ጋር ለርካሽ ፖለቲካና ለስልጣኑ ቀጣይነት ሲል አጋድሏል፡፡ በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ሌሎች ብሄሮችን በግፍ ባደራጃቸው ሄጎና መሰል ጋጥወጦች አስፈጅቷል፡፡
ይባስ ብሎም 27አመት ግድያና ጭቆና ሳይፀፀት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የሱማሌ ክልልን በማተራመስ ህዝቡ ያገኘውን ሰላምና ነፃነት ለማሳጣት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሟል፡፡
በአሁን ሰዓትም የአፋርና የሱማሌ ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች ሁለቱን ወንድም ህዝቦች በማጨራረስ ላይ ይገኛል፡፡
የሶማሌ ክልል ህዝብ የህወሓት የጥፋት ተልዕኮ ለማፍረስና ለማስቆም የአገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ የመከላኪያ ሠራዊት  እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሙሉ ልብ የሚደግፍ ሲሆን ለተልዕኮም መሳካት የበኩሉን ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡
በጥላቻ የተሞላውና ህዝቦችን በመከፋፈልና በማጋጨት ፖለቲካ ሲያተርፍ የቆየው ህወሓት  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያዊያን ትግል ከስልጣን ከተባረረ በኃላ በተለያዩ  ክልሎች የጥፋት ኃይሎችን በማስማራት ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ የተፈፀሙ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎችን  ጨምሮ  በርካታ ንፁሃን ኢትዮጵያዊያንን አስገድሏል፡፡
ይህን እኩይ ተግባር ለማስቀጠል በሱማሌ ክልል ውስጥም የጥፋት ኃይሎችን ለማሰማራት ቅንጣት ያህል እንደማያመነታ ስለምናውቅ ህዝባችን ይህንን ለመመከት ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም ሰላሙን እንዲጠብቅ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
በመጨረሻም የሶማሌ ክልል ህዝብ ሌሎች ብሄሮችንና ሃይማኖቶችን  በማክበር ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ  ያስመሰከረውን ጨዋነቱን ዛሬም እንደሚደግመው አንጠራጠርም፡፡
ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ!!
ድል ለመከላከያ ሠራዊታችን!!
Filed in: Amharic