>

ኢትዮጵያን የማዳኛ ብቸኛው መንገድ!  ( ይነጋል በላቸው)

ኢትዮጵያን የማዳኛ ብቸኛው መንገድ! 

ይነጋል በላቸው


እንዴት ብዬና በምን እንደምጀምር ግራ ገባኝ፡፡ ግን  ጥቂት ነገር መናገር አለብኝ፡፡

ያለንበት ሁኔታ አንዲት ሕጻን ለእናቷ  “እማዬ ጣቴን አሳከከኝ” ስትላት “እኔንም በአንድ ቀን አልቆመጠኝም” ብላ እንደመለሰችላት ያለ ሁኔታ አይደለም፡፡ ከዚያ ዓይነቱ በቀላሉ ሊፈወስ የሚችል ችግር ከወጣንና ቀስ በቀስ ጠላቶቻችን በተናጠልና በኅብረት ወደደገሱልን የመከራ ውርጅብኝ ከገባን ቢያንስ ሁለት ዓመታትን አስቆጠርን፡፡ የሊቢያ ውድመት በአንድ ቀን አልተጠነሰሰም፤ የሦርያ ዕልቂትና መበታተን በአንድ ቀን ተዘርቶ አላሸተም፤ የየመንና የሶማሊያም፣ የኢራቅና የሌሎቹም እንዲሁ፡፡ ችግሩ “የጨው ተራራ ሲናድ ብልኅ ያለቅስ ሞኝ ይስቅ” እንዲሉ ሆኖብን አንዳችን እየሆነ ባለው ስናነባ ሌላኛችን ማሾፋችን ነው፡፡ የሚታየውና የሚሰማው ውሸት እየመሰለን፤ እዚያ ታች የሚታየው መከራ እዚህ የማይደርስ እየመሰለን፤ የድንቁርና ሞራ ጋርዶን ተጃጅለናል፡፡

አሁን ያለን ብቸኛ አማራጭ ወደፈጣሪ መጮህ ብቻ ነው፡፡ በመሠረቱና እንደ እውነቱም ይህ ተፈጥሯዊ መብት ነው፤ መንግሥት ሊከለክለን እንደሚችል ግን መጠርጠር አይከፋም፡፡ ለምን ቢባል የችግራችን መንስኤ ክፋታችንና ኃጢኣታችን ቢሆንም አለንጋና ጨንገሩ ግን አራት ኪሎ ከተሰየመው ልዝብ ሰይጣን ጀምሮ መቀሌና አሥመራን አቆራርጦ ወለጋ ጫካዎች ውስጥ ተዝናንቶ የተቀመጠው የዐውሬው ልዑክ የአጋንንት መንጋ ጸሎትን ስለሚጠላ፡፡ ያን የፈረደበትን “The Prince” የተሰኘ መጽሐፍ ያነበበ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት አጼ በጉልበቱ ሁሉ ለሥልጣን ማቆያ የሚጠቅም እየመሰለው በግራና በቀኝ የሚፈጥረው የተጻራሪ ኃይላት መንጋ በሁለንተናዊ የመንግሥትና ዓለም አቀፍ ድጋፍ እየደለበ መጥቶ ለተራ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለፈጠረው የመንግሥት ኃይል ሳይቀር ታላቅ የሥጋት ምንጭ በመሆን ላይ ነው፡፡ 1200 ልፍስፍስ ጦር ይዞ በመቀሌ በኩል የመጣው ኦነግ ለምንና በምን ምክንያት አሁን ለያዥ ለገራዥ እንዳስቸገረ የማያውቅ ቢኖር ማወቃችንን ማወቅ የማይፈልገው አቢይ አህመድ ብቻ ነው፡፡ ከሰዶ ማሳደድ ጋር ፍቅር የያዘው ይህ ጠ/ሚኒስትር እነዮሐንስን እያሠረና እየገደለ እነበርባንን ከእሥር ፈትቶ በማደለብ የት እንደሚደርስ የቆዬ የሚያየው ይሆናል፡፡ መካሪ ያጣ ንጉሥ ካለአንድ ዓመት አለመንገሡን በቅርቡ ሳናይ አንቀርም፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ የሰሜኑ ሰሞነኛ የጦርነት ዐዋጅና ተግባራዊ እንቅስቃሴ አደገኛ ዙር ላይ ነው፡፡ ነገሮች ወዴት እያቀጣጩ እንደሆነ አሁን ላይ በጣም ግልጽ ሆኗል፡፡

ብሔራዊ የሀገር ስሜት በሌለበት፣ ባህልና ሃይማኖት ለይስሙላ ካልሆነ በተግባር በጠፋበት፣ ዜጎች በዘርና በጎሣ ተቧድነው አንዱ ሌላውን ለማጥፋት በሚያደቡበትና በተለይም ጽንፈኛ ኦሮሞዎች በፌዴራልና ክልል መንግሥታት ተደግፈው አማሮችን በሚያርዱበት፣ ፍቅርና መተዛዘን በጠፋበት፣የኑሮ ውድነቱ ሽቅብ በተወነጨፈበት… ሁኔታ ለሀገራችን ችግር ከሰው መፍትሔ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡

ስለሆነም በቃሉ የምትኖሩ አንድም ሁለትም የሃይማኖት አባቶች ካላችሁ ሀገራዊ የጸሎትና የምህላ መርሐ ግብር ወጥቶ ሁላችንም ወደ ፈጣሪ እንድናለቅስ ይደረግ፡፡ ሰይጣን ቤተ መንግሥቱን ብቻ ሳይሆን ቤተ አምልኮዎችንም በመቆጣጠሩ ይህ ጥሪየ ሰሚ ያገኛል ብዬ ብዙም አላምንም፡፡ የታየኝን መጠቆም ግን የዜግነት ግዴታየ ነውና በቡድን መጸለይና እግዚዖ ማለት ባንችልም ወይም ያን ለማድረግ ብንቸገርም በየግላችን ፈጣሪን እንለምን፡፡ የመከራ ዶፉን እንዲያለዝብልንና የፈተናውን ጊዜ እንዲያሳጥርልን አምርረን እናልቅስ፡፡

አማራ ከሞላ ጎደል የሁሉም ዒላማ ሆኗል፡፡ በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ቀድሞ ክብርና ሞገሱ እንደሚመጣ በበኩሌ ጥርጥር የለኝም፡፡ ካለፉት 30 እና 40 ዓመታት ወዲህ ግን ይህን በ50 እና 60 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ከ5 ወይ ከ6 ሚሊዮን የወጡ ሽፍቶች ሣይቀሩ በዓለም አቀፍ የሤራ ጥልፍልፍ አማካይነት የመንግሥትን ሥልጣን ይዘው መረገሙን እስኪጠላ በበደል ላይ በደል እየከመሩ በግፍ አኮርባጅ ጀርባው እስኪላጥ ገርፈውታል፡፡ የተጣለበት አዚም ሲለቀው ግን እነዚያንና እነዚህን ግፈኞች አያድርገኝ፡፡ ለማንኛውም ግን አማራው ከኢትዮጵያዊነቱ ሳያፈገፍግ እርሱን ከሚደግፉ ሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር ሆኖ የብርሃንን ቀን ማምጣት አለበት፡፡ የሞቱ ሞተዋል፤ አይመለሱምና በነሱ አንቆዝም፡፡ ቀሪዎችን እናድን፡፡ በእስካሁኑ ጉዞው የትም እንደማይደረስ በመረዳት በየአካባቢው በጎበዝ አለቃ መደራጀት፣ በሞረሽ ባህሉ መጠራራትና ወጣቶቹን ማንቃት፣ እርስ በርሱ ከመጠላለፍና ከመገዳደል ተቆጥቦ ጠላቶቹ ለራሳቸው እንደሚያደርጉት በመሀሉ ንፋስ አለማስገባት፣ ግጭቶችንና የእጅ መተላለፍን በባህላዊ የሽምግልና መንገድ መፍታት፣ በፍቅረ ንዋይም ይሁን በሌላ ምክንያት ለጠላት አለማደር፣ ከቂም በቀልና ጥላቻ መራቅ፣ ከባዕድ አምልኮና ከጠንቋይ አስጠንቋይ ኋላ ቀር (ጎጂ) ልማድ መላቀቅ፣ በዘመናዊ ትምህርትና በሥልጣኔ ቅባት ራስን እያዋዙ ከዘመኑ ጋር መጓዝ፣ ንባብን ማፍቀር፣ ጥበብን መውደድ፣ የዕርቅና የይቅርታ ወግ ልማድን ማጠናከር፣ ተሰባስቦ በችግሮችና መፍትሔያቸው ላይ መወያየትና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ፣ ሁሉም ኃላፊነትን ወስዶ የየድርሻውን መወጣት፣ ትልቅ ማኅበረሰብኣዊ ኃላፊነትን ለአንድ ሰው ብቻ አለማሸከም… ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ ይሄ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎና ሸዋ የሚባል የወያኔ ውርስ የሆነ ክፍፍል ደግሞ አስቂኝ ነው፤ በወረዳና በቀበሌም መቧደን ተጀምሯል ይባላል፡፡ ይህ የሚያሳየው የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ቤት ሲልከሰከስ መታየቱን ነው፡፡ አማራን ከሚያሰድብ ቅሌት ውጡ፤ ትልቅ ቅሌት ነው! 

… እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ በኦህዲድና በወያኔ እንዲሁም በብአዴን ሥውር ሤራ እየተጨፈጨፉ ያሉ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፡፡ የዕዳ ደብዳቤያችንን በቶሎ ቀዳዶ ይጣልልንና ለዘመናት በጉጉት ስንጠብቀው የነበረውን ነፃነታችንን ያጎናጽፈን፡፡ ma74085@gmail.com ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ. ‘ ም ‘  

Filed in: Amharic