>
6:58 pm - Monday May 29, 2023

አዎ የወንድማማቾች ጦርነት ነው...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አዎ የወንድማማቾች ጦርነት ነው…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ታዬ ደንደአ ከመሳሳት አልፈህ አብረን ገደል እንግባ ማለትህ ቢገርመኝ ነው ይህንን ማስታወሻ ልጽፍልህ የተነሳሁት። ትላንት በማህበራው ድህረ ገጽ ካስተላለፍካቸው መልክቶችህ በአንዱ “ባንዳ ወንድም የለውም … የወንድማማቾች ጦርነት አትበሉ” የሚል ምክር የመሰለለ የሹም ትዕዛዝ አይነት መልዕክት አስተላልፈህ ባይ ገረምከኝ። ነገሩን በግርምት ብቻ ላልፈው ሞክሬ ነበር። እየቆየ ግን የአስተሳስ ግድፈትህ ይከነክነኝ ጀመር። አንድ ባንተ ደረጃ ያለ ሹም እንዲህ አይነት የሾቀ እና ሚዛኑን የሳተ ሃሳቡን እንደ አዋቂነት ቆጥሮ በአደባባይ ተቀበሉኝ ሲል ዝም ማለት የጥፋቱ ተካፋይ አንደመሆን ስለተሰማኝ ይህን መልዕክት ልጽፍልህ ወደድኩ።
የአንተ አስተሳሰብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ልክ ይሆን የነበረው ሜዳ ላይ መሳሪያ አንግባችው የምትዋጉት አንተ ታዬ ደንድአ እና በዛ በኩል ደግሞ ጌታቸው አረዳ፣ በዚህ በኩል ደመቀ መኮንን እና በዛ ማዶ አባይ ጸሀዬ፣ በዚህ ማዶ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና እዛማዶ ደብረጺዬን ቢሆን ነበር። ያኔ ወንድም እና ባንዳውን ለዩ ብትለን የአንተም የደከመ የሃሳብ እገዛ ሳይሻን፤ ታዩ ወንድም ነው፤ ጌታቸው አገሩን የከዳ ባንዳ ነው ለማለት ይዳዳን ይሆናል።
እኛ እኮ የወንድማማቾች ጦርነት ነው፤ ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት ፍልሚያ ነው የምንለው ሜዳ ላይ ግራ ቀኝ አሰልፋችሁ የምታዋጓቸውን፣ የፖለቲካው ውል ያልገባቸውን፣ ወጣት የድሀ ልጆችነ ነው። እናንተማ ያማረ ሱፍ እና ውድ ከረባት አስራችሁ፣ ከሞቀ ቢሯችሁ ውስጥ ተቀምጣችሁ፣ በቃላትና በመግለጫ ለምትጠዛጠዙት ካድሬና ሹማምንት ምን ገዶን። እናንተን እማ ከዚህ መለስ ባንዳ ከዛ መለስ ለአገሩ የቆመ ታማኝ ብሎ መፈረጅ ምን ማሰብና ምርምር ይጠይቃል ብለህ። የኢትዬጲያ ሕዝብ ማን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።
እኛን ያስጨነቀን እና እንቅልፍ የነሳን እናንተ ያሚረ ቢሯችሁ ቁጭ ብላችሁ እና ትኩስ ቡና እያጣጣማችሁ በምትሰጡት ቀጭን ትእዛዝ እርስ በርስ የሚገዳደሉትን ወንድሞቻችንን እያሰብን ነው። በሁለቱም ወገን የተሰለፉት ኢትዬጵያዊያን ወንድሞቻችን እናንተ ፖለቲከኞቹ አብኩታችሁ ባበላሻችሁት ፖለቲካ ጦስ የሚማገዱ የአንድ ቤተሰብ፣ የአንድ አገር ልጆች ናቸው። በአንድ አገር ውስጥ የሚካሄድ የእርስ በርስ ጦርነት የፖለቲከኞች ክስረት መገለጫ እንደሆነ ብትረዳው ኖሮ የእኛ ስጋት ይጋባብህ ነበር እንጂ እንዲህ በግብዝነት አደባባይ ወጥተህ የተወጫበረ እና የጨነገፈ አስተሳሰብህን በድፍረት ተጋሩኝ አትልም ነበር።
የፖለቲከኞች ችግር የእናንተን እርስ በርስ ትከሻ መለካካት እና ፉክክር ሁሉ የሕዝብ ችግር ለማድረግ መውተርተራችሁ ነው። አንተ ከትላንት አለቆችህ ጋር በገባኸው ፉክክር ልክ ለመቧቀስ ሜዳ የወረዳችሁት እናንተ ብትሆኑ ኖሮ ‘እኔን የሀገር መከታ፤ የህውሃት ሹሞችን ደሞ ባዳ እና ባንዳ አድርጋችሁ አስቡ’ ማለትህ  አይከፋኝም ነበር። ጦርነቱን ግን የወንድማማችች እልቂት የሚያስከትል ነው አትበሉ ማለት ግን ድንቁርናዬን ተጋሩኝ ማለት ነው።
ህውሃት በድሃ የትግራይ ወጣቶች ህይወት መነገድ ልማዷ ነው። ከደርግና ከሻቢያ ጋር ባደረገችው ፍልሚያ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የትግራይን ብቻ ሳይሆን፤ በተለይም በኢትዬ-ኤርትራ ጦርነት የመላው ኢትዬጵያን ወጣቶች አስበልታለች። ዛሬ ደግሞ በነዛው በቀሩት ስግብግብ እና ነፍሰ በላ መሪዎቿ ታዳጊ ህጻናትን ትርጉም ለሌለው ጦርነት ለመማገድ አሰልፋ በትንኮሳ የጦርነቱን ችቦ ለኩሳለች። ነገ በሺዎች የሚቆጠሩ የድሃ ልጅች ገብረን የምናመጣው ሰላም ክፉ ጠባሳ ትቶ እንደሚያልፍም የገባህም አልመሰለኝም።
ዛሬ አንተም ሆንክ ከማዶ ያሉት የህውሃት ካድሬዎች ቢሯችሁ ቁጭ ብላችሁ እና ከረባታችሁን አስራችሁ በመግለጫ የምታዋጓቸው ወንድማማች የድሃ ልጆች የሞቱትን አሞራ ይበላቸዋል። አካላቸው ጎድሎ የተረፉትን ደግሞ የእኛው ተመጽዋች አድርገን ሳንቲም እና ዊልቸር ወንበር እየሰጠን በሱም የጽድቅ መንገዳችንን እናደላድላለን። ትላንትም የሆነው ይሄው ነው። ዛሬ ኢሳያስ አፎርቂ አዲስ አበባ ቀይ ምንጣፍ አንጥፋ ልትቀበለው ትላንት ቀንደኛ የኢትዬጵያ ጠላት ተብሎ ከ70ሺ በላይ ወገንቻችንን አሳጥቶናል። ኢሳያስ አዲስ አበባ በተመላለሰ ቁጥር የሚረግጠው ቀይ ምንጣፍ የእነዛ 70ሺ ወጣቶች ደም ነው። ነገም ባንዳ ላልካቸው የትላንት አለቆችህ ለደብረጺዬን እና ለአባይ ጸሐዬ ሌላ የቀይ ምንጣፍ ቦሌ ኤርፖርት ላለማንጠፋችን ምን ዋስትና አለን?
ወንድሜ ታዬ ደንድአ አብረንህ በከሸፈ ሃሳብህ ውስጥ እንድንከሽፍ ባጠራን ጥሩ ነው። አዎ የወንድማማቾች ጦርነት ነው። አገሪቱ በሁኔታዎች ተገዳ የገባችበት የእርስ በርስ ጦርነት ነው። ብዙ ወንድሞቻችንን ሳያሳጣን ቶሎ እንዲቋጭ እንመኛለን። የባንዳውን ሂሳብ ከድል መልስ ለማወራረድ ጊዜ አይጠፋም።
Filed in: Amharic