>
5:13 pm - Thursday April 19, 9246

ብልፅግና ወንጌል...!!! - ክፍል ሁለት ((ዘማሪ ደረጀ ከበደ (ዶ/ር))

ብልፅግና ወንጌል…!!! – ክፍል ሁለት
ዘማሪ ደረጀ ከበደ (ዶ/ር

የምእራቡ አለምና የአፍሪካ የብልፅግና ወንጌል ጠንሳሾችና ተጠቃሚዎች
 
የወንጌል ሸቃጮች
ብልፅግና ወንጌል የምእራቡ አለም በተለይም የአሜሪካው ካፒታሊዝም ውጤት ነው። በቱሌን ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎስት ፕሮፊርሰር የሆነው ሻይን ሊ (Shayne Lee) ሲናገር ሃይማኖትን ከካፒታሊዝም፣ ግለኝነትን ከምድራዊ ንብረት ጋር ማዋሃድ በአሜሪካ የተጠነሰሰ አሰራር ነው ይላል። ችግሩ ይህ የአሜሪካ ውላጅ ሴጣናዊ ትምህርት እዛው አሜሪካ አለመቅረቱና ወደ አፍሪካና ወደ ሌሎችም ክፍላተ አለማት መጋዙ ነው።
በምእራቡ አለም የካፒታሊስት ሃገሮች ዘንድ የስኬታማነት ዋነኛው መለኪያ ገንዘብ በመሆኑ የህዝቡ አእምሮ  ከትንሽ እስከ ትልቅ በገንዘብ ፍቅር ተይዞኣል። የሚያስደንቀው ነገር ግን በመንፈሳዊው ክፍልም ገንዘብ የስብከትም የዝማሬም መጀመሪያና መጨረሻ የሰማይ በረከት መለኪያ ሆኖ መቅረቡ ነው። ገንዘብ፣ የናረ የአባላት ቁጥርና ያሸበረቀ መሰብሰቢያ አዳራሽ መጋቢውን ዝነኛ ያደርጉታል። የታላቁ ነጭ ቤት (White House) ተቀማጮች ሳይቀር ቤተመንግስታቸው ጠርተው የሚያስተናግዱት ሃብታም መጋቢዎችን ነው። በምእራቡ ካፒታሊስት ስርአት የመንፈስ ሃብታምነት ቦታ የለውም። በምእራቡ አለም ሰው በእድሜውና በጨዋነቱ ሳይሆን ባንክ ባለው ዶላርና ዩውሮ (Dollar and Uro) መጠን ነው አንቱ የሚባለው።ስለዚህ ህዝቡ ገንዘብ ያግኝበት እንጅ ሃጢአት ወይም ነውር ነው ብሎ የማያደርገው ነገር የለውም።  ባል ሚስቱን፣ ሚስት ባሉዋን፣ ልጆች ወላጆቻቸውን፣ ለውርስና ለኢንሹራንስ ገንዘብ ሲሉ ስለሚያደርሱባቸው ጉዳት፣ አንዳንዴም ሞት፣ በሬዲዮና በቲቪ መገናኛ መስማት የተለመደ ነው። በየሳምንቱ የቴሌቪዥኑ ፕሮግራምም የሚያሳየው በገንዘብ የተናከሱ ሰዎችን ታሪክ ነው። እንግዲህ በእንደዛ ኣይነት ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ቤተክርስትያንትና መንፈሳዊ ተቁዋማትም ገንዘብ  የሚሰጠውን ክብርና ምቾት በማየት ቀስ እያሉ የብልፅግናን ህልም እንዲያልሙ ተገደዋል። ችግሩ ግን ለብዙ ዘመናት ሲጎመጁ ቢቆዩም፣ ከመንግስት በማያጣላ መንገድ በወንጌል ስም ጠቀም ያለ ገንዘብ ከአማኙ የሚሰበስቡበት መንገድ ሳይከሰትላቸው ርጅም ዘመናት አሳልፈዋል።
በሁዋላ ግን በ1970ቹ ኬነት ሃገን የተባለው የክርስማቲክ ጴንጤቆስጤ ሰባኪ ብልፅግናን ከእመነት ጋር ያጣመረ ትምህርት ማስተማር ሲጀምር ትምህርቱን ይከታተሉ የነበሩ የተለያዩ የጴንጤ ቆስጤ ቤተክርስትያን ሰባኪዎችና መጋቢዎች ሲጎመጁለት የነበረውን ምድራዊ ሃብት የሚያገኙበትን ሰበብ ስለፈጠረላቸው ያለምንም ቅሬታ ተቀበሉት። ኬነት ሃገን የብልፅግና ወንጌል ፈጣሪ ወይም አባት ቢሆንም በእነኛ በመጀመሪያዎቹ አመታት ትምህርቱን አብረውት ያስፋፉ ኬነት ኮፕላንድና (Kenneth Copeland) እና ፍረደሪክ ፕራይስ (Frederick Price) የተባሉ ጴንጤቆስጣል መሪዎች እንደነበሩ የፅሁፍ ጥናት ያሳየናል። በ80ዎቹ ግን የብልፅግና ወንጌል ፈር የለቀቀ አይኑን ያፈጠጠ (ለምን ፈር የለቀቀ አንዳልኩ እፅፋለሁ) ደቀመዝሙር አፈራ። ያም ደቀመዝሙር ኦራል ሮበርት ነበር። ከዛም አከታትሎ በ90 ዎቹም ሆነ ባለንበት በዚህ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ብልፅግና ወንጌል ወጣቶችና አፈ ስኩዋር የሆኑ በግል ጄት የሚንሸራሸሩ በሚሊዮን ዶላር ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰባኪዎችና ሚኒስትሮች አፍርቶአል። በአሜሪካ ያሉ ቀንደኞቹ የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች ስራ አልባ ባለፀግነት በአማኙም በማያምነውም አሜሪካዊ መሃል ትልቅ መነጋገሪያ ጉዳይ ነው። ያም ስለሆነ በ 2007 ከአሜሪካ ሴነተሮች አንዱ የአየዋ ስቴት ሴኔተር ቻርልስ ግራስሌይ (Iow senator Charles, Grassley) ሰባኪዎቹ የሚያስገቡትን የአመት ገቢ ለአሜሪካ ፓርላማ ለምርመራ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ የሰጠበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል።
ለመሆኑ ቀንደኞቹ የብልፅግና ወንጌል (የብልፅግና ወንጀል ብለው እመርጣለሁ) ጀማሪዎች ፣ ተጠቃሚዎችና አዛማቾች እነማናቸው?  ምን ያህልስ አያተረፉበት ነው? በሃገራችንስ እነማናቸው በግልፅ ይህንን የዲያቢሎስ ትምህርት የሚያስተምሩ? በእርግጥ
እነኝህ ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆነ የወንጌል መልእክት ቀያጮች ሌላው ቢቀር በፎቶአቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ አይደሉም። በሃገራችን በመንፈሳዊ ስም የሚታተሙ የአሉባልታ ሜጋዚኖች ፎቶግራፋቸውን እየደረደሩ ታላላቅ የእግዚኣብሄር ሰዎች እያሉ ያስተዋውቁዋቸዋል። እንዲያውም አንዱ ሜጋዚን እኔ በ2009 አ. ም ኢንተርቪው የሰጠሁበት ሜጋዚን ነው።
ኬነት ሄገን
የብልፅግና ትምህርት አባት። በኬነት ሄገን እምነት ሰው የሚፈልገውን ነገር የልቡን መሻት ሁሉ ሃብት ቢሆን፣ ጤንነት ቢሆን፣ በእምነት ከተናገረው ያገኘዋል። ይህም “የቃል እምነት በሁዋላም የብልፅግና ወንጌልን ትምህርት የወለደ ነው። በኬነት ሄገን እምነት “ቃል ከእመነት ጋር ከሰው አንደበት በወጣ ጊዜ “ሃይል ይፈጥራል። ያም ሃይል ነገራት እንዲፈፀሙ የማድረግ ችሎታ አለው (name it claim it)። ነገር ግን ትኩረቱ የአንደበቱ ቃል ላይ ሳይሆን እምነቱ ላይ ነው።  “እመነቱ ላይ ማተኮሩ ደግሞ ለዚህ ትምህርት አስፋፊዎች ደህና መደበቂያ እንደፈጠረላቸው እሙን ነው። ምክንያቱም ሰዎች እንደተባለው “በእምነት ቃል የጠየቁትን ሳያገኙ ቢቀሩ ሰባኪው እምነት ስለሌለህ ነው ወይም እምነት ስለሌለሽ ነው በሚል ሰበብ ሃላፊነቱን ከራሱ ላይ ማውረድ ስለሚችል ነው። ከዛም በላይ እምነት የለሽም፣ እምነት የለህም በሚል ልባስ ማጭበርበሩን ይቀጥላል ማለት ነው።
ኬነት ሃገን እንደምን እዚህ ትምህርት ላይ እንደደረሰ ሲናገር እንዲህ ይተርከዋል፡
“በፀሎት መንፈስ ባለሁበት በአንድ ወቅት ኢየሱስ ተገልፆ ብእርና ወረቀት አዘጋጅና የምነግርህን ፃፍ ኣለኝ። ኢየሱስም ከአንድ እስከአራት ያሉ መመሪያዎችን እንድፅፍ ነገረኝ።
1ኛ/ የልብህን መሻት በአንደበትህ ተናገረው (confess it). ክፉም   ሆነ መልካም የምትፈልገውን ተናገረው።
2ኛ/ በአንደበትህ የተናገርከውን አድርገው።
3ኛ/ ተቀበል። ከሰማያት ሃይል ምንጭ ጋር ግንኙነት መፍጠርና  መቀበል። ይህም ግንኙነት እውን የሚሆነው በእምነት  አማካኝነት ነው።
4ኛ/ ተርከው። የሆነልህን ነገር ለሌሎች ንገር።
ኬነት ሃገን ከኢየሱስ አገኘሁ ያላቸውን መመሪያዎች ተከታዩና ሌላው የብልፅግና ወንጌል ጭልፊት ኬነት ካፕላንድ አጠር አድርጎ ሲያቀርበው በሶስት ደረጃ ያጠቃልለዋል። እንደሱ (ካፕላንድ) አባባል ሰው የፈለገውን ለማግኘት የሚጠበቅበት የሚፈልገውን ነገር በአእምሮው እያመላለሰ ማየት (visualization) ፣ ከዛ በሁዋላም የተፈለገውን ነገር ከመፀሃፍ ቅዱስ ጋር ማመሳከር፣ በመጨረሻም ነገሩ ሆኖአል ብሎ መናዘዝ (በአንደበት መናገር)። በቃ ይህው ነው። ንብረት ሆነ ሹመት ሆነ ገንዘብ ሆነ ጤንነት ሆነ ሌላም ሌላም ኬነት ሃገንና ኬነት ካፕላንድ ባመጡት መንገድ ያለምንም ውጣ ውረድ ወዲያው ይገኛል ማለት ነው። የብልፅግና ወንጌል ቅዠት ማለት እንግዲህ ያ ነው።
ኬነት ሄገን ያመጣው መዘዝ አለምን ሁሉ እያገማ ነው። እንደ ኬነት ካፕላንድ ሌላው የኬነት ሄገን ተከታይ በትልቅነቱ በአለም አንደኛ የሆነው በደቡብ ኮሪያ ያለው ቤተክርስትያን መጋቢ ፖል ዮንጊ ቾ እነኛን የኬነት ሄገን አራት መመሪያዎችን አሻሽሎና አስጊጦ፣ “የምርት ህግ (Law of Incubation) በሚል መጠሪያ አቅርቦአቸውል። መጋቢ ቾ ሰው የሚፈለገውን ነገር ከእግዚኣብሄር ለማግኘት በመጀመሪያ ሰው የማያሻማ አላማና ግብ ይኑረው፣ ከዛም ያንን አላማና ግብ በአእምሮው ይሳለው፣ በህሊናው አጥርቶ ያልመው፣ ቀጥሎም ራእዩን እውን ምርት ያድርገው ፣ በመጨረሻም በአንደበት ኑዛዜ ሃይል ወደ ተጨባጭነት ያምጣው ይላል። የአለመኞች ቅዠት ብዬዋለሁ እኔ።
ኬነት ሃገን ኢየሱስ አናገረኝ ቢልም በእርግጥ ጌታ አናግሮት ይሆን አይሁን ማረጋገጫ ምንም ነገር አልነበረም፣ ዛሬም የለም። እንዲያውም ሳዮኮሎጂስቶች የሚያወሩትን የአእምሮ ሃይልን የመጠቀም ዘዴ ይመስላል። ችግሩ ግን ማንም ቁጭ ብሎ ገንዘብ ገንዘብ ስላለ ወይም ዶሮ ወጥ ዶሮ ወጥ ብሎ በአንደበቱ ስለተናገር ገንዘቡንም ሆነ ዶሮ ወጡን ያገኛል ማለት አይደለም። እንዲያው የህልም ቅዠት ነው። ኬነት ሄገንም ያፈራውን ሃብት ያፈራው እሱ ከኢየሱስ አገኘሁ ባላቸው አራት መመሪያዎች ሳይሆን በቀጥታ ምእመናኑን በመለመን ነው። ኬነት ሄገን ኢየሱስን ሳይሆን ያየው በልቡ ውስጥ ሲመላለስ የነበረውን ሃይለኛ የገንዘብ ምኞት ከአእምሮው ጉዋዳ ሞልቶ የፈሰሰውን ቅዠት ነበር። ሰው ምን እምነት ቢኖረው ምን የሚፈልገውን ነገር በአንደበቱ ሲለፈልፍ ቢውል ጉሮሮውን ያመዋል እንጅ ጠብ የሚል ነገር የለም። ኢየሱስን መከተል እንካችሁ ለእንካችሁ ወይም መስጠትና መቀበል ላይ ያተኮረ ከሆነ ክርስትና ቁማር ጨዋታ ይሆናል። ኢየሱስ የዘለአለምን ህይወት በነፍሱ ሰጥቶናል ካልን ትኩረታችን ይህንን ህይወት ያላገኙ እንዲያገኙት ተግተን መስራት ላይ መሆን አለበት እንጅ ከንቱ የሆነውን የአለም ቁሳቁስ ማትረፍ ላይ ሊሆን አይገባውም።
ክራፍሎ ዶላር ( ግምት ጥሬ ሃብት 27 ሚሊዮን ዶላር) ውነትም ዶላር።
በሰኔ ወር 2015 የአሜሪካን ሃገር ዜና አሰራጮች ፓስተር ክራፍሎ ዶላር የ65 ሚሊዮን ብር የግል ጄት እንዲገዛለት በጠየቀው መሰረት የሚኒስትሪው (የክራፍሎ ዶላር የግል ሚኒስትሪ) ቦርድ ሊገዛለት ዝግጁ እንደሆነ ማስታወቁን ገለፀ። ታሪኩን ጠለቅ ብዬ በሌላ ክፍል እመጣበታለሁ። ነገር ግን ይህ ሰው አማኙን ህዝብ የግል ጄት ግዙልኝ ብሎ ማስታወቂያ መጀመሪያ ሲያወጣ የአሜሪካ ህዝብ ስላወገዘው ማስታወቂያውን አውርዶ ነበር። ነገር ግን ውስጥ አዋቂዎች እንደገለፁት የራሱ ሚኒስትሪ ቦርድ አባላት የሚንስትሪው ፓስተርና ባለቤት መጋቢ ክራፍሎ የጠየቀውን ከመፈፀም ማሸግሸግ ስለማይችሉ የሚፈልገውን ጄት ለመግዛት ተገደዋል ማለት ነው። የግል ሚኒስትሪ ወይም ቤተክርስትያን ያለው ማንም ሰው መወስለት ከፈለገ በአገልግሎቱ ስም ከምእመናን የሚያገኘውን ንብረት ሁሉ በፈቀደው መንገድ መመንዘር ይችላል። የክራፍሎ ዶላር ምሳሌ ያንን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።
ገንዘብ ስጡ እግዚኣብሄር ሃብታም ያደርጋችሁዋል ብለው ከሚሰብኩት ቀንደኛ የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች አንዱ ነው። በዚህም ሳቢያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከአማኞች እየሰበሰበ የናጠጠ ኑሮ ይኖራል። ቢዝነሶችና ሪል ኤስቴት (Real estate) አሉት። ይህ ሁሉ የግል ንብረት ከምእመናን በየሳምንቱ ገንዘብ ስጡ ሃብታም ትሆናላችሁ እያለ በማታለል በሰበሰበውና በአስራት አማካኝነት  የተገኘ ነው ገንዘብ ነው። የአሜሪካ መንግስትም ይህንኑ በአንክሮ ሲታዘብ ከቆየ በሁዋላ በአንድ ወቅት የሰበሰበውን ሃብት በተመለከተ የህግ ምርመራ እንዲደረግበት ከሌሎች አምስት የብልፅግና ወንጌል ሸፍጠኞች ጋር ለምርመራ ይፈልገው እንደነበር ይታወቃል።
ክራፍሎ ዶላር ከአባላቱ የሚሰበስበው ገንዘብ እንዳይጉዋደል ከትምህርቱና ከስብከቱ ትልቁ ክፍል የአስራት መክፈል ጉዳይ ነው። አስራት በታማኝነት ያልከፈሉትን እንደ ወንጀለኛ ነው የሚቆጥራቸው። ገንዘብ የለመዱ ሰባኪዎችና መጋቢዎች አንዱና ዋና መለያቸው መድረክ ላይ በወጡ ቁጥር በስብከታቸውና በትምህርታቸው ሁሉ አስራትና ምፅዋእት ወይም ስጦታ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ላይ ነው። አስራት ያልከፈለን ሰው እንደባለአዳ ያሳድዱታል፣ ያኮርፉታል፣ ፊት ይነሱታል። የምቾት ኑሮአቸው እንዳይቀርባቸው ከእግዚኣብሄር ሙዳይ የሚሰርቁት እንዳይጉዋደል አስራት አስራት አስራት ብለው ይወተውታሉ። ሌሊትም ተኝተው በእንቅልፍ ልባቸውም አስራት አስራት እያሉ ሚስቶቻቸውን አላስተኛ ሳይሉ አይቀሩም (ቀልድ አይደለም)።
ክራፍሎ ዶላር ባንድ ወቅት ህዝቡ ፊት ሲናገር “በኢየሱስ ደም ምህረት ባይሆን ኖሮ አስራት የማይከፍሉ ሁሉ በድንጋይ ይወገሩ ነበር ካለ በሁዋላ ፣ የራሱን ምኞት ሲገልፅ “አስራት ለስጡት በሙዚቃ የታጀበ መልካም አቀባበል ይደርግና አስራት ላልሰጡት ግን ዱርዬ ዱርዬ እየተባሉ በእግርብረት ይታሰሩና በሁዋላም በሰልፍ ተደርድረው እንዲቆሙ ከተደረገ በሁዋላ ኢየሱስ በኡዚ ሁሉንም ሲረሽናቸው” ያ ነው የሚታየኝ አለ።
እንግዲህ ይህን የመሰለ ውስጣዊ ቁጣ ይዞ የሚዞረው ክራፍሎ ዶላር እስከሰላሳ ሺ የሚደርሱ ምእምናን መንፈሳዊ መሪ ነው። በአዲስ ኪዳን ሰዎች አስራት መስጠታቸውና  አለመስጠታቸው የውዴታ እንጅ የግዴታ አይደለም። በእግዚኣብሄር ቃል መሰረት አስራትና ስጦታ በቤተክርስትያን የሚሰጡት በእግዚኣብሄር ቤት ውስጥ መብል ይሆን ዘንድ ነው። የተራቡና  የደህዩ እንዲሁም ሽማግሌውችና አሮጊቶች ቤተክርስትያን ተርበው መጥተው ተርበው እንዳይመለሱ ነው። ክራፍሎ ዶላር ግን የራሱን ከርስ መሙያ፣ የሆሊዉድ ደረጃ ኑሮውን ለሞኖሪያና የግል ጄት መግዥያ አድርጎ ይጠቀምበታል።
ክራፍሎ ዶላር መጀመሪያ ወደ አገልግሎት ሲመጣ ጤናማ ወንጌልን ለመስበክ ነበር ጥማቱ። አጀማመሩ መልካምና ያማረ ነበር የዛሬን አያድርገውና። ዛሬማ ክራፍሎ ዶላር ግንባር ቀደም የብልፅግና ወንጌል” (prosperity Gospel; name it claim it; word of faith) አሰራጭና ገንዘብና ምቾቱ ያበላሸው ሰው ነው።
ከፅሁፍ ምርምር እንደምናየው ክራፍሎ ዶላር አገልግሎቱን የጀመረው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምግብ አዳራሽ ውስጥ በ1986 ነበር። በጊዜው በጣት ለሚቆጠሩ  ተማሪዎች አገልግሎቱን እየሰጠ ያለነቀፌታና ያለነውር ቢቆይም ውሎ አድሮ ግን ስብከቱና ትምህርቱ የህይወት ባለፀግነትን ሳይሆን የገንዘብ ባለፀግነትን የሚያጎላ ሆኖአል። የኢየሱሱን ጌትነት፣ የክርስትያኖችን ፈተናና መፃተኝነት፣ በኢየሱስ ማረፍንና መጥገብን፣ ብሎም መታመንን፣ ከስብከቱ እያስወገደ የገንዘብን ታላቅነትና ነፃ አውጭነት እየለፈፈ ይኖራል። ደህነት ከእምነት ጉድለት የሚመጣ ነው ይላል ክራፍሎ ዶላር። ስንቶች የታመኑ ክርስትያኖች በኑሮ ውጥረት ሲማቅቁ ስናይ እንደ ክራፍሎ አባባል ለደህነቱ የጋረዳቸው እምነተ አናሳ መሆናቸው ነው ማለት ነው።ስለዚህም የራሳቸው ጥፋት መሆኑ ነው።መፀሃፍ ቅዱስ ስለደሃዎች በተለያየ ስፍራ ሲናገር በአማኞች መካከል በማጣት የሚንገላቱ ቅዱሳን እንዳሉና ስለእነሱም እግዚአብሄር እንደሚገደው ነው የምናየው።የብልፅግና ወንጌል ጮካዎች እንደሚሉት ደህነት የእምነት ማነስ ምልክት አይደለም።የብልፅግና ወንጌል ትምህርት  ግን በአንደበት ኑዛዜና በእምነት ብቻ ደህነትና ደዌ ሁሉ በቅፅበት ይጠፋሉ ይለናል። በእነሱ አባባል ባለፀጋ ያልሆኑ አማኞች በማጣት የሚቆራመዱት “ሃብታም እንሆናለን ወይም “ሚሊዮን ዶላር በፅብአቱ እናገኛለን ብለው በእምነት መፈክር ስላላሰሙ ነው ማለት ነው። ስለዚህም የራሳቸው ጥፋት ነው ማለት ነው። በክራፍሎ ዶላር እምነት ክርስትያን መታመም የለበትም። ጤና ያጣ ክርስትያን  በበሽታ የሚሰቃየው ከእምነት ማጣት የተነሳ ነው እንጅ እምነት ኖሮት ቢሆን ኖሮ ተፈውሶ ከአልጋው እመር ብሎ በተነሳ ነበር። ክፉ አልመኝለትም ነገር ግን እሱ የታመመ ቀን ምን ሆኜ ነው ይል ይሆን??? የሚገርመው በአዲስ ኪዳን ተፅፎ እንደምናየው ጳውሎስ በራስ ምታትና በአይን ህመም ይሰቃይ ነበር። እግዚአብሄር ግን ለምክንያት ነበር ያልፈወሰው ። ጳውሎስ በተደጋጋሚ ለፈውስ ፀልዮ እግዚአብሄር ግን ከበሽታው ሊፈውሰው እንዳልፈቀደም ይናገራል። ጵውሎስ የራስ ምታት በሽታውን ከእግዚአብሄር የተሰጠው መጎሸሚያና ደካማነቱንም የሚያስብበት መንገድ ብሎ በቀና መንገድ ተቀብሎታል (2 ቆሮንጦስ 12 ፡ 7) ።
ክራፍሎ ዶላርና ሌሎችም የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች ጳውሎስን የሚያህል የእመነት ሰው እምነት አንሶህ ነበር በራስ ምታት በሽታ ስትሰቃይ የኖርከው ይሉት ይሆን? እነሱ ምን የማይሉት ነገር አለ?  የሌብነት ስራቸውን ለማስተባበል የማይሉት ነገር አይኖርም። በሽታ ከጀርምና ራስን በጥንቃቄ ካለመያዝም ይመጣል። ሰዎች ለራሳችን ሃላፊነትን እንድንወስድ እግዚኣብሄር የረቀቀ አእምሮ ሰጥቶናል። አንዳንድ ግዜ በሽታም ሆነ ደህነት የህይወት ትምህርት ይሰጠናል።ያሸናል።
ክርስትና ህይወትና የገንዘብ ፍቅር በአንድ አይሄዱም ለሚሉት ተቃዋሚዎቹ መልስ ለመስጠት ክራፍሎ ዶላር ብዙ ይቀባጥራል።
“”መንፈሳዊ አገልጋይ ነኝ ትላለህ የምድራዊ  ሃብትን ደግሞ ታጠራቅማለህ ፣ እነደመንፈሳዊ መሪም ራስህን ቆጥበህ አትኖርም”
ብለው ታዛቢዎች ሲወቅሱት ክራፍሎ ዶላር ኢየሱስም የግል ሃብት የነበረው ባለፀጋ ነበር ብሎ በመፀሃፍ ቅዱስ በብዙ ስፍራ ስለኢየሱስ ማደሪያ የለሽነት የተፃፈውን እውነት ይደመስሰዋል። ኢየሱስ ሃብታም ነው ያለበትን ምክንያት ወንጌላዊ ዶላር ሲገልፅ ኢየሱስን ያንገላቱትና ያሰሩት የሮማ ወታደሮች በለበሰው ጨርቅ የተሻሙበት ምክንያቱ ጨርቁ ውድ ስለነበረ ነበር ይላል። ያም የሚያሳየው ኢያሱስ ከሃብታምነቱ የተነሳ የሚለብሰው ውድ የዲዛይነርስ ልብስ አንደነበረና ሃብታምም ስለነበረ ነበር ብሎ ተናግሮኣል። ጨምሮም ሲናገር በአዲስ ኪዳን እንደተጠቀሰው ኢየሱስ የግል ገንዘብ ያዥ እንዲኖረው የተገደደበት ምክንያት ሃብታም ስለነበረ ነው ብሎ የማይረባ ምክንያት ሰጥቶኣል። ጥያቄው ግን የሮማ ወታደሮች በኢየሱስ ጨርቅ መሹዋኮታቸው ውድ ጨርቅ ስለነበረ ነው? ወይስ በጊዜው ታዋቂ የነበረው ኢያሱስ የለበሰው ጨርቅ ስለነበረና ለማስታወሻ (souvenir) ያህል ሊወስዱት ስለፈለጉ ነበር? በዘመናችን እንደምናውቀው የታወቀ ሰው የተገለገለበትን ትልቅም ሆነ ትንሽ ቁሳቁስ  ለማግኘት ሰዎች ባለ በሌለ ሃይላቸው ይረባረባሉ አንዳንዴም በሚሊዮን በሚቆጠር ብር ገዝተው ያስቀምጡታል።  ያ ማለት ታዋቂው ሰው ለቁሳቁሱ የግዴታ ብዙ ገንዘብ አውጥቶበት ነበር  ማለት አይደለም። አስታውሳለሁ ትውልዱ በሜናሶታ የነበረው ባብ ዴላን (Bob Daylon) የተባለው ታዋቂ ዘፋኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ስቱዲዮ ገብቶ የተጫወተባትን የደህነት ጊዜ ቦክስ ጊታሩን ለሽያጭ ሲያውል አድናቂዎቹ ተረባርበው ከግማሽ ሚሊዮን  ብር በላይ በሆነ የጨረታ ዋጋ ገዝተውታል። ጊታሩ በዚህ ዘመን ዋጋ ምናልባት ከ150 ዶላር በላይ አያወጣም። ነገር ግን የታወቀ ሰው የተጫወተበት ስለነበር ውድ እቃ ሆነ። የሰውን ሃብታምነትና ደሃነት በአንድ ካኔቴራ ወይም ጃኬት መገምገም አይቻልም። ክራፌሎ ዶላር ለታወረበት የገንዘብ ፍቅርና የማታለል ተግባር ማስተባበያ (excuse) ሲሰጥ በአዲስ ኪዳን በብዙ ስፍራ በማያሻማ ሁኔታ የተፃፈውን የኢየሱስን ማደሪያ የለሽነት ሽምጥጥ አድርጎ ክዶአል። ሉቃስ 9፡58 ማቴዎስ 8፡20  ላይ ለቀበሮዎች ዋሻ ኣላቸው ለወፎች ጎጆ ኣላቸው የሰው ልጅ ግን ለራሱ ማደሪያ እንኩዋን የለውም ተብሎ የተፃፈውን ክራፍሎ ዶላር ዘንግቶታል። ኢየሱስ ተልእኮው የእግዚኣብሄር መንግስት ቀርባለችና ንስህ ግቡ የምትለው ስትሆን የክራፍሎ ዶላርና የጠቅላላው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች ተልእኮ ግን ምድራዊ ሃብትና የባንክ ሳጥናችሁን እንዲያብጥ ገንዘብ ስጡ (ስጡን) የሚል ነው።የሚሰቀጥጠው ነገር ግን ይህንን ቆሻሻ ስራቸውን ከእምነት ጋር ሊያዛምዱት መሞከራቸው ነው።
ብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎችን ከምንለይባቸው ምልክቶች ሌላው መንገድ ደግሞ ስለእምነት ዘር (seed of faith) መዝራት ደጋግመው ያወራሉ ። እነሱ ደጋግመው የሚሰብኩት የእምነት ዘር ግን ኢየሱስ ከሚያስተምረው የእምነት ዘር የሚለይበት አንድ ትልቅ ነገር አለው። የእነሱ የእመነት ዘር አላማው ከመለኮታዊ ጉዳይ ጋር ሳይሆን ከምድራዊ ከረንሲ (currency) ገንዘብ ጋር የተያያዘ በጨ ጠቆረ ቁማር ነው።
የብልፅግና ወንጌልን ትምህርት ክራፍሎ ዶላር የወሰደው ኦራል ሮበርትና ኬነት ሃገን ከተባሉት የቴሌቪዥን ሰባኪዎች ነው። ከአህያ የዋለች ጊደር ምን ተምራ ትመጣለች እንደተባለው ወንጌላዊ ክራፍሎ ዶላር ከሱ የቀደሙት ብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች ከቤተክርስትያናቸው ህዝብ በሚለቅሙት ገንዘብ ሚሊዮነር እንደሆኑ ሲያይ እኔስ ከአይስ ክሪሙ (icecream) ድርሻ ለምን አይኖረኝም ብሎ የእነሱን አሰራር ጠንቅቆ አጠናው።እንደገመተውም ከሚኒስትሪው (World Changers Church International) አባላት በጥቂት አመታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሰበሰበ።
ዛሬ የ58 አመት ግድም እድሜ ያለው ክራፍሎ ዶላር
1/ የ 18 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቢያ አዳራሽ
2/ 5 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ የግል ጄት ቡዋላም በ2015 በኣደባባይ ህዝቡን ጠይቆ ከ 60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያወጣ አዲስ ጄት
 3/ 2 ሮልስ ሮይስ (Rolls Roce) መኪናዎች
4/ 100 ተጨማሪ መኪናዎች
 5/ 1 ሚሊዮን ዶላር (16 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር) ያወጣ የግል ቤት ባለቤት ነው።
ክራፍሎ ዶላር ሮልስ ሮይስ መኪናዎቹን እንዴት ልትገዛቸው ቻልክ? ተብሎ ሲጠየቅ የቤተክርስትያን አባሎች በስጦታ መልክ ሰጥተውኝ ነው ብሎ ተናግሮአል። እውነቱ ግን እሱ እራሱ ከአፉ አውጥቶ ግዙልኝ አላለ ይሆናል ነገር ግን ስለእሱ የሚናገሩለት ጋሻ ጃግሬዎች አሉት። ለእነሱ የሚፈልገውን ይናገራል እነሱ ለህዝቡ ለፓስተራችን ይህንን አናደርግለት ብለው ከፓስተሩ ሳይሆን ከራሳቸው የመጣ ሃሳብ አስመስለው ይናገሩለታል። ህዝቡም እንዳይቃወም በሁዋላ የሚመጣበትን ስለሚያውቅ በሃሳቡ ይስማማል። ያ ሃሰተኛ አይኑን በጨው ያጠበ እንግዲህ ስጦታ ብሎ የሚያወራው በእንዲህ ኣይነቱ ዘዴ ያገኘውን ነው።
ይህ አሰራር የሃገራችን ብዙ መጋቢዎች በቤተክርስትያን ገንዘብ ለግላቸው አንድ ነገር መግዛት ሲፈልጉ  የሚጠቀሙበት መንገድ ነው። ለቅርብ ሰዋቻቸው (እኔ ፍርፋሪ ለቃቃሚዎች ነው የምላቸው) ሃሳቡን ሹክ ይላሉ፣ እነዚያ ጋሻ ጃግሬዎች ደግሞ ህዝቡ ዘንድ ሄደው ለፓስተራችን ይህን እናድርግለት ይላሉ። እንዲያው ለወጉ ያህል ቅስቀሳ ያደርጋሉ እንጅ ሃሳቡን መቃወም የሚችል ማንም ኣይኖርም ማንም አይደፍርም።ወዲያው ህዝቡ ለፓስተሩ እንዲህ አደረገለት ተብሎ ይወራል። እውነተኛ ክርስትያን የሆነ አገልጋይ ከፍተኛ ወጭ ለሚጠይቁ ተብለጭላጭ ነገሮች አይጎመጅም። ራሱን ይገዛል። ብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች ግን አላማቸው ሃብትና ባለፀግነት እንጅ መለኮታዊ ክንውን አይደለምና ይዋሻሉ ፣ያምታታሉ ፣እጃቸው ከቤተመቅደስ ሙዳይም ውስጥ አይወጣም።
ክፋሎ ዶላር ያጠራቀመውን ሃብት ከየት አመጣህው ተብሎ ሲጠየቅ የእግዚኣብሄር ስጦታ ነው ወይም የእግዚኣብሄር በረከት ነው ብሎ ይመልሳል። እውነቱ ግን ማንም የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ የሚያከማቸው ምድራዊ ሃብት ከእግዚኣብሄር የተሰጠው ሳይሆን ከሚያታልላቸው ምእመናን ኪስና ባንክ የተሰበሰበ ነው። ክራፍሎ ዶላር በሩን ዘግቶ ፀልዮ ገንዘብ ከሰማይ አልወረደለትም ወይም ስራ ስርቶ በላቡ አላተረፈም። ክራፍሎ ዶላር በየሰንበቱ በቴሌቪዥን የሚከታተለውን ህዝብ በገንዘብ ወሬ እያደነቆረና ገንዘብ ካልሰጣችሁ የእግዚኣብሄርን ህግ ጥሳችሁዋል እያለ በማስፈራራትና በልመና እያሰለቸ የሰበሰበውን የሰው ገንዘብ ነው የእግዚኣብሄር በረከት የሚለው። የብልፅግና ወንጌል ወንጀል አምን ላይ ነው ያልን እንደሆነ መልሱ ቀላል ነው። ብልፅግና ወንጌል ሰባኪውን እያደለበ ምእመናኑን የሚያከሳ ነው። መጋቢው ያበልፅጋል አማኙ ህዝብ ግን ይደሀያል።
የእግዚኣብሄርም ህዝብ ላም አለኝ በሰማይ አያለ ሰባኪው ቃል የገባለትን አስር እጥፍ ገንዘብ በመጠባበቅ አንጋጦ ይነጋለታል
ክፍል ሶስት ማክሰኞ ጌታ ቢፈቅድ
Filed in: Amharic