>

መሪነት ጥበብና ማስተዋል እንጂ ኃይል አይደለም !! (በረከት ኣብርሃም (ቲሞ))

መሪነት ጥበብና ማስተዋል እንጂ ኃይል አይደለም !!

 በረከት ኣብርሃም (ቲሞ)

* ” የተኩላዎች ጥፋት ፤ ለበጎች ዋስትና ነው !!”
 
የአንጋፋዎቹ የሻዕብያና ወያኔ ደርቢ፡ የመጨረሻው ዙር የዋንጫ ፍልሚያ የደረሰ ይመስላል። ከሽምቅ ተዋጊነት ወደ መንግስትነት የመጡት እነኝህ ሃይሎች፡ ለሩብ ክፍለ ዘመን የአፍሪካው ቀንድ የፖለቲካ ስህበት ማእከል ሆነው ዘልቀዋል።
በኢጋድም ሆነ በአፍሪካ ህብረት፡ የምስራቅና የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ሚና በመለየት ጎራ እንዲፈጥሩና፡ አካባቢው ሰላም አልባ ቀጠና እንዲሆን ሰበብ ሆነዋል። አንዱ አንዱን ለመጣል የሃያላንና ሃብታም ሃገራት ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነዋል። ይህንን የማያምን ወይም የማይቀበል ካለ፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የአካባቢውና የምካከለኛው ምስራቅ ሃገራትን የፖለቲካ አስላለፍ ማጤን ሁነኛ መልስ ነው። ልክ እንደ ሞኖሮቪያና ካዛብላንካ የሁለት ካምፕ ስልታዊ ጥቅምና አቋምን ያስቀደመ ቲፎዞነት ነበር ፎርሜሽናቸው።
እነዚህ ስትራቴጂካል ወዳጅ የነበሩ ድርጅቶች፡ መንግስት ከሆኑ በኋላ፡ የሁለቱን አገር ወንድማማች ህዝቦችን ደም፡ በከንቱ እልህ እንዲፈስ አድረገዋል። በሁለት አመራሮች እልህ የተጀመረው መካረር፡ ወደ ሁለቱ ድርጅቶች መዋቅር ተሻግሮ፡ አጉራ ዘለል ጀብደኝነት በመፍጠር፡ በሰው ህይወትና በአገር ሃብት ነበር፡ አቅም መፈታተሹን የጀመሩት።
ሁለቱ ባላንጣዎች በድንበር ሰበብ የጀመሩትን ውዝግብ በህጋዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፡ በለመዱት የጦርነት ቋንቋ ሊንጋገሩ፡ የሸምጋዮችን ጠረጴዛ ገፍተው፡ አንዱ አንዱን ለማጥፋት የጦር መሳርያ ሸመታ ላይ ነው የተሯሯጡት። የሃይል አማራጭን መርጠው በጦርነት አቅም ከተፈታተሹም በኋላ፡ በድርድር ወደ ፍርድ ቤት ሄደው ይግባኝ የሌለው ውሳኔ ቢያገኙም፡ ከህግ በላይ የግለሰቦች ስሜት ነግሶ No, Peace No, war በሚል ድባብ ውስጥ፡ አንዱ አንዱን ለመቅበር ያልተሸረበ ሴራ፤ ያልተቆፈረ ጉድጓድ አልነበረም።
ከኢጋድ እስከ ሰነዓ ፎረም ፤ ከአፍሪካ ህብረት እስከ መንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት፡ በዲፕሎማሲው ወያኔ የበላይነቱን ሲይዝ፡፡ ኤርትራ ላይ ማእቀብ በማስጫን የምእራባውያን ፋይናሻል እርዳታና ብድር እንዳታገኝ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ክራክ በመፍጠር፡ ስርዓቱ አልወደቀም እንጂ ለተወሰነ ጊዜ ተሸመድምዷል።
ሻዕብያም ከግብጽ እስከ ሊቢያ ከኳታር እስከ ዩናይትድ አረብ ኢማሬትስ ፤ ከአልሸባብ እስከ ኦጋዴን ነጻ አውጪ፡ ከኦነግ እስከ አርበኞች ግንቦት ሰባት፡ ከትህዴን እስከ ሲዳማ ሓርነት ወዘተ አስልጥኖ እያስታጠቀ፡ በጎሪላ ትጥቅ ትግል የበላይነቱን ይዞ፡ የወያኔ የጎን ውጋት በመሆን፡ የመከላከያና የጸጥታው ተቋም ራስ ምታት ሆኖ ያደረሰው ኪሳራና ውድመት ስለማይገለጽ እንጂ፡ ይህ ነው አይባልም።
የአርበኞች ግንባርና የትህዴን በርካታ ጥቃትን ጨምሮ በኦጋዴን ሶስት የውጪ ሃገር የማእድን ዳሰሳ ተቋማት ላይ በኦብነግ የተፈጸመው ዘጠኝ ቻይናውያንና በርካታ ዜጎች የተገድሉበት ሚሽን ላይ፡ ከጥናት እሰከ ጥቃት የተሰረው ዘመቻ አንድ አብነት ነው።
በኤርትራም ‘ቢሻ’ የወርቅ ማዕድን ላይ የተካሄደው የድሮን ጥቃት ተመጣጣኝ ግብረ መልስ ተብሎ ይታሰበል። ወያኔና ሻዕብያ አለማቀፋዊ የፖለቲካ ተሰሚነትና ትኩረት ለማግኘት፡ በህንድ ውቅያኖስና በኤደን ባህረ ሰላጤ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ እገታ የሚፈጽሙ፡ በፈለጉ ጊዜ ለእነሱ ቅድሚያ የሚታዘዙ ሶማላውያን ፓይረሲ (የባህር ላይ ሸፍታ) ሳይቀር ያደራጁ ግንባሮች ናቸው።
ለሁለት ዓመት በአሜሪካና በኢጋዳ/ኢትዮጲያ አደራዳሪነት ኬንያ ላይ የተመሰረተው የሶማልያ የሽግግር መንግስት፡ የኢትዮጲያ ድንበር አጠገብ የምትገኘው ባይድዋ ከተማ ላይ ተወስኖ፡ በኢትዮጲያ ጦር እየተጠበቀ ለረጅም ጊዜ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ በኋላ በኢትዮጲያ ሰራዊት ሙሉ የማጥቃት ዘመቻ ታግዞ ሞቃዲሾ ቢገባም፡ እስካሁን ድረስ በ’አሚሶም’ ጥበቃ ስር ነው። በሶማልያ ኣማጺያን ጉዳይ ኤርትራ ሁለት ጋዜጠኞችና አንድ የመከላከያ ስትራቴጂሺያን በአጠቃላይ ሶስት ሰዎች እንደተያዘባት በማስረጃ ቀርቦ የማእቀብ አርጩሜ እንዲያርፍባት የኢጋድ አባል ሃገራትን ያለተቀናቃኝ (ኤርትራ ከኢጋድ ራሷን ስለ አገለለች) ትልቁን የማስተባበር ስራ የሰራው ህወሓት ቢሆንም፡ ኢሳያስ ግን በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እገዳ አልተንበረከከም። በሶማልያ ጉዳይ አሁንም ኣክቲቭ ነው።
የኣስመራው የሶማልያ የሽግግር መንግስት ኮንፈርንስ !
በህይወት ላለው ብቸኛ የአሊታሐዱ መሪ ጣይር ኣዌስ ታላቅ ክብርና ታዝዥነት ያላቸው የጦር አበጋዞች፡ በሃገሪቱ አስፍሪ የሃይል ሚዛን በያዙበት ጊዜ ነበር የአስመራው ኮንፈረንስ የተጀመረው።
(አሊተሐድ በኬንያ እና ታንዛንያ-ዳሬ ሰላም የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት የፈጸመ የአልቃይዳ ክንፍ ነው። ከአመራሮቹ ውስጥ ጣይር ኣዌይስ ብቻ ነው ከአሜርካን ግድያ አምላጦ ተደብቆ በህይወት ያለው። ኣዌስ በአሸባሪዎች መዝገብ ውስጥ ሰፍሮም ለአገሩ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጥ አደገኛ ሽማግሌ ነው)
በህዝብ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ” የሶማል እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” በእነ ሼክ ሸሪፍ ተወክሎ፡ ከዲያስፖራው ቡድን እነ ሁሴን አይዲድ፣ ዘካሪያ መሓመድ፣ አስመራ የመሸገው ጣይር ኣዌስ ወዘተ ፓርላሜንተሪ አድርጎ፣ ከሁሉም ጎሳና ንዑስ ጎሳ የተወከሉ መንግስት ተመስርቶ፡ የአገሪቷ መሪ ሼክ ሸሪፍ እንዲሆን ወስነው፡ የስልጣን ክፍፍሉን ፍትሓዊ ባሉት መንገድ ደልድለው ጉባኤውን ጨረሱ።
ማስታውቂያ ሚንስቴር ‘ሃገር አዳራሽ’ ውስጥ፡ በነ ጠዓመ ጎይትኦም አደራዳሪነት በስንት ወዝግብ የሶማልያ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም፡ ከበርካታ የአረብ ሃገራት በሚደረግለት ፈንድ ነበር ኢሳያስ በፋይናንስ ስፖንሰር ያደረገው።
በዚያድ ባሬ ሶማልያ፡ የባይድዋ መንግስት፤ የአስመራ መንግስት፤ ፑንት ላንድና ፤ ሱማሊ ላንድ መገንጠል፣ የአልሸባብና የውጪ አክራሪ ሃይሎች ሃይማኖታዊ ፍላጎት ታክሎበት፡ አንድ ብሔር፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ እየተናገሩ መግባባት ተስኗቸው የሰላሙ መፍትሔ እየራቀና እየተወሳሰበ እንዲሄድ ካደረጉት መካከል፡ እነኝህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ግጽታ ድርጅቶች ናቸው።
በሶማልያ የውክልና ውጊያውን በአዝማችነት የመሩት እነኝህ ድርጅቶች፡ በደቡብ ሱዳንም ከሰልቫ ኬር እና ሪክ ማቸር ጀርባ ሆነው፡ በኤፈርት እና በቀይባሕሪ (09) የኢኮኖሚና የስለላ ተቋማቸው ሳይቀር፡ ለአዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን መሰረተ-ልማት እንዲውል ከአሜሪካ የተመደበውን በመቶ ቢልየኖች ዶላር፡ ከሙሰኛ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር ተሻርከው እየተሸቀዳደሙ፡ ተቀራምተው ነው የመዘብሩት፡፡
ከትግል ጀምሮ የንግድ ተቋማታቸው የሆኑት እነዚህ የድርጅቱ የኢኮኖሚ ክንፎች፡ ዛሬ ኤፈርትና ቀይሕ ባሕሪ (09) የተሰኙት ፈርጣማ የኢኮኖሚ ጡንቻ ያላቸው ግዙፍ ድርጅቶች ሆነዋል፡፡ እነዚህ የኮንትሮባንዲስት ባህርይ ያላቸው ማፍያ የንግድ ተቋማት፡ የሁለቱ ድርጅቶች ሃይልና ጉልበት ናቸው።
ሻዕብያና ወያኔ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካም ከፍተኛ ትንቅንቅ ሲያካሄዱ ቆይተዋል። ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ትግል ሲያካሂድ የነበረው የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ድርጅትን፡ ከመንግስቱ ሃይለማርያም በኋላ ኢሳያስ ተቀብሎ በስልጠናም ፤ በስንቅና ትጥቅም አያደራጅ፡ ትግሉ ለነጻነት እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሁንና ከዲንካ የሚወለደው ጆን ጋራንግ በአይሮፕላን አደጋ ከሞተ በኋላ፡ መንበረ ስልጣኑን የተረከበው ሳልቫ ኬር ግን፡ ወዳጅነቱን ያጠናከረው ከነ መለስ ጋር ሆነ። ይሄ ለኢሳያስ ትልቅ ሽንፈት ነው። በመጨረሻ እንደሆነው ከንዌር የሚወለደው ሪክ ማቻር ዲንካዎችን በቃችሁ ተራው የንዌር ነው ማለት ጀመረ። ሁለቱ ባላንጣዎችም በእጅ አዙር ውጊያውን በማቀጣጠል የተለያይ ውጤት እያስመዘገቡ፡ አንዳንዴም በኢጋዳ ካባ የሽምግልና ወግ አቋም በመያዝ የእርቀ-ሰላሙን ጫፍ ሲያወሳስቡት፡ ሶማልያም ደቡብ ሱዳንም ልክ እንደ ኤርትራና ኢትዮጲያ No, Peace No, war ሆነው እስካሁን አሉ።
#
ሁለቱ ባላንጣዎች ለረጅም ጊዜ በተለያየ ሜዳ በርካታ ተዝርዝሮ የማያልቅ ፍትጊያ ሲፋተጉ ቆይተዋል። ላለፉት አሰርታት ዓመታት በአለማቀፍ መድረኮች በበላይነት ነጥብ ሲያስቆጥር የነበረው ወያኔ፡ የዶ/ር አብይ አህመድን መምጣት ተከትሎ ከአራት ኪሎ ወደ መቐለ ‘ሺፍት’ በማድረጉ ነጥብ እየጣለ፡ በተገላቢጦሽ ተቀናቃኙ ሻዕብያ በዲፕሎማሲም በፖለቲካ ሴራም በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበ አስካሁኗ ሰዓት ደርሰናል።
አሁን ደግሞ ተጠባቂው የመጨረሻው ድርጅታዊ የሞት ሽረት ፍልሚያ ላይ የደረሱ ይመስላል። ጫወታውን በአዲስ አበባ ስታዲዮም ሻዕቢያ የበላይነቱን ይዟ እየመራ ነው።
የኢሳያስ ቡድን በዶ/ር ኣብይ ቡራኬ በኢኮኖሚ ምዝበራ ዘመቻ ስም (Economy Sabotage Operation) የወያኔን የኢኮኖሚና የስለላ መዋቅር እየበጣጠሰው ይገኛል። በፍልስጤሙ ‘PLO’ ታክቲክ በግለሰቦች ስም በንግድ ሚንስቴር የተመዘገበ የድርጅቱ ካፒታል የሆኑ ተቋማትን ነቅሶ በማውጣት፡ የወያኔን የገቢ ምንጮችን እያደረቁና፡ ፈርጣማ ኢኮኖሚያዊ ጉልበቱን እያሟሸሹ፡ ህወሓትን የማዳከም ስትራቴጂ ነበር ኣብይና ኢሳያስ ስያከናውኑ የከረሙት።
በብ/ጀ ጠዓመ ጎይቶኦም (መቐለ) የሚመራው የሻዕቢያ የድህንነት ስኳድ፡ የኢትዮጲያን Economy intelligence mision እየመራ፡ በስውሩ ጦርነት ለዶ/ር ኣብይ ይህ ነው የማይባል ውጤት አስመዝግቧል። የሻዕቢያ ሰላዮች የወያኔ ስውር እጆች፡ በትግራይ ብቻ ታጥረው እንዲሰበሰቡ ለማድረግ፡ የስለላ ምንጠራው ከሙሉ ስልጣን ጋር በዶ/ር ኣብይ ኣህመድ ተሰጥቷቸው፡ ሌት- ተቀን በዚህ ተግባር ላይ ተጠምደው እየተጉ ነበር የከረሙት።
ኣብይና ኢሳያስ የመጨረሻው ግባቸው ትግራይን ደሴት አድርጎ በማቆየት፡ የህወሓትን ፋይናሻል ምንጮች በማድረቅ ማዳከምና፡ በሁለንተናዊ ዘመቻ የጋራ ጠላታቸው ህወሓትን፡ በሜካናይዝድ – ሻዕቢያ፡ በአየርና በምድር – የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት፡ ተጨማሪ ረዳት – የአማራ ልዩ ሃይል በሁመራ-ኡምንሓጀር ኮሪደር፡ በጎን ጥቃት በመሰንዝር፡ የህወሓትን ግብዓተ መሬት ፍጽሞ፡ በአሸናፊነት የድል ዋንጫውን ማንሳት ነበር።
ይሁን እንጂ ጦርነቱ ከታሰበው የጊዜ ገደብ በፊት፡ አዲስ አበባ ላይ ፈንዳ። በስውሩ ጦርነት ያልተጠበቀ የአንድ አርቲስት (የቄሮ ‘አይከን’) ግድያ ተፈጽሞ ሌላ ግንባር ተፈጠረ። የዚህ ስልትና ስትራቴጂ ባለቤት ማን ይሆን ?
.
በመሰረቱ ህወሓቶች በህግደፍ እየተደገሰላቸው ላለው ድግስ፡ ቁጭ በለው ጥፋታቸውን የሚጠብቁ የዋሆች አለመሆናቸው ይታወቃል። ለዓመታት በስጋት ውስጥ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ኢሳያስ፡ ያገኘውን ይህን ወርቃማ እድል ያለ ማመመንታት፡ ህወሓትን ለመቅበር ሳያንገራግር እንደሚጠቀምበት በሚገባ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ባላንጣቸው ኢሳያስና ኣብይ ለደገሱላቸው የጥፋት ድግስ፡ ቀደም ብለው የቤት ስራቸውን እየሰሩ መሆናቸው ግልጽ ነው። “መስመርና” የሚሉትን ነጠላ ዜማ ለቀው፡ የማይቀር የሚመስለውን ፍልሚያ ለመፋለም ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ይመስላል።
በቅርቡ ደግሞ ከኤርትራዊው የጦር አበጋዝ ታጋዳላይ መስፍን ሓጎስ ጋር ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወቃል።
.
በመጨረሻ 
በወያኔ ስትራቴጂ መሰረት፡ ከሌሎች የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ ሃያላት ጋር ግንባር ፈጥረው፡ በኤርትራ ያለው የኢሳያስ አመራር ተወግዶ፡ በሃገሪቱ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት፡ የኤርትራ ተቃዋሚ ሃይሎች የሽግግር መንግስት እንዲመሰርቱ ማድረግ፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ከኦሮሞ ፈደራሊስት ሃይሎች ጋር ህብረት ፈጥሮ፡ የኣብይን መንግስት ለመገልበጥ በሙሉ ኣቅም መስራት። የሚለው የህወሓት መንገድ ነው ወደ ዋንጫው ለመድረስ ወንዙን የሚያሻግረው ወይስ፡-
ኢሳያስና ኣብይ በፈንቅል ዘመቻ የህወሓትን ግብዓተ መሬት ፈጽመው፡ በህወሓት ከርሰ-መቃብር ላይ፡ የደምሕት ሰራዊትና የትግራይ/ብልጽግና ፓርቲን የክልሉ ህጋዊ መንግስት እንዲሆኑ፡ የመሰረት ድንጋይ በትግራይ ክልል ለማስቀመጥ፡ ዶ/ር ኣብይ እንዳለው በመቀሌ ጎዳናዎች ኢሳያስን የትግራይ እናቶች እልል እያሉ ይቀበሉት ይሆን ?!
ወጤቱ ባይታወቅም የፍልሚያው መርሐ-ግብር በግርድፉ ይህንን ይመስላል።
ሻዕብያ Vs ወያኔ … Who is the Winner ?
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የመጨረሻው ዙር ፍልሚያ የሚወስነው ይሆናል። ግን በዚህም ሆነ በዚያ የጥሎ ማለፉ ውጤት፡ ለማንም የማይበጅ አገር አውዳሚና የሰውን ልጅ ክቡር ህይወት የሚነጥቅ ጥፋት ነው።
ሁለቱ አንጋፋ ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጪዎች፡ በሰላም ወደ መቃብራቸው ቢሄዱ፡ ለአካባቢው ህዝቦች እፎይታና የደህንነት ዋስትና ነበር። ለታሪክም ለሃገራቱም የሚበጀው ይሄ ነው። እስቲ ደግሞ በቅርቡ የሚሆነውን እናያለን። ለማንኛውም፡-
” የተኩላዎች ጥፋት ፤ ለበጎች ዋስትና ነው !!”
ፈጣሪ ቸር ያሰማን !!
Filed in: Amharic