>

የጆ ባይደን መመረጥ ለግብፅ ስጋት ለኢትዮጵያ ትሩፋት! እኮ እንዴት? (አንዱዓለም ቡታ ሞላ)

የጆ ባይደን መመረጥ ለግብፅ ስጋት ለኢትዮጵያ ትሩፋት! እኮ እንዴት?

በአንዱዓለም ቡታ ሞላ

•የግብፁ ፕሬዝዳንት አብድል ፈታህ አልሲሲ እና የአሜሪካ አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ወዳጆች ናቸው፡፡ ወዳጅነታቸው የቅቤ እንጥበስ አይነት እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡ እርስ በርሳቸውም ‹‹ጓደኛዬ›› ይባባላሉ፡፡
ግብፅ ከአረቡ ዓለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት፡፡ ተደማጭነቷም ቀላል አይደለም፡፡ በአረቡ ዓለም ያላትን ተጽኖ ፈጣሪነት ደግሞ አሜሪካ አንደ ዋዛ አትመለከተውም፡፡ ስለሆነም ለአሜሪካ ያላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ  ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ በዚህም ምክንያት አሜሪካ ለግብፅ በየዓመቱ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ለወታደራዊ ድጋፍ በሚል ትሰጣለች፡፡ አሜሪካ ከሀገራት ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ  ወታደራዊ የገንዘብ ድጋፍ የምታደርገው ለእስራኤል ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ ለግብፅ፡፡ ስለሆነም ትራምፕ እና አልሲሲ ቁርኝታቸው እንዲሁ በአለፍ ገደም እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡
ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ይህ ለትራምፕም ለአልሲሲም ዱብዳ ነው፡፡ ለምን ለአልሲሲ ዱብዳ ይሆናል?
ጆ ባይደን የአብድል ፈታህ አልሲሲ ወዳጅ አይደሉም፡፡ እንዃን ሊወዳጁ ቀርቶ እንዲያውም  ባይደን አልሲሲን ‹‹አምባ ገነን›› ብለው ነው የሚጠሯቸው፡፡ የዚህ ሁሉ አመክንዮ ደግሞ በግብፅ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ነው፡፡ ባይደን በአልሲሲ የአገዛዝ ዘመን በተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከባድ ተቃውሟቸውን ያሰሙባቸውን የተወሰኑ ኬዞችን እንመልከት፡፡
•  ሙስጠፋ ቃሲም አሜሪካዊ ዜጋ ነበር፡፡
ቃሲም 2013 እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር ወደተወለደባት ግብፅ አቀና፡፡ ወቅቱ ደግሞ የቀድሞ የግብፅ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ሙርሲ በአመጽ ግልበጣ ከመንበራቸው የተወገዱበት ሰሞን ነው፡፡ በሀገሪቱ ወደ አንድ የገበያ ማዕከል ለግብይት ወጣ ያለው ቃሲም ያልጠበቀው  ገጠመው፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ  መፈንቅለ መንግስቱን ተቃውመሀል በሚል በፖሊሶች ተይዞ ዘብጥያ ወረደ፡፡ ለ5 አመታትም ያለ ፍርድ ተንገላታ ተሰቃየ፡፡ ኋላ ላይም ቃሲም 15 አመት ተፈረደበት፡፡ የስኳር ህመምተኛ የሆነው ሙስጠፋ ቃሲም 2018 ላይ ብያኔው ስህተት ነው ፍርደ-ገምድል ነው በሚል የርሀብ አድማ ማድረግ ጀመረ፡፡ ጥር 2020 ላይ ወህኒ ሳለ ሞተ፡፡ ባለቤቱን እና ሁለት ልጆቹን ትቶ አፍሪቃ የተገኘው ሰው በ54 አመቱ ሞቱ በተወለደበት አፈር ላይ ሆነ፡፡ ይህም በርካቶችን ያስቆጣ ድርጊት ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ከኮናኞች መካከል ጆ ባይደን ይገኙበታል፡፡ ‹‹አሰቃቂ የሆነ ድርጊት›› ሲሉም ኮነኑት፡፡
• ሞሀመድ አማሻህ— 486 ቀናት ያለፍርድ በግብፅ እስር ቤት
ሞሀመድ አማሻህ ይባላል፡፡ አሜሪካዊ የህክምና ተማሪ ነው፡፡ 2019 በፈረንጆቹ አቆጣጠር አማሻህ ግብፅ ጣህሪር አደባባይ ላይ ብቻውን ቆሞ ታየ፡፡ በአረብኛ ቋንቋ ‹‹ፍትህ ለሁሉም የፖለቲካ አስረኞች›› የሚል ጽሁፍ አንግቧል፡፡ ከመቅጽበት ህግ አስከባሪዎች እያዳፉ ካይሮ በሚገኝ ወህኒ ውስጥ ወረወሩት፡፡  መጋቢት 2020 ላይ የርሀብ አድማ አደረገ፡፡ 16 ወራትን ወይንም 486 ቀናትን ያለፍርድ በዚህ እስር ቤት በእንግልት ኣሳለፈ፡፡ ከዚያም ተለቆ ወደሀገሩ አሜሪካ ተመለሰ፡፡ ይህም ወሬ ተዳረሰ፡፡ ግብፅን ኮናኙ በዛ፡፡ ጆ ባይደን በተዊተር ገፃቸው ሞሀመድ አማሻህ ከ486 ቀናት በኋላ ለሀገሩ መብቃቱን ገልፀው የአልሲሲን መንግስት ተቃወሙ፡፡
ሞሃመድ ሶልጣን፡- ታሰረ – ተደበደበ – ተገረፈ – ለ500 ቀናት የርሀብ አድመኛ ሆነ
ግብፃዊ-አሜሪካዊ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነው ሞሀመድ ሶልጣን፡፡ የ2013ቱ የግብፅ ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ ተቃዋሚ ነው፡፡ ነሀሴ 25 – 2013 ላይ ከ3 ጋዜጠኞች ጋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ወህኒ ገባ – ታሰረ – ተደበደበ – ተገረፈ – እጁም ተሰበረ፡፡ በታሰረ በወሩ የርሀብ አድማ ማድረግ ጀመረ፡፡ 500 ቀናት ያህልም ርሀብ አድማው ፈጀ፡፡ የዚህ ሰው ስም ናኘ፡፡ ግብፅንም ይህንን ሰው ፍቺ የሚላት በዛ፡፡ ኋላ ላይም ነፃ ወጣ፡፡ ጆ ባይደንም ዛሬ ላይ ድርጊቱን ወደ ኋላ መለስ ብለው ይወርፉታል፡፡
•በነገራችን ላይ ግብፅ በበርካታ የፖለቲካ እስረኞች ላይ የምታደርሰው የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣ፤ ያለ ፍርድ ተጠርጣሪዎችን በእስር ቤት ማንገላታት፤ ግርፋት፤ ስቅላት፤ ድብደባ እና እንግልት ቁጥራቸው ጥቂት በማይባሉ ሀገራት እን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ስሟ እንዲብጠለጠል አድርጓታል፡፡
ለማንኛውም ቀጣዩ የአሜሪካው መሪ ጆ ባይደን በትዊተር ገጻቸው ላይ ከላይ የተጠቀሱትን መከራ ተቀባዮችን አስታከው የግብፅን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ክፉኛ ይኮንናሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ፕሬዝዳንት አብድልፈታህ አልሲሲን አምባ ገነን በማለት ጠርተዋቸዋል፡፡ ይህም ባይደን እና አልሲሲ የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደረገ መልዕክት ነበር በትዊተራቸው ላይ ያሰፈሩት፡፡ ‹‹ለዶናልድ ትራምፕ ተመራጩ አምባ ገነን መሪ(አብድል ፈታህ አል ሲሲ) ከእንግዲህ ባዶ ቼክ ይበቃል›› ብለው ነበር ባይደን ሀምሌ 2020 ላይ፡፡ ይህም አሜሪካ ለወታደራዊ ድጋፍ በማለት ለግብፅ የምትሰጣት የገንዘብ ድጋፍ(1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር) መቆም አለበት ማለታቸው ነው ሲሉ በርካታ የውጭ መገናኛ ብዙሀን የባይደንን ሀሳብ ያብራሩታል፡፡
•እንደሚባለው ከሆነ ታዲያ የጆ ባይደን መመረጥ የግብጽ ራስ ምታት ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ቃላቸው ሆኖ አሜሪካ የገንዘብ ድጋፉን ብትነሳ የግብጽ የቀጠናው ክንደ-ብርቱነቷን የሚያርድ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ተሰሚነቷን እና የበላይነት ተገዳዳሪነቷንም በእጅጉ የሚጎዳ እንደሚሆን እየተተነበየ ይገኛል፡፡ ይህም በራሷ ጥረት ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም መርህን በመንተራስ ታላቁ የህዳሴ ግድብን እየገነባች ላለችው ለለፍቶ አዳሪዋ ሀገር ኢትዮጵያ ትልቅ የምስራች ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ለወዳጃቸው አብድል ፈታህ አልሲሲ ወግነው ኢትዮጵያን አይንሽ ላፈር አይሏትም፡፡ ምክንያት ጥር 20-2020 ላይ ትራምፕ ኦቫል ኦፊስን ይለቃሉ፤ እምቢየው አሻፈረኝ ካሉም የአሜሪካው Secret Service አንጠልጥሎም ቢሆን ያስወጣቸዋልና ነው፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃት!!!
Filed in: Amharic