>

እዚያ ጋር ደግሞ ሌላ ትኩሳት  !! (ዘመድኩን በቀለ)

እዚያ ጋር ደግሞ ሌላ ትኩሳት  !! 
   ዘመድኩን በቀለ

 

የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ
ያውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጅ
 
 ግብጽና ሱዳን ሀላየብ እና ሻላጢን በሚባሉ የድንበር ግዛቶች አማካኝነት ሊጠዛጠዙ እንደሆነ ተሰማ።  
•••
በሱዳንና ግብፅ መካከል የሚገኘው ሀላየብ-ሻላጢን ግዛት ሁለቱን አገራት ሲያወዛግብ የቆየ ነው። መሬቱ የሱዳን እንደነበር በርካቶች ይስማማሉ።
•••
ነገር ግን ግብፅ በዲፕሎማሲ ውስብስብ መንገዷ የራሷ አድርጋ ቆይታለች። ሱዳን በተለያዩ ጊዜያት ስትጠይቅ ነበር። 2017 ላይ ያቀረበችው የይገባኛል አቤቱታም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
•••
ይሁንና ሱዳን ከአሜሪካና ከእስራኤል ጋር የነበራት ሻካራ ግንኙነት ድምጿ በግብፅ ተውጦ እንዲቆይ አድርጎባታል። ሱዳን ከእስራኤል ጋር ያደረገችው የሠላም ስምምነት ደግሞ ዛሬ ለተዘገበው ውዝግብ ማገርሸት ቆስቋሽ ነው ተብሏል።
•••
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል አይሮፕላኖች በሱዳን አየር ክልል ሊበርሩ መሆናቸውን አስመልክተው ባደረጉት ቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ ሃላዬብ እና ሻላቴን ግዛት ሱዳን ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ተካትቶ የሚታይበት ካርታ በማሳያነት አቅርበዋል።
•••
ይህን ተከትሎም ካይሮ ለቀናት ተወጥራ እንደቆየች የግብፅ መንግሥት ደጋፊ ዜና አውታሮች አልዘገቡትም ነበር። በአሜሪካና እንግሊዝ የሚገኙ የአረቡ ዓለም ላይ ያተኮሩ ሚዲያዎች ናቸው ይፋ ያደረጉት። Al Monitor አንዱ ነው።
•••
ሞኒተር የአል ጄዚራን የነሐሴ ወር ዘገባ በማውሳት ሱዳንና እስራኤልን ለማስማማት ግብፅ አወዛጋቢውን ግዛት ለሱዳን አሳልፋ እንድትሰጥ አሜሪካ ጫና አድርጋለች ብሏል።
•••
ይህ ደግሞ የአል ሲሲን ፖለቲካ በትልቁ የሚያበላሽ ነው። ግዛቷ ወሳኝ በመሆኗ የዘንድሮው የግብፅ ምክር ቤት ቅድመ ምርጫ በዚቹ ግዛት ነበር ድምፅ ሲሰጥ የነበረው።
•••
አህመድ ሙክታር በካይሮ ዩኒቨርሲቲና በአፍሪካ ጉዳዮች ጥናት ተቋም የሱዳን ጉዳይ ተመራማሪ ናቸው። “እስራኤል የሀላየብና ሻላጢን ግዛት ይገባኛል ውዝግብን አረባዊ አገራትን ለመወዳጀት ስትል ገፀ በረከት ታረገዋለች ሲል እይታውን ለአል ሞኒተር ገልጿል። ጉዳዩ የግብፅ ተፈላጊነት ማሽቆልቆሉን አመላካች ነው።
•••
ግብፃዊው የፓለቲካ ጉዳዮች ጋዜጠኛ አብደላህ ሳናዊ በበኩሉ “ናታንያሁ ያሳዩት ካርታ ሀላየብና ሻላጢን ግዛትን ለሱዳን አድርጎ ማሳየቱ ትልቅ አንድምታ ያለው ነው” በማለት ለቀጣይ ዲፕሎማሲ እስራኤል ወደ ሱዳን መወገኗ እንደማይቀር ጠቁሟል።
•••
ቤንያሚን ናታንያሁ የሱዳን አየር ክልልን መጠቀም መጀመራቸው አቋራጭ የበረራ መስመር በመሆኑ አትራፊና ቀልጣፋ ይሆንልናል ነው ያሉት።
•••
የሀላየብ እና ሻላጢን ግዛት ለማን ይሁን የሚለውን ቀጣይ ዓለምአቀፋዊ የዲፕሎማሲ ጫና ከእስራኤል በተጨማሪ ሳዑዲ አረቢያም ከግብፅ የተኳረፈችባቸውን ደሴቶች ጉዳይ የምትመዝዝበት ግጥምጥሞሽንም ይፈጥራል ተብሏል።
•••
የሁለቱ አገራት የአቋም ጥንስስ ከሱዳን ፍላጎት ጋር ተደምሮ የነጩን ቤተ መንግስት መፃኢ ቀጭን ትዕዛዝ የሚወስን ስለመሆኑም እንዲሁ።
ዘገባው የ Esleman Abay ነው።
•••
እኔ ደግሞ እላለሁ። ኢትዮጵያን አትንኩ። ኢትዮጵያን የነካ የእምቧይ ካብ ነው የሚሆነው። ሳይነኩት ይፈርሳል። ይቀልጣል። ይናዳል።
•••
ትራንፕ እና ትህነግን ማየት ብልህነት ነው። ከእነሱ መማር ይበጃል። ግብፅ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ፣ ለመቆራረስ እንዳልሠራች ሁሉ አሁን ደግሞ ከቀኝ ከግራ፣ ከታች እና ከላይ የገና ዳቦ ልትሆን ነው። እግዚአብሔር ሲጣላህ አርጩሜውን ከደጅህ፣ ከበራፍህ ነው የሚቆርጠው። ሱዳን፣ እስራኤል፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ከጎን ደግሞ የፈራረሰችው ሊቢያ ሳትቀር ለግብፅ ረመጥ ሊሆኑባት ነው። ኢትዮጵያ ሰላምሽ ይብዛ።
Filed in: Amharic