>

ወንድምነት ከወንጀለኛነት ይልቃል...!!! (አባይነህ ካሴ)

ወንድምነት ከወንጀለኛነት ይልቃል…!!!

አባይነህ ካሴ

* የሀገርን ሰው ወንድም ማለት በደል የለበትም ከማለት ምን ያገናኘዋል? በግብሩ አጥፊነት ይጠየቃል እንጅ ወንድሜ አይደለም እንዴት ይባላል? ይህ አዲስ ጽንፈኝነት ነው። 
ቃየን አቤልን ከገደለ በኋላ እግዚአብሔር ቃየንን ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? ብሎ መጠየቁን አትዘንጉ። ዘፍ ፬ ፡ ፱። ቢገድለውም ወንድምነቱ ግን አይፋቅም። በዔሳውና በያዕቆብም መካከል መከፋፋት ነበር። ግን ከወንድምነት አልተናጠቡም።
ይቅርታ ማድረግ አልተበደልሁም ማለት አይደለም። የበደልኸኝን ተውልህ ማለት እንጅ አልበደልኸኝም ማለት አይደለም። ወንድምህ ቢበድልህ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት ተውለት ይላል መምህርነ ወአምላክነ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ። አሁንም በዳዩ ወንድም መባሉን ያዙ።
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ጦርነት በወንድማማቾች መካከል ነው። በእርግጥ አለቆች መስለው በሚታዩት ብዙ በደል ሲደርስ ኖሯል። የወንድማቸውን ደም ሲያፈስሱ የኖሩ በደም የጨቀዩ ግለሰቦች መኖራቸው አይካድም። ከሀገር ሰው ይልቅ የጎረቤት ዜጋ ይቀርበናል እስከማለት ነገሩን የለጠጡት መኾናቸውም አይካድም። ይህን የሚሉት ወንድምነታቸውን ክደዋል። እነርሱ ያሰማሯቸው ምስኪኖች ግን አሁንም ወንድሞች ናቸው።
ሃይማኖትን ከመካድ በላይ አብሮ መቆምን የሚፈታተን የለም። የካዱትንም ግን መጽሐፍ ሐሰተኞች ወንድሞች ብሎ ይጠራቸዋል። ወንድምነት ገመዱ ረዥም ቋጠሮው ጥብቅ ውሉ ውስብስብ ነው። ድንገት ቆርጠው የሚጥሉት ጭራሮ አይደለም።
ሰሞኑን በተነሣው ጦርነት ምክንያት የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ሁሉ በጅምላ ወንድም አይደሉም ማለት ከፍተኛ እና ታሪክ ይቅር የማይለው ስሕተት ነው። ይህ ዓይነት ገጽታ በኹለት በኩል እየተንጸባረቀ ነው።
አንደኛው በቀደመው የሥልጣን ዘመኑ የሰውን ደም በዋንጫ ከመጠጣት ያልተናነሰ ግፍ ሲፈጽም በነበረው አገዛዝ ቁልፍ ሚና በነበራቸው ሰዎች ይናፈሳል። ትግርኛ ተናጋሪው ሁሉ “ወንድም አይደለህም ተብሏል” በማለት መላውን ሕዝብ ቀስቅሶ ለራሱ መደበቂያ ዋሻ ያመቻቻል። ይህ ፍጹም ውሸት ከመኾኑ በላይ የወንድምነትን እሴት ጥሶ ከሀገር ሰው ይልቅ ሱዳን ይቀርበኛል ካለ አፍ መውጣቱ ነገሩ ከይሲአዊ ተንኮል የተጣባው መኾኑን ግልጥ ያደርግልናል። ለመደመጥ ሞራል ያጥረዋል። ቢያንስ እርሱ ሲለው “ጽድቅ” ከኾነ ሌላው ብሎት ከኾነ እንኳ “ኃጢአት” አይኾንማ።
ኹለተኛው በስመ ትግርኛ ተናጋሪነት ያገኘኸውን ሁሉ ወንድም አይደለህም የሚል ስሜት ውስጥ መዶል ነው። ድንገተኛ ፍተሻዎች ሁሉ ወደ አንድ አቅጣጫ ማምራታቸው ከዚህም ወንድምነትን የመግፋት የጥረግ ስሜት መኖሩን ይጠቁማል።  በተለይም አጋጣሚውን በመጠቀም ትግርኛ ተናጋሪውን ሁሉ የሚያሸማቀቅ ተግባር የሚፈጽሙ የጎበዝ አለቆች እንደ አሸን መፍላታቸው ነገሩን የመንግሥት ፍላጎት ያስመስለዋል። ወንድሜ እያለ ከእነ ትጥቁ እየወጣ የሚመጣውን ወታደር ማየትም ይገባል።
በኢትዮጵያዊነታቸው ለአፍታ የማይደራደሩ እንዳሉ ሁሉ ለነፍሰ በላዎቹ ዘብ የቆሙ አይጠፉም። መለየት ያስፈልጋል። መንግሥት ቢፈልግ እንኳ ሕዝቡ ለዚህ ድውይ ሥራ መንገድ መስጠት የለበትም። “በኢትዮ ኤርትራ” ጦርነት ጊዜ ከመንግሥት ይልቅ ልቡን ያዳመጠ ዕንቁ ሕዝብ መኾኑ አይረሳ። ለ፴ ዓመት ንብረት ጠብቆ የሚያስረክብ ከሕግ በላይ የሚያስብ ምስጉን ሕዝብ አለ። ከ፲፭ ዓመት በላይ ለያዝኸው ንብረት ሕጉ ባለቤትነት ይሰጥሃላ።
ወንጀለኞቹ በጦርነትም ባይኾን በፍትሕ መጠየቅ አለባቸው ማለትና የትግራይ ሕዝብ ወንድም አይደለም ማለት ፍየል ወዲያ ይኾናል። መረሳት የሌለበት ቁም ነገር አለ። አይደለም በደል የሌለበት ሕዝቡ ወንጀለኞቹ አሁንም ወንድሞች ናቸው። ወንጀለኛ ወንድሞች።
እነርሱ አይደለንም ቢሉ እንኳ ወንድምነት በእነርሱ እጅ ተቆርጦ የሚጣል አይደለም። ሥልጣኑ የእግዚአብሔር ነው። ወንድምነት ግን በወንጀል ከመጠየቅ አያድንም።
ጠላቶቻችን ከወንድማማችነታችን ውጪ ናቸው። ገና አላወቅናቸውም። ለእናታችን ሔዋን ዋነኛ ጠላቷ እባብ ሳትኾን በጀርባዋ የታዘለው ሰይጣን ነበረ። ሰው ጠቡ ከእባብ መሰለው።  እግዚአብሔር ግን ዋነኛው ጠላት ላይ አተኮረ እንጅ እባብ ላይ አይደለም። የእኛም እንዲያ ቢኾን። ከማደሪያው በላይ አዳሪው ላይ እንሥራ።
እንደዚያ ሲኾን አሁንም ወለጋ፣  ጉራፈርዳ እና ቤንሻንጉል ላይ ወንድም አይደላችሁም የተባሉት እኩል ይታወሱናል። የዚህኛውስ ሰይጣን ማደሪያ ወዴት ነው?
የኃይል ሚዛን ዐይቶ የተሸራረፈ አቋም ያጠያይቃል።
Filed in: Amharic