>
5:26 pm - Tuesday September 15, 9772

የቅዱስ ሲኖዶስ ጎርበጥባጣ ውሳኔዎች...!!! ( በመሪጌታ ጋዜጠኛ ብርሀኑ ተክለያሬድ )

የቅዱስ ሲኖዶስ ጎርበጥባጣ ውሳኔዎች…!!!

( በመሪጌታ ጋዜጠኛ ብርሀኑ ተክለያሬድ )

በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባዔ የቤተክርስቲያኒቷ የበላይ አካል የሆነው ጉባዔ ታላላቅ ታሪካዊ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ የተጠበቀና ምናልባትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሁሉም መስክ ለተከፈተባት ጥቃት መፍትሔ የምታስቀምጥበት፣በአባቶችና በምእመናን መካከል የተቆረጠው ድልድይ የሚጠገንበት ጉባዔ ይሆናል ተብሎም ተጠብቆ ነበር። ይህ ተስፋም ብዙ መነሻዎች ነበሩት።
ወደኋላ;-
በአመት 1 ጊዜ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ቀድሞ የሚደረገውና የቤተክርስቲያኒቷ መዋቅሮች ካሉበት ቦታ ሁሉ ተወካዮች መጥተው የሚመክሩበት የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን” በሚል መነሻ ጥቅስ  የቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ የመክፈቻ ንግግር ጠጠርና ጠንከር ያሉ ነጥቦችን የያዘ ከመሆኑም በላይ “የሚጠብቀን የለንምና ራሳችንን አደራጅተን እንከላከል” የሚለውን የብዙ ምእመናንን ጥያቄ በትእዛዝ መልክ ያወረደ፣ሲኖዶሱ በአግባቡ ምእመናንን አልጠበቀም በማለት ለራስ ወቀሳ ያቀረበ፣ ጡንቸኛ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‘ከሰላምና ከድርድር ውጪ አማራጭ የላችሁምና በስክነት ተነጋገሩ’ የሚል ጥሪ ያቀረበ የመክፈቻ ንግግር መደረጉ በውስጥም በአፍኣም ያሉ ወዳጆችን ያስደሰተ “ባለጊዜ ነን” ባዮችን ደግሞ ያስደነገጠ ነበር። ይህን ተከትሎም ልዩ ውይይት ሊደረግባቸው የነበሩ ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ችግሮችና መፍትሔዎች እያሉ የጉባዔው ማጠናቀቂያ ዕለት ተብሎ ከተያዘ ፕሮግራም ቀድሞ በባለ ስውር እጆቹ ትእዛዝ ‘በኮቪድ ስጋት ምክንያት’ ተብሎ እንዲበተን ተደረገ። (የሰቲት ሁመራና የአክሱም ሀገረስብከት ተወካዮች በጉባዔው አለመገኘታቸውና ለመጀመሪያ ጊዜ ለጠቅላይ ቤተክህነት ማስገባት የነበረባቸውን የገቢ ፐርሰንትም መከልከላቸው ሌላ አንድምታ ያለው ክስተት ነበር።)
እንደገና ወደኋላ:-
ቅዱስ ሲኖዶስ በነሐሴ ወር መጨረሻ በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው መከራ መዋቅራዊ ፣ ርእዮተ-ዐለማዊና ጂኦፖለቲካዊ ዳራ ያለው ጥቃት መሆኑን በመግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን ከተገለፀ በጥቂት ቀናት ውስጥ  በ2013 የዘመን መለወጫ ዋዜማ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ቢሮ “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማመስገን” ተገኝተው ነበር። ይህ ክስተትም በቤተክህነት አካባቢ መወራከቦች መፍጠሩ አልቀረም። በአንድ በኩል ሁለቱን ሲኖዶሶች ወደአንድ ያመጣና ለቅዱስ ፓትርያርኩም ልዩ እንክብካቤ ሲያደርግ የነበረ ጠቅላይ ሚኒስትር በአዲስ አመት ዋዜማ ቢመሰገን ችግሩ ምንድነው የሚሉ በሌላ በኩል ደግሞ ቤተክርስቲያኗ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በኩል እየተጠቃሁ መንግስት አልተከላከለልኝም ብላ እየወቀሰች በሌላኛው ፓትርያርክ በኩል ደግሞ ለምስጋና መሄዷ ያለመናበብ ምልክቶችና ከፈለግን ይኽኛውን ቡድን ይዘን አንድ ያደረግነውን ለመክፈል አቅም አለን የሚሉ ፖለቲከኞች ተግባር ነው የሚሉ ሀሳቦች ያገባናል በሚሉ ወገኖች ተነስተው አወዛግበዋል የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ከምንጮች እንዳረጋገጠው ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ ቤተመንግሥት እንዲሄዱ ፕሮግራሙን ያዘጋጁ “ባለጊዜ ነን” ባይ መነኮሳት እንደነበሩ ፅሁፉንም ያዘጋጁት አብረዋቸው የተጓዙ ሊቀ ጳጳስ እንደሆኑና እነዚህ አካላትም ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር ያላቸውን አስተዳደራዊ ቅራኔ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ያለ ፍላጎትና ፈቃዳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በማገናኘት በፖለቲካ የመከለል ፍላጎት እንዳላቸው፣በብልፅግና መሪዎች በኩልም የቤተክርስቲያንን የብሶት መግለጫ የሌላ አካል ተልእኮ ብሎ ለመፈረጅ እንዲመች ከአኩራፊዎቹ ጋር መወዳጀትና በግሁሱና ቅዱሱ አቡነ መርቆሬዎስ መከለል ወደር የሌለው ምርጫ እንደሆነ ማወቅ ቀላል ነበር። ለዚህም ምቹው መንገድ ቤተክርስቲያኒቷ በምክንያተ እርቁ ከሁለት አመት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበችውን ምስጋና ደግሞ ማቅረብ ነበር። ይህን የተረዱና ያለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እውቅና በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተደረገው ጉብኝትና ምስጋና ከሁለቱ ሲኖዶሶች የእርቅ ውል ያፈነገጠ መሆኑን ያመኑ ሽማግሌዎች በበዓሉ እለት በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቢሮ በተገኙበት ወቅት ፓትርያርኩ እየተደረገባቸው ያለው መገለል ተገቢ እንዳልሆነ፣ (በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር ወቅት በቤተ እምነቶች የሚደረግ ምዝበራን የተመለከተ ሀሳብ ሲነሳ የቀጥታ ስርጭት ካሜራው ቅዱስነታቸውን ብቻ ያሳይ የነበረ መሆኑ ሆን ተብሎ እሳቸውን ለማነወር እንደተደረገ እንደሚያምኑ) ሌሎችም ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች ካልቆሙ ለቤተክርስቲያን ከባድ አደጋ እንደሆነ በሀዘን መግለፃቸውን ሰምተናል።
ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር እንዲል መፅሀፍ ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ የሚፈታ ነው ተብሎ ታምኖ የነበረ  ቢሆንም ምልዐተ ጉባኤውም በውሳኔዎቹ ሌሎች በአስተዳደራዊም ሆነ በቀኖናዊ ጉዳዮች ግራ አጋቢና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ይዞ መጥቷል። ጥቂቶቹን በወፍ በረር እንቃኛቸው ።
 
፩ የኦሮሚያ ቤተክህነት እርቅ:-
እርቅና ሰላም ቤተክርስቲያን የቆመችበት መሰረትና ለሌሎችም የምትሰብከው በራሷ መዋቅርም መተግበር ያለባት ጉዳይ ቢሆንም በተለይ የቤተክርስቲያን ልእልናን የተዳፈሩ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ እርቅና ስምምነቶች ግን ነገሩን ግልፅ ያደረጉና አጥፊና ጥፋቶችን ዘርዝረው በክርስቲያናዊ ትህትና ይቅርታ አስጠይቀውና እንዳይደገሙ አስጠንቅቀው ማለፍ የሚገባቸው ቢሆንም የኦሮሚያ ቤተክህነት ምልሰት ግን ይህን ያላካተተና  ኦርቶዶክሳውያንን ወራሪ ሰፋሪ መጤ ብለው የፈረጁና ለጥቃት ያጋለጡ፣በጃዋር ‘ምናባዊ መከበብ’ ወቅት ወንድማችንን የሚነካ ማነው? ብለው መግለጫ ሲሰጡ የነበሩ፣ኦርቶዶክሳውያን ሲታረዱ “የታረዱት በሃይማኖታቸው ሳይሆን እምዬ ምኒልክ በማለታቸው ነው” ብለው የተሳለቁ፣ ለነዚህ ስህተቶቻቸው ይፋዊ ይቅርታ እንኳን ሳይጠይቁ ÷ በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱ ክህነታቸው እንደተያዘ ቢገልፅም ማንም እኛን የማውገዝ ስልጣን የለውም በሚል እብሪት መግለጫ በመስጠትና በተያዘ ክህነት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ለመሆናቸው ቀኖናዊ ቅጣት ሳያገኛቸው÷ (ለአስታራቂ ሽማግሌዎቹ ያለኝ ክብር እንደተጠበቀ ሆኖ) ቡድኑንና ቅዱስ ሲኖዶስን በአቻነት ያስቀመጠና ማንም አሸናፊና ተሸናፊ የለም በሚል ሽፍንፍን የታለፈው እርቅ አነጋጋሪ ሆኗል። የሚያገረሽ ስጋት !!
፪ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት :-
ህገ ቤተክርስቲያን አንቀፅ ፶ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደሆነ ይገልፃል። በቅዱስነታቸው አቅራቢነት ረዳት ጳጳስ እንደሚሾምም እንዲሁ፧ ይሁንና ለቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳነት ቀርቦ የነበረው “ህገ ቤተክርስቲያን በሙሉ እንዲሻሻል” የሚል ቢሆንም አጀንዳው ላይ ሲደረስ ግን ከአበው የተሰማው “አንቀፅ ፶ በአስቸኳይ መሻሻል አለበት” የሚል ነው። በዚህ አጀንዳ ላይ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተቃውሟቸውን ያቀረቡና ጉዳዩ ጥናት የሚፈልግ እንደሆነ የገለፁ ቢሆንም በብልፅግና ወዳጆችና በብፁዓን አበው ግፊት ውሳኔው ተወሰነ። ቅዱስ ፓትርያርኩም ልዩ ሀገረ ስብከታቸውን ያለ ህግ ተነጠቁ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ።(ያለ ህግ ያልኩት ሲኖዶሱ ይህን ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ የህገ ቤተክርስቲያን ማሻሻል አጀንዳውን ለግንቦት አሳድሮታል። ስለሆነም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውሳኔ ባልተሻሻለ ህግ ላይ የፀና ነው ማለት ነው።) ይህን ተከትሎ ቅዱስ ፓትርያርኩ በውሳኔው ላይ እንደማይፈርሙ ቢገልፁም አሁንም ከህግ ውጪ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሀፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሹመቱን ደብዳቤ በአስቸኳይ ፈርመው ከመስጠታቸውም በላይ የሲኖዶሱ ጉባዔ ሳይጠናቀቅ አዲሱን ተሿሚ ሊቀ ጳጳስ አጅበው ወደ ሀገረ ስብከቱ አስገቡ። ሌላ የመለያየት ስጋት!!
፫ ነገረ ቅብዓት :-
ከወራት በፊት ማረፊያውን በምስራቅ ጎጃም ቆጋ ምስካበ ቅዱሳን ኪዳነምህረት ያደረገ የቅብዓት እምነት አራማጅ ቡድን የራሱን “ፓትርያርክና ሊቀ ጳጳስ” መሾሙንና ሲኖዶስ እያቋቋመ መሆኑንም ይፋ ካደረገ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ቦታው አጣሪ ኮሚቴ ልኮ ነበር። ይህ ለረጅም ዘመናት በሊቃውንት መካከል ክርክሮችን የጋበዘና በተደጋጋሚ ጉባዔያት የተረታና የተወገዘ አስተሳሰብ ግዘፍ ነስቶ እንዲመጣ የመንግስት መዋቅር አካላት፣ፕሮቴስታንታዊ የተሀድሶ አራማጆችና የፖለቲካ ኃይሎች ሲደግፉት እንደነበር እሙን ነው። በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ይህ ጉዳይ ጠንካራ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ለኑፋቄያዊ እሳቤው ትኩረት ያልሰጠ፣አጥፊዎችን በአካል ጠርቶ ያልጠየቀና የተጣሰው የነገረ ክርስቶስ ዶግማ ሆኖ ሳለ ቀኖናዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ‘ጵጵስናችሁን ሽረናል’ የሚል ላልተሰጠ ሹመት የሽረት ውሳኔ በማስተላለፍ ተጠናቋል። ሌላው የምንፍቅና ስጋት!!!
፬ አወዛጋቢው ዝውውርና ምደባ:-
በጥቅምቱ ምልዐተ ጉባዔ ቅዱስ ሲኖዶስ የአባቶች ዝውውርና ምደባ ሲያደርግ የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ምእመናን በተደጋጋሚ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት በአስተዳደራዊ በደሎችና በኑፋቄያዊ አስተምህሮ ቸልተኝነት ተከሰው ወደ ኒውዮርክ ተዛውረው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተመልሰው ምስራቅ ጎጃም መመደባቸው ሌላው የጣት ቁስል ረገጣ ሆኗል። ውሳኔውን ተከትሎ የአካባቢው ምእመናን ቅሬታቸውን ለማሰማት ከደብረማርቆስ ሌሊቱን ሲጓዙ አድረው በጠዋት አዲስ አበባ ቢደርሱም ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ዝር እንዳይሉ በፖሊስ ተከልክለው በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ታግተው የዋሉ ሲሆን ጥቂቶቹም በፖሊስ ተወስደው እስከ ምሽት ታስረዋል።
ሲጠናቀቅ:-
ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔውን ባጠናቀቀበት እለት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት ጥሪ በማድረጉ ጋዜጠኞች በሰአቱ ተገኝተዋል። በመንበረ ፓትርያርክ አዳራሽ አካባቢ የጭንቀት አየር ይነፍስ ነበር፤የተጨነቁ የሚመስሉ ሊቃነ ጳጳሳት ወጣ ገባ ይሉ ጀመር፤ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ መግለጫ አዳራሹ አልመጣም ማለታቸው በዘወርዋራ ተገለፀ። በእድሜ የገፉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እየተመሩ ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ መኖሪያ ቤት ገቡ። ከብዙ ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ የቅሬታ ፊት እየተነበበባቸው ተመልሰው ወጡ። ወደ አንዳቸው ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ጠጋ ብዬ
“ብፁዕ አባታችን ተሳካ?” አልኳቸው።
“የለም አልተሳካም አባታችን አዝነዋል በጄ አላሉንም” አሉኝ
“ነገሩ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ጉዳይ ብቻ ነው?” አልኩ።
እሱም አንዱ የቅሬታ ምንጭ እንደሆነ ነገር ግን ሌላም ጊዜ የሚፈታው ብዙ ነገር እንዳለና በመንግስትና በአንዳንድ አባቶች በኩል የማይካድና በግልፅ የሚታይ ቅዱስ ፓትርያርኩን የመግፋትና የማግለል አዝማሚያ እንዳለ ፣በጠዋቱ የስብሰባ ክፍለ ጊዜም የፓትርያርኩ ጠባቂዎች አንድ መነኩሴን ደብድባችኋል ተብለው ባልተለመደ መልኩ  ወደ እስር ቤት መወሰዳቸውም ነገሩን እንዳባባሰው ገለፁልኝ፤ ፊታቸው ላይ ምን ይበጀን ይሆን? የሚል ጭንቀት አነበብኩ።
ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅሬታ ከተመለሱ በኋላ ጋዜጠኞች እንዲገቡ ተደርጎ መግለጫው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ባሉበት በሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ በአቡነ ዮሴፍ ተነበበ። በአንዳንድ አባቶች ላይ የድል አድራጊነት በሌሎች ላይ ደግሞ የሀዘን ፊት ይታይ ነበር። መንበሩን የኢትዮጵያ ካደረገ ጥቂት አስርታትን ያሳለፈው፦ በደርግ ዘመን ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ቴዎፍሎስ በሰው ቀላዎች ሲታረዱ በቸልታ የተመለከተው፦በህወሓት ዘመን በሁለት ሲኖዶስ ተከፍሎ የተወጋገዘውና የታረቀው የቤተክርስቲያኒቷ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ በብልፅግና ዘመን ዳግም የመከፈል አልያም ቅዱስ ፓትርያርኩን አሳልፎ የመስጠት እጣ ይደርሰው ይሆን?
ፀልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት!!!
Filed in: Amharic