>

ነገር በየፈርጁ:- ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ጦርነት ማካሄድ፣ የጦርነቱ ስያሜ፣ ወንድማማችነት...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ነገር በየፈርጁ:-

ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ጦርነት ማካሄድ፣ የጦርነቱ ስያሜ፣ ወንድማማችነት…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም

አንዳንድ ሰዎች ሆነ ብላችሁ፤ አንዳንዶችም ነገሮችን በቅጡ ካለመረዳት ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በሰነዘርኳቸው ስጋቶቼ ላይ ቅሬታ አዘል አስተያየት እና የተዛባ አረዳድ ስታንጸባርቁ ስላየሁ ነገሩን በየፈርጁ በግልጽ ለማስቀመጥ ወደድኩ፤
+ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፤
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ዝግጅት የገለጹበትን፤ እንዲሁም ሕዝቡ ለዚህ ጥረታቸው የበኩሉን ድጋፍ ለመንግስት እንዲያደርግ ያስተላለፉትን ጥሪ ይበል የሚያሰኝ ጥሩ ጅምር ስለሆነ እኔም እደግፈዋለሁ። አዎ አገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት ጨርሶ የጠፋ እስኪመስል ድረስ የተደራጁ ቡድኖች እና እንደ ህውሃት ያሉ መሰሪ ድርጅቶች ያሻቸውን ሲያስገድሉ፣ ዜጎችን በማንነታቸው ሲያስጨቸጭፉና ሲጨፈጭፉ፣ ሚሊዮኖችን ሲያፈናቅሉ እና ሲዘርፉ ቆይተዋል። ኢትዮጵያን መንግስት የሌለባት አገር ሊያስመስሏት አንድ ሐሙስ ሲቀራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደገፍ እና ሁሉም ከጎናቸው ሊቆምበት የሚገባ አቋም ነው። መንግስት ሕግ እንዲያስከብር ስንወተውት ለኖርን ሰዎች እና በተለይም እጃቸው በንጹሃን ደም የጨቀየው የወያኔ ባለሥልጣናት ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ስንጮኽ ለነበርን ሰዎች ይህ የመንግስት ዘግይቶም ቢሆን መንቃት ትልቅ ዜና ነው።
ይህ የተጀመረው አገራዊ ዘመቻ መቀሌ የመሸጉ እኩይ የህውሃት መሪዎችን እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዳሻው ዜጎችን የሚያርደውን ኦነግ ሽኔን ለፍርድ የማቅረብ እስከሆነ ድረስ መንግስት በቁጥጥ ስር ሊውሉ የሚገባቸውን የወንጀል ተጠርጣሪዎች በስም፣ በፎቶ እና በኃላፊነታቸው መጠን ዘርዝሮ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግ ይገባል። ይህ የመንግስትን ዓላማ ግልጽ ከማድረግም ባሻገር የዚህን ጦርነት ተልዕኮ ለአለምም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ያደርጋል። የሕዝብም ትኩረት እነዛ በወንጀል ተፈላጊ የሆኑ ግለሰቦች ላይ ብቻ ይሆናል። ይሄ ደግሞ ጉዳዩ የእርስ በርስ ግጭት ከሚለው ይልቅ መንግስት ተፈላጊ ወንጀለኞችን ለመያዝ የሚያደርገው ጥረት ነው የሚለውን አቋሙን ግልጽ እና ጠንካራ ያደርግለታል። በወንጀል ተፈላጊዎቹን ሰዎች በዝርዝር ሳይገለጽ በጅምላ የሚደረገው ፍልሚያ መጨረሻው እንዳይታወቅ እና ሌሎች የአተገባበር ክፍተቶችንም ይፈጥራል። ንጹሃን ዜጎችም በዚህ ግርግር ሊጎዱ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ጥሩ ተመክሮ የሚሆነው በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ግማሽ የኢትዮጵያዊ ደም ያላቸው ሰዎች ሳይቀሩ በግርግር እና በግል ቂም ታፍሰው ወደ ኤርትራ መላካቸውን ልብ ይለዋል።
+ የህውሃት መሰሪነት
የህውሃት አመራሮች በሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ተወሰደ የተባለው ዘግናኝ የጭካኔ እርምጃ የህውሃትን ባህሪ ማሳያ ከሆኑንት ነገሮች አንዱ ነው። ህውሃት ከፍጥረቱ አንስቶ በግፍ፣ በሸር እና በጭካኔ የተካነ፣ ዜጎችን ሲያሸብር የኖረ እና ለጥፋት የተፈጠረ ድርጅት መሆኑን ከትጥቅ ጊዜ አንስቶ አገር በመራበት ዘመን ሁሉ የሠራቸውን ወንጀሎች መመርመር ይቻላል። በዚህ ጽሁፍ የህውሃትን ወንጀሎች ለመቁጠር ጊዜ አይበቃም። ህጻናት፣ አዛውንት፣ እርጉዝ ሴት፣ የኃይማኖት አባቶችን፣ አካል ጉዳተኛ እና አቅመ ደካማ ሳይል በጠላትነት በፈረጀው ሰው ላይ ሁሉ ተገልጾ የማይጨረስ ግፍ እና በደል ሲፈጽም የኖረ እኩይ፣ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ እና በሌሎች ወንጀለኛ መጠየቅ ያለበት ቡድን ነው። ለዚህም ነው በትዕግስትና በይቅርታ ስም ይሄ ቡድን ከተጠያቂነት ሊያመልጥ አይገባም እያልን ላለፉት ሦስት አመታት ስንወተውት የቆየነው። ህውሃት አሁንም እድሜ ከተሰጠው እና የድርጅቱ መሪዎችም ተጨማሪ ጊዜን ካገኙ ሌሎች ዘግናኝ የጭካኔ ሥራዎችን ከመፈጸም የሚመልሳቸው የሞራል እንጥፍጣፊ ስለሌለ ብዙ ግፍ ሊያሳዩን ይችላሉ።
+ ህውሃት በመከላከያ ላይ የፈጸመችው ጥቃት እና ትንኮሳ
ህውሃት ለማዕከላዊ መንግስቱ እውቅና ከነፈገ ከራረመ። ዳርዳርታው ትግራይን የማስገንጠል ስለሚመስል ይሄ ሃይል በጊዜ ካልተያዘ ወደ ከፋ ግጭት አገሪቱን ሊያመራት እንደሚችል እኔን ጨምሮ ብዙዎች ደጋግመን በየመድረኩ ገልጸናል፤ ጽፈናል። ለዚህ እኩይ ተልኳቸው እንዲሆን
ከሌላው እኩይ ቡድኖች ጋር፤ በተለይም ኦነግ ሽኔ ጋር በመሆን የጀመሩት በዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የዚህ ጦርነት የቁስቆሳ ምልክት ነበር። የመንግስት ትግስት እነዚህን አካላት በመግለጫ ከመወንጀል ያለፈ አለመሆኑን ሲያዩ በሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላት ላይ የተገለጸውን የጭካኔ እርምጃ ወሰዱ። ይሄ የትንኮሳ እና የጥቃት እርምጃ አላማውም መንግስት በሰሜን ከኛ ጋራ ሲጋጭ መሃሉን ኦነግ ሽኔ ያምሰዋል ከሚል ቅዠት የመነጨ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ህውሃት ውጊያ ውስጥ ስትገባ ኦነግ ሽኔ በአንዳንድ አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት እንቅስቃሴውን ማስፋት መጀመሩ የሁለቱን ኃይሎች መቀናጀት በደንብ ያሳያል።
 
+ ከህውሃት ትንኮሳ በኋላ የመንግስት ምላሽ፤
ህውሃት ሰራዊቱን ማጥቃቷን እና ለዚህም አጸፌታ ምላሽ የመከላከያ ሠራዊቱ እርምጃ እንዲወስድ ጠ/ሚ አብይ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የአገርን ሉዑዓላዊነት ከማስጠበቅ ረገድ ትክክለኛ እርምጃ ነው። ይሁንና ትንኮሳውን ተከትሎ ሁለቱም አካላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ለሕዝብ ይፋ ያደረጉበት መንገድ አለምም ሆነ ብዙዎቻችን ግጭቱን Intrastate war or Civil War አድርገን እንድናስብ አድርጎናል። የግጭቱ ባህሪ እና ስያሜም የተበየነው ገና በመጀመሪያዎቹ ቀናት ከሁለቱም አካላት በተሰጡት ኦፊሴላዊ መግለጫዎች ነው።  ይህ በአየር ጥቃት እና በከፍተኛ የጦር መሳሪያዎች እየተደገፈ የሚካሄደው ጦርነት ዓላማው እና የመነሻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በአንድ አገር ውስጥ ባሉ ሁለት አካላት፤ በፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህውሃት በኩል የተደረገ ጦርነት ስለሆነ የእርስ በርስ ጦርነት የሚለውን መስፈርት የሚያሟላ ነው። አንዳንድ ጋዜጠኞች፤ በተለይም የAP ጋዜጠኛ ኤሊያ መሰረት #EliasMeseret, Civil War የሚለውን ቃል በዘገባው ላይ በመጠቀሙ ክፉኛ ሲወገዝ ታዝቤያለሁ።  ለምን Civil War አልክ በሚልም የተወሰኑ በግልም የማውቃቸው የመብት ተሟጋቾች ሳይቀሩ ሲዘልፉት እና አካኪ ዘራፍ ሲሉ አስተውያለሁ። ይህ አይነቱ አካሄድ የጋዜጠኞችን ነጻነት የሚጋፋ እና የሃሳብ ችግርም ያለበት ነው።
አዎ Civil War ማለት በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ እና በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጁ አካላት በሰለጠኑ እና በመሳሪያ በታገዙ ወታደሮች የተደገፈ ውጊያ ሲያደርጉ ነው። ይህ አይነቱ ግጭት የአገር ውስጥ ጦርነት ወይም intrastate war ም ይባላል። የእርስ በርስ ጦርነትም ተብሎ ይገለጻል። በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉት መንግስት እና አንድ የተደራጀ አማጺ ወይም እራስ ገዝ ክልል ወይም በሌላ መልክ የተደራጀ ቡድን ሊሆን ይችላል። የእርስ በእርስ ግጭት ማለት በሕዝብ መካከል የተደረገ ግጭት ነው፤ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተፈጠረም፣ ጦርነቱ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አይደለም የሚል መከራከሪያ ይዛችሁ የግጭቱ አጠራር እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው የምትሉ ሰዎች ነገሩን በቅጡ እንድታጤኑ እመክራለሁ። አዎ ግጭቱ በሕዝቦች መካከል አይደለም። በትግራይ ሕዝብ ላይ የተነጣጠረም ጥቃት አይደለም። ነገር ግን አሁን ከፌደራል መንግስት ጋር እየተፋለሙ ያሉት የህውሃት ታጣቂዎች የሕዝብ አካል እና ኢትዮጵያዊያን ናቸው። በሌላኛው ማዶ ሆኖ ለአገር ሉዓላዊነት ይሁን ወንጀለኞችን ለመያዝ እየተፋለመ እና ታላቅ መስዋዕትነት እየከፈለም ያለው ኩሩ ኢትዮጵያዊ ኃይል ነው። የሁለቱም ተዋጂዎች ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ ግጭቱን የእርስ በርስ ጦርነት ወይም Intrastate war or Civil War ያስብለዋል።
+ የወንድማማቾች ጦርነት
እላይ ባለው ትርጓሜ ከተስማማን ጸቡ በአንድ አገር ዜጎች መካከል እስከሆነ ድረስ እና ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ግጭቱን የወንድማማች ከማስባል ሊያስቀረው አይችልም። አንድ ቤት ውስጥ ያሉ የአንድ እናት እና አባል ልጆች፤ ወንድማማቾች አንዱ አንዱን በጥላቻ ወይም በሌላ ጥቅም ተነሳስቶ ቢጣሉ እና ቢገድለው ወንድም ወንድሙን ገደለው አይደል የሚባለው። ህውሃት ባንዳ ሆነች አልሆነች፣ ተዋጊዎቹ የህውሃት ተላላኪ ሆኑ አልሆኑ፣ ውጊያው በሁለት ጎራ በተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን መካከል ነው እየተካሄደ ያለው። የህውሃት ክፉ፣ ጨካኝ እና አውሬ መሆን ኢትዮጵያዊነታቸውን እና የኢትዮጵያ ልጆች መሆናቸውን አያስቀረውም። ውንድማማች መሆን እና መባል አጥፊዉን ከተጠያቂነት አያስቀረውም። የስጋ ወንድሙን የገደለ ሰው የወንድሙ ገዳይ ተብሎ እንደሚጠየቅ ሁሉ የህውሃትም አመራሮች በአገር ላይ ክህደት የፈጸሙ፣ ንጹሃን ዜጎችን የገደሉ፣ በርካቶችን በሃያ ሰባት አመት ውስጥ አሰቃይተው የአካል እና የአዕምሮ ጉዳተኛ ያደረጉ፣ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ የጣሉ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የምትለዋን ዝነኛ የሆነች እና እነሱ ሌሎችን ሲከሱባት የኖሯትን አንቀጽ ጨምሮ ጠቅሶ ከወዲሁ ክስ መመስረት ይቻላል። በተያዙም ጊዜ በዚያ ክስ ውስጥ እንዲዳኙ ማድረግ ይቻላል። ይሄ ሁሉ ሆኖ ሰሞኑን በአየር እና በመሬት በተደረጉት ጥቃቶች ምን ያህል ሰው እንደሞተ እና እንደቆሰለ ከሁለቱም ወገን ትክክለኛ ቁጥር ባይገለጽም የሞቱት እና የቆሰሉት ሰዎች ወንድማማቾች ናቸው። ይሄ የማይዋጥለት ሰው ካለ ሸክሙ ለራሱ ነው። እንኳን በዛሬው ግጭት ይቅርና በትላንቱ በኢትዮ-ኤርትራው ጦርነት የሞቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሁለቱም ወገኖች ቀደም ሲል የአንድ አገር ልጆች የነበሩ ወንድማማቾች ናቸው።
የውስጥ ግጭቶችን የወንድማማች ብሎ ማሰብ በራሱ ግጭቶቹ ቶሎ እንዲቆሙ እና በተቃርኖ የቆሙ ሰዎች ልክ ዛሬ ኢትዮጵያና ኤርትራ አብረው መጓዝ እንደጀመሩት ነገም ተጋጪዎቹ አብረው ሊኖሩ እና ሊሰሩ እንደሚችሉ የሚያሳስብ ጥልቅ የሆነ የስነ ልቦና ጫና እንዳለው ብዙዎች የተረዱት አይመስልም። ብዙዎች ውስጥ እልህ፣ በቀል እና ቁጭት ብቻ ሲንቀለቀል ይታየኛል። አዎ ህውሃት ላይ የማያቄም፣ በቀል ያልቋጠረ እና ያልተቆጨ አብሯቸው አገር ያራቆተ፣ አብሯቸው የዘረፈና የበላ፣ አብሯቸው ግፍ የፈጸመ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ለዛም ነው ህውሃት እንደ ድርጅት ቢጠፋም ከሚደሰቱት ነኝ። አመራሮቹ ግን በምንም መንገድ፣ በይቅርታም ስም ቢሆን ከፍትህ ተጠያቂነት እንዳያመልጡ ስታገል የኖርኩት። እንኳን ህውሃቶች ሎሌዎቻቸውም አብረው ባጠፉት ልክ እንዲጠየቁ ነው ዛሬም የምሟገተው።
+ ምኞቴ
ምኞቴ ጦርነቱ ቶሎ እንዲቆም ነው። ምኞቴ ከሁለቱም ወገን የተሰለፉ ወታደሮች እርስ በርሥ ብዙ እንዳይጎዱ ነው። ምኞቴ የህውሃት መሪዎች ሁሉም ተለቃቅመው በሕግ ጥላ ስር እንዲውሉ እና ለፈጸሙት  ወንጀል በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ ነው። ምኞቴ ህውሃቶች ዘርፈው ያከማቹት ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ተወርሶ እነሱ ላራቆቷቸው እና የአካል ጉዳተኞች ላደረጓቸው ዜጎች መቋቋሚያ እንዲሆን ነው። ምኞቴ የምንደማመጥባት፣ እንስበርስ ላንገዳደል እና ጦር ላናነሳ ቃል የምንገባበትን አንድ ቀን ልክ እንደ አውሮፓዊያኖቹ “የጦር መሳሪያ የማንማዘዝበት ቀን” ብለን በመሰየም በየአመቱ እሱን ሙታንን እየዘከርን ማክበር ነው።
አሁንም የበቀደም ጸሎቴን ልድገመው እና ጽሁፌን ልቋጭ፤ ይህ ጦርነት በአጭር ጊዜ፣ በጣም እጅግ አነስተኛ በሆነ የሰው ህይወት ጉዳት እና ንብረት መውደም፣ በህውሃት ሹሞች እና በኦነግ ሽኔ ኃይሎች ፍርድ ፊት መቆም እንዲጠናቀቅ እግዚያብሔር ይርዳን። ይህ የወንድማማቾች ጦርነት ቶሎ በርዶ አገራችን ወደ ሰላም እንድትመጣ እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን ይወጣ። የጦርነትን ክፋት ለመመስከር የእኛን ያህል እድል የተሰጠው ህዝብ የለም እና ወድ ኋላ መለስ ብለን በጦርነት ምን እንዳተረፍን እና እንዳጣን እናስብ፣ ከአሥርት አመታት በፊት የሞቱብንን ወገኖቻችንን እናስብ፣ ለሰላም እንቁም፣ የመደማመጥ እና የመነጋገር ባህል እናዳብር።
Filed in: Amharic