>

የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦነግ የሚባል ጠላቱን እንጂ ሸኔ የሚባል አያውቅም (ከይኄይስ እውነቱ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦነግ የሚባል ጠላቱን እንጂ ሸኔ የሚባል አያውቅም

ከይኄይስ እውነቱ


ወዴት ሸርተት ሸርተት፣ የምን ደብቁኝ ነው – ኦቦ ቀጀላ? የኦሮሙማው አፈ ቀላጤ – ታዬ ደንድአ – ከሕውሓት ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች የሆነውን ኦነግ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው አሸባሪ አረመኔ ድርጅት መሆኑን ነው፡፡ ባንድ ወቅት ሸኔና ኦነግ አንድ ናቸው፡፡ የኦነግ የጦር ክንፉ ነው፡፡ ብለህናል፡፡ አንረሳም፡፡ የኦሕዴድ ባለሥልጣናትም ይህንኑ አረጋግጠውልናል፡፡ ዳውድ መሀል አገር ሆኖ ማን ማንን ትጥቅ ያስፈታል? ያለው ለኦነግ አሸባሪ ኃይል ካልሆነ ለማን ነው? የኦሮሙማ ዓላማ አንድ ስለሚያደርጋችሁ ብቻ አንዱ የሌላውን ነውር ለመሸፈን የምታደርጉት ሩጫ የትም አይደርስም፡፡ ቆሻሻ ፖለቲካችሁን ሕዝብ ላይ አታራግፉ፡፡ 

በበቂ ሁናቴ የተሰነደው የኦነግ አስነዋሪ የኋላ ድርጊቱ (track record) ሁሉ የሚያሳየው ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ጠላትነቱን፣ በተለይ ደግሞ ለአማራው ሕዝብ በዘር ፍጅት ከሕውሓት ጋር ባንድነት ተጠያቂ የሆነ የፈሪዎችና ጨካኞች ወንጀለኛ ስብስብ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ አይደለም፡፡ ለማና ዐቢይ ኦነግን ወዳገር ውስጥ ከማስገባታቸው በፊት ‹ሸኔ› የሚባል ቃል ሰምተን አናውቅም፡፡ ዛሬ ተነስቶ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ለማለት ስምን በመቀየር ለማምለጥ የሚደረግ የጅል ሙከራ አይሠራም፡፡ አገዛዙም ለኦነጉ አፈ ቀላጤ ለቀጀላ ሽፋን መስጠቱን የሚቀጥል ከሆነ ፀቡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ይሆናል፡፡ እንደዚህማ አትጨማለቁብንም፡፡ ጥጋባችሁን በልኩ አድርጉት፡፡ የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) በተፈጸመባቸው በንጹሐን የማይካድራ (አማራ) ወገኖቻችን እልቂት ላይ ከመሳለቅ ለይቼ አላየውም፡፡ በነገራችን ላይ የኦነጉ ቃል አቀባይ ቀጀላ የኦነግ ኃይሎች ከሕወሓት ጋር መሰለፋቸውን ‹ኦነግ የሚለው ስም ከሸኔ ጋር ተቀጽሎ እንዳይጠራ እየተነጋገርን ነው› በሚለው መግለጫው አምኖ ነግሮናል፡፡ እውነትህን ብለሀል፡፡ እኛም የምንለው ሸኔ የሚል ቅፅል ሳንጨምር አሸባሪዎቹን በትክክለኛ ስማቸው ኦነግ ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ 

በአማራ ወገኖቻችን ላይ ከጉራ ፈረዳው የዘር ፍጅት ጀምሮ እስከ ቅርቡ ወለጋ (ጉሊሶ) ለተፈጸመው የዘር ፍጅት ከሕወሓት ጋር በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም የወንጀለኛ መቅጫ  ፍርድ ቤት ሊጠየቅ የሚገባው ሽብርተኛ ድርጅት ነው፡፡ ድንቄው ሰላማዊ ተቃዋሚ!!! ለማያውቁሽ ታጥበሽ ታጠኚ፡፡ በዝርፊያ ያደፈና በንጹሐን ደም የተጨማለቀ እጁን ሊያነጻው የሚችለው እውነተኛ ፍትሕ ብቻ ይሆናል፡፡ 

በዚህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የቆማችሁ ሜዲያዎች በሙሉ አደራ የምለው ‹ሸኔ› የሚባል ነገር ስለሌለ በትክክለኛ ስሙ ኦነግ በማለት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ጠላቱን ልታሳውቁ ይገባል፡፡

Filed in: Amharic