>
5:26 pm - Monday September 15, 0887

ኮሚኒዝም በቀል አስተማሪ ይሆን?  (መንግሥቱ ደሳለኝ)

ኮሚኒዝም በቀል አስተማሪ ይሆን?  ከመንግሥቱ ደሳለኝ

መንግሥቱ ደሳለኝ


ቁጭ ብሎ የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ይቸግራል እንዲሉ፣ዛሬ ህወሃት በእዚህ አቅም መንግሥትን ሊገዳደር የቻለው በሰአቱ ተገቢው እርምጃ ባለመወሰዱ ነው፡፡ አንድ ጉዳይ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን የጊዜ ቀመሩም ወሳኝ ነው፡፡ በሰአቱ ካልሆነ ጉዳዩ ውጤት አለማስከተሉ ብቻ ሳይሆን ጉዳትም ሊያስከትል ይቻላል፡፡እውነታው ከሚፈልገው ውጪ በሃሳባዊ እሴቶች ላይ ተመስርቶ የማይሆንን በማለም መተግበር (ከውሳኔ ያለመድረስ) ራሰን ለጥፋት ይዳርጋል ይላል ማኪያቬሊ፡፡ከሩቅ ልትመክት የምትችለውን ዘንዶ እንዲጠመጠምብህ ዕድል እንደመስጠት ነው፡፡ለወደፊቱም ከእዚህ ትምህርት መውሰድ በእጅጉ ይገባል፡፡

ኮሚኒዝም በቀል አስተማሪ ይሆን? ፍሬዴሪክ ኤንግልስ  በቀልን እንዴት አጣጥመህ  እንደምትጠቀምበት ከሚሰብካቸው አንዷን ልጥቀስ ‘’ Do not forget any affront done to you and to our people, the time of revenge will come and must be put to good use’’ ይላል፡፡

‘’አብዮታዊ ዴሞክራሲ’’ /የጫካው ህግ/ ለህውሃት ሃይማኖትም፣ የስነ-ምግባር መመሪያም ነበር፣አካዳሚያዊ ዕውቀት፣ክሕሎት፣ሞራላዊ ብስለትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮ አልነበራቸውም፡፡አለመኖር ብቻ ሣይሆን ትምህርት ጠልም ነበሩ፡፡ትምህርት ከድል በኋላ በሚል ስልጣን-ስልጣኗን ሲያባርሩ ትምህርት፣ሞራልና ክህሎትን የሚያክል ሃብት አመለጣቸው፡፡  አንዳንዶቹ ሆሄያቱን ያወቁት እኮ ከስልጣን በኋላ ነው፡፡በእዚህም ምክንያት ትልልቆቹ አመራሮች እንኳን ቢሮአቸው የመጡትን ባለጉዳዮች የሚያስተናግዱበት መንገድ እጅግ ስነምግባር የጎደለው በፀያፍ ቃላት የታጀበ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነበር፡፡ሃገር ጠልቶ፣ሃይማኖት አንኳንሶ፣ሞራል አኮስሶ ስጋዊ ፍላጎትን ብቻ ለማርካት የሚደረግ ግብግብ በእርግጥም ችግር ነበረው፡፡  

ህውሃቶች ወደ ስልጣን ሲመጡ ልጆች ናቸው – የማንጁስ መአት፡፡ክህሎታቸው ውጊያ፣ዝርፊያና ጎሰኝነት ነው፤እሴቶቹም እነዚሁ ናቸው፤ጨዋታቸው ውጊያ ነው፣ስነልቡናቸው ውጊያ ዝርፊያና ጎሰኝነት ነው፣አመራሩ የማፍያ አይነት ሚስጥራዊ የቤተሰብ ስብስብ ነው፡፡ ይህው ነው ክህሎቱም፣ ይህው ነው ልማዱም፤ ‘’A man is what he mostly does, excellence is then not an art but a habit’’ – እንዲል Aristotle. በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ ያደረጉት በመሆኑ ስብዕናቸውን ገዝቷቸዋል፤የዕለት ተዕለት ልማድም ነው፤ሰው ያደገበትን ነው የሚሆነው፡፡ክፋትም በጊዜ ሂደት ቁስኣካለዊ ሃይል ይሆናል – ከውስጥ ሰርጿል፣ደርጅቷልና፡፡በልጅነት የሰረፀ በስተርጅናም አይገፋም፡፡ 

ከስታሊን ፣ማኦ ዜዱንግና እና ከሰንሱስ የብሄር ጥያቄ፣ ስደስቱ የውትድርና ጉዳዮች፣ የጦርነት ጥበብ፣የሽምቅ  ውጊያ ወዘተ. ከሚባሉት መፃህፍት ለውጊያ የሚጠቅሙትን በመልቀም በትግርኛ ተገልብጠው ተሰጡ፣ በልጅ አዕምሮ መርዝ ተረጨ/ሰረፀ፡፡የህውሃት እሴት ይሄው ሆነ፡፡በእዚህም፡-

‘’እንደ አድዋ ስላሴ እንደ አክሱም ፅዮን፣ 

ተሳልሜው ልምጣ አይንና ጥርሷን፡፡ ‘’ የተባለለት የትግራይ የኦርቶዶክስ ምድር የኤቴኢስቶች /ሃይማኖት የለሽ/ መፈልፈያ ሆነ፡፡

እንዲያው ልጅነት ሆነና ክፉ ክፉውን ያዙት አመረሩበት እንጂ ማኪያቬሊ እኮ ክርስtያናዊ አስተምሕሮ የሚመስሉ /Christian virtues / እሴቶችን ንግሥትና ንጉሶች እንዲተገብሩ መክሯል፡፡ለምሳሌ፡- አትጨክን፣አትስረቅ፣አንብብ፣ከጥሩው ነገር ተማር፣በቦታህ/በሃላፊነትህ  ተገኝ ወዘተ. ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ይሁን እንጂ ህወሃት በጎ ምግባር /Decency/ የጎደለው የፀላዬ ሰናይ ቡድን እንደነበር አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በህይወት እያለ መናገሩን አስታውሳለሁ፡፡’’Better be right than being popular ‘’ የሚለው ምክር ህወሃት ጋ የለም፤ልክ/ትክክል  መሆንን ይጠየፈዋል፡፡

ላብ፣ስራና ጥረት የሃብት ምንጭ ናቸው የሚለው ተግልብጦ ‘’ get rich quick – wealth without work ‘’ በሚል ስሌት በዝርፊያ ወረት ተቋጥሯል፡፡ ጆን አዳም ፖለቲካ መሃል መንገድ አያውቅም ብሏልና የሃብትና የኢፍትሃዊ ጥግ ተይዛል፡፡መሃሉን ሞኝ እንዲሄድበት፡፡ 

ሕወሃት በመንግሥት ደረጃም የሚያውቀውን ያህል ነው የሆነው፡፡የማያውቀውን መጠበቅ ልክ አይሆንም፡፡ከሌላው የኢትዮጵያ ክልል ወደ ትግራይ በህግወጥ መንገድ ሃብት ያሸሽ የነበረ ድርጅት በለመደ እጁ ወደ ውጭ አገር ቢያሸሽ ምን ይፈረድበታል – አሁንም የሚያውቀውን ነው የሆነው፣የሚጠበቅም ነው፡፡ 

ወያኔ ርዕየተ አለም አልነበረውም ፡፡ አብየታዊ ዴመክራሲ ለኤሊት ፍጀታ የቀረበ ባዶ ዲስኩር ነበር፡፡ጭራም ቀንድም፣ደምም ስጋም የሌለው በድን ርዕዮት ነው፡፡ ህወሃት ገንዘብ ጌታው የሆነበት ስብስብ ነው፡፡ህወሃት ሃገራዊ ራዕይ የራቀው ሲነሳም የሚተናነቀው መልቲ ቡድን ነው፡፡ ዕውቀትና ሃብት አሰባስቦ  ሃገርን የመለወጥ አጀንዳ ኖሮት አያውቀም፡፡የሃገረ ሃብት ወደ ግል ተዞረ፣ተመዘበረ፣የተለየ ሃሳብ ያለው ታሰረ፣ተገረፈ፣ተሰደደ፣ተገደለ፡፡ታሪኩ ይህው ነው፡፡

በውስጥም በውጭ ሃገርም ልጆቹን አስተምሮ፣ኩሎና ድሮ፣የዕድሜ ልክ ሃብት አውርሶ፣ ለወግ ለማዕረግ አብቅቶ፣ሃገር እንድትፈርስ የሚያሴር በእዚህ በገዘፈ መልኩ ብልፅግናዋን ሳይሆን ሞቷን የሚመኝ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚታወቀው ወያኔ ነው፡፡ከራስ ጉያ እንዲህ አይነት ወገን መብቀልን የመሰለ መርገምት የለም፡፡ለኢትዮጵያ ከህወሃት ግብፆች እንደሚያዝኑ መከራከር ይቻል ይሆናል፡፡

የአልባኒያ ኮሚኒዝም እና የኢንቨር ሆጃን አመራረ ለመኮረጅ የተፈለገው ለምንድነው? ሁሉን ጠቅላይ ብረታማ አምባገነን በመፍጠር ከውስጥ በሚፈጠሩ የጥቂት ከበርቴዎች ስርዓት Plutocracy በመፍጠር በጮሌነት ለመመንተፍ ነው፡፡ 3 ሚሊየን የማይሞላ ህዝብ ያላት አልባንያ የኮሚኒዝም ጣጣ ባወረሳት ድህነት ምክያንት በአውሮፓ የመጨረሻው የድህነት ጠረዝ ላይ ያለች አገር ናት፡፡ ጦሱ ዛሬም ድርስ አለቅ ብሏት መተዳዳሪያዋም በአብላጫው  የሚመነጨው ከአገር ውጭ ባሉ የአልባኒያ ዜጎች በሚልኩት ገንዘብ ነው /Remittance/፡፡

የታሰበው ከህወሃትና  እና ከጥቂት  እርሱ ከሚፈቅድላቸው የተለያዩ የብሄረሰቦች ወኪሎች በሃብት በልፅገው የካፒታለስት ስርአት ተጠሪ እንዲፈጠር እና እነርሱው ተመልሰው ደግሞ ስርአት አሸጋጋሪ በመሆን ‘’ ከእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለሁሉም እንደፍላጎቱ’’ በሚል የኮሚኒስት መርሕ አስፈፃሚ የመሆን ነው፡፡ በመሰረቱ በኮሚኒዝም 3 መደቦች ጎልተው ይወጣሉ፤ሙሁራዊ መሳዩ አድብቶ ሊበላ ያሰበው የኮሚኒስት ስብስብ፣ላብ አደሩና፣ቡርዣው/ከበርቴው ናቸው፡፡የኮሚኒስቱ ስብስብ በላብ አደሩ ዙሪያ በማንዣበብ የፓርቲ አደረጃጀትና ገፅታ በማስያዝ በሰው ሰርግ የመሞሸር አይነት ስራ ይሰራል፡፡ በተግባር እንደታየውም በኋላ ላይ  የላብአደሩም ጭምር ፀር ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሚኒስታዊ እሳቤዎች የተተገበሩበት መንገድ ግልብና ውልግድግድ ያለ ነው፡፡ስለ ላብ አደር/ወዝአደር እና ከበርቴ በሚኖራቸው የስርአት ተጠሪነት ውስጥ የኮለኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም /የጭቁን ወታደሮች ስብስብ/ እና የአቶ መለስ ዜናዊ የብሄር ተኮር ፖለቲካ አጋፋሪዎች ምን ይሰራሉ፡፡እውነቱ ግን አፍሪካ ውስጥ ከጥቂት አገሮች በስተቀር የመንግሥት ስልጣን እንዳደረጓት ትደረጋለች፡፡ የድሃ ሃገር ህዝብ ደግሞ ፈቃጅ ነው፡፡ፖለቲካውም ይህው ነው ሌላው ማስመሰያ ነው፡፡ 

በደርግና በትህነግ ሰሻሊዝምን አስታኮ የተመሰረቱት ስርአቶች ከጥቅማቸወ ይልቅ የጉዳትና ክፋት ውርሳቸው /legacy/ ይበረታል፡፡ ሀዘን የሞላበት፣የንብረትና የገንዘብ ኪሳራ የገዘፈበት በመሆኑ ሶሻልስታዊ እሳቤ /Populist view/ እንደ ስዊድንና ጀርመን ያሉ ሃገራት የተገበሩትን አይነት አንኳን አንዳናስብ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ሄዷል፡፡

አንሰማም እንጂ ከ2500 አመት በፊት ኮንፊሽየስ ወደ መንግሥታዊ አመራር የሚመጡ  ግለሰቦች አካዳሚያዊ ሰፊ ዕውቀት፣ የካበተ የሞራል ስብዕና /Superior moral quality/ እና ጥልቅ ክህሎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁሞ ነበር፡፡በስነ ምግባር የታነፁ፣የተከበሩ፣የሚከብሩ፣ለሌሎች መልካም ለመስራት የተዘጋጁ፣በፍትህ ርትዕ የተካኑ፣ራሳቸውን ያላኩራሩ እና የአገልጋይነት ስሜት የገዛቸው መሆን አለባቸው ይለናል፡፡ ይሄ እንግዲህ የወደፊቱ የቤት ስራችን ነው፡፡አሁን የለንም፡፡

ሁሉ ለበጎ ነው! እንደሚባለው ከእዚህ ትምህርት መውሰድ ለሁሉም ዜጋ ተገቢ ነው፡፡ሣያውቁ መሾም፣ሌላንም ለሹመት ማብቃት ለሃገርና ለህዝብ ኪሳራ ነው፣ለትውልድም ዕዳ ነው፤አካዳሚዊ ዕውቀት፣ክህሎት፣ሞራላዊ ብስለትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮ፣ የሌለው ለህዝብ አገልጋይነት ማሰብ ጎጂ እርምጃ ነው፡፡ከወያኔ ፍልስፍና የማይሻል አስተምህሮ በምድር ያለ አይመስልኝም፡፡

ስለዚህ ትግሉ ይህን ፍልስፍናና እምነት ጎጂነቱን በመገንዘብ ከዶክትሪን እስከ ተቋማት ግንባታ ሁለገብ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ምንም ነገር በግማሽ ልብ መጀመር ስኬት ይነሳልና በሙሉ ልብ መጋፈጥ ይገባል፡፡ ለጊዜው መሳሪያ ፖለቲካን ይከተላል ተብሏልና የህወሃት ፖለቲካም ሸማች ስለአጣ እየተጋፈጠ ያለውም ህዝባዊ ሰራዊት በመሆኑ ህወሃት ታሪካዊ ሽንፈቱን በቅርቡ የሚያጣጥም መስሏል፡፡ ‘’ the army of the people is invincible ‘’  Mao Tsedung፡፡

Filed in: Amharic