>

ጄኔራሎቹ ስለጦርነቱ ይናገራሉ !   (ውብሸት ታዬ)

ጄኔራሎቹ ስለጦርነቱ ይናገራሉ !

  ውብሸት ታዬ

*…ጦርነት የሰለጠነና በቂ ተዋጊ የሚያስፈልገው ሲሆን በግንባር/War front/ እንዲሁም በመጠባበቂያ/Reserve/ የሚሰለፍ ይሆናል። በቂ ሎጂስቲክ(ትጥቅና ስንቅ እንዲሁም ሕክምናና የመሳሰሉት) የሚዋጋለት ዓላማ፣ የሕዝቡ ሞራልና አጋርነት፣ ለጦርነቱ ምክንያት የሆነው ተጨባጭ እውነትና ጦርነቱን ድል በማድረግ ፍትሕን ወደቦታዋ የመመለስ ጀግንነታዊ ቁጭቶች ናቸው ሲሉ ዘርዝረዋል።
 ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ በታሪክ ተሰምቶ በማያውቅ አስነዋሪ መንገድ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የአጸፋ እርምጃ እየተወሰደበት ይገኛል።
   የጥፋት ሃይሉ የአጸፋ እርምጃውን በመፍራት እየፈረጠጠ በመሄዱ በርካታ አከባቢዎች ከከሃዲው ሃይል ነፃ እየወጡ ነው። የመጨረሻው ከበባም መቀሌ ባለው ጁንታ ላይ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሰነዘረ መሆኑን የሚመለከታቸው የጦር አዛዦች መግለጫ ሰጥተውበታል።
  ሆኖም በእንደዚህ ዓይነቱ የጦርነት ንቅናቄ ወቅት ሕዝቡ በቂ መረጃዎች እና ሙያዊ ትንታኔዎችን ማግኘት ያለመቻሉን እየገለፀ ይገኛል። ይህን የመረጃ ክፍተት/እጥረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለመሸፈን የኢትዮጵያን ዳይጀስት ባልደረቦች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
   በዛሬው ዕለት አብረናቸው አጭር ቆይታ ያደረግነው ሦስት የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች በአንዳንድ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አጭርና ሲቪሉ ማሕበረሰብ ሊገባው በሚችለው አገላለጽ ያጋሩን ሃሳቦች አሉ።
   ጄኔራል መኮንኖቹ ከግራ ወደቀኝ፤ ሜ/ጄ/ል መርዳሳ ሌሊሳ፣ ብ/ጄ/ል ዋሲሁን ንጋቱ እና ብ/ጄ/ል አሰፋ አሕፈሮም  ናቸው።
  ከሁነቱ ውስብስብነት አኳያ፤ ካቀረብንላቸው ጥያቄዎች ለዛሬ በሁለቱ ላይ የሰጡንን አስተያየት እነሆ።
  የመጀመርያው በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያደረጉ አዛዦችና ተባባሪዎቻቸው በምን ዓይነት ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይገባል? የሚለው ሲሆን ጄኔራል መኮንኖቹ ጉዳዩ በግዳጅ ላይ በተሰለፈ ሠራዊት ላይ የተፈጸመ በመሆኑ በወታደራዊ ፍርድ ቤት(Court Martial) የሚታይ፣ ጉዳዩም በአገር ክህደት የሚያስከስስ፣ ከሁኔታው አሰቃቂነት አኳያ ‘ይግባኝ የማይጠየቅበት'(Extrajudicial Punishment) ሊሆን የሚገባው ነው ብለዋል።
   እንደጄኔራል መኮንኖቹ አገላለጽ በወታደራዊ ፊልድ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚታዩበት የመከላከያ ሠራዊቱ ሕግ ያለ ሲሆን ጉዳዩን የሚመለከቱ፣ ሁኔታውን በተጨባጭ የሚረዱ ወታደራዊ ዳኞችም አሉ ብለዋል።
   ሁለተኛው ማብራሪያ እንዲሰጠን የጠየቅንበት ጉዳይ ደግሞ አንድን ውጊያ በድል ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ምንድናቸው? ከዚያ በመነሳትስ በአገር መከላከያ ሠራዊታችንና በከሃዲው ሃይል መካከል ስላለው የሐይል አሰላለፍ ምን ለማለት ይቻላል? የሚል ነበር።
  ጄኔራል መኮንኖቹ በምላሻቸው፤ ጦርነት የሰለጠነና በቂ ተዋጊ የሚያስፈልገው ሲሆን በግንባር/War front/ እንዲሁም በመጠባበቂያ/Reserve/ የሚሰለፍ ይሆናል። በቂ ሎጂስቲክ(ትጥቅና ስንቅ እንዲሁም ሕክምናና የመሳሰሉት) የሚዋጋለት ዓላማ፣ የሕዝቡ ሞራልና አጋርነት፣ ለጦርነቱ ምክንያት የሆነው ተጨባጭ እውነትና ጦርነቱን ድል በማድረግ ፍትሕን ወደቦታዋ የመመለስ ጀግንነታዊ ቁጭቶች ናቸው ሲሉ ዘርዝረዋል።
  በእነዚህ ሳይንሳዊ ስሌቶችና እውነቶች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሰከንድ እንኳ ጥያቄ ውስጥ በማይገባ ሁኔታ ፍጹማዊ የሆነ ወታደራዊ የበላይነት፣ ሞራላዊ ልዕልናና የአገራዊ ክብር ማስጠበቅ ባለአደራነትን ተሸክሞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በተቃራኒው ከሃዲው ሃይል ለውርደታዊ ሞትና በታሪክ ፊት ሁሉ በሚያሸማቅቀው መስመር ላይ ቆሟል ብለዋል።
  ዝርዝሩ እንዳይበዛባችሁ በማሰብ፤ በተነሱ ተጨማሪ ሃሳቦች ላይ ሁለተኛውን ክፍል ነገ እናቀርባለን።
ከኢትዮጵያን ዳይጀስት ጋር ይቆዩ !
Filed in: Amharic