>

ይድረስ ለሽመልስ አብዲሣና መሰል አክራሪዎች! (ይነጋል በላቸው)

ይድረስ ለሽመልስ አብዲሣና መሰል አክራሪዎች!

ይነጋል በላቸው


  1. የታሪክን ዱካ አይተው ምንም መማር ከማይችሉ ገልቱዎች ጋር መለፋለፌ ያሳዝነኛል፡፡ ግን ሌላ ምርጫ የለኝምና ለ“ብዬ ነበር” ፍጆታ ያህል ጥቂት ልበል፡፡ ፖለቲካዊ ሸፍጥና ወር-ተራዊ የዘረኝነት ስካር ሀገራችንን ከመኖር ወዳለመኖር እየለወጧት ነው፡፡ እግዚዖ እንበል፡፡
  2. የኦሮሙማ መጤ ፍልስፍና አራማጆች በአፈ ቀላጤያቸው በሽመልስ አብዲሣ በኩል እንደነገሩን አማርኛን በኦሮምኛ ለመተካት ጫፍ ላይ ደርሰዋል፡፡ ለዚህ ዓላማቸው ስኬትም ከፀሐይ በታች የማያደርጉት አንዳችም ነገር እንደሌለ በግልጽ ነግረውናል – ሰምተንማል፡፡ ይህ ግን እንደኔ እምነት የማይሣካ የቅዠት ውጤት ነው፡፡ ቅዠቱ እውን ቢሆን ደስታው ይበልጥ ትልቅ የሚሆነው አማሮች ለሚባሉቱ ነበር፡፡ ይሁንና በመቶዎች ምናልባትም በሽዎች ዓመታት በኦሮሞ ነገሥታት ጭምር ወደሰማየ ሰማያት የተሰቀለን የሀገር የወል ሀብት በአንድና በሁለት አሠርት ዓመታት ለማጥፋት መሞከር ከትዝብት ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ አርቀው ነው ሽቅብ ያጓኑትና በስሜትና በሰው ደም ጭዳ እንዲህ በቀላሉ አይወርድም፡፡ አማሮችን በተወሰነ ደረጃ ማጥፋት ይቻላል፡፡ ይህንንም ኦሮሚያ በሚባለው ግዛትና ኦሮሙማ በሚንደላቀቅበት ቤንሻንል አካባቢዎች በተግባር እያየን ነው፡፡ ከሁኔታዎች እንደምንረዳው ዕርዱ ጀመረ እንጂ በዕቅዳቸው መሠረት ገና አልተሟሟቀም፡፡ እነሸመልስ በሰሜን ከወያኔ ጋር የተጀመረውን ጦርነት ሽፋን በማድረግ በተለይ ሰሞኑን አማራን በማስጨፍጨፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዕጥፍ ድርብ እንደሚከፍሉት ባውቅም የወገኖቻችን መጨፍጨፍ ከወያኔ ጋር በሚደረግ ጦርነት ተሸፍኖ ሊድበሰበስ አይገባምና የሚመለከታችሁ ወገኖች እንድታስቡበት በግሌ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ እንዲህ የምለው የደምን መልስ ጠንቅቄ ስለማውቅም ነው፡፡ የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀረው ጌታ፣ የደርግንና የወያኔን መጨረሻ ሣልሞት ያሳየኝ ጌታ … ፍርዱን የሚቀጣጠቡት አይደለም፡፡  
  3. እንዳልኩት አማርኛ በትግሬዎችም፣ በአገዎችም፣ በኦሮሞዎችም … በሁሉም የኢትዮጵያ ገዥዎች አማካይነት ለአገዛዝ እንደሚያመች ታምኖበት ይመስለኛል ወደ ትልቅ ከፍታ ወጥቷል፡ ከዚያ ከፍታ ማውረድና በሌላ መተካት የሚቻለው ይህን ቋንቋ ይናገረዋል ተብሎ የሚታሰበውን የአማራ ሕዝብ ከምድረ ገጽ በማጥፋት ሳይሆን በተለዬ ሥልጡን አካሄድ በመጓዝ ነው፤ ጀብደኝነትንና የቋንቋ አርበኝነትን  ሳይሆን ጥበብንና ብልኃትን ይጠይቃል፤ እንዲህም ሲሆን አስፈላጊነቱ ከታመነበት እንጂ የተዘጋጀን ምግብ ደፋፍቶ አዲስ ምግብ ለመሥራት ጫካ ምንጠራና እሳት ፍለጋ መንከራተትን ወደው የሚገቡበት ድካም ሊሆን አይገባም፡፡ 86 ነገድ ኦሮምኛን በወራት ለማስተማር ሱሪ ባንገት ከማለት በሚያውቀውና በሚያግባባው የወል ሀብት ቢያስተዳድሩት ክፋት የለውም፤ ወያኔዎችም ያደረጉት ይህንኑ ነበርና፡፡ ምንም እንኳን ከ1983ዓ.ም ወዲህ በወያኔ ሤራና ተንኮል የማይናቅ ተፅዕኖ ቢደርስትም አማርኛ ቋንቋ እዚያ ላይ የወጣውና የመላው ኢትዮጵያዊ የወል መግባቢያ ሊሆን የቻለው አማሮች የተባሉት አሁን በአንዳንድ አክራሪዎች እንደ ዐውሬ የሚታዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች 86ቱንም ብሔር ብሔረሰቦች በያሉበት በሜንጫና በቆንጨራ በማረድ አልነበረም፡፡ ስለሆነም አክራሪ ኦሮሞዎች ከገባችሁበት የቅዠት ዓለም በቶሎ ውጡና ወደየኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ይህንንም የምታደርጉት ለራሳችሁ ስትሉ ነው፡፡ ነገ ሌላ ቀን መሆኑ አይቀርምና፡፡
  4. ኢትዮጵያውያን የማያሸንፉትን ጦርነት አይጀምሩም፡፡ ከጀመሩም ሳይጨርሱ አይተውም፡፡ አሁን ጦርነቱ ተጀምሯል፡፡ ይህ “በጉጉት ይጠበቅ” የነበረ ጦርነት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ሊወስድ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ብዙ ፀረ ኢትዮጵያ የውስጥም የውጭም ኃይሎች በርካታ ውድመትና ኪሣራ እንደሚያስከትሉ ይገመታል፡፡ በዚህን አጋጣሚ ጤነኛ የሆናችሁ በተለይ ኦሮሞዎችና  ትግሬዎች እንዲሁም ሌሎችም የማኅበረሰብ አባላት በሽተኞችን በማከምና ከዕብደት በመመለስ ረገድ ብዙ ይጠበቅባችኋል፡፡ አለበለዚያ የሕይወትና የንብረት ውድመቱ ከሚጠበቀው በላይ ይሆንና የነፃነታችን ዋጋ “የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ጠፋች” እንደሚባለው እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ በዚህን ዓይነት የውዥንብር ዘመን በሚናፈሰው ሁሉ አለመወሰድ ጠቃሚ ነው፤ ማስተዋልን ገንዘብ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የገበያ ግርግር ለሌባ እንደማመቸቱ ይህ ጊዜ በተለይ ለአቅለቢስና ጥቅም ፈላጊ ወገኖች ዋና መገልገያ ነው፡፡
  5. ላጠቃልል፡፡ ብዙ የሚበለሻሽ ነገር መኖሩ ከፋ እንጂ አጥፍቶ ጠፊዋ ወያኔ በፈተለችው ገመድ በቅርብ ታንቃ ከዚህኛው ዓለም “እሳቱ ወደማይጠፋው፣ ትሉ ወደማያንቀላፋው” ወደዚያኛው የሲዖል ዓለም ታልፋለች፡፡ ጅምሩን እየታዘብን ነው፡፡  የነብር ዐይን አይቷታል፡፡
  6. እነሽመልስ አብዲሣ ጦርነት ከናፈቃቸው የታጠቁ “ወንዶች” ጋር ይግጠሙ እንጂ ንጹሓን ሴቶችንና ሕጻናትን በአሳቻ ሰዓት እየሄዱ አይረዷቸው፡፡ ለምንም ዓላማ ይሁን ይህ ዓይቱ ድርጊት እግዜርም ታሪክም ይቅር የማይሉት ወራዳ ተግባር ነው፡፡ ማረድ ካማራቸውም ይቀጥሉበት – ጨካኝ ሆኜ አይደለም፤ ተስፋ ከመቁረጥም አይደለም፤ ከአራጅ ይልቅ ታራጅ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆኑን ከመረዳት እንጂ፡፡ የታረደው ሰማዕት ነው፤ ነፍሱ ወደሰማይ ሄዳ ምታመጣው የመከራ ዶፍና መቅሰፍት ግን ለአራጆቹ ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻቸውና ለሌላውም የሚተርፍ ነው፡፡ “ለኃጥኣን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል” እንዲል መጽሐፉ፡፡ “የኦነግና ወያኔ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆኜ ነው የጥፋት ሠራዊት አባል የሆንኩትና ንጹሓንን ባለማወቅ ያረድኩት” ማለት  ከምንም አያድንም፡፡ ከወልጋዳ የጠላት ትርክትት ራስን በጊዜ በማጽዳት ሰው መሆን ብቻ ነው አንገትን ቀና አድርጎ የሚያስኬድ የነገ ንጹሕ ዜጋ የሚያደርግ፡፡ እንዲህ በልና ጩኽ የሚል መንፈስ በውስጤ ያናግረኛል፡፡ 
  7. አበሻ “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” የሚለው አለነገር አይደለም፤ የነሽመልስን ጥጋብና ዕብሪት የሚያበርድ ኃያል ዝናብ ሲመጣ ይታየኛል፡፡ ውርድ ከራስ፡፡ መልካም የዕርድ ዘመን ያድርግልን፡፡ እግዚአብሔር ሆይ! ለአራጆች የሚያስተውል ልብን ስጥልን፤ የመከራ ዘመናችንንም አሳጥርልን፡፡ ትልቅ ሰው ጠፍቷልና ዘጠኝ ወርና ዓመታትን ፈጅተህ ሳይሆን በአንድ ቀን አዳር ፍጠርልን፡፡ ሰው ተራብን ….
Filed in: Amharic