>

ከሕዝብ እውነተኛ ፍላጎቶች መማር ብልኅነት ነው! (አምባቸው ደጀኔ)

ከሕዝብ እውነተኛ ፍላጎቶች መማር ብልኅነት ነው!

አምባቸው ደጀኔ


martyrof2011@gmail.com


እንደመጥፎ ዕድል ሆኖ ተከታታይ መንግሥቶቻችን የራሳቸውን እንጂ የሕዝብን ፍላጎት አያጤኑም፡፡ ይህን ተወራራሽ የመንግሥታት ጠባይ አንድ ቦታ ካላቆምነው ጉዳቱ ሀገርን እስከማፍረስ ሊያደርስ እንደሚችል በግልጽ እያየነው ነው፡፡

ጅማሮው ርግጥ ነው በየቤታችን ነው፡፡ ከቤት ያልጀመረ መልካምነት ወይም ክፋት በመንግሥት ደረጃ አይታይም፡፡ “ማንነትህን እንድነግርህ ጓደኛህን ንገረኝ” የሚባለው አባባል እውትነት አለው፡፡ ቤታችንን ስንፈትሽ ሚስት ባሏን፣ ባል ሚስቱን፣ ወንድም ወንድሙን፣ እህት ወንድሟንና እህቷን፣ ጎረቤት ጎረቤቱን፣ ጓደኛ ጓደኛውን … የማክበሩና የመውደዱ ባህላችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈዘዘ መጥቶ በተለይ አሁን አሁን ሀገራችን በሰው አምሳል የሚንቀሳቀሱ አሻንሊቶች ሀገር ልትሆን ምንም አልቀራት፤ ብዙዎቻችን ገንዘብን ወደማምለክ ተለውጠናል፤ ፍቅርን ተርበናል፤ ሰው ሰው መሽተታችንን አቁመናል፡፡ ነገረ ሥራችን ሁሉ ገሞራው በግጥም እንደተናገረው “ምን ያለ ዘመን ነው ዘመነ ግርምቢጥ፤ ውሻ ወደ ግጦሽ አህያ ወደሊጥ” እንደተባለው ነው፡፡ ይህ ሸውራራ አካሄድ ካልተስተካከለ አደጋው ትልቅ ነው!

አንዲት የተዘወተረች ቀልዳዊ ተረት ላስታውሳችሁ፡፡ አኳኋኗ ሁሉ ከባሏ በተቃራኒ የሆነ አንዲት ሴት ነበረች፡፡ እንብላ ሲሏት እንተኛ ዓይነት፡፡ ከዕለታት በአንደኛው አንድ እንግዳ ወደቤታቸው ይመጣል፡፡ ራት በልተው ሊተኙ ሲሉ ባል ሆዬ “አንቺና ልጆችሽ መደቡ ላይ ተኙ፤ እኔና እንግዳው የጠፍር አልጋው ላይ አጎዛ ቢጠየ ይነጠፍልንና እዚያ እንተኛ” ይላታል፡፡ ሚስት ቀበል ታደርግና “ሞኝህን ፈልግ! እኔና እንግዶ አልጋው ላይ፤ አንተና ልጆችህ መደቡ ላይ እንተኛለን” ብላ ድርቅ! ወያኔን ማነው ደረቅ ሰውን ዱሮውንስ ማን ያሸንፋል፡፡ … 

ያቺ ሴት አሁንም ከዕለታት በአንደኛዋ ደራሽ ጎርፍ ይወስዳትና ሬሣዋን ለመፈለግ መንደርተኛው ሁሉ ከባሏ ጋር ወደ ወንዙ ይሄዳል፡፡ የሚስቱን ዐመል የሚያውቀው ባል “ወንድሞቼ፣ የኔን ሚስት ጠባይ መቼም ታውቃላችሁ፡፡ ስለዚህ ሬሣዋን ከወንዙ ወደታች ሳይሆን ከወንዙ ወደላይ ነው መፈለግ ያለብን” ብሎ ልቅሶውን ወደ ፈገግታ ለውጦታል ይባላል፡፡ እንደኛ ሀገር ነገር – እያነቡ እስክስታ፡፡

አላማጣ በመከላከያና በአማራ ጦር ከወያኔ የባርነት አገዛዝ ነፃ ስትወጣ እውነተኛ የሕዝብን ስሜት አየን፡፡ ከንግግራቸው በበለጠ በሰውነታቸው የተገለጸው ስሜታቸው ብዙ ይናገራል፡፡ እንዴት ታፍነው እንደነበር በጣም ያስታውቃል፡፡ እንደገና የተፈጠሩ ያህል ተሰምቷቸዋል – እነሱም አልሸሸጉም፡፡ የያዙት ባንዲራም የመለስን የቤተ ሙከራ ፍጡር ባለኮከቡን ሳይሆን እውነተኛውን የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው፡፡ ከወያኔ የባርነት ቀምበር በቅርቡ ነፃ የወጡ ዜጎች ሁሉም ስሜታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ከነሱ መማር ታዲያ ብልኅነት ነው፡፡

ከእውነት ጋር የሚጋጩ ብዙ የመንግሥት ሰዎችና ተቋማት አሉ፡፡ የወያኔን ህገ መንግሥት እንደመጨረሻ የእግዚአብሔር አሠርቱ ትዕዛዛት የሚቆጥሩ ወያኔ ወለድ ባለሥልጣናት የሕዝብን ፍላጎት ቢያነቡና ቢገባቸው ይህን ማንም የማይወደውን ባለኮከብ የሰይጣን ባንዲራ ለአንዲት ሴከንድም በሀገራችን እንዲውለበለብ ባልፈቀዱ ነበር – ግን ለዚህ አልታደሉም፡፡ በምኒልክ የደነቆረ በምኒልክ ሲምል ይኖራል እንደተባለው ነው ነገረ ሥራቸው፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ ተዋድቆ ወያኔ እንዲገረሰስ የተደረገው ለዚህ ባንዲራና ለዚያ ከወረቀቱ ያነሰ ዋጋ እንዳለው ለሚነገርለት ህገ መንግሥት ተብዬ አልነበረም፡፡ ግን ልክ እንደዚያች በተቃርኖ ተሞልታ ቤቷን ለማፍረስ እንደተዘጋጀችው ግጅል ሴት የሚቆጠሩት ባለሥልጣናት እነሱ ራሳቸው እንኳን ከቁብ የማይቆሩትን ባንዲራ ሕዝብ እንዲጠቀምበት ያስገድዳሉ፡፡ በእውቱ እንደዚህ ባንዲራ የሚያሳዝን ባንዲራ በዓለም የለም፡፡ ሲሰቀልም ሆነ ሲወርድ ከጉዳይ የሚጥፈው የለም፤ በብዙ ቦታ እንዲያውም አንዴ ከተሰቀለ ተቀዳዶና ነትቦ አንዱ ቅዳጅ ወደ ሰሜን ሌላኛው ቅዳጅ ወደ ደቡብ ሲውለበለብ እዚያው ይውላል፤ ያድራልም፡፡ የሚገርመው አንዳንድ ባንዲራ አውራጅና ሰቃይ የመሥሪያ ቤት ጥበቃዎች ባንዲራውን እየሰቀሉና እያወረዱ ወሬያቸውን ከጓደኞቻቸው ጋር ይጠርቃሉ፡፡ የኔ ነው የሚለው አንድም ወገን ያለ አይመስለኝም፡፡ ሰው የሚወደውን ባዲራ እንዳይዝ መከልከልና ባዕድ ባንዲራ መስቀል ስምየለሽ ድንቁርና ነው፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ባንዲራ የላትም፡፡ ኦሮሞው የራሱ አለው፤ ትግሬው የራሱ አለው፤ ሶማሌው የራሱ አለው፤ ገሃነም ይመቸውና መለስ ሠርቶ የሰጣቸው ሁሉም ክልሎች የየራሳቸው ባንዲራ አላቸው፡፡ በሕዝብ ደረጃ ያየን እንደሆነ ግን ለምሣሌ ከተላላኪው ብአዴን ውጪ ለአማራ ተሠርቶ የተሰጠውን ባንዲራ (ሰንደቅ ዓላማ) ሕዝቡ አልተቀበለውም፤ መልኩ ምን እንደሚመስል እንኳን የማናውቅ አለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ባንዲራን በግድ ተቀበሉና አውለብልቡ ብሎ የማስገደድ ነውረኝነት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ይመስለኛል፡፡ ወንጀል ነው፡፡

የትግራይ ሕዝብ ወድዶ ይሁን ተገድዶ ሸሚዝና ቀሚስ ሳይቀር እያሠራ ሲያጌጥበት እናያለን፡፡ የጥንቱን ባንዲራ መያዝ ምናልባት ያስቀጣ ይሆናል፡፡ የኦነግን የተለያዩ ባንዲራዎች በፈለገው ቦታ የሚያውለበልበው ኦቦ ሽመልስ አብዲሣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲያይ ደሙ ይንተከተካል፤ በወታደሮቹም እንዲሰበሰብና እንዲቃጠል ያደርጋል – ያው ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብር የለም? ነገሩ እንደዚያ ነው፡፡ ይህ ሰው እጅግ ሲበዛ ጋጠ ወጥ ነው፡፡ ሰሞኑን በፌስቡክ እንዳነበብኩት ባንዲራችንን ከአንድ ሰው ጋር ሲያጣብቃትና ስንትና ስንት ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን የተዋደቁላትን አረንጓ ቢጫ ቀይ ባንዲራችንን ሲያንኳስስ ታዝቤያለሁ፡፡ ይህን ሰው በባልደረባነት ይዞ ዶክተር አቢይ የት ድረስ ሊወስደን እንደሚችል አላውቅም፤ መገመትም ይቸግረኛል፡፡ ኢትዮጵያንና ታሪኳን እየጠሉ ለኢትዮጵውያን ነፃነት መታገል አይቻልም፡፡

ስለሆነም ይህን ባንዲራ የሚጠሉ ሰዎች አደብ እንዲገዙ፣ የኢትዮጵያ የጋራ ሀብት የሆነን ቋንቋም ሆነ ቅርስ የሚያነውሩ ከብልግናቸው እንዲታቀቡ፣ በቋንቋ መሥፈርት በተካለለ የፌዴራል አወቃቀር አገር እንምራ የሚሉ ደናቁርት ከዚህ የጅልነት እሳቤ እንዲወጡ ካልተደረገ አሁን በተያዘው አካሄድ ከሄድን ተመልሰን በወያኔያዊ አዛባ ውስጥ እንደመንቦራጨቅ ነው፡፡ ሲጀመር የዘረኝነት በሽታ በዘረኝነት ክኒና ሊፈወስ እንደማይችል መረዳት ከተደጋጋሚ ውድቀትና ስብራት ይታደጋል፡፡ ወያኔ የፈጠረብንን ቁስል ለማዳን ኦህዲድ በጀመረው መንገድ ብንጓዝ ቁስሉን የበለጠ ያነፈርቀዋል እንጂ እንድናለን ብለን ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ለከበበን ችግር መፍትሔው ሐጎስን በደቻሣ መተካት ሳይሆን ከሐጎስም ከደቻሣም የተጎሳቆለ አስተሳሰብ ተምረን፣ ወጥ የሆነና ከሰብኣዊነትና ከአንድ ሀገር ዜግነት ውጪ በምንም ሁኔታ ለዚህ ወይ ለዚያ ወገን የማያዳላ፣ በብቃትና በችሎታ ላይ  ብቻ የተመሠረተ አሠራርን የሚዘረጋ ሥርዓተ መንግሥት መትከል ብቻ ነው፡፡ በቃ፡፡   

Filed in: Amharic