‹‹ ስለማይችሉን አይወዱንም…!!!››
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን
ታርቆ ክንዴ
*… ሲሞግቱን እንረታቸዋለን፣ ሲገጥሙን እንመታቸዋለን፣ ሲገምቱን ከአቅም በላይ እንሆንባቸዋለን ኢትዮጵያዊያን ለባንዳ ልጅ አንመችም…!
አፈጣጠራችን ለጣለት መብረቅ ለወዳጅ መረቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዉያንና የኢትዮጵያን የማይፈልግ የለም፡፡ ፍላጎቱ ለክፋት ወይም ለበጎነት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙዎቹ ግን የሚፈልጓት ታሪኳን ሊዘርፉ የእነርሱ ሊያደርጉ ነው፡፡
ይህ ሲሆንላቸው አልታዬም፣ አይታይምም፡፡ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዉያንን ማሸነፍ የሚቻለው ይሁን ይደረግላችሁ ብሎ በመፍቀድ ብቻ ነው፡፡ ዓለም ኢትዮጵያን የሚያሸንፍበትን አማራጭ ሁሉ ሞክሯል አንዱም አልተሳካም፡፡ ቀሪ ያልሞከሯቸው ነገሮች ካሉም አይሳካም፡፡ ስለማይችሉን አይወዱንም፤ ስለሚፈልጉን አይተውንም፤ ስለማይሆንላቸው አያሸንፉንም፤ አፈጣጠሯና አኗኗሯ ሚስጥር ነው፡፡ ሚስጥሩን የሚፈታው ደግሞ የሚጥሩ ባለቤት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ዘበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የተኮሱ ተመለሱ፣ ተደመሰሱ፣ ያሴሩ ተቀበሩ፣ ታሪክ የሚያሳዬው ይሄን ነው፡፡ ለጠላት መጋኛ የሆነ አርበኛ መውለድ አዲሷ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ወታደር የማይሰበር አጥር፣ የማይመለስ ግንባር፣ የማይፈታ ሚስጥር፣ ዝቅ የማይል ክብር ያለው ለአሸናፊነት ብቻ የተፈጠረ ነው፡፡ ዘምቶ ተሸንፎበት የመጣ የጦር ግንባር የለም፡፡
በሁሉም አሸንፎ ሁሉንም አክሽፎ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ አሸናፊነትን ከዘር የወረሰው ሠራዊት አሁንም ለሌላ አሸናፊነት እየተጓዘ ነው፡፡ የውስጡን አረም ነቅሎ የውጩን አረም ከድንበር ማዶ ለማስቀረት፡፡
ስለወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና ስለ ኢትዮጵያ ሠራዊት ጀብዱነት ያወጉን የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የኢትዮጵያ አርበኞች በጀግንነት ለሀገራቸው መሥዋት ሲሆኑ የኖሩ ናቸው፤ አሁን ያለው ሠራዊት የእነዚያ ጀግኖች ልጅ ነው ይሉታል፡፡ የእነዚያ ልጆች የአሁኖቹ ሠራዊቶች በስነመግብር፣ ሀገርን በመጠበቅ፣ ሕግ በማስከበርና ሀገር ባለማስደፈር ወኔ የተላበሱ ናቸው ይሏቸዋል፡፡
በጀግናው ሠራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት እንዳበሳጫቸው የተናገሩት ልጅ ዳንኤል ከሰሞኑ ጥቃት አስቀድሞ የቀድሞ የኢትዮጵያን ሠራዊትን የደርግ ሠራዊት አባላት እያሉ ለሀገራቸው የከፈሉትን መስዋዕት ከንቱ ሲያስቀሩ ነው ስህተቱ የተጀመረው ነው የሚሉት፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያና በሌሎች ግንባሮች የፈፀመውን ገድል ከንቱ አስቀርተውበታል፤ በዚህ ሥራው ጀግንነቱ አልተነገረለትም፣ ይህ ደግሞ የሠራዊቱን ጀብዱ አለመዘከር ብቻ ሳይሆን ወዳጅ ዘመዶቹንም አንገት አስደፍቷል ብለዋል፡፡ በደረግ ሠራዊት ላይ የፈፀሙት ግፍ ባለመነገሩና ግፈኞቹ ለህግ ባለመቅረባቸው ዛሬ ላይ በሠራዊቱ ያደረጉት ነገር አዲስ ነገር ሆኖ መቅረብ የለብም ነው ያሉት፡፡ በደል መሥራት የመጡበት ነውና፡፡
የመከላከያ ሠራዊት የአንድ ሀገር ደም ስር ነው፤ ደም ሥር ውስጥ ደም ኬሌለ ሕይወት የለም፤ ሠራዊቱ በዱር በገደል የሚንከራተቱት ለሀገር ለወገን ነው እንጂ ለማንም አይደለምም ብለዋል፡፡ ትህነግ በሠራዊቱ ላይ የፈፀመው በደል ከኢትዮጵያዊነት ባሕል ያፈነገጠ ክህደት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሠራዊቱ ዘብ የሆኑት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊያን እንጂ ለማንም አይደለም ያሉት ልጅ ዳንኤል የሚገባቸው ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተነክቶ ነው የተነሳው፣ ሳይነኩት አልነካቸውም አሁን ሀገርን የማዳን ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡንና ጦሩን ያስቆጣው አታለው መውጋታቸው መሆኑንም በመግለፅ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከማንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ ጥቃት የደረሰበት ነው ያሉት ልጅ ዳንኤል ኢትዮጵያዊነቱንም ያስመሰከረ ነውም ብለዋል፡፡
ትህነግ ያደረገው እኩይ ተግባር ጀልባውን በማነቃነቅና በየቦታው እሳት በማስነሳት የማዕከላዊ መንግሥቱን አቅም በማሳነስ ስልጣን ለመያዝ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝብ ሳይፈቅድ ስልጣን መያዝ አይቻለም ነው ያሉት፡፡ ማንም ሰው በሀገሩ ጉዳይ መፍራትና ማፈግፈግ እንደማይገባውም አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሕዝብን በማቀፍ ህገወጦችን ወደሕግ ለማቅረብ በሚያደርገው ተጋድሎ ሊደገፍ ይባልም ብለዋል፡፡
ድህነትም ጌትነትም በሀገር ነው ያሉት ልጅ ዳንኤል አባቶች መስዋዕት የሆኑት ለሀገርና ለወገን ነው፤ ኢትዮጵያ የምትቀናባት ሀገር ስለሆነች በየትኛውም ጊዜ ጠላት አታጣም፤ የኢትዮጵያ የይቻላል መንፈስና አይደፈሬነት ጠላቶች እንዳይወዱን አድርጓል፤ ከውጭም ሆነ ከውስጥም ያሉ ጠላቶች የተቀናጁ ናቸው፤ ጠላቶቻችን ለመመከት አንድነታችን ሊጠነክር ይገባል ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመከላከያው እያሳዬው ያለውን ድጋፍ በዚሁ ከቀጠለ ጠላቱን በብቃት ይከላከላልም ብለዋል፡፡ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕርበርም ሠራዊቱን በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየትኛውም ሀገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን በመጠበቅና መንባከብ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
አሁን ለማትፈርሰው ዘላላማዊት የጋራ ቤታችን በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ነው፡፡ ጠላቶች ያፍራሉ፤ ኢትዮጵያዉያንን ይኮራሉ፤ ሰላም፡፡