“ጦርነቱ መቆም ያለበት የሕወሓት ቀንደኛ አመራሮች ተይዘው ተጠያቂነት ሲሰፍን ብቻ ነው”
አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)
ሲራራ፡–
ሲራራ፡– አንዳንድ የውጭና የአገር ውስጥ ኀይሎች ውጊያው እንዲቆምና ድርድር እንዲጀመር እየጠየቁ ነው። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፡- አንድ ተዓምር የሚመስል ነገር ከተፈጠረ የፌዴራል መንግሥት እና የጁንታው ቡድን ወደ ድርድር ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የፌዴራል መንግሥቱ በርካታ ጊዜ ሽማግሌዎችን ወደ ሕወሓት ቡድን ልኮ ነበር፡፡ ለምድር ለሰማይ የከበዱ የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች ለሽምግልና ተልከው በሕወሓት በኩል የተሰጣቸው ምላሽ በጎ አልነበረም፡፡ ለሰላም ለእርቅ ተብለው የሄዱ ሽማግሌዎችን ሌባው የሕወሓት ቡድን አንገላትቶ ነው እንዲመለሱ ያደረጋቸው፡፡ በሽማግሌና በሃይማት አባቶች ላይ የሚሳለቁ ግፈኞች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ጦርነት ጭሮ የፌዴራል መንግሥቱን ገፍቶ ወደ ጦርነት አስገብቷል፡፡ የገባበት ጦርነት የማያዋጣ መስሎ ሲሰማው ነው ቡድኑ ሰላም ሰላም ማለት የጀመረው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ሲመች ጦርነት ሳይመች ሰላም የሚለው አካሄድ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ሕወሓት ጨርሶ ለሰላም ቦታ እንደሌለው፤ ዛሬም እንደትናንቱ የሰላምን ጥያቄ እንደ ማዘናጊያና ጊዜ መግዣ እንደሚጠቀምበት ነው በግልጽ እያየን ያለነው፡፡ ጨርሶ የሚታመኑ ሰዎች አይደሉም፡፡ ጦርነቱ መቆም ያለበት የሕወሓት ቀንደኛ አመራር እጁን ሲሰጥና ተጠያቂነት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ቀድሞ የጣሰው ማን ነው? የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያራዘመውን ምርጫ በሕገ ወጥ መንገድ ያደረገው ማን ነው? በአንቀጽ 9 በግልጽ እንደተቀመጠው ከሆነ የትኛውም ክልል የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ እንዲያከብር እና በዚያም እንዲገዛ በግልጽ ደንግጎ ያስቀምጣል፡፡ ሕወሓት ሕገ መንግሥቱን ጥሶ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ጥሶ ነው ምረጫውን ያደረገው፡፡ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ምርጫን መምራት የሚችለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ቡድኑ ይህን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ወደ ጎን ትቶ የራሱን ምርጫ ቦርድ አቋቁሞ ሕገ-ወጥ ምርጫ አድርጓል፡፡ ይህ ድርጊቱ ከሕገ መንግሥቱ ያፈነገጠ ነው፡፡ ነገር ግን ይኸው ቡድን ዳግም የሕገ መንግሥቱ ጠበቃ እና ጋሻ ነኝ ሲል እናገኘዋለን፡፡ ይባስ ብሎ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ቃታ ከሳበ ቡድን ጋር ምን ተብሎ ነው ውይይት እና ድርድር የሚደረገው? የማይታሰብ እና ሊታሰብም የማይገባው ነው፡፡
#ሲራራ፡- በመጨረሻ ለትግራይም ሆነ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው?
አረጋዊ (ዶ/ር)፡- በዚህ ሰዓት የትግራይ ሕዝብ ትልቅ ፈተና ውስጥ ነው ያለው፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ውጭ ያለውም ትግራዋይ በነዚህ መዥገሮች ምክንያት ያለ ሥራው ተወቃሽ እየሆነ ነው ያለው፡፡ ዜጋው ባልዋለበት ተግባር አበሳውን እያየ ነው፡፡ በየትም ቦታ ይሁን ከቡድኑ ጋር ተባባሪ የሆኑ አካላት ካሉ ያለ ቅድመ ሁኔታ ተይዘው መጠየቅ መቻል አለባቸው፡፡ አሁንም ቢሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የቡድኑን እኩይ ዓላማ የሚያስፈጽሙ አካላት በወለጋ፣ በጉራ ፈርዳ፣ መተከል ወዘተ… እኩይ ተግባራቸውን እየፈፀሙ ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ተላላኪ የሆኑ አካላት በፍጥነት መያዝ አለባቸው፡፡ ለዚህም ደግሞ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት፡፡ አገሬ ብሎ ከሚኖረው የትግራይ ሕዝብ ላይ ግን ጣት መቀሰር መቆም አለበት፡፡ በዚህ ላይ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ሌላው አካላት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ሕዝቡን በጥንቃቄ አቅፈው የሚሄዱበትን ስልት ነድፈው መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው፡፡ አንዱ ጠርጣሪ ሌላው ተጠርጣሪ የሚሆንበትን ሁኔታ መቆም አለበት፡፡ አገር እስከሆነ ድረስ የሚገነባው በዚህ ላይ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ሌላው አካል ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ሕዝብን ባልተገባ መልኩ የሚፈርጁ አካላት ካሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል፡፡
በየቦታው አድፍጠው ጥፋት የሚያደርሱ አካላትን የትግራይ ሕዝብ በደንብ ያውቃቸዋል፡፡ እነዚህን አካላት ለሕግ አሳልፎ በመስጠቱ ረገድ የትግራይ ሕዝብ በደንብ መተባበር መቻል አለበት፡፡ ልጆቹንም ትርፍ ለሌለው ውጊያ ከመማገድ ማስቆም መቆጠብ አለበት፡፡ በእኔ እምነት ይዋል ይደር እንጂ የትግራይ ሕዝብ የከሃዲውን ቡድን አባላት ራሱ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ በስሙ ሊነግዱበት አይገባም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ እህትና ወንድሙ ጋር ዛሬም ወደፊትም በፍቅርና በመግባባት ይኖራል፡፡
Via፦ሲራራ–