መውደድ አባ ፀፀት – ከመለስ አብዮት እስከ ሜሪ ሼሊ ፍራንክስታይን!
አሰፋ ሀይሉ
«ከረፈደ ፀፀት ደረት እየደቁ ከእግዜር ቢዋቀሱ፣
ትርጉሙ ምንድነው ሲኖር ተቃቅሮ ሲሞት መላቀሱ፡፡» – «የማጀት ስር ወንጌል»፣
ኅሊና ደሳለኝ፣ (በአዲስ ዓመት ዋዜማ በቤተ መንግሥት ካቀረበችው ግጥም።)
በዚህ ሰዓት ላይ ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ላይ ላሉት የህወሃት ደጋፊ ወዳጆቼ በዚህ የሀዘናቸው ሰዓት በቁስል ላይ ቁስል ላለመጨመር ስል ስለ መለስ ዜናዊ ክፉ ነገር ከማንሳት እቆጠባለሁ፡፡ አንድ ልጠይቅ የምፈልገው ነገር ግን አለ፡፡ ስለ ፀፀት…፡፡ ሎሬቱ ስለተቀኘለት ስለ… መውደድ አባ ፀፀት፡፡ ብዞር ብዞር አጣሁ በምድሪቱ የፀፀትን ቃል፡፡ እና ወደ ሠማይ አረግሁ የግዴን፡፡ ልጠይቅ ስለ ፀፀት፡፡ ከባለቤቱ፡፡ እና ጀመርኩ እንዲህ ስል መጠየቄን በምናቤ – በሹክሹክታ ለራሴ እያጉተመተምኩ፡፡
እውን አሁን መለስ ዜናዊ በትግራይና በመላው ኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ሁሉ ከሠማይ ቤቱ ሆኖ መመልከት ቢችል… ምን ያስብ ይሆን? እውነት በፈጠረው ዜጋን በዘርና ቋንቋ እየሸነሸነ ሀገርን የመከፋፈል ተግባሩ አይፀፀትም አሁንም?
በዜግነቱ ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር እኩል 100% የዜግነት መብትና ድምፅ ሊኖረው ይችለው የነበረውን የትግራይ ህዝብ በዘሩ፣ በጎጡና በቋንቋው አጥሮ በቁጥሩ ልክ 6% ድምፅ ብቻ ያለው፣ ለራሱ ራሱ ብቻ የቆመ፣ ማንም አይዞህ የማይለው፣ አናሳ ‹‹ክልል›› አድርጎት መሞቱን ሲመለከት፣ መለስ ዜናዊ አይፀፀትም ይሆን በሠራው ሥራ?
ለዘመናት ተጎራብቶ፣ ነግሦ፣ አንግሦም አብሮት ከኖረው የጎረቤቱ የአማራ ህዝብ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ ጥላቻን ሲዘራ ኖሮ በማለፉ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣ እና በወሎ (በአማራ) አስተዳደር ሥር የነበሩ መሬቶችን በቅሚያ ወስዶ በመከፋፈልና ለራሱ በመውሰድ በብዙ ነገር ከሚመስለው ጎረቤቱ ጋር ጠላትነትን፣ ቂምና ቁጭትን ዘርቶበት መኖሩ ለወደፊቱ ጥሩ እንዳይደለ ሲመከር አሻፈረኝ ብሎ ኖሮ አሁን ያ ሁሉ ነገር የፈጠረውን ውጤት ሲመለከት አይፀፀት፣ አያዝን ይሆን መለስ?
የትግራይን ህዝብ ከወንድሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጥሎ እንዲህ ብቻውን ቆሞ የዘነበበትን መከራ ሲቀበል ሲመለከት ትንሽ ፀፀት አይገባው ይሆን በሰማይ ቤቱ?
የዘረኝነት ሥርዓቱን ልክነት ለማረጋገጥ ሲል በታሪከ አንድ ነን ብለው የማያውቁትን ወለጋን፣ ከፋን፣ ሐረርጌን፣ አርሲን፣ ባሌን፣ ኦጋዴንን፣ ኢሉባቦርን፣ ሸዋን፣ ወዘተ.. አንድ ላይ ጨፍልቆ ‹‹ኦሮሚያ›› ብሎ በመፍጠሩና ያም የወያኔ ጠላት ሆኖ በመነሳቱ ከልቡ አይፀፀት ይሆን መለስ ዜናዊ?
በታሪክ እርስ በርሱ ለሥልጣን ሲዋጋ ከመኖር ውጪ አንድ ላይ ተሰብስቦ ‹‹አማራ ነኝ›› ብሎ የማያውቀውን የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎ፣ የመንዝ፣ የመርሃቤቴ፣ የሠላሌ፣ ወዘተ ህዘብ በአንድ ላይ ሰብስቦ ‹‹አማራ ክልል›› ብሎ በመፍጠሩ እና በጋራ አማራ እያለ ባደረሰባቸው በደል በጋራ ተያይዘው ተነስተው ወያኔን ሊያጠፉ እየወጉት መሆኑን ሲመለከት – እውን መለስ ዜናዊ ከሠማይ ቤቱም ሆኖ ፀፀት ድጋሚ አይገለው ይሆን?
የትግራይን ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ወንድሙ ከሆነውና በ‹‹ነፃነት›› ስም ደሙን ሲያፈስ፣ አጥንቱን ሲከሰክስለት ከኖረው ከኤርትራ ህዝብ ጋር ተው አትጣላ፣ ቂም አታትርፍ ተብሎ ሲመከር አልሰማ ብሎ… አሁን የትግራይ ህዝብ እንደ ጠላት በቆጠረችው ኤርትራ እየተወጋ እንደሆነ ሲመለከት… እውን መለስ ምን ያስብ ይሆን? በፀፀት ብዛት ደግሞ ደጋግሞ አይታመም፣ ደግሞ ደጋግሞ አይሞት ይሆን?
መለስ በመቃብራችን ላይ ካልሆነ አንቀይረውም እያለ ሲምልለትና ሲገዘትለት የኖረው የዘረኝነት ፖሊሲ በእውንም የትግራይን ወጣቶች ያለ ኃጢያታቸው መቃብር ውስጥ እየጨመራቸው በመጠናቀቅ ላይ እንዳለ ሲመለከት – እውነት መለስ ዜናዊ ከሰማይ ቤቱ ሆኖ ቢመለከት አይፀፀትም ይሆን በእነዚህ ሁሉ ነገሮች?
መለስ ዜናዊ ታላቁን የኢትዮጵያ መሠረት የጣለውን ኃይማኖተኛውን ጀግናውን የትግራይ ህዝብ እንደምን ያለ የአናሳነት ቅርቃር ውስጥ ከትቶት፣ ምን ዓይነት የጥላቻ ቤርሙዳ ውስጥ ጨምሮት፣ ዙሪያውን እንዴት ባለ የጥፋት ቀለበት ውስጥ ከትቶት እንደሞተ ሲመለከት – እውነት ደግሞ ደጋግሞ አይፀፀትም?
የዱር እንስሳት መቆያ ‹‹ዙ›› ውስጥ ሁሉም እንስሳ በየዘሩ እየተለየ ለየብቻ ተከልሎ እንደሚቀመጠው ባለ አኳኋን – መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያውያንን ከያሉበት በጡሩንባ እየነፋ – በየዘሩ፣ በየጎጡ፣ በየቋንቋው፣ በየቆዳ ቀለሙና በየፀጉር ቁመቱ ሳይቀር እየለየና እየለካ ሸንሽኖ ሸንሽኖ አንድ ሆኖ አንድ ላይ የሚቆም ህዝብና ሀገርን አጥፍቶ – ሁሉም በየፊናው የየራሱን እሳት የሚተፋ አፈሙዝ ወድሮ እርስ በርስ ተይይዞ በመጠፋፋት ዋዜማ ላይ መገኘቱን መለስ ዜናዊ ሲመለከት ምን ይሰማው ይሆን?
የህይወት ግቡ፣ የቆመለት ዓላማው ብዙዎች እንደሚያስቡት ኢትዮጵያን እርስ በርስ አበላልቶ፣ አጫርሶ፣ አናክሶ፣ በመጨረሻ ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክን መመሥረት ነው ብዬ እጅግ ካንዴም ሁለቴ ብጠረጥርምና ለደቂቃ እንኳ አምኜ ተቀብዬው ባላውቅም ቅሉ – መለስ ዜናዊ ግን የፈጠረው የዘር ማናከሥ ሥርዓት የፈጠረው የመጨረሻ ውጤቱ የእርስ በእርስ መባላት መሆኑን ይኸው እያየነው ነውና – መለስ ዜናዊ ከሠማይ ቤት ሆኖ ይህን ቢመለከት ምን ይሰማው ይሆን? እውነት በሚሆነው ነገር እርካታ ይሰማዋል? እውነት ይህን ነበር የተመኘውና የፈለገው? እና በደስታ ተውጦ እየሆነ ያለውን ጥፋት በእርካታ ይመለከት ይሆን?
ወይስ… ሁሉም ነገር እርሱ ካሰበው በተቃራኒው ሆኖ፣ ከዋናው ውጤት ይልቅ የጎንዮሹ አሉታዊ ውጤት ገንኖ፣ እጅግ በሀዘን አቆራምቶት፣ በማያልቅ የፀፀት ባህር ውስጥ በሀዘን ተኮራምቶ ነው ይህን ሀገሪቱ፣ የሀገሪቱ ህዝብ፣ እና በተለይ የትግራይ ህዝብ እየሆነና እየደረሰበት ያለውን ነገር የሚመለከተው? እውነት ምን ይሰማው ይሆን የሁሉንም ነገር ፍፃሜ ቢመለከት? ይህን ጥያቄ ሁልጊዜ ራሴን እጠይቃለሁ! አብረውት ከኖሩት የህወሃት ሽማግሌዎች ዘንድ አንድም ቀን ስለዚህ የዘረኝነት ማጥ እና ስለወለደው ጦስ – አንድም ቀን – ሲፀፀቱም ሆነ ስህተትነቱን ሲያምኑ አይቼም፣ ሰምቼም አላውቅም!
ምናልባትም ዛሬ የህወሃት ሰዎች – ለጉልበተኛ አንንበረከክም ብለው እየተጋደሉ ያሉት ለፍትህ፣ ለእኩልነት እና ለነፃነት ቢሆን ኖሮ… እንጂ ከነህዝባቸው እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሳቸው ዘረኝነት ለምን ይቅርብን ብለው ባይሆን ኖሮ… ይህ ግፈኛና ጉልበተኛን የመቋቋም ተግባራቸው – ምንኛ በታሪክ ፊት ሲዘከሩ የሚኖሩ፣ ራሳቸውን ለሀገራቸው ክብር እንደሰዉት እንደ መንፈስ አባታቸው አፄ ዮሐንስ ያሉ የተከበሩ ሰማዕታት ጀግኖች አድርጓቸው ሊያልፍ ይችል እንደነበር ሳስበው በሆነው ሁሉ ከልቤ አዝናለሁ!
እስከ መጨረሻው ድረስ ከጥንት ጀምሮ ይዘውት የመጡት ነገር – ትልልቅ ጠላት ጭምር ፈጥሮላቸው – እምን እንዳደረሳቸው እያዩትም – አሁንም ድረስ አንድም የመፀፀትም ሆነ ይዘውት ከኖሩት አቋማቸው ሸብረክ የማለት ነገር አለማሳየታቸው እጅግ ግርም ይለኛል፡፡ ለዚህ ነው ቋሚዎቹን ትቼ ሟቹን ካለበት በመንፈስ መሞገት የጀመርኩት!
ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ወያኔዎቹ እየተወጉ ያሉት – በዚያው እነርሱው በፈጠሩት፣ ራሳቸው ጠፍጥፈው ነፍስ ዘርተው ዳዴ አስብለው ባቆሙት በራሳቸው ጭራቅ ሥርዓት መሆኑ ነው! የህወሃት መጨረሻ – ከብዙ ዓመታት በፊት ይሄንኑ አንስቶ በጥቂቱ እንደተነበየው እንደ አንድ የሀገራችን ሰው ሁሉ – እኔንም በእኛ በ1810 ዓመተ ምህረት ላይ (የዛሬ 200 ዓመት) የተጻፈውን ታዋቂውን የሜሪ ሼሊን ‹‹ፍራንከንስታይን›› (Frankenstein) የተሰኘ ድርሰት ያስታውሰኛል!
Frankenstein የሚለው የድርሰቱ ርዕስ ‹‹The Modern Prometheus›› እየተባለም ይጠራል፡፡ ፕሮሜቲየስ በጥንታዊ የግሪክ ሚቶሎጂዎች ውስጥ የሰውን ልጅ እንዲፈጥር አደራ የተሰጠውና፣ ራሱ በፈጠረው የሰው ልጅ አኳኋን ከመመሰጡ የተነሳ አማልክቱን ሳያስፈቅድ ከአማልክቱ መኖሪያ ገብቶ የእነርሱን እሳት ዝቆ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ የጨመረበት እና በዚያም ለሰው አምላክን የመሰለ የባህርይ ውርስ በማላበሱ ከባድን ቅጣት ስለ ሰው ልጅ የተቀበለ የአፈታሪኩ የሰዎች ፈጣሪያችን ነው፡፡ ፕሮሜቲየስ፡፡ እና ድርሰቱ ‹‹ዘመናዊው ፕሮሜቲየስ›› – ወይንም ‹‹ፍራንከንስታይን›› ተብሎ የተጠራው በጥንቱ ትውስታ ነው፡፡
እና ‹‹በፍራንከንስታይን›› ወይም ‹‹ዘ ሞደርን ፕሮሜቲየስ›› በሚለው ድርሰት ውስጥ ቢሽ ሼሊ የሚነግረን ከራሱ የተሻለ፣ የሰው ልጆችን የሚያስከነዳ የላብራቶሪ ሰው ለመፍጠር ቀን ከሌት ለዓመታት ሲባዝን ኖሮ በመጨረሻ ይሳካለትና ያንን በሁሉ ነገሩ ሰውን የሚያስከነዳ ሰው ሰራሽ ፍጡር ነፍስ ይዘራበታል፡፡ ያ ፍጡር በብዙ ነገሮቹ ሰዎችን የሚያስከነዳ ፍጡር ይሆናል፡፡ ግን ፍጡሩ እጅግ አስቀያሚም ሆነ፡፡ ሰዎች ሊጠጉት አልቻሉም፡፡ ይፈሩት፣ ይፀየፉት ጀመር፡፡ እና የሳይንቲስቱ የላብራቶሪ ጭራቅ – ፍራንከንስታይን – ራሱን የፈጠረውን ሳይንቲስት ወንድም፣ እህት፣ ቤተሰቦቹን፣ ዘሮቹን፣ ባጠቃላይ የሰው ልጆችን ከሰው በላቀ ፍጥነትና ቅስፈት እያሳደደ መጨረስ ጀመረ፡፡ በመጨረሻ ሳይንቲስቱ ያን ፍጡሩን ሊያመክነው በምድሪቱ የበረዶ ዋልታዎች እየተከተለ ሲያሳድደው ነው የሚጠናቀቀው ድርሰቱ፡፡
ሳይንቲስቱ ፍራንከንስታይንን ሲፈጥር ከዚህ በፊት ከነበረው የሰው ልጅ የተሻለ የሰው ልጅ መፍጠሩ ነበር፡፡ ግን በእርኩሰቱም፣ በጥፋቱም፣ ቀድሞ ከነበረው የሰው ልጅ እጅጉን የላቀ ጭራቅ ፈጥሮ አረፈው፡፡ የዓመታት ትግሉ መና መቅረቱ ብቻ አይደለም የሚያሳዝነው፡፡ የሚያሳዝነው በፈጠረው ፍጥረት ተፀፅቶ መልሶ ስህተቱን ለማረም ቢሞክርም የሚሆንለት ስለማይመስልም ጭምር ነው፡፡ እና ሰዶ ሲያሳድድ ይኖራል ያን ከሚጨበጥ አካልነትም ልቆ ወደ መንፈስነት ደረጃ የተሻገረን እርኩስ ፍጥረተ አዳም!
የመለስ ዜናዊ መጨረሻም፣ የእነ ስብሃት ነጋ፣ የእነ ስዩም መስፍን፣ የእነ አባይ ፀሐዬ፣ የእነ ዶ/ር ደብረፅዮንም መጨረሻ፣ እና የመነሻ ውጥናቸው፣ የዘረኝነት ሥርዓት ጅማሮና፣ አሰቃቂው የመጨረሻ የቁልቁለት መዳረሻ ጉዞው… ባጠቃላይ እነርሱ በፈጠሩት ዘመናዊ ፕሮሜቲየስ፣ እነሱ እስከዛሬ ከነበረው ሁሉ የተሻለ ነገር አገኘን ብለው የፈጠሩት የዘር ሽንሸና ሥርዓት ከናስከተው ውጤትና – አሁን ና ተነቀል ቢባል በየት በኩል ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ ሁሉ…. ይሄንኑ ፍራንከንስታን የተሰኘ ድርሰት ሆነብኝ!!
የሚገርመው ደግሞ – አሁንም ላይ እንኳን ሆነን – ብዙዎቻችን – እነ መለስ የፈጠሩትን ወይም የተፈጠረልንን ፍራንከንስታይናዊ ሥርዓት ክፋት ሳይሆን ለማየት የታደልነው እና የቻልነው፣ ፍራንከንስታይኑን የፈጠረውን ወያኔን እና የወያኔን ፈጣሪዎች ክፋት ብቻ መሆኑ ይገርመኛል፡፡ ትኩረታችን በተፈጠረው እርኩስ ፍራንከንስታይናዊ ሥርዓት ላይ ሳይሆን፣ ያንን የፈጠረው እና የፈጠሩት ከሁሉ ጎልተው ሲታዩን አስተውላለሁ፡፡
እና ገና ፍራንከንስታይናችንን ለይተን እስክናይ ድረስ ወዮልን እላለሁ! ብናየውም ይሄን ያህል አሰርት ዓመታትን እልም ባለ ፍራንከንስታይናዊ መንገድ ስንመላለስ ኖረን፣ እንዲህ በቀላል ለመለወጡና ለመገላገሉ ከተሳካልን እኮ ነው ያውም! ፈጣሪ ይርዳን ማለት ነው ገና! እንጂ በኛ ብርታት፣ እና አሁን በተነከርንበት ደረጃ ብቻ፣ ተብትቦ የያዘን ካስማ በቀላሉ ከላያችን የሚነቀል አልመሰለኝም! እንደ ሰው ሃሳብ ሳይሆን፣ እንደ ፈጣሪ ሃሳብ ያኑረን ማለት – ትልቅ ምርቃት ነው በእውነቱ፡፡
አዎ፡፡ እንደ ሰው ሳይሆን – እንደ ፈጣሪ ያኑረን፡፡ ይፍታን ከፍራንካይናዊ የዘር እስራታችን፡፡ የዘመናይ ፕሮሜቲየሱን ፈጣሪ ነፍሱን ይማርለት፡፡ አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይጠብቅ!
የብዙሃን እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር!
Attachments area