>

እኛ ነበርን❗️ (አሳዬ ደርቤ)

እኛ ነበርን❗️

አሳዬ ደርቤ

➺የደደቢቷ ወያኔ ከትግራይ አልፋ ኢትዮጵያን እንድታስብ ያደረግናት እኛ ነበርን፡፡
➺ህውሓት ሥልጣን ከያዘች በኋላ በደርግነት ተፈርጀን ስንገደል እና ስንፈናቀል የነበርን እኛ ነበርን፡፡
➺እንደ ጠላት የምትቆጥረን ትሕነግ በውጫዊ ጠላት ስትጠቃ ጠመንጃችንን ይዘን ባድሜ ላይ የተሰዋን እኛ ነበርን፡፡
➺በአኖሌ ሐውልት፣ በምኒልክ የጥላቻ ስብከት ተኮትኩቶ ካደገው ቄሮ ጋር በመጨፋጨፍ ፈንታ ‹‹የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው›› በሚል አስተሳሰብ ጥምረት የፈጠርነው እኛ ነበርን፡፡
➺በጥላቻ ፈንታ ፍቅር መስበክ የጀመረው የጃዋር መሐመድ የፌስቡክ አካውንት ሲዘጋ ‹‹#Free ጃዋር መሃመድ›› የሚል ዘመቻ የከፈትን እኛ ነበርን፡፡
➺ኢትዮጵያን ከፍርሰት ለመታደግ ስንል በአማራው ደመቀ መኮነን ፈንታ ኦሮሞው ዐቢይ አህመድ እንዲመረጥ ያደረግነው እኛ ነበርን፡፡
➺ጃዋር ወደ አገር ቤት ገብቶ ወያኔን አጋሩ ሲያደርግ የተካድነው እኛ ነበርን፡፡
➺ ዐቢይ ወደ ቤተ-መንግሥት ከገባበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ ስንገደልና ስንፈናቀል የነበርነው እኛ ነበርን፡፡
➺የለውጡ ተጋሪ መሆን ሲገባን ‹‹ሰብረናቸዋል›› በሚል የሽመልስ አብደሳ ፉከራ ተባራሪና ተሰባሪ ሆነን የቀረብነው እኛ ነበርን፡፡
➺አርባ ዓመት ሙሉ ዝንጀሮ ጋር ሲኳትን የኖረው ‹‹የኦነግ ጦር›› አቦይ ስብሐት ድግስ ላይ ታድሞ ፍትፍቱን ከበላ በኋላ ለስደቱ ተጠያቂ የሆንነው እኛ ነበርን፡፡
➺የተጠቃሚነት እና የክልልነት ጥያቄ በአፋጣኝ መልስ እንዲያገኝ የአማራን ደም ማፍሰስ ያስፈልጋል በተባለበት ሁኔታ ‹‹የለውጡ ተጠቃሚ›› የተባልን እኛ ነበርን፡፡
➺በማንነታችን እየተገደልን፣ በቋንቋችን እየተበደልን በጨፍላቂዎችና በአገር አፍራሾች ፕሮፖጋንዳ ‹‹አሀዳዊያን›› ስንባል የከረምን እኛ ነበርን፡፡
➺ቤኒሻንጉል ላይ እየተገደልን ስለ ግድቡ ስናስብ የነበርን፣ በኢትዮጵያዊነታችን እየተጨፈጨፍን ስለ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ስንጨነቅ የሰነበትን እኛ ነበርን፡፡
➺በዜግነታችን ከዜጎች ተለይተን፣ በአማራነታችን ከሰሜን እዝ ተመርጠን የተገደልን እኛ ነበርን፡፡
➺ማለቂያ በሌለው ግፍ ውስጥ ስንበደል ከርመን ሰሜን እዝ ሲጠብቀው በኖረው አካል ሲካድ ታማኝ ሆነን የተገኘን፣ የቀድሞ ድላችንን ተነጥቀን ሳለ ለዳግማይ ትግል ስንጠራ ነፍጣችንን ተሸክመን ምሽግ ውስጥ የተገኘን እኛ ነበርን፡፡
ምን ልልህ ፈልጌ ነው?
‹‹ከሃዲ›› የሚሉን ሰዎች ሐቀኛ መሆናችንን የሚያውቁ ‹‹ከሃዲያን›› ናቸው፡፡ ‹‹አሃዳዊያን›› የሚሉንም አገር መሸጥ የሚፈልጉ ባንዳዎች ናቸው ለማለት ነው፡፡
Filed in: Amharic