የኢትዮጵያዉ ጠ/ምኒስትር የአፍሪካ ኅብረትን የድርድር ሀሳብ ተቀበለ…!!!
ዶችዌሌ
“የኢትዮጵያን መንግሥት ከህወሓት ለማሸማገል ነው” መባሉን የኢትዮጵያ መንግሥት አስተባበለ…!!!
ዶችዌሌ
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓትን ለማሸማገል የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ጨምሮ የሶስት አገራት የቀድሞ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ሊጓዙ ነው። የአፍሪካ ኅብረት የአመቱ ሊቀ-መንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለሽምግልናው የመረጧቸውን ልዩ ልዑካን ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ዕኩለ ለሊት ገደማ ጀምሮ ውጊያ የገጠሙትን የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን ለማሸማገል የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑካን ሆነው ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ሶስት መሪዎች መምረጣቸውን ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ውሳኔያቸውን ይፋ ያደረጉት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልዩ ልዑክ ሆነው ወደ ደቡብ አፍሪካ ካቀኑት ርዕሠ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከተገናኙ በኋላ ነው።
በዚህም መሠረት የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ክጋሌማ ሞትላንቴ እና የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖ በኅብረቱ ሊቀ-መንበር አሸማጋይ ሆነው ተመርጠዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እንዳሉት “ልዑካኑ በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን ለማሸማገል” በመጪዎቹ ቀናት ወደ አዲስ አበባ ይጓዛሉ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሽምግልናውን ተቀብለዋል።
“የልዩ መልዕክተኞቹ ተቀዳሚ ተግባር ጠብን ለማስቆም በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉንም ወገኖች ማወያየት፤ ወደ ግጭት ለመሩ ጉዳዮች መፍትሔ ለማበጀት ለአካታች ብሔራዊ ውይይት ሁኔታዎችን መፍጠር እና ለኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት መመለስ ነው” ሲሉ ከፍ ያለ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ራማፎሳ ጠቁመዋል።
“በትግራይ እና በኢትዮጵያ ጦር መካከል ስላለው ግጭት” ከርዕሠ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ማብራሪያ የቀረበላቸው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ “በኢትዮጵያ ግጭት በመቀስቀሱ እጅግ እንዳሳሰባቸው” ለርዕሠ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ገልጸዋል። “ግጭቱ በተሳታፊ ወገኖች መካከል በሚደረግ ውይይት ማብቂያ እንዲበጅለት ያላቸውን ጥልቅ መሻት” ለርዕሰ-ብሔሯ አሳውቀዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሾማቸው ሶስት ልዑካን ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙት የኢትዮጵያን ፌድራል መንግሥት ከህወሓት ለማሸማገል ነው መባሉን የኢትዮጵያ መንግሥት አስተባበለ። ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ባሰራጨው መረጃ ዜናው ሐሰት ነው ብሏል። የኢትዮጵያን ፌድራል መንግሥት ከህወሓት ለማሸማገል ሶስት የአፍሪካ አገራት የቀድሞ መሪዎች መምረጣቸውን የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ-መንበር ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አስታውቀው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ዜናውን ይፋ ባደረጉበት መልዕክት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሽምግልናውን ጥረት በመቀበላቸው አመስግነዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ሶስቱን ልዑካን አንድ በአንድ ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ ብቻ አስታውቋል።