>

ይነጋል...!!! (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

ይነጋል…!!!

(ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

*… ይህ አምላክ የኬንያ የሶማሊያ የግሪክም የየመንም አምላክ ነው። ነገር ግን ለኢትዮጵያ የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ሰሞኑን የምናየውንና የምንሰማውን ያክል ተበልታ፣ ይሄንን ያክል ግጠዋት ግን አለመጥፋቷ፣ ይሄንን ያክል ጨፍጭፈዋት ግን አለመሞቷ፣ የዶሮ አጥንት እንደሚወድ ሰው እንዲህ በልተዋት ግን በህይዎት መኖሯ አምላኳ የተለየና ታላቅ መሆኑን ያሳያል
*    *    *
በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሌም የማይቀር ነገር ቢኖር ንጋት ነው። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ንጋት ቀናትን ወይም ወራትን ያስጠብቃል። ለምሳሌ በኖርዌ ሰሜናዊ ክፍል ለ6 ወር የሚጨልምበት ቦታ አለ። በሌሎች ሀገራትም ንጋትን ለማየት ቢያንስ ከ14 እስከ 24 ሰዓት የተዘረጋውን ጨለማ መታገስ ያስፈልጋል። በኛ ሀገር ግን ሌሊቱ (ጨለማው) ረዘመ ቢባል ከ13 ሰዓት በላይ አይቆይም። ኢትዮጵያ ብዙ ሌሊቶችን አሳልፋለች፤ ብዙ ንጋቶችንም አስተናግዳለች።
ንጋት በሁለት ነገሮች ይታዎቃል። የመጀመሪያው በምልክቶች ሲሆን እነዚህ ምልክቶችም ምናልባት የወፎች ዝማሬ፣ የአውራ ዶሮ ጩኸት፣ የጀምበር ብርሃን ወጋገን በመስኮት ሲገባ አሊያም የእጅ ሰዓታችንን በማየት ንጋት መሆኑን እናውቃለን። ሁለተኛው ደግሞ ተፈጥሯዊ ሲሆን ሌሊቱ ምንም ያክል ቢረዝም፣ ጨለማው የቱንም ያህል ጊዜ ቢወስድ አንድ ቀን እንደሚነጋ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የገጠሟት አያሌ ጨለማዎች እንደሚያልፉና በምድሪቱ ንጋት እንደሚሆን በምልክት ያዩ እድለኛና ታላላቅ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ሼህ ሁሴን ጅብሪልን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሰዎች በአሁን ዘመን በመጽሀፍ ቅዱስ እንደተገለጸው “ጆሮን ጭው” የሚያደርጉ ነገሮች በአገራችን እንደሚከሰቱና በአገሪቱ ንጋት እንደሚመጣ አስቀድመው በማየት ለብዙዎቻችን ተናግረዋል፣ ጽፈዋል፣ በየበረሀውም ጩኸዋል። ብዙ ቅዱሳንም ከፍ ከፍ ያሉት እንደሚወርዱ፣ ዝቅ ዝቅ ያሉትም ከፍ እንደሚሉ፣ የወጡት እንደሚገቡና የገቡትም እንደሚወጡ በምልክት አይተው ተናግረዋል።
ሌላው ሰው ደግሞ ንጋት ተፈጥሯዊ በመሆኑ እንደማይቀር ስለሚያውቅ የኢትዮጵያ አምላክ አገራችንን አይጥላትም እያለ ንጋትን ሲጠባበቅ ኖሯል። መንጋት በዚች አገር ውስጥ የማይቀር ነገር ነው። በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ መንጋት ፈጽሞ የማይቀር ነው። አሁን እያየን ያለነውም ይህንን ነው። እድለኞች አስቀድመው ቢያዩትም እኛ ግን አሁን እያየነው ነው። የጀምበሯ የብርሃን ወጋገን አድማስን ተሻግሮ በየቤታችን በየመስኮቶቻችንና በየበሮቻችን እየገባ ነው።
ለእኔ አሁን ኢትዮጵያ ያለችው ቦገግ ባለ ደማቅ ብርሀን ውስጥ አይደለም። ግን ቢያንስ ከአድማስ ባሻገር ያለ፣ ከተራራው ባሻገር ከሩቅ የተንጠለጠለ መብራት ይታየኛል። ይህ መብራት የት እንደምንሄድ ይነግረናል። መንገዱ ምናልባት አስቸጋሪ ነው። መንገዱ ላይ አውሬ ይኑር፣ ገደል ይኑር፣ ምን ይኑር አይታወቅም። መንገዱ የቱንም ያክል አስቸጋሪ ይሁን እንጅ መብራቱ ላይ እንደርሳለን። ሲያዩት የተሰነጠቀ የሚመስል ቀርበው ሲያዩት ግን መሰረቱ ምንም ያልሆነ አንዳንድ ግድግዳ አለ። ኢትዮጵያም የተከፋፈለች የፈረሰችና የተሰነጣጠቀች የሚመስላቸው አሉ። ግን መሰረቷ ምንም አልሆነም። የቱንም ያህል ብንጣላ የቱንም ያህል ብንገዳደል ይህን ጨለማ አልፈን ቦገግ ያለ ብርሀንን በጋራ የምናይበት ጊዜ አለ። ይነጋል።
ኢትዮጵያ ከዚህም በላይ የሆኑ አያሌ የመከራ ሌሊቶችን አሳልፋለች። ከዚህም በላይ የሚያስፈራ ጨለማን አልፋለች። ስለዚህ ይነጋል። የቀደሙት አባቶቻችንና እናቶቻችን “የኢትዮጵያ አምላክ” ብለው የሚጠሩት የማይደክም፣ የማያንቀላፋ፣ የሌለ ሲመስለን ግን ከጎናችን የምናገኘው፣ የዘገየ ሲመስለን ማንም የማይቀድመው ታላቅ አምላክ አለና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ይነጋል።
ይህ አምላክ የኬንያ የሶማሊያ የግሪክም የየመንም አምላክ ነው። ነገር ግን ለኢትዮጵያ የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ሰሞኑን የምናየውንና የምንሰማውን ያክል ተበልታ፣ ይሄንን ያክል ግጠዋት ግን አለመጥፋቷ፣ ይሄንን ያክል ጨፍጭፈዋት ግን አለመሞቷ፣ የዶሮ አጥንት እንደሚወድ ሰው እንዲህ በልተዋት ግን በህይዎት መኖሯ አምላኳ የተለየና ታላቅ መሆኑን ያሳያል። አንዳንዴ ይህ ሁሉ ችግር ኬኒያን ቢገጥማት፣ ሶማሊያን ቢገጥማት ይተርፉ ነበር ወይ? ብየ እጠይቃለሁ። ሶማሊያ’ኮ ትንሽ ችግር ገጥሟት ይኸው ዛሬ ሶስት ትናንሽ ሆናለች። ኢትዮጵያ ግን ያንን ሁሉ ችግር ተሸክማ፣ ያንን ሁሉ መከራ አሳልፋ፣ ሳትወድቅ ዛሬም ቆማለች።
ይህም ጠንካራ የፖለቲካ ሥርዓት ስላለን፣ ጠንካራ የአገር ሽማግሌዎች ስላሉን ወይም ጠንካራ የሐይማኖት መሪዎች ስላሉን ወይም ጠንካራ ወታደር ስላለን አይደለም (መከራዋን ያየችው በራሷ ወታደር ነው)። ታዲያ ረጅም ወንዝ ስላለን ነው? ተራሮች ስላሉን ነው? አይደለም። በአፍሪካ ከሌሶቶ በላይ ተራራ ላይ የተመሰረተ አገር የለም፣ ከኪሊማንጃሮ የሚበልጥ ተራራም የለም፤ ነገርግን ከቅኝ ግዛት አላመለጡም። ኢትዮጵያ ያልጠፋችው በምድራዊ ምክንያት አይደለም፣ እናቶቻችን “የኢትዮጵያ አምላክ” የሚሉት ጠንካራ አምላክ ስላለን እንጅ።
በአድዋ ጊዜ ከሰራዊቱ ጋር ሆኖ የተዋጋ፣ በሁለተኛው ወረራ ጊዜ ለምሳሌ በጎጃም በመንጋ ንብ ተመስሎ ጠላትን የተዋጋ የማይታይ ግን ያለ፣ የማይደክም ብርቱ፣ ብንተወውም የማይተወን አምላክ ስላለን ነው አሁንም ቆመን ያለነው። አንድ ወዳጀ ሰሞኑን “ይሄንን የኢትዮጵያን መከራና ያላትን ስውር ጥበቃ እያዩ እንዴት ሐይማኖት የለሽ መሆን ይቻላል?” ብሎ ጠየቀኝ። እውነት ነው የኢትዮጵያን ፈተናና ያለፈችበትን መከራ እያዩ ግን ጸንታ መቆሟን እየተመለከቱ እንዴት ሐይማኖት የለሽ መሆን ይቻላል?
ኢትዮጵያ የሚመሽባት ግን ንጋት የማይቀርባት አገር ናት።
 እኔ በበኩሌ የኢትዮጵያ ልጅ በተለይም የኢትዮጵያ አምላክ ልጅ በመሆኔ ሁሌም ደስ ይለኛል። አገር ይሄን ሁሉ ተበልቶና ተግጦ ግን ዛሬም በየከተማው ሰርግ አለ። ሥጋ ቤቶችን ተመልከቱ በሰው ተጨናንቀዋል። ሰው ዛሬም መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ ቡና ይጠጣል። አገሩ የተበላ አይመስልም። ይህን እያዩ ሐይማኖት የለሽ መሆን እንዴት ይቻላል? መንገዱ አስቸጋሪ ቢሆንም ከሩቅ ከምናየው መብራት ጋ እንደርሳለን። በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ንጋት የማይቀር ነውና አይዟችሁ ይነጋል።
(ኅዳር ፭ ፳፻፲፩ ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር የመጽሐፍ ምረቃ ዝግጅት ላይ የተደረገ ንግግር)
Filed in: Amharic