>

ብዙው ነገራችን አስተያየት ብቻ ይሆንብኛል! ( አሰፋ ሀይሉ)

ብዙው ነገራችን አስተያየት ብቻ ይሆንብኛል! 

አሰፋ ሀይሉ

 

“የምንመኘው ለውጥ ሣይንሳዊ፣ ሙያዊ፣ የተጨበጠና የተረጋገጠ ይሆን ዘንድ – ምሁራን የቤት ሥራቸውን ሊወጡ ይገባል! ምሁራን የለውጥ ቅመም ሁኑ!”
በኢትዮጵያ ውስጥ የተሰሩ ቁጥራቸው የበዛ የሶሺዮሎጂና ዲሞግራፊክ ጥናቶችን የተመለከተ ሰው፣ ላለፉት አሰርት ዓመታት በኢትዮጵያችን ሰዉ ሁሉ ከሁሉም አቅጣጫ እየፈለሰ ያለው ወደ አዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ያለጥያቄ ይቀበላል! በተለይ አዲስ አበባ ከምትችለውም አቅም በላይ ብዙውን የሀገር ውስጥ ስደት በማስተናገድ የተጠመደች፣ በየዕለቱ በሺህዎች የሰው ብዛት እየጨመረች የምትሄድ ከተማ ሆናለች፡፡ ይህ እንግዲህ በየዕለቱ በተለያዩ ምክንያቶች በአዲስ አበባ በኩል፣ ወይም አዲሳባን ረግጦ የሚያልፈውን ብዙ ሺህ አላፊ-አግዳሚ ሳይጨምር ነው፡፡
በበኩሌ ከ2 ዓመት በፊት በነበሩት ቢያንስ 10 ተከታታይ ዓመታት በበኩሌ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የመ.ያ.ድ. እና የመንግሥት ጥናቶችንና የፖሊሲ ሪኮመንዴሽኖችን ከማገላበጥ ባለፈ፣ በየሄድኩበት የማገኛቸውን ከዚያም ከዚህም የማገኛቸውን ወደ አዲስ አበባ የፈለሱ፣ እና ለመፍለስ በእጅጉ የሚናፍቁ ሰዎችን ምክንያታቸውን ሳልጠይቅ ቀርኤ አላውቅም!
እጠይቃቸዋለሁ ‹‹ለምን እዚሁ አርፋችሁ አትቀመጡም? አዲሳባ ምን ያደርግላችኋል?›› የሚገርመኝ ከብዙዎች ላይ ያገኘሁት ተመሳሳይ መልስ፡- ‹‹ለእኛ አይደለም፣ ቢያንስ ለልጆቻችን ጥሩ ነገር አይተው ይማራሉ፣ ጥሩ ትምህርት ተምረው ያድጋሉ፣ ለልጆቻችን ነው!››፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ጭፍጨፋና ሰብዓዊ ቀውስ የተከሰተባቸውን ብዙዎቹን ሥፍራዎች አስተውላችሁ ካያችሁ – ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ብዙ ዓይነት ግለሰቦችና ማህበረሰቦች በሚኖሩባቸው ትላልቅ ከተሞች (ቢግ ሜትሮፖሊስ) ውስጥ እነዚህ ቀውሶች ጎልተው ሲወጡ አልታየም፡፡
የኢህአዴግ መንግሥት በዓለማቀፍ አበዳሪ ደንበኞቹ አማካይነት ጭምር እያስነገረ ሲነዛብን የከረመው የ2 ዲጂት እድገት… ብዙው የመሠረተ ልማትና ፈጣን ኢኮኖሚ አመንጪ እድገቶችና መሻሻሎች የታዩት በእነዚሁ ከሞላ ጎደል ኢኮኖሚክ-ድራይቭን የሆነ ብዙ ዓይነት ማህበረሰብ በሚኖሩባቸው ትላልቅ የሀገሪቱ ከተሞች ነው፡፡
ይህ የሚያሳየን ምንድነው? የጎሳ ሥርዓቱን ክሽፈት! እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ‹‹አንተ እንዲህ ነህ›› ‹‹አንቺ ከእገሌ ብሔር ነሽ›› ሳይባባል የሚኖርባቸው መዳረሻዎች የእድገት ብልጭታ ማሳየታቸውን! ዜጎቻችን በጎሳ ሥርዓቱ ከታነቁት ሥፍራዎች ይልቅ ለልጆቻቸው የተሻለ ህይወትን ወዳመላከቷቸው ሁሉን አቻችለው ወደሚያኗኑሩ ለሁሉም ዜጋ ለኑሮ ክፍትና ምቹ ወደሆኑ ከተሞች ላይ ምርጫቸውን ማድረጋቸውን በሚገባ ያመለክታል!
በእርግጥ ከላይ የሰጠሁትን ድምዳሜ – በሳይንሳዊ መልኩ አስረግጦ በእርግጠኝነት በሀገራችን የሰፈነውን የጎሳ ሥርዓት ክሽፈት እና የመልታይናሽናል የዜግነት ሥርዓትን ለኢኮኖሚያዊ ብልፅግናና ለተረጋጋ ሠላም ያለውን ታላቅ ፋይዳ ለማሳየት – እነዚህን የመሰሉ ጥናቶች – ለዚሁ ዓላማ ተብለው የተዘጋጁ የመረጃ መሰብሰቢያና መመርመሪያ ዘዴዎችን ተጠቅመው ራሳቸውን በቻሉ ባለሙያዎች ዓለማቀፍ የምርምር ወይም አካዳሚክም ከሆነ አካዳሚክ ደረጃቸውን ጠብቀው መሠራት እንዳለባቸው ምንም አያጠራጥርም፡፡
ወደፊት እንዲህ ዓይነት ጥናቶች በተለይ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ባላቸው የአካዳሚክ ሰዎችና ተማሪዎች፣ እንዲሁም በሀገር ደረጃ ገለልተኝነትን በተላበሱና ተዓማኒነት ባላቸው የፖሊሲ ተመራማሪዎች አውጪዎች አማካይነት እንደሚሰሩ ትልቅ ዕምነት አለኝ፡፡
ያረጀው ያፈጀው እና በያካባቢው ኢትዮጵያዊን ከኢትዮጵያዊ እያናከሰና እያባላ ያለው – ወይም የተጠናቀቀው – ‹‹የብሄር (የጎሳ) ፌዴራሊዝም›› ሥርዓት ራሱ በተግባር ሥርዓቱ የተጣባውን ክሽፈት አመላካች ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ – በተጨማሪም ግን – ይህ ጎሰኛ ሥርዓት ሀገራችንን ወደ ውድቀት እየከተታት እንዳለ፣ እና በህዝቡም የተተፋ፣ ህዝቡ ራሱ አንገፍግፎት እንደ አዲስ አበባ ወደመሳሰሉ የሁሉም የሆኑ ከተሞች በሚሊዮኖች እየፈለሰ እንዳለ – በጥናቶች ተደግፈው የሚቀርቡ የፖሊሲ አማራጮች ለሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከፍተኛ ገንቢ አስተዋፅዖ እንዳላቸው በእጅጉ አምናለሁ! ልናምንበትም ይገባል! ፍላጎታችን ሳይንሳዊና ተጨባጭ ምክንያቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ እንጂ መሠለኝና ደሳለኝ እንዳይሆን አበክሮ መሥራት በእጅጉ ያሻል፡፡ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
ምሁራን የሚፈለጉት በእነዚህ ለሀገር ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች እውነተኛ ጥናቶቻቸውን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ሀገራዊ የፖሊሲ ዳያሎግ፣ ሀገራዊ የሥርዓት ለውጥ ውይይት፣ የሀገሪቱን ሕዝብ ዓይን የሚከፍቱ ግኝቶቻቸውን በማቅረብ ነው ለሀገራቸው ውለታቸውን ሊመልሱ፣ ሀገራቸውን ወደተሻለ የእድገትና ብልጽግና መንገድ ሊያሻግሩ እና ከሌላውም ተራ የሀገሪቱ ዜጋ የተሻለ አበርክቶት ሊኖራቸው የሚችሉት!
ምሁር መሆን ማለት የዜጋ ዓይንና ጆሮ ሆኖ መገኘት ማለት ነው! ምሁርነት ማለት ችግርን አንቅሮ መለየት፣ እና ለሀገራዊ ችግር ሀገራዊ መፍትሄን መጠቆም ማለት ነው፡፡ ምሁሮቻችን በፖለቲካው ምድጃ ሥር ከመጣድ ባለፈም፣ በየሙያችሁ ህዝባችሁ የሚሻውን የቤት ሥራችሁን ተግታችሁ ተወጡ! እጃችሁ ከምን ብትባሉ ይኸው አለን ለማለት እንዳታፍሩ ሁኑ!
ምሁራን የለውጥ ቅመም ሁኑ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic