>

በአማራው ላይ  የተካሄደው የማይካድራው ጭፍጨፋ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ለምን አገኘ ? (ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ)

በአማራው ላይ  የተካሄደው የማይካድራው ጭፍጨፋ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ለምን አገኘ ?

ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ


በአማራው ላይ  የተካሄደው የማይካድራው ጭፍጨፋ ሰፊ ትኩረት አግኝቷል፤ ማግኘቱም ተገቢ ነው፡፡ እንኳንስ ከስድስት መቶ በላይ የሆኑ ዜጎች ያለቁበት ጭፍጨፋ ይቅርና የአንድም ሰው ህይወት በግፍ ሲገደል እንዲሁ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንዲህ አይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በሰው ልጅ ላይ ሲፈፀም ማውገዝ ተገቢ ነው፡፡ በማይካድራ ህይወታቸው ላጡ ወገኞቸ ፈጣሪ ነፍሳቸውን  እንዲምራቸው እመኛለሁ፡፡ ዘወትር እንደማዝነው በጥቃቱ አዝኛለሁ፡፡

ዳሩ ግን የአማራ ህዝብ ሞት እና ጭፍጨፋ የተጀመረው በማይካድራ አይደለም፡፡ በህወሐት የ27 ዓመት የአገዛዝ ዘመን በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማፅዳት ሲፈፀምበት እንደቆየ ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከለውጡም በኃላ በአለፉት ሁለት/ሶስት ዓመታት በአማራው ህዝብ ላይ በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ ጥቃት ተፈፅሟል፡፡ በሻሸመኔ፣ በደራ፣ በዝዋይ፣ በጉራ-ፈርዳ፣ በቤንሻንጉል -ጉምዝ በተከታታይ በአማራው ላይ ጥቃት ደርሶበታል፡፡ በቅርቡ እንኳን በምዕራብ ወለጋ በ22/02/2013ዓ.ም. ጉሊሶ ወረዳ በአማራ ተወላጆች ላይ በደረሰው ጥቃት ከ250 በላይ አማራዎች እንደተገደሉ ተገልፆል፡፡ እነዚህ ሁሉ በቂ የሚዲያ ሽፋን አላገኙም፤ በጊዜው የሚጮህላቸውም ድርጅት እና ፓርቲም አላገኙም፡፡ 

የማይካድራው ጭፍጨፋ ሰፊ ትኩረት ያገኘበት ምክንያት ጥቃት ፈፃሚው ሊወድቅ የተቃረበ ቡድን ስለሆነ እንጅ በስልጣን ላይ ያሉ ተረኞች ሲፈፅሙት ግን ተደባብሶ ነው የሚቀረው፤ ይህን ያህል የሚዲያ ትኩረት አይሰጠውም፡፡ አሸባሪው ቡድን ህወሐት ብቻ ሳይሆን ኦነግ-ሸኔ ተብየውም አሸባሪ ነው፡፡ ኦነግ-ሸኔን የሚያህል አሸባሪ ቡድን በጉያው የታቀፈ እና በመተከል እንዲንቀሳቀስ የፈቀደ አመራር እንዳይቀየም ሲባል ጉዳዩን ኦነግ ሲፈፅመው ትኩረት አይሰጠውም፤ ህወሐት ሲፈጽመው ግን ለአማራው መጨፍጨፍ ግድ የማይላቸው የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሁሉ የማይካድራውን ጭፍጨፋ ሲያወግዙት ሲታይ ምን ያህል አድርባይነት እንደተጣባን ያሳያል፡፡ የአጥቂውን እና የተጠቂውን ማንነት ግምት ውስጥ ሳናስገባ ሁል ጊዜም ኢ-ሰብዓዊ ደርጊቶችን ማውገዝ እና እነዚህ ድርጊቶች እንዲቆሙ መታገል እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎች የማንኛውም ዜጋ ግዴታ ይመስለኛል፡፡  

አሁንም ቢሆን በስልት እና በሴራ ፖለቲካ እሳቤ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ በየጊዜው ከማውገዝ ይልቅ አማራን መግደል፣ ማሳደድ፣ ማፈናቀል፣ ማሸማቀቅ እንዲቆም ህገ መንግስቱ እንዲቀየር፣ የጎሳ ፖለቲካ እንዲቆም  እና ፍፁም ለውጥ እንዲመጣ ተባብሮ መስራትን ይሻላል፡፡  

Filed in: Amharic