>

ጦሩ «3ኛዉን ምዕራፍ» ዉጊያ እንዲከፍት ታዘዘ (D.W)

ጦሩ «3ኛዉን ምዕራፍ» ዉጊያ እንዲከፍት ታዘዘ

D.W

የኢትዮጵያ የፌደራል ጦር ኃይል በሕወሓት መሪዎችና ታጣቂዎች ላይ የከፈተዉ የጦር ዘመቻ ከመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ አስታወቁ።ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ በቲዊተርና በፌስቡክ ገፃቸው (በእንግሊዝኛና በአማርኛ) ባሰራጩት መልዕክት የሕወሓት መሪዎችና ታጣቂዎች እጃቸዉን በሰላም እንዲሰጡ «የተሰጣቸዉ» ሠዓተ ገደብ «ተጠናቅቋል» ብለዋል።የኢትዮጵያ መንግስት «ጁንታ» የሚላቸዉ የሕወሓት መሪዎችና ተከታዮቻቸዉ ለፌደራሉ መንግሥት እጅ እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት የ72 ሰዓተ- ገደብ ትናንት 16፣30 GMT ላይ ተጠናቅቋል።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በዛሬ ማስታወቂያቸዉ ሰዓተ-ገደቡን ተጠቅመዉ «በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልዩ ኃይልና የሚሊሺያ አባላት እጃቸዉን መስጠታቸዉን» ገልፀዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለዉ እንዳሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር «የመጨረሻዉንና 3ኛዉን ምዕራፍ ዘመቻ» እንዲጀምር ታዟል።የኢትዮጵያ ጦር ኃይል የትግራይን ርዕሠ ከተማ መቀሌን መክበቡን ካለፈዉ ዕሁድ ጀምሮ ሲያስታዉቅ ነበር።ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባት በሚገመተዉ በመቀሌ ከተማ የሚደረገዉ ዉጊያ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተፋላሚ ኃይላት ይጠነቀቁ ዘንድ እየተማፀኑ ነዉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በዛሬ መግለጫቸዉ ጦራቸዉ የከተማይቱን «ሕዝብ፣ ቅርሶች፣ቤተ ዕምነቶች፣ የልማት ተቋማትና ንብረቶች ላይ ጉዳት የማያደርስ— ስልት» መንደፉን አስታዉቀዋል።
Filed in: Amharic