ፈጣሪ የአንድ ሣምንት ሥልጣን ቢሰጠኝ…?!
ነፃነት ዘለቀ
በተለይ በአፍሪካ ሥልጣን በምርጫ ወይም በጡጫ እንጂ በምኞትና ፍላጎት እንደማይገኝ አምናለሁ፤ ቢሆንም በምናብ ደረጃ “ይህ ነገር ቢኖረኝ፤ ያ ነገር ቢሣካልኝ” ማለት የተለመደ ነውና እኔም የኢትዮጵያ መሪ ሆኜ ለአንድ ሣምንት ብሾም ቀጣዮቹን ተግባራት አከናውን ነበር፡፡ ዕድሜሽ ከ50 እና 60 በላይ የሆንሽ ሁሉ በይ እንደፈረደብሽ ተቃጠይ፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ አጭሩ የንግሥና ጊዜ የንጉሥ አዙር ግማሽ ቀን ነበር፡፡ ሥልጣኑ በአጭር የተቀጨውም የንጉሡን ሹመት ተከትሎ በተፈጠረው ደስታና ፈንጠዝያ አዲሱ ንጉሥ በመንጋው ተረጋግጦ በመሞቱ ነው አሉ፡፡ ያሳዝናል፡፡ እንደዛሬ የብረት አጥር የሚሆን የሪፓብሊካን ጋርድ ያኔ አልነበረም (አሉ) – አሉ ነው መቼም፡፡
በመጀመሪያው ቀን – ይህን አዳዲ ማርያምን መሣም፣ አዲስ ዓለም ማርያምን መሳለም፣ የዝቋላ አቦ ክበረ በዓልን መሣተፍ፣ አክሱም ጽዮንን በአካል ተገኝቶ ማክበር … እንኳን ያላስቻለንን ድውይ የጎሣ ፖለቲካ በቲራ ዘርዬ የቀድሞውን የአስተዳደር ዘይቤ እመልስ ነበር፡፡ በየትም ሀገር እንደሌለ የሚነገርለትንና በቋንቋና በነገድ ዜጎችን እየከፋፈለ እርስ በርስ የሚያባላውን ህገ አራዊት ማነው ህገ መንግሥት ውድቅ አድርጌ ለህዝብ አመቺ በሚሆን አዲስ ህገ መንግሥት እተካለሁ፡፡ ያ ህገ መንግሥት ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ነገድን ከነገድ የማያበላልጥና ሁሉንም በአንዲት ሀገር ዜግነትና በሰው ልጅነት እኩል የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡ ሽል ምንጠራ እስከወዲያኛው ይወገዳል፡፡ መሬትን ጨምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት የሁሉም ዜጎች ንብረት ይሆናል፡፡ያኔ ወልቃይትና ራያ ከከምባታና ማጂ ወይም ከቦንጋና ጎሬ የተለዬ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡
ኢትዮጵያን በሚከተሉት ጠቅላይ ግዛቶች መድቤ አስተዳዳሪዎችንም ከፊት ለፊታቸው በተቀመጠው መሠረት እሾማለሁ ወይም በነፃነት በሚንቀሳቀስ ፓርላማ ፊት አቅርቤ ህግ በሚያዘው መሠረት አሾማለሁ፡፡ ህጎችን ዐዋጆች በግለሰብ አምባገነኖች እንዳይረገጡም አደርጋለሁ፡፡
- ሸዋ ጠቅላይ ግዛት – ዶክተር ዓለማየሁ ቦንገር
- አርሲ ጠ/ግዛት – ዶክተር ስንሻው አበጋዝ
- ሲዳሞ ጠ/ግዛት – ፕሮፌሰር ኡጁሉ ኡኩፑዋ
- ወለጋ ጠ/ግዛት – ዶክተር ተከስተ ሐጎስ
- ትግራይ ጠ/ግዛት – ዶክተር ቶሎሣ ዱጉማ
- ጎጃም ጠ/ግዛት – ዶክተር ሻመና ቶቆ
- ወሎ ጠ/ግዛት – ዶክተር ኤርሱሎ ጌታሁን
- ጎንደር ጠ/ግዛት – ዶክተር መሐሪ ጎይቶም
- ኢሊባር ጠ/ግዛት – ፕሮፌሰር አህመድ መሀመድ
- ጋሙጎፋ ጠ/ግዛት – ዶክተር ሙሣ ኮንቴ
- ሐረር ጠ/ግዛት – ዶክተር አብደላ ገ/መስቀል
- ባሌ ጠ/ግዛት – ኢንጂኔር አብዲሣ ገረመው
- ከፋ ጠ/ግዛት – ዶክተር አስመሮም ገመቹ
- ኤርትራ ጠ/ግዛት (በበኩሌ እንደምትመጣ አምናለሁ) – ፕሮፌሰር አብርሃም ታረቀኝ
እነዚህ ሹሞች ስማቸው “አጋጣሚ” ሆኖ አንዳንድ ነገር ቢጠቁምም የምርጫውን ሂደት የሚወስነው ግን ትምህርታቸው፣ ችሎታቸውና የቀደመ የሥራ አፈጻጸም ብቃታቸው ነው፡፡
በመቀጠል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንድ እርሱም ንጹሕ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ እንጂ 30 እና 40 እንደማይሆን በዐዋጅ አጸድቃለሁ፡፡ የተዋረደችዋን የቀድሞዋን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በክብር እንድትውለበለብ አደርጋለሁ፡፡ ማንም እየተነሣ ክብሯን እንዳያጎድፍ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ የጠፋው ብሔራዊ ስሜት፣ የደበዘዘው ፍቅራችን፣ የጠወለገው ግብረ ገብነታችን፣ የተሰወረው አስተዋይታን፣ የወደቀው ሀገራዊ ክብራችን፣ ባፍጢሙ የተደፋው ርህራሄያችን … እንዲመለስ ሌት ከቀን እሠራለሁ፡፡
በሌላ በኩል ዜጎች በሃሳብ አንድነትና በአቋም ተመሳሳይነት እንጂ በጎሣና በቋንቋ ወይም በሃይማኖትና በመሳሰለው ነገር የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ምንም ዓይነት ድርጅት እንዳይመሠርቱ በህግ አግዳለሁ፡፡ ሰው እንደውሻ ደምና አጥንት እያነፈነፈ መሰባሰቡ የሚያስከትለውን አስከፊ ጉዳት ከሀገራችን የ30 ዓመታት አስቀያሚ ታሪክ ኅብረተሰቡ እንዲማር መድረኮችን አመቻቻለሁ፤ ጎሠኝነትንና ዘረኝነትን እንዲጸየፉት አጥብቄ እሠራለሁ፡፡ ሩዋንዳ የጨፍጫፊ ሁቱዎችን ጭካኔ የተሞላበት የዘር ፍጅት ለማሳየት እንዳደረገችው የወያኔን የግፍ ታሪክ በሙዚየም አስቀምጬ ትውልድ እንዲማርበት አደርጋለሁ፡፡
ዘመናዊ የግብርናና የኢንዱስትሪ ቴክሎጂ ትምህርትን በማስፋፋት ሀገራችን በምግብና በቴክኖሎጂ ግብኣቶች ራሷን ከመቻል አልፋ ለውጭ ገበያ እንድትተርፍ አደርጋለሁ፡፡ ለፖለቲካና ለወሬ እንዲሁም እርስ በርስ ለሚደረግ የሥልጣን ሽኩቻና ሥልጣንን ለማስጠበቅ ሲባል አላግባብ የሚባክነውን በቢሊዮኖች የሚገመት የውጭ ምንዛሪና የሀገር ውስጥ ገንዘብ እንዲሁም ጊዜ፣ ጉልበትና ዕውቀት ወደ ጠቃሚ ምርት በመለወጥ ርሀብና ርዛት ከሀገር እንዲጠፉ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ታሪክ ሆኖ እንዲመዘገብ፣ በውጤቱም ሀገር በሁሉም ዘርፍ እንድትበለጽና ከድህነት ተምሣሌትነት ወደ ሀብታምት ተለውጣ ስደት ከኢትዮያ መሆኑ ቀርቶ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሆን የዜጎችን አስተሳሰብ ከመለወጥ ጅሬ በርትቼ እሠራለሁ፡፡ ውይ … ከምነዜው የሣምንቱ የሥልጣን ጊዜ አለቀብኝ በል … ተተኪየ ግን አደራህን የሠራሁትን ሁሉ በዜሮ እንዳታባዛው፡፡ ጃዋር ሞሀመድና “ፕሮፌሰር” ሕዝቅኤል ጉዳንሣ እንደማትሆኑ መቼም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እስኪ ወደ ጦርነቱ ወሬ ጎራ ልበልና ደግሞ ምን አዲስ ሰበር ዜና እንዳለ ልቃኝ … ቸር ያሰማኝ፡፡