“ትሕነግ የትግራይን ሕዝብ ከወገኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳይገናኝ ያደረገ የእሾህ አጥር ነበር!!!”
አብን
* “እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን!
*
በአገራችን የታሪክ ክፍተት እንደዋዛ ለመንበረ ስልጣን የበቃው የትሕነግ ስብስብ እድሜውን ሙሉ የጥላቻና ጥፋት ስምሪት በማድረግ ምድቡና ዝርዝሩ የማያልቅ በደል ሲፈፅም መቆየቱ ይታወቃል።
ይህ ስብስብ ዳግም በአገራችንና በሕዝባችን ላይ የጥላቻና የግፍ ስርአቱን ለማንበር በግድ ወደጦርነት አስገብቶን ቆይቷል።
ትሕነግ ራሱ በከፈተው ጦርነት በጀግናው የአገር መከላክያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ቅጣቱን ተቀብሎ ታሪክ ሆኖል። ቀሪው ጉዳይ ትሕነግ የተከላቸውን የጥላቻ ትርክት፣ ሕገ-መንግስትና መዋቅሮችን በማፈራረስ በአገራችን ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ፍትኅ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ይሆናል።
የትሕነግ መደምሰስ ለአገራችን ፋይዳው ዘርፈብዙ ነው። በተለይም ከውልደት ጀምሮ በጠላትነት ለፈረጀውና የትየለሌ ግፍ ሲፈፅምበት ለቆየው ለአማራ ሕዝብ የትህነግ መጥፋት ኅልውናውን የማረጋገጥ ትግል አይነተኛ ድል ነው። በተጨማሪም ትሕነግ የትግራይን ሕዝብ ከወገኑ የኢትዬጵያ ሕዝብ እንዳይገናኝ ያደረገ አጥር ድርጅት ነበር።
ለዚህ ድል መረጋገጥ መላው አገር ወዳድ ኢትዬጵያዉያን፣ አገር ወዳድ የፖለቲካ በጎ ጥምረቶች ሁሉ ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ልትመሰገኑ ይገባል። በተለይ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ መስዋእትነት ከፍላችሁ ለዚህ ቀን ስላበቃችሁን ክብርና ምስጋና ይገባችኋል።
የትሕነግን የግፍና በደል ማሽን ዘዋሪዎች በፍትኅ አደባባይ የማዋሉ ቀጣይ ስራ የዚህን ድል ወሳኝ ምዕራፉ እንደሚቋጭ ይጠበቃል። ድሕረ ትሕነግ የኢትዬጵያ ዘመን በዜጎችና ሕዝቦች መካከል በሰለጠነ ውይይትና ድርድር ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ፍትኃዊ አማካይ ላይ የምንደርስበት ይሆናል።
ለመላው አገር ወዳድ ኢትዬጵያዉያን እንኳን ለዘመናት ኢትዬጵያዊነትን ሲያዋርድና ዜጎቿን ሲበድል ለኖረው የጥላቻ አባትና እናት ለነበረው የትሕነግ ግበዓተ መሬት መፈፀም አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)!