በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ሁሉ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን የቀደመ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ፣ ስለ ሕዝቦቿ የአይበገሬነት የነጻት መንፈስና ጀግንነት ያላቸው ብሔራዊ ኩራትና ስሜት በእጅጉ ይገርመኛል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ስለታሪክ ያላቸው እውቀት/መረዳትና ክብር ባሰብኩ ቁጥርም ሁሌም እገረማለሁ፣ አደነቃለሁም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሺሕ ዓመታት ታሪክ የበለጸገችውን ኢትዮጵያን ጠንቅቆ ማወቅ አስፈላጊነትን በእጅጉ የተረዱ ሰው ናቸው፡፡ በዚህም የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊው ምሁር/ፖለቲካል ኢኮኖሚስቱ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ እንደሚሉት፤ ‘‘የታሪክ እውቀት በተለይ ለቤተመንግሥት ሹማምንት የሚያስፈልግ ነው፤’’ የሚለውን ወርቃማ ሐሳብ በቅጡ እንደተረዱት የሚያሳይ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ስለታሪክ እውቀት እንዲል የሚል የቆየ ድንቅ አባባል አላቸው፤ ‘‘ታሪክ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው፣ ታሪክን የሚመረምር እርሱ- ላለፉት ትውልዶች እውነተኛ ጓደኛ፣ አሁን ላለው ትውልዱ መልካም መምህር፣ ለሚመጡት ትውልዶች ደግሞ ነቢይ ነው፤’’ በዚህ ረገድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተ-መንግሥታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ- ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሕዝቦቿ ነጻነትና ክብር የተዋደቁ የኢትዮጵያን የታሪክ አዕማዶችን ክብር በመስጠት ትውልድ ይማርበት ዘንድ ትልቅ ታሪካዊ ሥራን ዕውን በማድረግ፣ ላለፈው ትውልድ ጓደኛ፣ አሁን ላለው ትውልድ መልካም መምህር ለሚመጡት ትውልዶች ደግሞ ነቢይነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡
ለዚህች አጭር መጣጥፍ ምክንያት የሆነኝ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው ዕለት በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው፣ በኢትዮጵያዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በተመለከተ ከታሪክ በማጣቀስ የሰጡት ማብራሪያ ሰሜቴን ቢኮረኩረው ነው፡፡ እስቲ ብትሰሙትም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግሮቻቸው መካከል ጥቂቶቹን ዳግመኛ ላስታውሳችሁ፤
‘‘ኢትዮጵያውያን እያሉ ኢትዮጵያን ፈጽሞ ማሸነፍ የሚታሰብ አይደለም፤ አይቻልምም፡፡ ያሸነፈው ይህ የድልና የጀግንነት ባለቤት የሆነ ባለታሪክ ታላቅ ሕዝብ ነው፤ ያሸነፈው የኢትዮጵያ እናቶች ጸሎት እና እንባ ነው፡፡’’
‘‘ኢትዮጵያውያን የሺ ዘመናት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ያለው ሕዝብና ሀገር ነው፡፡ ድህነታችንን ምክንያት አድርገው የዲፕሎማሲ ጫና ለማድረግ የሚጥሩ ሀገራት ልንነግራቸው የምንፈልገው ሐቅ ቢኖር፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ፈጽሞ በክብራችን እና በነጻነታችን/በሉዓላዊነታችን የማንደራደር መሆናችንን ነው፡፡’’
‘‘ይህ ሕዝብም ድሀ ሆኖም እንኳን በነጻነቱና በክብሩ ፈጽሞ የማይደራደር መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡ በታሪካችን በዘመናዊ መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን የአውሮፓ ሰራዊት ሽንፈት ተከናንቦ እንዲመለስ በማድረግ ታላቅነቱን ያስመሰከረ ሕዝብ ነው፡፡’’
ኢትዮጵያችን እዚህ ያላችሁ አንዳንዶቻችሁ ሀገራትና መንግሥታት ገና ሀገር ሳትሆኑና መንግሥትም ሳትመሠርቱ ከሺሕ ዓመት በፊት በነጻነቷና በሉዓላዊነቷ ጸንታ የኖረች ሀገር ናት፡፡ በዲፕሎማሲው መስክም ቢሆን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ማኅበርን፣ አፍሪካ ኅብረትን ያቋቋመች ቀዳሚ ሀገር ናት፡፡’’
‘‘ኢትዮጵያውያን በሰላም አስከባሪነት ረገድም ከኮሪያ ልሣነ ምድር ከሰሜን አፍሪካ እስከ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ድረስ ሰላምን በማስከበር ትልቅ ሚናን የተጫወተ ታላቅ ሀገርና ሕዝብ መሆኑን- ለወዳጆቻችንም ሆነ ለጠላቶቻችንም ቁጭ ብለው ታሪክ እንዲማሩ ልንነግራቸው እንወዳለን፡፡’’
ለመውጫ ያህልም፤ የጥቁሮች መብት ተጋይ የነበረው፣ አፍሪካ አሜሪካዊው ማርከስ ጋርቬይ፤ the Universal African Anthem በሚለው ‘የአፍሪካ ብሔራዊ መዝሙሩ ግጥም’ ውስጥ- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያኒዝም- የነጻነት ትእምርት፣ የአንድነት ውብ ኅብር፣ የጥቁር ሕዝቦች ነጻነት እኩልነትና መብት አብሳሪ የተስፋ ጎሕ መሆኑን የጠቀሰበትን- ከአፍሪካ ብሔራዊ መዝሙር ስንኞች እንሆ በጥቂቱ እንሆ በማለት ልሰናበት፤
‘‘… ኦ! ኢትዮጵያ!
ኦ! ኢትዮጵያ!
የአማልዕክት ምርጫ ሰገነት
የዝናቡ ደመና ሲሰበሰብ በማታ
ሰራዊታችን በአሸናፊነት ሲገባ በዕልልታ
ኦ! ኢትዮጵያ… ተዋጊው ጦሩን እየሰበቀ ሲመጣ
በቀይ ጥቁር አረንጓዴ ባንዴራ ሲመራ
አውቀነዋል ድል የእኛ መሆኑን
የጠላት ኃይል
ብትንትኑ መውጣቱን
ኦ! ኢትዮጵያ…’’
ኢትዮጵያዊነት የማይበገር የነጻነትና የአንድነት ሕያው መንፈስ ነው!!
ሰላም!!