>

የአሜሪካን የርስ በርስ ጦርነት የቀሰቀሰው የፎርት ሰምተር ጥቃት እና በኢትዮጵያ ሰሜን ዕዝ  ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፤ አብርሃም ሊንከን እና ኢትዮጵያ  [ ክፍል ፩] አቻምየለህ ታምሩ

የአሜሪካን የርስ በርስ ጦርነት የቀሰቀሰው የፎርት ሰምተር ጥቃት እና በኢትዮጵያ ሰሜን ዕዝ  ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፤ አብርሃም ሊንከን እና ኢትዮጵያ
  [ ክፍል ፩]
አቻምየለህ ታምሩ

* እኔና ወዳጄ Ermias Legesse Wakjira ከ20 ቀናት በፊት “የአሜሪካን የርስ በርስ ጦርነት የቀሰቀሰው የፎርት ሰምተር ጥቃት እና በኢትዮጵያ ሰሜን ዕዝ  ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፤ አብርሃም ሊንከን እና ኢትዮጵያ” በሚል  ርዕስ ያዘጋጀሁትን ጽሑፍ ተከትሎ  ጽሑፌን፣ ተያያዥ ጉዳዮችንና «የወልቃይት ጉዳይ»ን በማንሳት በኢትዮ 360 ውይይት አድርገን ነበር። በውይይታችን ያነሳናቸውን ታሪካዊ ተጠይቆች የተከታተሉ አንዳንዶች ከታሪካዊ ዳራው ተነስተን ያነሳናቸውን ዘላቂ መፍትሔዎች እዚህም እዚያም እንደ ነገሩ እያቀረቡ  ስለሆነ የነገሩን ስረ መሰረት  አጥርተን ያካሄድነው ውይይት በሕወሓት ላይ የተገኘውን  ወታደራዊ ድል ወደ ፖለቲካዊ ለውጥ ለመቀየር የሚፈጠረውን ማኅበራዊ ንቅናቄ በሀሳብ ስለሚያግዝ የአሜሪካ የርስ በርስ ጦርነት እና በኢትዮጵያ ውስጥ በሕወሓት ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት መካከል ያለው አንድነትና ልዩነት፤ ከጦርነቱ በኋላ ኢትዮጵያ ስለሚያስፈልጋት ለውጥ  የተወያየነውንና ለውውይታችን መነሻ የሆነውን ከ20 ቀናት በፊት ያዘጋጀሁት የጽሑፌን የመጀመሪያ ክፍል ከታች አትሜዋለሁ! ጽሑፉ የተዘጋጀው ከ20 ቀናት በፊት በመሆኑ ዛሬ ከምንገኝበት ሁኔታ አኳያ የቀን እና የሁነት ልዩነት ስለሚኖር አንባቢ ጽሑፉን ሲያነብ ይህንን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።
*      *     *
በአገራችን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በሚመለከት የአሰላለፍ ዘርፎች ተፈጥረው የተለያዩ አስተያየቶች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አስተያየት ስላልሰጠሁ እየተካሄደ ባለው ነገር የማምንበትን አስተያየት እሰጥ ዘንድ ወዳጆቼ ስለጠየቁኝ የሚታየኝንና የማምንበትን አስተያየት ለመጻፍ እነሆ ብዕሬን ከወረቀት ጋር አገናኝቻለሁ።
በቅድሚያ ነገሮችን የማየው በመዋቅር መሆኑን ማስታወስ እሻለሁ። ስለሆነም በአገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በሚመለከትም  ያለኝን አስተያየት የምሰጠው እየሆነ ያለውን ነገርና ተዋናዮችን በመዋቅር በመመልከት ነው። ባገራችን ውስጥ እየተካሄደው ያለው ጦርነት መግፍዔና ውጤቱ ለአገር የሚያስገኘውኝ  ፋይፋ በመዋቅር ለመመልከት በሰሜን ዕዝ የአማራ ተወላጆች ለይተው እንዲፈጁ ከተደረጉበት ጭፍጨፋ ጋር ተመሳሳይነት ያለውንና በአሜሪካን አገር የተቀሰቀሰው የርስ በርስ ጦርነት እንዲለኮስ ገፊ ምክንያት [Immediate Cause] ለመሆን ከበቃው የፎርት ሰምተር ጥቃት ጋር አነጻጽሮ ማቅረብ ይቻላል። በኢትዮጵያው በሰሜን ዕዝ እና በአሜሪካው ፎርት ሰምተር ላይ ጥቃት የፈጸሙት  ሁለቱም  ኃይሎች ተገንጣይ ኃይሎች መሆናቸውና በሁለቱ የጦር ማዕከላት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ማዕከላዊውን መንግሥት በተቆጣጠረውና ለመገንጠል በሚዋጉ ኃይሎች መካከል “የርስ በእርስ ጦርነት” እንዲቀሰቀስ እንደ ገፊ ምክንያት [Immediate Cause] በማገልገላቸው በአሜሪካው ፎርት ስምተር ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአሜሪካን አገር ያስተከተለው የርስ በእርስ ጦርነትና ያስገኘው አገራዊ ፋይዳ በኢትዮጵያው ሰሜን ዕዝ ላይ ተገንጣዩ ኃይል የፈጸመው ጭፍጨፋ የቀሰቀሰው “የርስ በእርስ” ጦርነት ሊያስገኘው የሚገባውን አገራዊ ፋይዳ ለመመዘን የሚያስችል መነሻ ሀሳብ ይሰጣል።
በአሜሪካውያን ዘንድ ቁጥር አንድ ተወዳጅ መሪ ሆነው የዘለቁት ፕሬዝደንት አብርሐም ሊንከን እ.ኤ.አ. በኅዳር 1860 ዓ.ም.  የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ በደቡብ የአሜሪካ ክፍል የነበሩ ሰባት ግዛቶች  ከአሜሪካ ማዕከላዊ መንግሥት ያፈነገጠ “የኮንፌዴሬት ግዛቶች” የሚል ስም የሰጡት ስብስብ በመፍጠር ከማዕከላዊ መንግሥቱ እውቅና ውጭ የሆነ  የራሳቸው መንግሥት ለመምረጥ ጉዞ ጀመሩ:: የተገንጣይ ግዛቶች ስብስብ መግፍዔያቸው ባርነት የተከለከለበት የሰሜኑ ክፍል ፓርቲ የሆነው የሪፒብሊካን ፓርቲ እጩ በመሆን ለፕሬዝደንትነት የተመረጡት አብርሐም ሊንከን በጥጥ ምርት ላይ ለተመሠረተው የእርሻ ምጣኔ ሀብታቸው አስፈላጊ ግብዓት ነው ብለው ለሚያምኑት የባሪያ ስርዓተ ማኅበራቸው ተቃማዊ በመሆናቸው ነው።
በዘመኑ አሜሪካኖች የመረጡት ፕሬዝደንት የስልጣን ርክክብ የሚካሄደው እንደ አሁኑ በጥር ወር  ሳይሆን በመጋቢት ወር ስለነበር የአብርሐም ሊንከንን መመረጥ ተከትሎ ቃለ መሐላ ፈጽመው በፕሬዝደንትነት ገና ሳይሰየሙ በአብርሐም ሊንከን አስተዳደር ስር እንደማይገዙ ለማሳየት በየግዛቶቻቸው ውስጥ ይገኙ የነበሩትን የፌዴራሉን መንግሥት ንብረቶች መውረስና መንጠቅ ጀመሩ።
በወቅቱ መሪ የነበረው ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ጄምስ ቢውካነን እና ኮንግረስ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሳይወጡ  አንዳንድ ነገሮች አቅደው እርምጃ ለመውሰድ ቢሞክሩም ኮንፌዴረቶች በፌዴራል መንግሥቱ ንብረቶች ላይ የሚፈጽሙትን ንጥቂያና ጥቃት ለማስቆችም አልተቻለም። አብርሐም ሊንከን እንደተመረጠ የተነሱት ኮንፌዴሬቶች በፕሬዝደንትነት ተሰይመው ቃለ መሐላ እስከሚፈጽሙ ባለው ጊዜ ውስጥ ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው እርቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ።  አሜሪካን ለዚህ የእርስ በእርስ ጦርነት  የበቃችው ግማሹ ክፍል ሰው ነጻ የሆነበት፤ በግማሹ  ክፍል ደግሞ ጥቁር ባሪያ ሆኖ እንደ ሰው  ሳይሆን እንደ ንብረት የሚቆጠርበት አገር ሆና መቀጠል የማትችልበት አፋፍ ላይ በመድረሷ ነበር።
ፕሬዝደንት አብርሃም ሊንከን ይህንን ሁኔታ ቢረዱም እ.ኤ.አ. በመጋቢት 4 ቀን 1861 ዓ.ም.  የስራ ዘመን መጀመሪያ ንግግራቸውን ሲያደርጉ ነገሮችን ለማለዘብና ተገንጣዮችን ለማባበል ኮንፌዴሬቶችን እና ለሌሎቹም የደቡቡ የአሜሪካ ግዛቶች የሚያግባባ ንግግር አደረገው ነበር። የፌዴራሉ መንግሥት የባርነት ሕግ ያላቸው ግዛቶች ባሮቻቸውን እንዲለቅቁና  ባርነት በነባር የአሜሪካ ግዛቶች እንዲታገድ የሚያስገድድ እቅድ እንደሌላቸው በመናገር  ኮንፌዴራል ግዛቶችን ለማባበል ሞክረው ነበር። ሆኖም ግን ይህ የአብርሐም ሊንክን ማባበያ ስላልተዋጠላቸው ዋይት ሐውስ ገብተው ስራ ሲጀምሩ እንደጀመሩ  ተገንጣዮቹ አላማቸውን ከግብ ለማድረስ ብሶባቸው ተነሱ። ሆነ ብለው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚያላትሙ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን አጠናክረው ቀጠሉ:: ፕሬዝደንት  አብርሐም ሊንከን ግን የመጀመሪያውን ጥይት ተኩሰው ነገር ፈላጊ ላለመምሰል  እስከ ትዕግስታቸው ጫፍ ድረስ ታገሰው ነበር።
የአብርሐም ሊንከን  ቃለ መሐላ በፈጸሙ በሁለተኛው ወር  ኮንፌዴሬቶች ቀይ መስመር የመጨረሻ ጫፍ ያለፈ ትንኮሳ አደረጉ። ይህም ትንኮሳ እ.ኤ.አ. በሚያዚያ ወር 1861 ዓ.ም.  የተገንጣዮቹ ተቀዳሚ ግዛት በሆነው  ሳውዝ ካሮላይና ውስጥ የታለፈው የቀዩ መስመር የመጨረሻ ጫፍ በሚቀጥሉት አራት አመታት ውስጥ የ600ሺ አሜሪካውያንን ሕይወት የቀጠፈው የእርስ በእርስ ጦርነት የለኮሰ ሕገወጥ እርምጃ ለመሆን በቃ።
ኮንፌደራሊስቶች ቀዩን መስመር ያለፉበት ትንኮሳ የአሜሪካ ማዕከላዊ  መንግሥት ንብረት በሆነውና ከኮንፌዴራል ግዛቶች እንዷ በሆነችው በሳውዝ ካሮላይና ወደብ ላይ በሚገኘው ፎርት ሰምተር የሚባለው የጦር ሰፈር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ነው። በነገራችን ላይ አሜሪካኖቹ ፎርት የሚሉት የጦር ሰፈራቸውን ወይም ዕዛቸውን ነው። በፎርት ሰምተር ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፌዴራል ወታደሮች ነበሩ:: አብርሐም ሊንከን ቃለ መሐላ ፈጽመው ፕሬዝደንት እንደሆኑ የሳውዝ ካሮላይና ተገንጣይ የኮንፌዴራል መንግሥት በኖርዝ ካሮላይና ለነበረው የማዕከላዊ መንግሥት የጦር ሰፈሩ አዛዦች ፎርቱን ለተገንጣዩ ስብስብ በማስረከብ ከኮንፌዴሬሽኑ ግዛት ለቅቀው ባስቸኳይ እንዲሄዱ ማስጠንቀቂያ ሰጡ። የፎርቱ አዛዦች  ግን ይዞታቸው የአሜሪካ ማዕከላዊ መንግሥት ሀብት ስለሆነ ጦር ሰፈሩን መልቀቅ እንደማይችሉ በማሳወቅ  ዋይት ሐውስ ተጨማሪ ስንቅና ትጥቅ እንዲላክላቸው ጠየቁ።
በዚህ ወቅት ፕሬዝደንት አብርሐም ሊንከን ለተጠየቁት ጥያቄ አሳጣኝ መልስ በመስጠት ትጥቅና ስንቅ በመርከብ አስጭነው  ወደ ጦር ሰፈሩ ላኩ። የሳውዝ ካሮላይና ግዛት ወታደሮች ግን መርከቧ ወደ ፎርት ሰምተር እንዳትደርስ በተኩስ አስፈራርተው ወደ መጣችበት መለሷት። የጦር ሰፈሩን በተቆረጠለት ቀን ለቅቆ እንዲወጣ የተቆረጠለት ቀን ያለፈባቸው  የፎርቱ አዛዦች እጃቸውን ይሰጡ ዘንድ  የአማፂው ግዛት ወታደሮች የመድፍ እና ሞርታር ውርጅብኝ ያዘንቡባቸው ጀመሩ:: ከሁሉት ቀን ያለማቋረጥ ድብደባ በኋላ የተገደለው ተገድሎ  በሕይዎት የተረፉት  ቁጥራቸው ወደ 85 የሚሆኑ ወታደሮች  እጃቸውን ለኮንፌዴራል ኃይሎች ለመስጠት ተገደዱ።
ይህ ማዕከላዊው መንግሥት በሚቆጣጠረው የጦር ሰፈር በአሜሪካ ወታደሮች እና ይዞታ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በተለይ የሰሜናዊ የአሜሪካ ክፍለተ ግዛት ዜጎችን እጅጉን  አስቆጣ:: በዚህ ወቅት አብርሐም ሊንከን ከሰሜኑ ክፍል ሰባ አምስት ሺህ ወታደሮች ለዘመቻ ጠሩ። ይህ  ለአራት ዓመታት የተካሄደው የርስ በእርስ ጦርነት  መፈንዳት ጅማሮ ሆነ። ጦርነት ምንጊዜም መልካም ነገር ባይሆንም የአሜሪካው የእርስ በእርስ ጦርነት ግን  ከአሜሪካ እንደ ሀገር ከተቆረቆረጅ ጀምሮ በሕዝብ መካከል ትልቅ መነጋገሪያና  ውሳኔ እንዲሰጥባቸው በየጊዜው በሚወጡ ሕግጋትና ስምምነቶችም ሲንከባለል የኖረው የባርነት ነቀርሳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ በማድረግ የሰላም መዳረጃ ለመሆን በቅቷል።
የማይሞት ራዕይ የነበራቸው አባቶች የመሰረቷት አሜሪካ ከተፈጠረች ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ የተፈጠሩ እንደ አብርሐም ሊንከን አይነት ትውልዶች የቆዳ ቀለማቸው ሊያስገኝላቸው የሚችለው የተረኛነት እና የአንደኝነት ጥቅም ሳያሳሳቸው፤ ከራሳቸው በላይ ለሆነ ዓላማ በመሰለፍ “All men are created equal” የሚለውን  በሰማይም በምድርም ከስብዕና ማማ ላይ የተሰቀለ ልዕለ ሀሳብ[idealism] በማስበለጥ የባርነት ሥርዓተ ማኅበራቸው እንዳይነካ ባመጹ ኮንፌዴሬቶች ስር ይማቅቁ የነበሩ ባሮችን ነጻ ለማውጣት በአንድነት መክረው ተነሱ። በወቅቱ “All men are created equal”  የሚለው ልዕለ ሀሳብ [idealism] በመሪዎቹ ዝነድ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ንቃተ ዘንድ እጅጉን ሰርፆ ስለነበር ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ በአብርሐም ሊንከን መሪነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነጭ አሜሪካውያን  ሕይወታቸውን ያለ ስስት ገብረውለታል:: በውጤቱም ባርነት በሕግ በሙሉ ተክለክሎ የተረፉት ባርያዎችን ነጻነት የሚያጎናጽፍ አዋጅ አወጡ። ይህም አዋጅ የባርነት ነቀርሳን  ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአሜሪካ ምድር እንዲፋቅ አደረገ።
የዘመኑ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት መገንጠልን አይከለክልም። የባርነት ሥርዓተ ማኅበርን አንተውም ያሉት የኮንፌዴራል ግዛቶች ወደቀድሞው የራስ መንግሥትነት ይዞታ ለመመለስ ሲወስኑ ያደረጉት ነገር ቢኖር በጋራ የመሰረቱትን የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች ኅብረት ለቅቀው መውጣት ነበር። ከተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች በገዛ ፈቃድ  መውጣትና የራስ መንግሥት መመስረት የመቻል አለመቻል ጉዳይ ግን  በርስ በእርስ ጦርነቱ  በተከፈለው የደም እና አጥንት ግብር ከሞላ ጎደል መልሱ በማኅተም ተገልጧል:: መልሱም “አይቻልም!”  የሚል ነው።
የአሜሪካ ኮንፌዴሬቶች በፎርት ሰምተር ላይ ከ160 ዓመታት በፊት የተፈጸመው ጥቃትና የሰሜኑ የአሜሪካ ክፍል ተወላጅ መኮንኖች ላይ ያካሄዱት ጭፍጨፋ ባለፈው ማክሰኞ የተገንጣይ ወንበዴዎች ድርጅት የሆነው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ካደረሰው ጥቃትና የአማራ ተወላጅ መኮንኖችን እየለየ ካካሄደው ጭፍጨፋ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ተገንጣይ ኮንፌዴሬት ግዛቶች ፕሬዝደንት አድርገው የመረጡት የግፍ ሥርዓቱ መሪ የነበረው ጀፈርሰን ዴቪስ ደግሞ  ተገንጣይ ወንበዴዎች የድርጅታቸው  የሕወሓት ሊቀመንበርና የግዛታቸው ፕሬዝደንታቸው አድርገው ከመረጡት ከደብረ ጺዮን ጋር አንድ አይነት ነው። ኮንፌዴሬቶች ፕሬዝደንታቸው አድርገው የመረጡት ጀፈርሰን ዴቪስ የተገንጣይ ግዛቶች ፕሬዝደንት ሆኖ ከመመረጡ በፊት ከሚሲሲፒ ተመርጦ የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት [ኮንግረስ]አባል ነበር። ተገንጣይ ወንበዴዎች የግዛታቸው መሪ አድርገው የመረጡት ደብረ ጺዮንም የተገንጣይ ወንበዴዎች ግዛት ፕሬዝደንት ሆኖ ከመመረጡ በፊት አድዋን ወክሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተብዮው አባል ነበር።
በመሆኑም አዲስ አበባ  በማዕከላዊ መንግሥትነት የተሰየመውን አገዛዝና ትግራይን በግዞት በያዘው በተገንጣዩ የሕወሓት ድርጅት መካከል እየሆነ የነበረው፤ በተለይም ባሳለፍነው ማክሰኞ “ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል” የተባለለትና በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለው ጥቃት የአሜሪካ የርስ በእርስ ጦርነት እንዲፈነዳ ገፊ ምክንያት [Immediate Cause] ከሆነው በሚያዚያ ወር 1861 ዓ.ም. ሳውስ ካሮላይና ውስጥ በሚገኘው ፎርት ሰምተር  ላይ  ከተፈጸመው ጥቃት ጋር ስለሚመሳሰሉ ሁለቱን አነጻጽሮ ማየት ይቻል ነበር።
ሰሜን ዕዝ የተመደቡ የአማራ ተወላጆችን ለይቶ የጨፈጨፈው ሕወሓት የኢትዮጵያ ካንሰር ነው። ይህ ካንሰር የጎሳ ፖለቲና በባለቤትነት ይዞ የሚመራ ትልቅ ኮብራ ነው። ይህ ካንሰር የሆነ የወንጀል ድርጅት መወገድ አለበት። እኔ ሕወሓት የተባለውን የኢትዮጵያ ነቀርሳ ለማስወገድ የሚያደረገውን ተጋድሎ የወንድማማቾች ጦርነት አድርጌ የምወስድ ነሆለል አይደለሁም። ሕወሓት ኢትዮጵያዊ ስሜት ያለውን፤ በተለይም ደግሞ የአማራ ተወላጅነት ያለውን ሁሉ ሳይበድለው ጠላት በማድረግ  ለወንጀል የተቋቋሙ ድርጅት ነው። አንድን ሰው ወንድም የሚያደርገው ተግባሩ ነው። በሕወሓትና በፋሽስት  ፓርቲ ሰዎች መካከል ከቆዳ ቀለም በስተቀር ምንም አይነት ልዩነት የለም። በመሆኑም አቅምና ጉልበቱን ሁሉ ሳይቆጥብ ለክፉ ተግባር ያዋለው፤ በእምነትና በቅን መንፈስ ተገፋፍቶ ያለፋቸው ክፉ ነገሮች በመብራት ተፈልገው የማይገኙለት፤ በትምህርት ተወልደው መልካም የሚሰሩና ለወገናቸው የሚያስቡ ሰዎችን በማጥፋት ክብረወሰን የተቀዳጀው፤ ድሀ ዘራፊና ገፋፊና ለወንጀል የተቋቋመው ሕወሓት የሚባለውን የኢትዮጵያ ነቀርሳ ከነአስተሳሰብ ሰንኮፉ እንዲነቀል የሚደረግ ጦርነት የወንድማማቾች ጦርነት ሳይሆን ፍትሐዊ የሆነ ጦርነት ወይም ፈረንጆች Just War የሚሉት አይነት ጦርነት ነው። ሕወሓት ፎርት  ሰምርተንን ካጠቁት የደቡብ አሜሪካ ተገንጣይ ባርያ አሳዳሪ ኮንፌዴራሊስቶች የከፋ አረመኔያዊ ድርጅት ወይም ፈረንጆቹ  Criminal Enterprise  የሚሉት አይነት ድርጅት ነው።
ሆኖም ግን በአሜሪካ ውስጥ ከ160 ዓመታት በፊት የነበረው ፌዴራል መንግሥት በዛሬ በኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግሥትነት የተሰየመው አካል በፍጹም  ተቃራኒ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ማዕከላዊ መንግሥቱን የተቆጣጠረው በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ እንደ አብርሐም ሊንከን አስተዳደር ማንነቱ ሊያስገኝለት የሚችለውን የተረኛነት እና የባለጊዜነት ጥቅም ንቆ ከራሱ በላይ ለሆነ አላማ የተሰለፈ የአርበኞች መንግሥት አይደለም።
ዐቢይ አሕመድ ድርጅቱን ወክሎ በመንግሥትነት ሲሰየም ቃለ መሐላ የፈጸመበት ደንብ እነዚህ ሁለት የኢትዮጵያ ነቀርሳዎች ኢትዮጵያን ለመቀራመትና ለማጥፋት በተዋዋሉበት ስምምነት ነው። በስልጣኑ ከመጡበት ሕወሓቶች ጋር  ጦርነት ውስጥ የገባውም ሕወሓት እና ኦነግ የጻፉትን  ሕገ አራዊት ለማስከበር እንደሆነ ነግሮናል።  ተመሳሳይ ችግር የገጠመው አብርሐም ሊንክን ግን ወደ ተገንጣይ ኮንፌዴሬቶች የዘመተው ሕግ ሊያስከብር ሳይሆን የግፍ ሥርዓትን ሊያፈርስና መገንጠልን ሊደመስስ  ነው።  በመሆኑም አብርሐም ሊንከን በዘመተባቸው ተገንጣይ ኮንፌዴሬቶች ላይ የሞራል የበላይነትና የአስተሳሰብ ልዕልና ነበራቸው።
በእኛ አገር  ግን  በማዕከላዊ መንግሥትነት የተሰየመው የአፓርታይድ አገዛዝ እንደ አብርሐም ሊንከን አስተዳደር የሞራልና የአስተሳሰብ ልዕልና ያለው ሳይሆን በአብርሐም ሊንከን አስተዳደር ላይ ጦር የሰበቁ  ኮንፌዴራል ግዛቶች የመሰረቱት አይነት ግፈኛ ሥርዓት ቅጂ ነው። በመንግሥትነት የተሰየመው በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ ጦር ሰብቆብኛል የሚለው የሕወሓት የአፓርታይድ አገዛዝ የባሕሪ ታናሽ ወንድም ብቻ ሳይሆን ወያኔ ሀያ ሰባት ዓመታት የፈጀበትን የአፓርታይድ ክብረ ወሰን በአስር ወር ውስጥ የተቀዳጄ የነውር ጌጡዎች አገዛዝ ነው። በመሆኑ በዐቢይ አሕመድ የሚመራው  የኦሮሙማ  የአፓርታይድ አገዛዝ የማይሞት ራዕይ ይዘው ማንነታቸው ሊያስገኝላቸው የሚችለውን የተረኛነት እና የባለጊዜነት ጥቅም ንቀው ከራሳቸው በላይ ለሆነ አላማ የተሰለፉት የአብርሐም ሊንከን አስተዳደር ወደረኛ ተደርጎ ሊቀርብ የሚችል አይችልም።
በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ ከሕወሓት ጋር ሳይሆን ሕወሓት ውስጥ ተፈጥሯል ከሚለው አንጃ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባው ዐቢይ አሕመድ እንደሚለው ሕገ መንግሥት ተብዮው የቅሚያና የዘር ማጥፊያ ደንብ በመተግበሩ እንጂ በመጣሱ አይደለም። በአሜሪካን አገር በጦርነቱ ማግሥት በሕገ መንግሥቱ ያልተገደበው የመንገንጠል መብት ከታገደና  በደቡቡ ክፍል የነበረው የግፍ ሥርዓተ ማኅበር ከተቀየረ በኋላ በደቡቡ ክፍል በነበሩ ተገንጣይ ግዛቶች  ውስጥ ይገኙ የነበሩ የማዕከላዊ መንግሥቱ ይዞታዎችና ይኖሩ በነበሩ ዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረው ጥቃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወገደ። በኢትዮጵያ ግን ወያኔና ኦነግ ኢትዮጵያን ያዋቀሩበት ሕገ መንግሥት ተብዮ ደንብ እስካልተሻረ ድረስ ሕወሓት የማዕከላዊ መንግሥቱ ይዞታ በሆነው በሰሜን ዕዝ ላይ ፈጸመ የተባለው አይነት ጥቃት ኦነግና ኦብነግ በስፋት በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ነገ የማይፈጸምበት ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይችልም።
ይቀጥላል. . .
Filed in: Amharic