>

በግማሽ እውነት አገር አትድንም...!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

በግማሽ እውነት አገር አትድንም…!!

ያሬድ ሀይለማርያም

የጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር አብይን የፖርላማ ንግግር ጊዜ ወስጄ ከአንዴም ሁለቴ ሰማሁት። ረዘም ያለ ሰዓት በወሰደው ንግግራቸው በርካታ መልእክቶችን እና አስደማሚ እውነቶችን ነግረውናል። ጠቅላዩ ከፖርላማ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሙሉ ንግግራቸው ቀደም ብለው በተዘጋጁበት እና ላለፉት ጥቂት አመታት እኩይ ከሆነው ከህውሃትን ጋር ያደረጉት ትንቅንቅ እና በሰሞኑ ግጭት ላይ ያተኮረ ነበር። የተነሱትን አብዛኛዎቹን ጥያቄዎች ባይመልሱም በንግግራቸው የፖርላማውን የጭብጨባ ድጋፍ እና የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ስበዋል። አቀራረባቸው ድንቅ ነበር።
ተነግሮ የማያልቀውን የህውሃት ሀጢያት ሁሌም እንደ አዲስ ለሚያስበረግጋቸው ብዙዎች የጠቅላዩ ንግግር ሌሎች የአገሪቷን ችግሮች ሁሉ የሚያስረሳም ሆኗል። ጠቅላዩም የሕዝባችንን ስነ ልቦና በደንብ የተረዱ ሰው ስለሆኑ ያጠራቀሙትን ብሶት አመቺ ሁኔታ ጠብቀውና ቀልብ በሚስብ መንገድ ዝርግፍ ስላደረጉት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ጆሮውንም፣ ቀልቡንም፣ ድጋፍ እና አጋርነቱንም ሰጥቷቸዋል። አገሪቱ ውስጥ ለተፈጠረው ሥርዓት አልበኝነት፣ ሰቅጣጭ የጅምላ ግድያዎች፣ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲወቅሳቸው የነበረ ሁሉ ሀጢያቱን ወያኔ ላይ ቆልሎ እሳቸውን ብጹ ያደረጋቸውም ሰው ቁጥር ቀላል አይደለም።
እርግጥ ነው እንደ ወያኔ ካለ የሴጣን አለቃ ጋር መስራት እና መታገል አይደለም አንድም ቀን በጉርብትና ማደር አይቻልም። ወያኔ አንገቷ ድረስ በወንጀል የተዘፈቀች፣ ሀጢያቷ እንደ ተራራ የተቆለለ፣ በንጹሀን ደም የጨቀየች ስለሆነች ወንጀሏን ለመደበቅ የማትፈነቅለው ድንጋይ፣ የማትንደው ተራራ የለም። ይገርመኝ የነበረው ከወያኔ ባህሪ አንጻር ጠቅላዩ የዘረገፉትን ሀጢያት ህውሃት ባትፈጽም እና በተቃራኒው በቅንነት ውላና አድራ ቢሆን ነበር።
ጠቅላዩ በዚህ የፓርላማ ውሏቸው የትላንቱን ስንክሳር ብቻ አውርተው መሄዳቸው አስገርሞኛል። አገሪቱ ዛሬ የተጋረጡባትን አደጋዎች፣ እሳቸው እና ፖርቲያቸው የፈጸሟቸውን ጉልህ ስህተቶች፣ ከገባንበት ቅርቃር እንዴት ልንወጣ እንደምንችል ከስንክሳሩ ለጥቀው አቅጣጫ አመላካች ሀሳቦችን ይነግሩናል ብዮ ጠብቄ ነበር። ያ ግን አልሆነም።
ፖርላማው የብሶት መድረክ ከመሆን ባለፈ የመፍትሔ ሀሳቦቻ ማፍለቂያ ሊሆን አልቻለም። የመፍትሔ ሀሳብ የሚመነጨው ችግሮች በአግባቡ ተነቅሰው ሲነገሩ ነው። ያንን ደግሞ ጠቅላዩ የፈለጉት አይመስልም። ህውሃትን ብቻ በማውገዝ እና ሀጢያቷን በመዘርዘር የተዘጋው የፖርላማ ውሎ የአገሪቱን ቀጠይ አግጣጫ የሚያመላክቱ ሃሳቦች እና ውሳኔዎችን ሳያስተላልፍ በተቆለለው የህውሃት አጢያት ደፍቀውን እና አስቆዝመውን ሄደዋል።
ለእኔ የጠቅላዩ መግለጫ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታን በአግባቡ ወይም ሙሉ በሙሉ የሚያያሳይ ግማሽ እውነት ነው። የተገለጸው ግማሽ እውነታ ጠቅላዩ የገጠማቸውን ፈተና በደንብ ያሳያል። አገሪቱ የገጠማትን ጠቅላላ እና ትልቅ ፈተና ግን አያሳይም። እንደ እኔ ዛሬ ለደረስንበት ችግር እና ለገባንበት ቅርቃር ከህውሃት ባልተናነሰ ሌሎች አካላትም ድርሻ አላቸው። ከነዚህ መካከል አንዱና ዋነኛው እራሱ ብልጽግና ፖርቲ ነው። አሁን ማን ይሙት በየክልሉ ለተፈጸመው በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እና ጭፍጨፋ ህውሃት ብቻ ነው ተጠያቂው? አፍንጫቸው ስር ሰው ሲታረድ ቆመው ጥርሳቸውን ይፍቁ የነበሩ የብልጽግና የክልል አመራሮችስ? አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ ነው።
እንደ እኔ፤
1ኛ/ ዛሬ ለደረስንበት ምስቅልቅል ሁኔታ ጠቅላዩም ሆነ ፖርቲያቸው ድርሻቸውን ቢያነሱ እና የነበራቸውን አወንታዊ ሚና በግልጽ ቢናዘዙ፣
2ኛ/ መንግስት ህውሃትን እና ኦነግ ሽኔን እንደ ድርጅት በቀጣይ በምን መልኩ እንደሚይዛቸው እና ስለሚወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎች በግልጽ ቢያስቀምጥ፣
3ኛ/ ተመሳሳይ ግጭቶች እና ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ድጋሚ እንዳይከሰቱ መንግስት ያደረገውን ዝግጅት እና መሻሻል በግልጽ ቢያስቀምጡ፣
4ኛ/ በብልጽግና ፖርቲ ጉያ ስር ሆነው ግጭቶች እና ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት በሆኑ ሹማምንት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ፤
እና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ ችግሮቻችን ላይ በግለሰጽ መወያየት እና የጋራ መፍትሔ መሻት የግድ ይላል።
Filed in: Amharic