ግፍ መቸ እንደሚጥል አይታወቅም
ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ
ምድር በኢ-ፍትሀዊ ነገሮች የተሞላች ስፍራ ነች፡፡ የሁሉም ፈጣሪ እግዚአብሄር እንደየስራው ለሁሉም ፍርድን ይሰጣል፡፡ ህወሐት በዚች ምድር ላይ ያልተሰሙ ግፎችን የፈፀመ አሸባሪ ቡድን ነበር፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን ነበር ለማለት በቃን፡፡ ምናልባት የህወሐት ግፈኞች ስጋ መልበሳቸው እንጅ የሳጥናኤል የባህሪይ ልጆች ሳይጣን ናቸው፡፡ ሳይጣናዊ ስራ አብሯቸው ተወልዶ አብሯቸው ያደገ፤ የክፋት ኃይል የሚገለፅባቸው፤ በክፋት የደነዘዙ ስጋዊ አረማውያን ናቸው፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድ በፓርላማ ቀርበው ህዳር 21/2013 ያቀረቡት ማብራሪያ በህወሐት የተንኮል ስራ ላይ ያጠነጠነ እና አብዛኛዎቹ ጉዳዬች (ፖለቲካን በቅርበት ለሚከታተል ሰው) የሚታወቁ ናቸው፡፡ ሁኖም ግን ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣኑን በተረከቡበት ወራት ያጋጠማቸውን ችግሮች የፈቱበትን አካሄድ ሊደነቅ የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ጠቅላዩ ካቀረቧቸው መረጃዎች መካከል ከነባራዊ ሁኔታው የራቁ ሁነቶች አሉ፡፡ እነዚህ እውነቶች ተደባብሰው ማለፋቸው ተገቢ አይደለም፡፡ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከተከሰቱት ግጭቶች መካከል አብዛኛዎቹ የህወሐት እጅ ቢኖርበትም የአክራሪ ኦነጋውያን ሴራ እና የሽብር ድርጊት በህወሐት ሊሸፈን አይገባም፡፡
ለምሳሌ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ እንዳረፈ በሻሸመኔ ከተማ ጥቃት እና ችግር እንደሚፈጠር የሻሸመኔው ከንቲባ ተማም ሁሴን ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳውቀው ነበር፡፡ ከንቲባ ተማም ሁሴን እንዲህ ነበር ያሉት፡
‘’የፀጥታ ችግር እንደሚያገጥመን ለሸመልስ አብዲሳ ነግሬው ነበር፤ ከጥቂት ደቂቃ በኃላ ከተማው መንደድ ስትጀምር ስልኩን ደግሜ ደወለሁ፤ ምላሹ ግን ዝም ብለህ ተኛ ብሎ ነው ያለው፤ ታዲያ እኔ ምን አድርግ ነው የምትሉኝ’’
ከንቲባ ተማም ሁሴን ይህን ያሉት ፍርድ ቤት በሰጡት ቃል ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመተከል የሚሰራው ስራ ስልታዊ እንደሆነ የሽመልስ አብዲሳ ንግግር የፓርቲውን ተልዕኮ ያሳብቃል፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ማሸማቀቅ፣ ማሳደድ እና መግደል ሰልታዊ እንደሆነ በድብቅ የተነገረው የሽመልስ አብዲሳ ንግግር በቂ ማሳያ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ግፍና በደል በህወሐት ላይ ማላከክ ተገቢ አይመስለኝም፡፡
ሌላም ልጨምር በብልፅግናው የመንግስት ስርዓትም የፍትህ መዛባት ብዙም ለውጥ አላሳየም፡፡ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው እስክንድር ነጋ ነው፡፡ ጠቅላዩ በፓርላማ የጠቀሷቸው ወንጀሎችን የሰሩ የህወሐት እና የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድኖች በአሸባሪነት ሳይከሰሱ እንደ እስክንድር ነጋ ያሉ ንፁኃንን በሽብርተኝነት መክሰሱ ለትዝብት ይዳርጋል፡፡ ንፁህን ሰው በሀሰት መወንጀል የሰይጣን የግብር ልጆች ያደርገናል እንጅ እውነት ጊዜዋን ጠብቃ ትወጣለች፡፡ በብልፅግናው የመንግስት ዘመንም የፍርድ ቤት ወሳኔ መሬት ለመሬት ተጎትቷል፡፡ የልደቱ አያሌው ጉዳይ ሌላው ማሳያ ነው፡፡ ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ አስፈፃሚው አካል አልቀበልም ብሎ ፍትህ አሁንም እንዳቀረቀረች ነች፡፡ ዜጎች ዛሬም እንባቸውን የሚያብስላቸው አጥተው ያነባሉ፡፡
የዘመናችን የትውልድ ብልሽት በለውጡ ይስተካከላል ብለን ተስፋን ብንሰንቅም የተረኝነት አባዜ ተጠናውቶን የግፍ ቅብብሎሽን ጀምረናል፡፡ አክራሪ ኦነጋውያን ከህወሐት ውድቀት መማር ካልቻሉ ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ ከስልጣን ጀርባ የሚሰራ ግፍ መቸ እንደሚጥል አይታወቅምና መጠንቀቁ መልካም ነው፡፡