>

እነ እስክንድር ነጋ የጻፉት ደብዳቤ! (ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ)

እነ እስክንድር ነጋ የጻፉት ደብዳቤ!

ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ

እነ እስክንድር ነጋ ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዘደንት እና ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዘደንት የፃፉት ደብዳቤ
ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዘደንት
                 እና
ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዘደንት
ጉዳዩ፡- የተፋጠነ ፍትህ ስለመጠየቅ
በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት እነ እስክንድር ነጋ በተከሰስንበት የወንጀል መዝገብ፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ምክንያቶች አቅርበን፣ ጉዳያችንን የያዘው ችሎት የተፋጠነ ፍትህ እንዲሰጠን መጠየቃችን ይታወሳል፡-
1ኛ. ተከሳሾች በህጋዊ መንገድ የተመዘገበ የፖለቲካ ድርጅት አባላት መሆናችንን፣
2ኛ. የታሰርነው በያዝነው ዓመት ይደረጋል ተብሎ እቅድ በተያዘለት ምርጫ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ በነበርንበት ጊዜ መሆኑን፣
3ኛ. የክሱ አላማ፡-
ሀ. ጥፋተኝነታችንን በፍ/ቤት አረጋግጦ ለማስቀጣት አለመሆኑን
ለ. በኮቪድ 19 ሳቢያ ተዘግተው የቆዩት ፍ/ቤቶች ያሉባቸውን የተደራረቡ መዝገቦች ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዋስትና የሚያስከለክል ክስ በመመስረት ጉዳዩ በእንጥልጥል እያለ በምርጫው እንዳንሳተፍ  ማድረግ መሆኑን፣
ሐ. በምርጫው እንዳንሳተፍ በፈጠራ ክስ የታሰርን መሆናችንን፣
መ. በተዘዋዋሪም ቢሆን፣ ፍ/ቤት የዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ተባባሪ መሆን እንደሌለበት፣
4. ፍ/ቤቱ ከምርጫ ጋር ባሉታዊ መልኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ላለመነካካት ለመዝገቡ ፈጣን ውሳኔ መስጠት እንዳለበት፣ ይህንንም ለመተግበር የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች አስፈላጊ እንደሆኑ፣
ሀ. በ1998 ዓ.ም በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል መዝገብ እንደተደረገው፣ ይህን መዝገብ ብቻ የሚመለከት ችሎት እንዲቋቋም፣
ለ. እንደገና፣ በ1998 ዓ.ም በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል መዝገብ እንደተደረገው ጉዳዩ በየእለቱ በተከታታይ እንዲታይ፣
ሐ. በምርጫው የሚሳተፉ እጩዎች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት በመዝገቡ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መሰጠት እንዳለበት አሳስበናል፡፡
በዚህም መሠረት፣ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም በነበረን ቀጠሮ ምላሽ እናገኛለን ብለን ጠብቀን የነበረ ቢሆንም፣ በዕለቱ ተግባራዊ ምላሽ ሳናገኝ ቀርተናል፡፡ ችሎቱ በሰጠን የቃል ምላሽም፣ ጥያቄያችንን ለበላይ አካል አቅርቦ ምላሽ እንዳልተሰጠው አስረድቶናል፡፡
ስለዚህም፣ አሁን ጥያቄያችንን የበላይ ስለሆናችሁ  የህግ ተርጓሚው አካላት እያቀረብን ሲሆን፣ በሀገራችን በቀጣይነት የሚደረገው ምርጫ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን በዚህ በኩል አስተዋፅኦ እንድታደርጉ በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ከሠላምታ ጋር
1ኛ. ተከሳሽ እስክንድር ነጋ
2ኛ. ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል
3ኛ. ተከሳሽ ቀለብ ስዩም
4ኛ. ተከሳሽ አስካለ ደምሌ
ግልባጭ፡
ለኢትዮጵያ፡- ምርጫ ቦርድ
ለኢትዮጵያ፡- ሰብአዊ መብት ኮሚሽን
Filed in: Amharic