>

የአማራ ልጆች  መከላከያ ሠራዊቱን ከሕወሓት ጥቃት ለመታደግ የፈጸሙት ተጋድሎ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትውልዱ ሁሉ ሊማረው የሚገባ ተግባር ነው! (አቻምየለህ ታምሩ)

የአማራ ልጆች  መከላከያ ሠራዊቱን ከሕወሓት ጥቃት ለመታደግ የፈጸሙት ተጋድሎ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትውልዱ ሁሉ ሊማረው የሚገባ ተግባር ነው!
አቻምየለህ ታምሩ

ሕወሓት “የአገር መከላከያ ሠራዊት” የሚባለውን ጦር ያሰለጠነው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ለሚባለው ድርጅታዊ  ርዕዮተ ዓለሙ ዘብ እንዲሆን አድርጎ ነው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባለው የሕወሓት ርዕዮተ ዓለም የአማራ ማጥፊያ ፕሮግራም ነው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጨቋኝ በሚል የተፈረጀን አካል ለማጥፋት የተፈጠረ አስተሳሰብ ነው። ሕወሓት በፕሮግራሙ አስፍሮ ሊያጠፋው የታገለውና በጨቋኝነት የፈረጀው አማራውን ነበር። በሌላ አነጋገር ሕወሓት በመንግሥትነት ተሰይሞ በነበረባቸው 27 ዓመታት ሁሉ “የአገር መከላከያ ሠራዊት” የሚባለውን ጦር ይጠቀምበት የነበረው የአገር ዳር ድንበርን  ለማስከበር ሳይሆን ጨቋኝ አድርጎ የሳለውን አማራን ለመጨፍጨፍ ነበር።
ባጭሩ ሕወሓት ጤናው በታወከ ቁጥር የአማራ ልጆችን ለመጨፍጨፍ የሚያሰማራው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዘብ አድርጎ ያሰለጠነውን የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚባለውን ኃይል ነበር። በዚህ  ሕወሓት ሲጠቀምበት በኖረው “የአገር መከላከያ ሠራዊት” የተጨፈጨፉ የአማራ ልጆች ነፍስ እልቆ ቢስ ነው።
በ2008 ዓ.ም. ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ወልድያ፣ መርሳ፣ ቆቦ፣ ወዘተ የተጨፈጨፉትን እምቦቀቅላ የአማራ ልጆች ትተን የሕወሓቱ ልሳን ሪፖርተር የሕወሓትን አገዛዝ ዋቢ በማድረግ ያወጣውን ከታች የታተመ ዘገባ ብቻ ብንመለከት  በሰሜን ጎንደር ውስጥ ብቻ  “የአገር መከላከያ ሠራዊት” የሚባለው  የሕወሓት ጦር በአንድ አመት ብቻ 597 አማሮች እንደፈጀ ማየት እንችላለን። ሕወሓት “የአገር መከላከያ ሠራዊት”  የሚባለውን አሰማርቶ ያስፈጃቸው 597ቱ አማሮች ዛሬ ፋኖ፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በሚል የሚጠሩትን የአማራ ልጆች ናቸው።
ሕወሓት  ሲያሰማራው በኖረው “የአገር መከላከያ ሠራዊት” ይህ ሁሉ ፍጅት ሲካሄድበት የኖረው አማራ  ግን  ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ሕወሓት ጦርነት ሲከፍትበት “አጋጣሚውን ተጠቅሜ ሲገድለኝ የኖረውን ሠራዊት ጦር ከከፈተበት ሕወሓት ጋር ተባብሬ  ቁሜን ልወጣ፤ አብሬ ልውጋው” አላለም።  “የአገር መከላከያ ሠራዊት” በሚለው የጦሩ ስያሜ ፊት “አገር” የሚል ነገር ስላለ የሠራዊትን ጥቃት የአገሩ ጥቃት አድርጎ በመቁጠር በሕወሓት እየተሰማራ ሲያጠቃው የኖረውን ሠራዊት ሲጠቀሙበት ከነበሩት ሕወሓቶች ጥቃት ለመታደግ ቀድሞ ደረሰና  ከመፈጀት ታደገው። አገር ማለት ይህ ነው። ይህ የአማራ ልጆች ሕወሓት እያሰማራ ሲያጠቃቸው የኖረውን ሠራዊት ከሕወሓት ጥቃት የታደጉበት ተጋድሎ አገር ማለት በመከፋት፣ በመበደል፣ በመገደልና በመገፋት የማትለወጥ እናት እንደሆነች ያሳዩበት ድንቅ ተግባር ነው። ይህ የተጋድሎ ታሪክ ሊካድ የሚገባው ተግባር ሳይሆን  ትውልዱ ሁሉ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይረዳ ዘንድ በተምሳሌትነት ሊማረው የሚገባው ታሪክ ነው።
ዐቢይ አሕመድ ግን የአማራ ልጆች ሕወሓት እያሰማራው ሲያጠቃቸውን የኖረውን የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሕወሓት ጥቃት የተደጉበትን ተጋድሎና  አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያሳዩበትን ተግባር አንገቱን ሲያዝ  የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻን በስም ጠርቶ እንዳላመሰገነ ሁሉ ድሉ ሲገኝ ግን ሊያስታውሳቸው አልፈለገም። ይህ ሕወሓት ሲጠቀምበት በነበረው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ከፈጸመው ነውር የማይተናነስ ክህደት ነው። ድሉ ሲገኝ ባለጊዜዎች ክህደት ቢፈጸሙበትም የአማራ አማራነቱ አገር መውደድ መሆኑን  ፊት ለፊት ቆሞ ሲሄድ የታየበት የተጋድሎ ታሪክ ግን  በተሠራው ገድል ዘላለም በትውልድ ዘንድ ሁሉ ሲዘከር ይኖራል። እንዲህም እንላለን. . .

አማራነት ታየኝ!

ደም የተነከረ ጥቁር ካባ ለብሶ፣
ብሶትና ቁጭት ቁጣ ተንተርሶ፤
ያለፈበትን መስክ አቀበት ተራራ፤
ቃላት ሳይተነፍስ ዝምታው ሲያወራ፤
መውጣቱን፣
መውረዱን፣
እጅግ መገፋቱን፣
መገደል መሞቱን፤
የበደሉን ብዛት ፊቱ እየነገረኝ፣
የተስፋው ወጋገን መልሶ እያጽናናኝ፣
ትናንት የሰራውን መልካም ስራ ሁሉ ክፋት አፍርሶበት፣
የካበውን ካቡን የደከመበቱን ‘ሳት አንድደውበት፤
ወንድሞቼ ብሎ መንገድ የመራቸው ያደረሱበት ግፍ ውስጡ ድረስ ዘልቆ፣
ቢሰማው ቢያመውም ተስፋውን አንግቦ እንደ ጋሻው ታጥቆ፤
ታድሶ እንደ ንስር አይኖቹ ቀላልተው፣
ተስፋ እያማተሩ በቁጣ ተሞልተው፣
ጋሻውን አንስቶ፣
መውዜሩን አንግቶ፤
አልቤን ምንሽሩን፣
ቤልጂግ ናስማስሩን፣
ክላሽ ዲሞፍተሩን፣
ጦርና ጓንዴውን፤
ካለበት ጎትቶ፣
ህመሙን ረስቶ፣
ልክ እንደ ሰንበሌጥ ካጎነበሰበት ራሱን አቃንቶ፣
እንደ በቆሎ ዘር ደርቆ በማለምለም ከማሳው አሽቶ፤
ህያውነኝ እያለ ሲናገር ደጋግሞ፣
ከበሽታው ድኖ ታክሞ አገግሞ፣
አማራነት ታየኝ ፊት ለፊቴ ቆሞ!!!
Filed in: Amharic