>
5:33 pm - Monday December 5, 7087

የኢሳት የቦርድ ሊቀመንበር የአባይ ሚዲያን ዩቲዩብ ቻናል ማዘጋቱን በሚመለከት፥ ከአባይ ሚዲያ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ!

የኢሳት የቦርድ ሊቀመንበር የአባይ ሚዲያን ዩቲዩብ ቻናል ማዘጋቱን በሚመለከት፥

ከአባይ ሚዲያ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ!

ህዳር 24 ቀን 2013 ዓ.ም
የአባይ ሚዲያ አስተዳደር አባላት፥ ኢሳትን ከመመስረት ጀምሮ ዛሬ ኢሳት የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ከማንም በላይ መሰዋዕትነት የከፈሉ ግለሰቦች መሆናቸው ይታወቃል። ኢሳት እና አባይ ሚዲያ በትግሉ ወቅትም ሆነ ከለውጡ በኋላ እጅና ጓንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩና አሁንም ቢሆን እንደተቋም የሚተጋገዙ ድርጅቶች ናቸው። ስለዚህም ይህ አሁን የተፈጠረው ችግር በኢሳት እና በአባይ ሚዲያ መሀል የተፈጠረ ችግር ነው ብሎ የአባይ ሚዲያ አስተዳደር አያምንም።
ይሁን እንጂ የኢሳት የወቅቱ የቦርድ ሊቀመንበር
ዶ/ር ሰለሞን ረታ፥ አላማውን ባልተረዳነውና ኢሳትን በህግ ሊያስጠይቅ በሚያስችል መልኩ የአባይ ሚዲያን ዩትዩብ ቻናል ካዘጋው ስድስትኛ ቀኑን ይዟል። የአባይ ሚዲያ አስተዳደር አባላትም በኢሳት ቦርድ ሊ/መንበር የተፈፀመውን ህገወጥ ድርጊት ለዩትዩብ ኩባንያ በአግባቡ በማስረዳታችን የአባይ ሚዲያ ቻናል በአስር የስራ ቀናት ውስጥ እንደሚከፈት አረጋግጠውልናል።
ይህ በቦርዱ ሊ/መንበር የተፈፀመውን ህገ ወጥ ድርጊት፥ ለቦርዱ አባላት በደብዳቤ እና በስልክ ያሳወቅን ሲሆን፥ ከቦርዱ ሊቀመንበር ውጭ ሁሉም የኢሳት ቦርድ አባላት በተደረገው ድርጊት በጣም ማዘናቸውን ገልፀውልናል። ይህንን ህገወጥ ድርጊት የቦርዱ ሊቀመንበር ያደረገው ከቦርዱ እውቅና ውጭ መሆኑንም በሚገባ ተረድተናል።
ስለሆነም ውድ የአባይ ሚዲያ ቤተሰቦች፥
ላለፉት አምስት ቀናት በስልክ፣ በኢሜል እና በሶሻል ሚዲያ የት ጠፋችሁ ስትሉን መልስ ያልሰጠናችሁ የእናንተን የውድ ተመልካቾቻችንን ጥያቄ ወደጎን ለመተው አስበን ወይም ችላ ብለን እንዳልሆነ እንድትረዱልን እንፈልጋለን። ኢሳት የሁላችንም ድካም ውጤት ስለሆነ ጉዳዩን በመወያየት በውስጥ ለመጨረስ ስላሰብን እንጂ፤ ነገር ግን ምንም እንኳን ጉዳዩን አሁንም በትዕግስትና በውስጥ ውይይት ለመፍታት እየሞከርን ቢሆንም፥ የአባይ ሚዲያ ቤተሰቦችን ጥያቄና ጭንቀት ከዚህ በላይ በዝምታ ማለፍ ስላልቻልንና ለእያንዳንዱ ጥያቄም በግል ምላሽ መስጠት ስለሚያዳግት ለሁሉም የሚዲያችን ቤተሰቦች እንዲደርስ በማሰብ በመግለጫ መልክ በይፋ ለሁላችሁም መልስ ለመስጠት ተገደናል።
ውድ የኢሳት እና የአባይ ሚዲያ ቤተሰቦች፥
አባይ ሚዲያ በኢሳት ቦርድ ሊቀመንበር በዶ/ር ሰለሞን ረታ የተደረገውን ህገ-ወጥ ክስ ለዩትዩብ ኩባንያ አሳውቆ ለማስነሳት የኢሳት ቦርድ ሊቀመንበሩንም ሆነ የሚዲያ ተቋሙን ችሮታ አይፈልግም። ይሁን እንጂ የኢሳት ቦርድ ይህንን ህገወጥ ድርጊት በመመርመር አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ለቦርዱ በጻፍነው ደብዳቤ አሳስበናል። የኢሳት ቦርድም በጠየቅነው መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ በአፋጣኝ ካልወሰደ ግን በመሰረትነው ሚዲያ የአገሪቱን ህግ እና የዩትዩብን የማህበራዊ ደንብ ተከትለን ህጋዊ እርምጃ የምንወስድ መሆኑን ልናሳወቃችሁ እንወዳለን።
ውድ የአባይ ሚዲያ ቤተሰቦች፥
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የአባይ ሚዲያ ዩትዩብ ቻናል በአስር የስራ ቀናቶች ውስጥ እንደሚከፈት ከዩትዩብ ኩባንያ የተነገረን ሲሆን፥ እስከዛው ድረስ ግን በፌስቡክ አካውንታችንና አዲስ በከፈትነው ዩትዩብ ቻናል
Abbay Media – 2 ልታገኙን የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን  (ከታች ያለውን ሊንክ በመጫን ቻናላችንን ሰብስክራይብ አድርጉ) ላልሰማም በማሰማት ተባበሩን፤
*    *   *
እንዲህ አይነት ትግል ነው የገጠመን ጎበዝ!
 ለማንኛውም በዚህ አይነት ጨዋታ ታጠነክሩን ይሆናል እንጂ አትሰብሩንም!!!
Filed in: Amharic