>
5:26 pm - Saturday September 15, 5066

እንደ ሰሜን እዝ የተካደውና ከጀርባው የተወጋው አባይ ሚዲያ! - (ኤርሚያስ ለገሰ)


እንደ ሰሜን እዝ የተካደውና ከጀርባው የተወጋው አባይ ሚዲያ!
 (በንዴት የተፃፈ)
ኤርሚያስ ለገሰ

የእለቱን የኢትዮ-360° “የዛሬ ምን አለ?” ፕሮግራም የፅሁፍ ዝግጅት የምጀምረው በጠዋት አዳዲስ ነገር መኖርና አለመኖራቸውን ካረጋገጥኩ በኋላ ነው። ከራሳችን የዜና ክፍል ቀጥሎ አዳዲስ መረጃዎች መኖራቸውን ከማረጋግጥባቸው ሚዲያዎች የቅድሚያ ቅድሚያ የምሰጠው አባይ ሚዲያን ነው።
መጀመሪያ “አባይ ማለዳ” ዜናቸውን አዳምጣለሁ። ቀጥሎ በጋዜጠኛ ኑርጀባ የሚዘጋጀውን “መስመር ላይ” እሰማለሁ። በማስከተል በትንታጐቹ ጋዜጠኞች የሚዘጋጀውን “አውድማ” እከታተላለሁ። የአገዛዙን ባህሪ ስለማውቀው አውድማን የምሰማው አንዳንድ ጊዜ በፍርሃት ሌላ ግዜ በስስት ነው።
ፍርሃቴ ስልጣን ያሰከራቸው ፣ አገር ለማውደም የተሰማሩ ዘራፊዎችና ጄኖሳይደሮች የክፋት ሰይፋቸውን ይመዙባቸዋል በሚል ነበር። በስስት የማያቸው ደግሞ በባቢሎናውያን እና እንደ ገብረ-ጉንዳኖች የፈሉ ጩኸታሞች ተደናግጠው ሊያፈገፍጉ ይችላሉ የሚል ስጋት ነበረኝ። ኢትዮጵያን “አሳምኖም ግራአጋብቶም” ለቀማቸው ተነጥፈው የሚሰግዱና የተመቹ ኃይሎች በበዙበት ሁኔታ ስጋቴም፣ ፍርሃቴም ከባዶ የሚነሳ አልነበረም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ላለፉት አራት ቀናት አባይ ሚዲያ ከዩቲዩቡ ፈልጌ የአጣሁት። ይብስ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታቀደበት ውዥንብር ለመፍጠር በሚመስል መልኩ አባይ ሚዲያን በፓርላማ ለመክሰስ መሞከራቸው ሌላ ጥርጣሬ አሳደረብኝ። እርግጥ በሰአታት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለማስተካከል መሞከሩ መጠነኛ እፎይታ የሚፈጥር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይሁን እንጂ ይሄ በራሱ በቂ አይደለም። በሚቀጥለው ጊዜ ጠሚሩ ወደ ፓርላማ ሲመጡ በይፋ ማረጋገጫ መስጠት ይኖርባቸዋል።
በነገራችን ላይ የአባይ ሚዲያን አፈጣጠር፣ ሚዲያው የሌላ ሚዲያ አላማን ለማሳካት ራስን ለማዳከም መወሰኑ፣ ከወደቁበት እንዴት መልሶ ማንሰራራት እንደሚቻል፣ እንደ ጆፌ አሞራ ከጫፍ እስከ ጫፍ አለምን እንዴት በሚዲያ መውረር እንደሚቻል፣ የድል ጥማተኞች እንደለመዱት ባልዋሉበት ሜዳ ሊጠቀልሉትና ፈጣሪው ለመሆን ሲሞክሩ ሚዲያውና ባለቤቱ ዘጠኝ ተከረባብተው በዝረራ ከጨዋታ ውጪ ያወጡበት ገድል ራሱን የቻለ መድብል ይወጣዋል።
በዚህ አጋጣሚ በሚዲያ አማካኝነት እንዴት ማህበራዊ ንቅናቄና ወረርሽኝ መፍጠር እንደሚቻል የሁለተኛ ዲግሪውን መመረቂያ ጽሁፍ ማዘጋጀት ለሚፈልግ ሰው ትክክለኛው ቦታ አባይ ሚዲያ ቢያደርጉ እንደሚያተርፉ ከወዲሁ እጠቁማለው። ድራይቨሩ ግሩም ይልማ (በበረሃ ስሙ አንድነት) ተፅፎ የማያልቅ የማህበራዊ ንቅናቄ ባለቤት ነው።
የሆነው ሆኖ ባለፉት አራት ቀናት አባይ ሚዲያ አየር ላይ የለም። እንደ እኔ ሁሉ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ግራ ከመጋባት አልፈው አዝነዋል። ሁኔታው በጣም ያስደሰታቸው ትላንት ሚዲያውን ለማሳደግ እላይ እታች ሲሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች ዛሬ ደግሞ ማህበራዊ መሰረታቸውን የካዱ ፓራሲቲካል ባህሪ ያላቸው ተደጋፊ ተደማሪዎች ናቸው።
ከጥቂት ሰአታት በፊት ከአንድ የአባይ ሚዲያ የቅርብ አመራር ጋር ለመወያየት ዕድል አግኝቼ ነበር። በሰማሁት ነገር በጣም አዝኛለሁ። ተናድጃለሁ። ምቀኛና ጠላት ከሩቅ አይመጣም እንዲሉ አባይ ሚዲያ የተመታው ከሩቅ አይደለም። እጅግ ልብ የሚያደማው ደግም አባይ ሚዲያ እንደ የመከላከያ ሰሜን እዝ የተካደውና ለእርድ እንዲቀርብ የተደረገው ካርቶን አነጥፎ በመሰረተው፣ የግል ጥቅሜ ይቅር ብሎ ቅድሚያ በሰጠው የሚዲያ ተቋም መሆኑን ነው። ምናልባት አንዳንዶች ባልዋሉበትና ባለቤት ባልሆኑበት የሰሜኑ የጦርነት ድል ሻምፓኝ እየከፈቱ የጨፈሩት በውስጣቸው አባይ ሚዲያ ላይ የጣሉት ግዳይ በመሳካቱ ይሆናል። ደሞም ነው!!
Filed in: Amharic