>

“በደንጎላ ኮሎኔል ማራኪ” እያሉ ሲኩራሩ የከረሙበትን ታሪክ በመናድ የሠራዊት መሪያቸው የሆነን  ኮሎኔል ብቻዋን ማርካ ገድል የሰራችው ጀግና እንስት ወታደር! (አቻምየለህ ታምሩ)

“በደንጎላ ኮሎኔል ማራኪ” እያሉ ሲኩራሩ የከረሙበትን ታሪክ በመናድ የሠራዊት መሪያቸው የሆነን  ኮሎኔል ብቻዋን ማርካ ገድል የሰራችው ጀግና እንስት ወታደር!

አቻምየለህ ታምሩ

ሻዕብያን ተከትሎ  አዲስ አበባ መግባቱን ከጀግንነት የቆጠረው ወያኔ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ስለ ወያኔ ሠራዊት ጀግንነት ያልደሰኮረው ፈጠራና ያልደረተው የጀግንነት ታሪክ የለም። የሻዕብያው ሰላይ ተስፋዬ ገብረዓብ በዋና ደራሲነት የተሳተፈባቸው “ተራሮችን  ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የሚሉ መድበሎችን በመድረስ የወያኔን ጦር 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያፈራው ብቸኛ ሽምቅ ተዋጊ አድርጎ ደስኩሮብናል።
በነገራችን ላይ “ተራሮችን  ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የሚለው የወያኔዎች አገላለጽ ውስጠ ወይራ ነገር አለው።  ወያኔዎች “ተራሮችን  ያንቀጠቀጠ ትውልድ” በሚለው አገላለጻቸው ውስጥ በተራሮች የመሰሉት አማሮችን ነው። በመሆኑም የወያኔን ሠራዊት “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ”  ሲሉ “አማሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ”  ሰራዊት ማለታቸው ነበር።  ሆኖም ግን አማራው ተራራው እንደ ሰንበሌጥ አጎንብሶ ከነበረበት ተነስቶ፤ እንደ በቆሎ ዘር ደርቆ  ከነበረበት በማለምለም መቃብሩን ፈንቅሎ በመውጣት አንቀጠቀጥነው ላሉት ግፈኞች የማይንቀጠቀጥና ተገፍቶ የማይወድቀው ተራራ መሆኑን  አሳይቶ ታሪካቸዉን ቀይሮታል።
ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ሲገባ ከዋሽንግቶን ዲሲ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ የተሾማውና  እንደ ንጉሥ ይቃጣው የነበረው  የሕግ አስተማሪው ፕሮፈሰር ተኮላ ሀጎስም  የወያኔ ጦር ሊወዳደር የሚችለው ከአሜሪካ ጋር ይዋጋ ከነበረው ከደቡብ ቬትናሙ የሽምቅ ተዋጊ ከቪይትኮንግ [Viet Cong] ጋር ብቻ እንደሆነ ይቀድ ነበር።
የወያኔ አለም አጫዋች የነበረው ኢያሱ በርሄም  እንዲሁ በአንድ ዘፈኑ “ብዶንጎላ ኮለኔል ማራኪ” ሲል አቀንቅኗል። ደንጎላ በአማርኛ መኮላ ማለት ነው። እንደኔ የገበሬ ልጅ ላልሆናችሁ መኮላ ማለት ገበሬ ሲያርስ የሚፈነቀለው ወይም ፍንቃዩ ነው። የኢያሱ ዘፈን  ትርጉምም የወያኔ ሠራዊት በመኮላ ኮሎኔል ይማርካል እንደማለት ነው።
ሰሎሞን አስመላሽም  “አጋዚ ኦፕሬሽን”  በሚል ርዕስ በሰራው ፊውም የወያኔ ሠራዊትን ጀግንነትና የፈጸመውን  የተሳካ ዘረፋ በፊልም ቀርጾ ለትውልድ አስተላልፏል።
ሆኖም ግን  እነ ፕሮፈሰር ተኮላ ሀጎስ “ምናልባት  የቪይትኮንግ ሽምቅ ተዋጊዎች ሊወዳደሩት ይችላሉ” ያሉለት፤ እነ ኢያሱ በርሄ በመኮላ ኮሎኔል ይማርካል ሲሉ የዘፈኑለት፤ እነ ተስፋዬ ገብረአብ “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” ሲሉ የጻፉለት፤ እነ ሰለሞን አስመላሽ “አጋዚ ኦፕሬሽን” ብለ ፊልም የቀረጹለት የወያኔ ሠራዊት መሪ የሆነ ኮሎኔላቸው በአንዲት ልጅ እግር እንስት ሽጉጡን እና ማእረጉን ተገፎ፣ ጫማዉን እንዲያወልቅ ተደርጎ ተማርኳል። ያ ሁ ቀረርቶ፣ ያ ሁሉ ፉከራ፣  ያ ሁሉ ጉራ፣  ያ ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ፣ ያ ሁሉ ዳንኪራ የቀረበለት የወያኔ ሠራዊት ምንም እንዳልነበር  ከ17 ዓመታት ሽምቅ ውጊያና ከ27 ዓመታት መንግሥትነት በኋላ በ15 ቀናት ውስጥ በተደረገ ውጊያ  ትጥቁን እየጣለ በፈረጠጠበት የሀፍረት ሽንፈቱ ወደ ታሪክ ገጽ ተቀይሯል።
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ የወያኔ ሠራዊት መሪ ኮሎኔልን  ማርካ ታሪካቸውን ወና ላደረገችውና የታሪክን ገጽ ለቀየረችው ለጀግናዋ እንስት  አርበኛ ገበያነሽ ደባልቄ ይሁን!
Filed in: Amharic