ከሕገ መንግሥት ወይም ከፖሊሲ ብልሽት እንጂ ከአተገባበር ጉድለት የሚመነጭ ችግር በአለም ላይ የለም!
አቻምየለህ ታምሩ
የኦሮሙማው አስኳድ ታዬ ደንደአ “ዋናዉ የሕገ-መንግስታችን ችግር ከይዘት ሳይሆን ከተግባራዊነት ይመነጫል” ሲል ወያኔ 27 ዓመታት ሙሉ “የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለበኝም” በማለት ሲቀልድበት የኖረውን ማስተባበያ ከወደቀበት አንስቶ አቧራውን በማራገፍ ሕይወት ሊዘራበት ሲውተረተር እያየነው ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞች በመንግሥትነት ተሰይመው ምድሩንም ሰማዩንም የኦሮሞ ለማድረግና የኦሮሙማን ፍላጎት ያለገደብ ለማስፈጸም ሲሉ ከሁሉ በፊት ያደረጉት ነገር ቢኖር ሕወሓት 27 ዓመታት ሙሉ ፍላጎቱን ያለ ገደብ ለማስፈጸም ሲጠቀምባቸው የኖሩትን ስልቶችን በጥንቃቄ ማጥናት ነበር። ሕወሓት ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎቱን ያለገደም ለማስፈጸም ሲጠቅምባቸው ከነበሩ ስልቶች መላከል አንዱ ፍላጎቱን ያለገደብ ለማስፈጸም ያወጣቸው ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲያደርሱት የኖሩትን ጉዳት “በአፈጻጸም እንጂ በፖሊሲ ችግር ምክንያት አይደለም” የሚል የብልጣብልጥ መከላከያ ነበረው።
የኦሮሙማ አስኳዶቹ እነ ታዬም ከሁሉ በፊት ያጠኑት የሕወሓት ጥበብ የኦሮሙማን ፍላጎት ያለገደብ ለማስፈጸምና በአስር ወራት ወስጥ በሕወሓት እግር እንዲተኩ ያስቻላቸውን የብልጠት ፖለቲካ ነበር።
እውነቱ ግን “ዋናዉ የሕገ-መንግስታችን ችግር ከይዘት ሳይሆን ከተግባራዊነት ይመነጫል” እንደተባለው ሳይሆን የአተገባበር ችግር ዋናው ምንጭ የሕገ መንግሥት ተብዮው ብልሽት ነው። በአለም ላይ የተደረጉ ጥናቶች ሁሉ የሚያሳዩት የአፈጻጸም ወይም የአተገባበር ችግር ምንጮች የፖሊሲና የሕገ መንግሥት ብልሽቶች ናቸው።
እነ ታዬ ግን የኦሮሙማ ሰልቃጭ ፍላጎታቸውን ያለ ገደብ ጥግ ድረስ ለማስፈጸም የሚጠቅማቸውን የሕወሓት ብልጠት እየደገሙ “ዋናዉ የሕገ-መንግስታችን ችግር ከይዘት ሳይሆን ከተግባራዊነት ይመነጫል” የሚሉን ፍላጎታቸው ያለገደብ የሚፈጽምበት ሕገ መንግሥት ተብዮ ደንብ ከሚቀየር የነሱ ድሎት በኛ መከራ ላይ ተደላድሎ እኛ ከችግሮቻቸን ጋር እየማቀቅን እነሱ ግን ሕወሓት በቆላን ላይ በተራቸው አብዝተው እያሳረሩን ደልቷቸው ተዘባነው እንዲኖሩ ነው።
ማጠናከሪያ:-
የተያያዘው ዶሴ ሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም. የታወጀውን የሽግግር መንግሥት ተብዮው ወቅት የኢትዮጵያ ክልሎች አከፋፈል የያዘ ካርታ ነው። በካርታው ላይ በግልጽ እንደሚታየው ወልቃይ፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የተካለሉት በክልል 1 ወይም በትግራይ ክልል ውስጥ ነው። ልብ በሉ! ይህ ካርታ በሽግግር መንግሥት ተብዮው የታወጀው ሕገ መንግሥት ተብዮው ከመታወጁ ከሶስት ዓመታት በፊት ነው። ለዚህም ነው ሕገ መንግሥት ተብዮው ከመታወጁ ከዓመታት በፊት በትግራይ ክልል ስር የተካለሉት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ ጉዳይ በትግራይ ክልል ስር ከተካከሉ ከዓመታት በኋላ የታወጀውን ሕገ መንግሥት ተብዮ ደንብ መሰረት አድርጎ በተቋቋመ የወሰንና ማንነት ኮሚሽን ሊታይ አይገባውም የምንለው።