>
10:12 pm - Thursday February 2, 2023

ዳዊት ከበደ እና ዳዊት ከበደ (በዳዊት ከበደ ወየሳ)

ዳዊት ከበደ እና ዳዊት ከበደ

(በዳዊት ከበደ ወየሳ)

እስክንድር ነጋ ያለሃጢያቱ በታሰረበት አገር ላይ ሆነን፤ የአውራ አምባው ዳዊት ከበደ ባህታ መታሰር ምንም እንደማለት ሊሆን ይችላል። አሁንም እውነት እንመሰክራለን። የእስክንድር ነጋን ጉዳይ በምንም የህግ ሚዛን ላይ ብንመዝነው፤ ሊያሳስረው የሚገባ፤ ህጋዊ መሰረት የለም። በዚህ የህግ ልእልና ላይ ሆነን… የእስክንድር እና የዳዊት ከበደ የእስር ጉዳይ ለንፅፅር የማይበቃ መሆኑን አምነን ነው የዳዊት ከበደ ባህታን መታሰር ጉዳይ የምናወጋው። በእርግጥ ከሁለቱም ጓደኞቼ ጋር  በሙያ አጋርነት ተርታ አብረን ተሰልፈናል። እስክንድር እስከመጨረሻው ባመነበት ጸንቶ፤ ወያኔን በብዕሩ ተዋግቶ ታሰረ። ዳዊት ደግሞ ያዝ ለቀቅ በሚያደርገው ብዕሩ ከኛም ከወያኔም ሳይሆን፤ መሃል መሃሉን ሲጫወት ቆይቶ ወህኒ ገባ። ድሮ ላይ ዳዊት በሚያሳትመው “አውራ አምባ” ጋዜጣ ምክንያት፤ ወያኔ ለእስር ሲዳርገው፤ ለሁሉም የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች በጮህንላቸው ልክ፤ ለዳዊትም ጮኸንለታል። ከእስር ከተፈታ በኋላ፤ ከባልደረባዬ ክንፉ አሰፋ ጋር ተነጋግረን አውራ-አምባ ጋዜጣ በEMF ድረ ገጻችን ላይ ሰፊ የቦታ ሽፋን እንዲሰጠው አድርገናል። ለCPJ “ምርጥ ጋዜጠኛ” ተብሎ ከመታጨት ጀምሮ፤ እስከሽልማቱ ድረስ ከጀርባው በውጭ አገር የምንገኝ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እጅ ነበረበት። የCPJን ሽልማት ለመቀበል ወደ አሜሪካ ሲመጣ… እግረ መንገዳችንን ትልቅ አቀባበል አደረግንለት። እናም በዚህ አጭር ጽሁፍ ስለሞክሼዬ የማውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች ለማለት ሳስብ፤ ‘ይህንንም ቢሆን እኔ ካላወራሁ ማን ያወራል?’ በሚል ስለሆነ፤ እስከመጨረሻው በትዕግስት ያንብቡ።
*     *     *
ሰሞኑን ነው። ሰይጣን በህወሃት መንደር ሲያልፍ ድርጊታቸውን አይቶ፤ “ፑፍ እኔን ብሎ ሰይጣን!?” በማለት ወደመጣበት መመለሱን ሰምተን ፈገግ ብለን ነበር።
ሰይጣን ልጅ አስቸገረው አሉ። ከዚያም ጠራውና…
“አንተ ልጅ ጥፋትህ በጣም እየበዛ ነው።” አለው። ትንሹም ሰይጣን አንገቱን ደፍቶ የአባቱን ተግሳጽ መስማቱን ቀጠለ። አባት ሰይጣን፤ የልጁን ጥፋት ከዘረዘረለት በኋላ፤ የጥፋቱ መብዛት ለራሱም ቢገርመው ጊዜ… “እኔ የምለው ግን” አለው ትንሹን ሰይጣን ቆጣ ብሎ።
“ጸባይህ በጣም ተቀይሯል። ከወያኔዎቹ ጋር መዋል ጀመርክ እንዴ?” በማለት ልጁን ትኩር ብሎ አየው። በዚያውም አዲስ ሃሳብ መጣለት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፤ ትናንሾቹን ሰይጣኖች በዲያቢሎስነት ማሰልጠን ሲያስፈልግ ወደ ህወሃት መንደር ለመላክ፤ ከሳጥናኤል ጋር ምክክር ተጀምሯል አሉ። እኛም እንደታዘብነው ከሆነ፤ እንኳንስ ፀበል ፀዲቁን ቀምሰው በህወሃት ስም የሚያማትቡት ሰዎች ቀርተው፤ በህወሃት መንደር ያለፉትም ጭምር ጸባያቸው ሲቀየር አይተን ማዘናችን አልቀረም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ… በማለት፤ ስለወዳጃችን ዳዊት ከበደ ባህታ ትንሽ እንጨዋወት። ዳዊት ከበደን የኔን ያህል ወይም ከኔ በተሻለ መልኩ የሚያውቁት፤ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች በአገር ቤትም በውጭም ሊኖሩ እንደሚችሉ አምናለሁ። ለዚህም ነው የዳዊት ከበደ መታሰር ሲሰማ በገደምዳሜ ዜናውን ሰሩት እንጂ፤ ጨክነው በብዕር ጫፍ አላደሙትም። አንዳንዶች ደግሞ ከምንጨክንበት ይልቅ፤ የምንጨነቅለት ጉዳይ በዝቶብን ይሆናል።
ከአስር አመታት በፊት… በውጭ አገር ስንሰራ ከነበርነው ጋዜጠኞች መካከል ደግሞ፤ እኔን ጨምሮ፣ ክንፉ አሰፋ፣ ሔኖክ አለማየሁ ወይም ሌሎቻችን ለዳዊት ከበደ “አውራ አምባ” ጋዜጣ ትልቅ ስፍራ ሰጥተን በአውደ መረቦቻችን ላይ አስተናግደነዋል። እኛ በEMF ላይ ሳምንታዊ ህትመቱን እንለጥፋለን፤ በአገር ቤት ደግሞ የራሱ አንባቢዎችን አፍርቷል። የጋዜጣውን ተወዳጅነት ይበልጥ ከፍ ያደረጉት ደግሞ፤ እነአበበ ቶላ (አቤ ቶኪቻው)፣ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና፣ ውብሸት ታዬን የመሳሰሉ ትንታግ የጋዜጣ ብዕረኞች መኖራቸው መሆኑ አይዘነጋም። ከዚያ በተጨማሪ እነሰርካለም ፋሲል፣ እስክንድር ነጋ፣  እነሲሳይ አጌና፣ ፋሲል የኔአለም፣ እነደረጀ ኃብተወልድ እና ሌሎችም ጋዜጠኞች አብረውት በቃሊቲ እስር ቤት የወያኔን ቀንበር የተሸከሙ ናቸው። እናም ምን ለማለት ፈልገን ነው…
የአውራ አምባው ዳዊት ከበደ  ወደ ህወሃትን መንደር ጠጋ ከማለቱ በፊት፤ እንደኛው ተቃዋሚ ሆኖ ሰርቷል። ችግሩ እየጎላ የመጣው ከነሱ ጋር ውሎ የነሱን ጸበል መረጨት ጀምሮ፤ “በቅርቡ የህዳሴውን ግድብ የሚያስረሳ ርዕስ ይመጣል። ካላመናቹህ እንወራረድ!” ባለ ማግስት የሐጫሉ ሁንዴሳ መገደል፤ ሁላችንንም አስደምሟል።
በአንድ ወቅት… አገር ቤት እያለ፤ ከብርሃነ መዋ ጋር ተያይዞ ያተመውን ጋዜጣ ድረ ገጻችን ላይ በለጠፍን ማግስት፤ አንባቢዎች ጠንከር ያለ የተቃውሞ አስተያየት ድረ ገጻችን ላይ ይጽፋሉ። አንዳንዶቹ “አንተ ወያኔ” ሲሉት፤ ሌሎች ደግሞ በትግሬነቱ ዘር ጠቅሰው ጎሻሸሙት። ዘር ጠርተው መሳደባቸው ትክክል ባይሆንም፤ የዳዊት ከበደ ውሳኔ ደግሞ ሁላችንንም ያስደነገጠ ነበር። “…በመሆኑም ከሚቀጥለው ሳምንት በኋላ የጋዜጣችን ህትመት በናንተ ድረ ገጽ ላይ የማይወጣ መሆኑን…” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ላከልን። በኋላ ላይ እኔም ክንፉም ደውለንለት ነገሩን ለማብረድ ሞከርንና እንደገና በሙያ ተወዳጀን።
እዚህ ላይ ለመጥቀስ የፈለግነው፤ ከሁሉም ነገር በላይ የዘር ነገር ሲነሳ ዳዊት ከበደ በጣም ስሱ መሆኑን ነው። ይህ መጥፎ ጸባይ ነው እያደገ ሄዶ፤ ከኛም ከሁላችንም የሚለይበትን አቋራጭ መንገድ የፈጠረለት። በደህናው ጊዜ… ዳዊት ከበደ ባህታ ወደ አሜሪካ ሲመጣ፤ ከኔ ዘንድ አርፎ ስለነበር የሆድ የሆዱን ለመጨዋወት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረልን። ከአስተዳደጉ ጀምሮ ወደ ጋዜጠኝነት እስከገባበት እና ስለ ቃሊቲ እስር ቤት ቆይታው ብዙ ተጫዋውተናል። አያቶቹ እነ አቶ ባህታ… የመለስ ዜናዊ አባት፤ ዜናዊ አስረስ ሲያገባ፤ በአገር ባህል ደንብ መሰረት… በአቶ አስረስ ወገን ሆነው ለጋብቻ ሽምግልና መላካቸውን… የመሳሰሉትን ወፍ በረር ጨዋታዎችን ጭምር አውግተናል።
እናም ልክ የዛሬ አስር አመት ነገር ግን በኖቬምበር ወር፤ ዳዊት ከበደ በ CPJ ታጭቶ ሽልማት ለመቀበል ወደ አሜሪካ ሲመጣ፤ በውጭ አገር የነበርን የነጻው ፕሬስ አባላት ደስታው ለኛም ጭምር በመሆኑ አቀባበላችን ደመቅ ያለ ነበር። ከሽልማቱ በኋላ… ዳዊት ከበደ ሚዲያውን ወክሎ በአሜሪካ ከተሞች ልዩ ልዩ ጉብኝት እንዲያደርግ መስመር ስንዘረጋ፤ ዲሲ፣ ሲያትል፣ ላስ ቬጋስ፣ አትላንታ እና ዳላስ በዋናነት እቅዳችን ውስጥ ገቡ። እኔ ወዳለሁበት አትላንታ ከተማ እንዲመጣ የደርሶ መልስ አየር ቲኬቱን አዘጋጀንና አትላንታ መጣ።
አትላንታ መጥቶ… ምሽት ላይ እነጋሽ ቸሩን ጨምሮ የከተማው ትላልቅ ሰዎች፤ በተለይም የቀድሞ በአትላንታ ከፍተኛ የቅንጅት አመራሮች በተገኙበት፤ ከሌሎችም ጓደኞቼ ጋር በመሆን የእራት ግብዣ ተዘጋጀ። ከዋናው ዝግጅት በፊት ግን ሌላ ወሬ ተጀመረ። የህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ነገር ተነሳና ስለኢትዮጵያ የወደፊት ጉዳይ ስናወራ፤ የግል አስተያየቴን ሰጠሁ። በአጭሩ… “አንቀጽ 39 ተግባራዊ ይሁን ቢባል አስቸጋሪ እንደሚሆን፤ ‘ይሁን’ ቢባል እንኳን፤ አደሬው ተገንጥሎ ያለሱማሌውና ኦሮሞው ህብረት ዘላቂ ማህበረሰብ እንደማይኖረው፤ ኦሮሚያ ቢገነጠል ደግሞ አምስት ቦታ እንደሚከፋፈል፤ ትግራይ እና አማራ እንገንጠል ቢሉ ደግሞ፤ ያልተመለሰው የወልቃይት እና የራያ ጉዳይ ደም እያፋሰሰ ምድሪቱ አኬልዳማ እንደምትሆን በዝርዝር ተናገርኩ።” በኔ ሃሳብ የተስማሙም ያልተስማሙም ሰዎች ነገሩ። ሞክሼ ዳዊት ከበደ ግን በዝምታ ከማዳመጥ ውጪ ምንም ምላሽ አልሰጠም። የሆኖ ሆኖ የግብዣውን መንፈስ ላለመረበሽ ርዕሰ-ጨዋታውን ስለሚዲያ አደረግንና ዳዊትም የራሱን ልምድ እና ገጠመኝ ሲያወጋን አመሸ።
ለሊት ላይ እቤት ገብተን፤ በንጋታው ቁርስ እየበላን ሳለ፤ ዳዊት አንድ ነገር በትህትና አነሳልኝ። “ትላንት ማታ ስለወልቃይት ስታወሩ በነበረው ጉዳይ ጣልቃ መግባት አልፈለኩም እንጂ…” አለና ትግራይ በወልቃይት ላይ ሊኖራት ስለሚገባው የባለቤትነት ጉዳይ አወጋኝ። እኔ ደግሞ ታሪክ እያጣቀስኩ፤ ስፍራው በጥንት ጊዜ ስሜን ቤጌምድር ይባል እንደነበርና ራሱን ችሎ ይተዳደር እንደነበር፤ አስተዳዳሪዎቹን… ከነገስታቱ እስከ ፊታውራሪ ጎላ፤ ከዚያም ስለደጃዝማች አያሌው ብሩ፣ ስለነቢትወደድ አዳነ ታሪክ አጫወትኩት። የትግራይ ገዢ የነበሩት ራስ መንገሻ ስዩም ሳይቀሩ፤ የትግራይ ክልል ከተከዜ መልስ መሆኑን መመስከራቸውን እያወጋን ሳለ፤ የETHIO Tube አዘጋጅ የሆነው አለማየሁ ገመዳ የቤታችንን በር አንኳኳ። እናም በወልቃይት ጉዳይ ያደረግነው ጭውውት ሳይቋጭ አስር አመታት አልፈው፤ ወልቃይትም የጦር አውድማ ሆና “ነግረንህ ነበር” ለማለት እንኳን ጊዜ ሳናገኝ፤ ሞክሼ ለመታሰር በቃ።
ከዚህ በኋላ የሆነው ነገር እንዲህ ነው። ሞክሼ ከአትላንታ በኋላ ወደ ዲሲ አልነበረም የተመለሰው። አሪዞና የሚገኘው ወንድሙ የህወሃት ደጋፊ መሆኑን ስለሰማሁ፤ “አደራ አሪዞና ሄደህ እንዳትቀየር!” ስለው፤ “እኔ መቀየር ቢኖርብኝ ድሮ እቀየር ነበር። ቃሊቲ እስር ቤት የምሰቃይበትም ምንም ምክንያት አልነበረም” ሲለኝ በሙሉ ልቤ አመልኩት። ሆኖም ከአሪዞና በኋላ ወደ ሲያትል ሲሄድ፤ በኋላም ሲያትል ከሚገኘውና የትግራይ ልጅ ከሆነው የኢትዮ ሚዲያ ባለቤት፤ አብርሃ በላይ ጋር ሲቀያየሙ፤ በሁለቱ መካከል የነበረውን ልዩነት እና ግጭት በሽምግልና እርቅ ለማውረድ፤ ሁለቱንም ወገን አነጋገርኳቸው። ነገሩ በሰላም ቢፈታም በሞክሼ ዳዊት ከበደ ላይ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዲኖሩኝ ሆንኩ። ይህም ሁሉ ሆኖ ሞክሼን በወያኔነት ገና አልፈረጅኩትም።
በመሃል ብዙ ነገር ሆነ። ዳዊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ፤ የስራ ባልደረቦቹ አቀባበል አደረጉለት። እኛ በውጭ አገር… በሌለንበት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶብን ስለነበር፤ ወደ አገር ቤት የመሄድ ነገር የሚታሰብ አልሆነም። እናም “ዳዊት ከበደ አገር ቤት ገባ” የሚለው ዜና ሲወጣ፤ አገር ቤት የሚገኙ የድሮ ጓደኞቼ፤ በስመ-ሞክሼ… እኔ የተመለስኩ መስሏቸው ደስታቸውን ለቤተሰብ ገልጸውላቸው ነበር። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ አሁን በማላስታውሰው ነገር ታሰረ። እናም የመታሰሩ ዜና ሲሰማ፤ አሁንም በስመ-ሞክሼ “አርፎ አሜሪካ አይቀመጥም? ምን አንቀለቀለው? እንኳንም ታሰረ።” የሚሉ አስተያየቶች ከዚህም ከዚያም ይሰነዘሩ ጀመር። በስመ ዳዊት ከበደ አንዳንድ የሚያስቁ ገጠመኞችም ነበሩኝ። ቦታው ስላልሆነ እሱን በመዝለል ወደ ቁምነገሩ ልውሰዳቹህ።
ሞክሼ ወደ አገር ቤት ከሄደ በኋላ ዳግም ወደ አሜሪካ ሲመጣ፤ አንዳንድ ሃሳቦችን ሰንቆ ነበር። በኋላ ላይ በሰፊው እንዳወራነው፤ ኢሳት ቲቪ ውስጥ ገብቶ መስራት ቢፈልግም የተገለለ መሆኑን አጫወተኝ። እንዲያውም ይህንኑ ሃሳብ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በሰፊው ተወያይተውበት፤ ነገር ግን ኢሳት ተጨማሪ ሰራተኛ ለመቅጠር በቂ ገንዘብ እንደሌለው፤ በሌላ ጊዜ ግን ሊቀጠር እንደሚችል ተስፋ ተሰጥቶት እንደነበረ… ነገር ግን እሱ እንደሚለው ከሆነ፤ “እኔ ካሁን አሁን ኢሳት ላይ እሰራለሁ ብዬ ስጠብቅ፤ ሳይጠሩኝ ቀሩ። በመሃል ተቦርነ ከአገር ቤት መጣ። ከኔ በኋላ ነው የመጣው። ነገር ግን…” አለና አስደንጋጩን የብሔር ካርድ መዘዘ። “ነገር ግን እኔ ትግሬ ስለሆንኩ…” አለና ምሬቱን አወራኝ። ላባብልም፤ ላስተባብልም ሞከርኩ። ማምረሩን ሳውቅ ግን ተውኩት።
ቀጥሎም በውጭ አገር ስለሚገኘው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ስናወራ፤ ጨዋታ መሃል… “እኔ እኮ አገር ቤት ገብቶ መስራቱ ነው የሚሻለኝ። ግፋ ቢል በረከት ስምኦን ያሰመረውን ቀይ መስመር አለማለፍ ነው ከኔ የሚጠበቀው” ሲለኝ ልቡ እየሸፈተ መምጣቱን ጠረጠርኩ።
እንዲያውም የውጭውን እንቅስቃሴ ካየ በኋላ፤ “አንድ የተረዳሁት ነገር አለ።” በማለት ለአንድ ጓደኛችን አጫወተው።
“ምን?” ቢለው ጊዜ…
“ትግሬ ሆኖ ተቃዋሚ መሆን አይቻልም።” የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱን ነገረው። ይሄም ሌላ አስደንጋጭ ቦንብ ነበር።
ነገሩን በትኩረት ካየነው፤ ይሄ ሰው ሁለት ያጣ ሆነ። በአንድ ወገን ዲያስፖራው ያደመበት እንደሆነ ተሰምቶታል። በሌላው ወገን ደግሞ ወያኔዎቹም ሙሉ ለሙሉ አምነው አላስጠጉትም። እንዲያውም አንድ ጊዜ፤ አንድ ትልቅ ስብሰባ ተጠርቶ በር ላይ ፍተሻ ይደረጋል። ፈታሾቹ የራሱ አገር ሰዎች ወያኔዎች ናቸው። ማሽኑን ወደ ዳዊት ጭንቅላት አስጠግቶ፤ “እዚ ማሽን ሃንጎልካ ኸትፈትሾ ጽቡቅ ነይሩ።” አለው። በአማርኛ “ይሄ ማሽን ያንተን ጭንቅላት ቢፈትሽ ጥሩ ነበር” አለው። ይህን ሲነግረኝ፤ ወያኔዎቹ ምን ያህል እንደማያምኑት ለመግለጽ ፈልጎ ነው።
እናም ወያኔዎቹም ቢሆኑ፤ ዳዊትን ለጥቅማቸው ካልሆነ በስተቀር የሚፈልጉት ሰው አልሆነም። ለምሳሌ አንድ ወቅት ላይ እንዲህ ሆነ። መከላከያ ዶክመንተሪ ፊልም ለመስራት ጨረታ አወጣ። የዳዊት አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ጨረታውን ቢያሸንፍም፤ የድሮው ethiopiafirst ወይም ያሁኑ ድሬ ቲዩብ ባለቤት (ቤን)… የአውራምባው ዳዊት ከኢሳት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ለመከላከያ ሃላፊዎች አሳይተው፤ “ዳዊት ማለት የግንቦት ሰባት ደጋፊ ነው” ብለው፤ ያሸነፈውን ጨረታ ከእጁ ፈልቅቀው ወሰዱበት።
ወደኋላ ተመልሼ አንዳንድ ነገሮችን ሳስብ ይገርመኛል። ዳዊት ከዲያስፖራው ጋር ሆኖ፤ የውጭውን ፖለቲካ ማራመድ አልቻለም። ሆኖም በወቅቱ ከውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት መመስረቱን አንዘነጋም። በኋላ ላይ የጋዜጣው ስራ ሲቀዘቅዝ… በተለይ ለሱማሌ ክልል ለነአብዲ ኢሌ መግለጫዎችን በማውጣት፤ ጽሁፎችን በማዘጋጀት ያግዛቸውና እነሱም ጠቀም ያለ ገንዘብ ይከፍሉት ነበር። እዚህ ላይ መጥቀስ የማያስፈልጉ የቤት እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን የማግኘቱን ነገር ስንደማምረው፤ በእርግጥም ዳዊት ከበደ ባህታ ቀስ በቀስ ወደ ጁንታው መንደር እየተጠጋ መምጣቱን አይተናል።
በመጨረሻ ግን እንዲህ ሆነ። 2013 ላይ… አውራ አምባ ታይምስ ያልታሰበ ሰበር ዜና ለቀቀ።
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአባላቱ ጋር ያደረጉትን የስልክ ስብሰባ መሰረት አድርጎ፤ በድምጽ የታገዘ ዜና ሰራ። ይህ ሰበር ዜና በአገር ቤት እና በውጭ ያለነውን ሰዎች አነጋገረ። ዜናው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለግንቦት 7 ትግል ብዙ ሚሊዮን ብር ወይም በአሜሪካ ስድስት ዲጂት የሆነ ዶላር ማግኘታቸውን የሚገልጽ ነበር። በዚያኑ ሰሞን በበጋው ወር… የሰሜን አሜሪካ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ፌስቲቫል ላይ ለመታደም ዲሲ ከትመናል። እኔ፣ ክንፉ እና ሞክሼ በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር ከአንድ ካፌ ቁጭ ብለናል። ዳዊት ይህን ዜና በምን መልኩ ሊለቀው እንደቻለ፤ የተጋጋለውን ሰላማዊ ትግል ሊያቀዘቅዝ እንደሚችል ደጋግመን ለሞክሼ እንነግረዋለን… ከሙያ አንጻር ምናምን እያልንም ለመምከር እንሞክራለን። ለካስ መስሚያው ጥጥ ሆኖ፤ ምንም ግን መግባባት አልቻልንም። ከዚህ ውይይት በኋላ፤ ከዳዊት ከበደ ባህታ ጋር በተለያየ የፖለቲካ ምህዋር ላይ መሆናችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ተገነዘብኩ። ከዚያች ምሽት በኋላ ዳዊት ከበደ ባህታን ዳግም ሳላገኘው …በዚያው ተለያየን…. በዚያው ታሰረ – ያሳዝናል።
አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁና በዚሁ እንሰናበት። ደግነቱ በሁለታችን ዳዊቶች መካከል ያለውን ብዥታ ለማስተካከል ስል፤ በስሜ ላይ የአያቴን ስም ጨምሬ መጠራት ከጀመርኩ ሰነባብቼ ነበርና… በዚያው ሳምንት 2013፣ ዲሲ ላይ በተደረገው የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰብ ላይ ተገኘሁ። ወደ አዳራሹ ለመግባት ስቃረብ፤ አንድ ወገን ላይ ሰብሰብ ብለው የቆሙ ሰዎች፤ ድንገት ወደ’ኔ ዞር ብለው ማየት ጀመሩ። ለካስ “ዳዊት ከበደ መጣ” ሲባል፤ የአውራምባው ዳዊት ከበደ መስሏቸው፤ እንደግስላ ተቆጥተው ኖሯል ወደኔ ያፈጠጡት። እናም ወደነዚህ ሰዎች ስጠጋ ታማኝ በየነም አብሯቸው ነበርና… ለሰላምታ ተጠጋኋቸው። (ታማኝ አንድ አሳሳቅ አለችው) ያቺን ሳቅ እየሳቀ፤ ግን ደግሞ ጮክ ብሎ፤ “አንተ ሰውዬ በደህና ጊዜ… የአያትህን ስም አስገብተህ ዳዊት ከበደ ወየሳ መባልህ ጠቅሞሃል” ሲል፤ እዚያ የተሰበሰቡ ሰዎች ፊት ፈገግ፤ የተኮሳተረ ግንባራቸውም ፈታ ሲል አየሁ። እናም ይሄም፤ በስመ ሞክሼነት ካጋጠሙኝ ነገሮች እንደ አንዱ ይመዝገብልኝ።
ወያኔ ፈርጀ ብዙ ጦርነት ከከፈተ በኋላ፤ ዳዊት ከበደ ድምጹን አጥፍቶ ነበር የቆየው። ሆኖም ከወልቃይት ወጥተው ሱዳን የገቡት ሰዎች ብዙዎቹ፤ ህጻናትና ሴቶች ሳይሆኑ ወጣቶች መሆናቸውን ዶ/ር አብይ ሲገልጹ፤ ሞክሼ ደግሞ ሌላ መረጃ ጠቅሶ እንዲያውም ብዙዎቹ ስደተኞች ህጻናት እና ሴቶች ናቸው በሚል አይነት የጠቅላይ ሚንስትሩን አባባል ፉርሽ ለማድረግ ትዊት አደረገ። ሞክሼ እዚህ ላይ ነጥብ ጣለ። ከዚያም በንጋታው ታሰረ። ይኸው ነው። ይህ ጉዳይ ለመታሰር ያበቃል ወይም አይበቃም የሚለውን ለህግ እንተወውና በዚያው ወደ ማጠቃለያዬ ላምራ።
ባለንበት ዘመን ብዙ ሰዎችን ታዝበናል። ቀድሞውኑም የህወሃት ደጋፊ የሆኑ፤ ምንም ተፈጠረ ምን ከደጋፊነታቸው ወደኋላ የማይሉ ጁንታዎች አሉ። በአገር ውስጥ እና በውጭ ግልገል ወያኔዎች አሉ፤ ገና ለወደፊት ያልፍልናል የሚሉ ተስፈኛ ጁንታውያንም አሉ። እንደዳዊት ከበደ ባህታ አይነት ደግሞ… ከሁለቱም ሳይሆኑ፤ ፈራ ተባ እያሉ ለእስር የሚበቁ ሰዎች አሉ – ይሄም ያሳዝናል።
የሚገርመው ነገር… ድሮ የአውራ አምባው ዳዊት ከበደ ሲታሰር፤ በኢትዮጵያዊነቱ በጋራ ድምጻችንን እናሰማለት ነበር። ያን ጊዜ እኛ ስንጮህ ይስቁብን የነበሩ ሰዎች፤ አሁን ደግሞ ጊዜው ተቀይሮ “የዳዊትን መታሰር ሲቃወሙ እና ፔቲሽን ሲያዞሩ አይተን “ወይ ጊዜ” ማለታችን አልቀረም። አንድ ነገር ታወሰኝ። በአንድ ወቅት ዳዊት ከበደ በጻፈው ጽሁፍ ምክንያት ውዝግብ ተነሳና፤ መቼም “ስም ያለው ሰው ሞኝ ነው” አሁንም ጉሽሚያው በዛ። በመጨረሻ ዳላስ የሚገኝ ሬዲዮ አዘጋጅ አቶ ዘውገ ደውሎ፤ “ልዩነት እና አንድነታችሁን ለአድማጮች ግለጽልን” በማለት ጋበዘኝ። ያን ጊዜ “ሁለታችንም ተመሳሳይ ስም እና ተመሳሳይ ሙያ አለን። ሁለታችንም በኢትዮጵያ ከተለያየ ብሔር ብንገኝም፤ በኢትዮጵያዊነት ግን አንድ ነን።” የሚል ምላሽ ሰጥቼ ነበር።
አሁን ላይ ሳስበው… እንደጁንታው እቅድ ሆኖ፤ አገር ቢተራመስና ወያኔ እንደገና ስልጣን ላይ ቢወጣ፤ የዳዊት ከበደ ባህታ አቋም ሌላ ሆኖ፤ ልዩነታችን ጎልቶና የሚያመሳስለን ነገር ጠፍቶ “የነበረው እንዳልነበር” ሊሆን እንደሚችል ሳስብ ውስጤን ያሳዝነዋል። የሰው ልጅ እላይ ደርሶ፤ በገዛ እጁ ቃሊቲ ደጃፍ ላይ ሲፈጠፈጥ ማየት ልብ ይነካል። ዳዊት ከበደ ባህታ በብዙ ጽሁፎቹ እና አነጋገሩ አናዶኛል። እኔን ስላናደደኝ ግን “ይታሰር” አልልም። ባልጠፋ ሰው እነጄነራል ጻድቃን፣ ደብረጽዮን ስብሐት ነጋ እና ከሌሎችም የህወሃት ባለስልጣኖች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። አንድም ቀን ጠንከር ያለ ጥያቄ ሳይጠይቅ፤ እንዲሁ በገደምዳሜ እሹሩሩ እንዳላቸው እሱም እስር ቤት ገባ፤ እነሱም ሊከተሉት ነው – ይሳዝናል።
አዎ በውስጣችን ፈሪሃ እግዚአብሔር ስላለ፤ የነዳዊት ከበደ ባህታ መጨረሻ ያሳዝነናል። እኛ ኢትዮጵያዊያን እኮ የምንገርም ፍጡራን ነን – እንዲህ አይነት ርሑሩህ ልብ ያለን መሆናችን በራሱ ያሳዝናል – እኛም እናሳዝናለን። የኢትዮጵያ አምላክ ከኛ ጋር ይሁን!!
Filed in: Amharic