>

የፌስቡኳ ‹‹ኢትዮጵያ›› ...!!! (እውነት ሚድያ)

የፌስቡኳ ‹‹ኢትዮጵያ›› …!!!

እውነት ሚድያ 

ፌስቡክ ላይ ያለችዋ ‹‹ኢትዮጵያ›› በተጨባጭ ምድር ላይ፣ በአፍሪካ ቀንድ ምሥራቃዊ አቅጣጫ ካለችዋ ኢትዮጵያ በእጅጉ ትለያለች፡፡ እንደ እውነቱ ከኾነ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በእውን የሌለች፣ የራሳቸውን ሌላ ኢትዮጵያ ፈጥረው የሚኖሩ እስኪመስል ድረስ ጉልኅ ልዩነቶች እየታዩ ናቸው፡፡ ለዚህም ማንም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ኹሉ ሊታዘብና ሊመሰክር የሚችላቸው ተጨባጭ ማሳያዎቸ አሉ፡፡ ‹‹ለመኾኑ ፌስቡክ ላይ የምናስተውላት፣ ምናባዊቷ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች?›› የሚለውን ስንታዘብ፡-
➊ ‹‹ተምሬአለኹ›› ከሚሉት ፕሮፌሰሮች ጀምሮ ፊደል በወጉ እስካልለዩት ማይሞች ድረስ ኹሉም በእኩልነት የሚያወሩባት፤ እንዲያውም አዋቂና ትኁታን ዜጎቿ ዝም ብለው አላዋቂዎቹ ደፋር ዜጎቿ ‹‹የክብር እንግዳ›› እና የመድረክ ፊታውራሪዎች የኾኑባት፣ እልፍ ተከታዮችንም ያፈሩባት ናት!
➋ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉባት ሳትኾን ራሳቸውን ‹‹የሀገሪቱ አውራ ነን›› ብለው የሾሙ ሦስት ብሔሮች ጡንቻቸውን (የበላይነታቸውን) ለማሳየት የሚራኮቱባት፤ በዚኹ ምክንያትም ሦስት የተለያዩ ‹‹ብሔራዊ›› ሰንደቅ ዓላማዎች ያሏት ናት!
➍ አክቲቪስቱ ከሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም በላይ የጦር ግንባርን የሚመራባት፣ ‹‹ሰበር ዜና›› በሚል መሣርያ ጠላቶቿን የሚደመስስላት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀድሞ ጦርነቱ ‹‹በድል መጠናቀቁን›› የሚያውጅላት ዕድለኛ (¡) ሀገር ናት!
➎ ዜጎቿ ኹሉ በስድብ የተመረቁ እስኪመስሉ ድረስ፣ ‹‹የሃይማኖት መምህራን ነን›› የሚሉቱ ጭምር ከሐሳባቸውና አቋማቸው በተቃራኒ የቆመን ሰው ኹሉ ከፍ ዝቅ እያደረጉ የሚያዋርዱባት፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገሪቱ መሪዎች ሳይቀሩ ጸያፍ በኾኑ ቃላት የሚብጠለጠሉባት ናት!
➏ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በዋናነት የተመሠረተው በግብርናው ዘርፍ ላይ ኾኖ ሳለ፣ የዜጎች ሕልውናም በአርሶና አርብቶ አደሩ ጫንቃ ላይ ማረፉ እየታወቀ፣ በአንጻሩ ጣታቸው የሞባይልና ኮምፒዩተር ስክሪን እንጂ እርፍ ጨብጦ የማያውቅ ዜጎቿ ሞያው የውርደት ምልክት ይመስል ‹‹ገበሬ!›› በሚል ቃል የሚነቃቀፉባት ናት!
➐ ራሳቸው የባሩድ ሽታ በማያገኛቸው ቅንጡ ቦታዎች ተቀምጠው፣ ልጆቻቸውንም ደረጃውን በጠበቀና ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ (ሀገር) ልከው እያስተማሩ፣ የገመጡትን በርገር በውስኪ እያወራረዱ ቆሎ እንኳን በልቶ ማደር ያቃተውን ድሃ ወጣት ‹‹ተነስ! ተሰለፍ! መንገድ ዝጋ! ወደ መንግሥት ታጣቂዎች ድንጋይ ወርውር!›› እያሉ የሚቀሰቅሱ፤ ወደ እሳት ከማገዷቸው፣ የጥይት ሲሳይ ካደረጓቸውና የወላድን አንጀት ካቃጠሉ በኋላ ደግሞ በፍጥነት የሐዘንና የውግዘት መግለጫ የሚያንጋጉ ግፈኞች የተበራከቱባት ናት!
➑ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በባህርና በአየር ጥለዋት ከተሰደዱ በኋላ፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻቸውን ኹሉ ረስተው በምዕራባዊ ባህልና አኗኗር ተመሰቃቅለው እያለ፣ ኾዳቸውን ለመሙላት ሲሉ የሞላ ታሪካቸውን ካጎደሉና ክብራቸውን ካቃለሉ በኋላ ‹‹ያለ እኔ ኢትዮጵያዊ የለም! ሀገሪቱ የቆመችው በእኔ ተጋድሎና መሥዋዕትነት ነው! ሀገሬን ከማንምና ምንም አብልጬ እወዳታለኹ!…›› እያሉ በሚደነፉ ዲያስፖራዎች የተሞላች ናት!
➒ ለሞት ሲያጣጥር ያዩት ወገናቸውን ነፍስ ፈጥነው ከመታደግ ይልቅ ስለ ጻዕረ ሞቱና ሕይወቱ ፍጻሜ በፎቶና በቪድዮ ቀርጸው ለማኅበራዊ ሚዲያ ለማብቃት የሚቻኮሉ ትውልዶች የተፈጠሩባት፤ ለመርዳት ከሞከሩ እንኳን ከነ ምጽዋታቸው ሰልፊ ተነስተው ፌስቡክ ላይ ለመለጠፍ የሚሽቀዳደሙ ጉዶች የበዙባት ናት!
➓ ከኹሉም በላይ ደግሞ መረር ያለውን እውነት መናገርና መጻፍ ትኩረት የማይሰጥባት፤ ተደጋግሞ የሚነገር ሐሰትን እንጂ ጊዜ የከዳትን እውነት ለመስማት ትዕግሥት ያለው ትውልድ ለማየት ያልታደለች፤ ይልቁንም አጠር ተደርገው ለተጻፉ የፈጠራ ትርክቶችና የሐሰት ፕሮፖጋንዳዎች #LIKE እና #SHARE የሚያጎርፉ የፌስቡክ ሠራዊት የሞላባት፤ አማናዊቷ ኢትዮጵያ (እምነታቸው ምንም ይኹን) ከ99% በላይ ዜጎቿ ‹‹ሃይማኖተኛ›› ኾነው የተመዘገቡባት ሀገር ኾና ሳለ የፌስቡኳ ግን ከሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ሥዕለ ቅዱሳን ይልቅ በኮስሞቲክስ የተጨማለቁ ከፊል እብዶች ትኩረት የሚስቡባት፤ ዜጎቿ ለ10 ደቂቃ ጸሎት ጊዜ አጥተው ከ10 ሰዓታት በላይ ፌስቡክ ውስጥ ‹‹ሰላም›› ፍለጋ ሲዳክሩ የሚውሉባት፤ …በአጠቃላይ ልጆቿ ኾነው ሳለ ከጠላቶቿ በላይ የሚፈታተኗት ዜጎች ያሏት ምስኪን ሀገር ናት!
እንደ ማጠቃለያ፡- ‹‹ዐዲስ ነገር›› ይባል የነበረው ጋዜጣ ላይ እናውቀው የነበር፣ መሐመድ ሰልማን የተባለው እውቅ ጋዜጠኛ ‹‹ፒያሳ፥ መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ›› በተባለው መጽሐፉ ኢትዮጵያና ‹‹ኢቲቪዮጵያ›› የተለያዩ ናቸው ብሎ ነበር፡- ኢትዮጵያ በትክክል የምናውቃትና በእውን እየኖርንባት ያለችዋ ስትኾን ‹‹ኢቲቪዮጵያ›› ደግሞ ብሔራዊው ተለቪዥናችን (ኢቲቪ) የሚናገርላት፣ አስፈላጊው መሠረተ ልማት ኹሉ የተሟላላት፣ 24 ሰዓት መብራት የማይቋረጥባት፣ ውኃ የማይጠፋባት፣ ዲሞክራሲ ከአፍ እስከ ገደፍ የተረጋገጠባት፣ ወዘተ. እያለ ይገልጻል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እውነተኛዋ ኢትዮጵያና አኹን ያለው ትውልድ በተሳሳተ የታሪክ ትርክት የሚውቃት፣ ፌስ ቡክ ላይ የሚኖርባት ‹‹ኢትዮጵያ›› እውነትም ተለያይተዋል፡፡
Filed in: Amharic