>

የወታደሯ የ3 ቀናት የመቃብር ውስጥ ቆይታ (የመከላከያ ሰራዊት ገጽ)

የወታደሯ የ3 ቀናት የመቃብር ውስጥ ቆይታ

የመከላከያ ሰራዊት ገጽ

 

መ/ወ/ር ተስፋነሽ ጋቢሳ ትባላለች። የመከላከያ ሠራዊታችን ልዩ ሀይል አባል ናት ፡፡ ጁንታው በከፈተው ውጊያ ለመፋለም በራያ ግንባር ከክፍሏ አባላት ጋር ተሰልፋ በርካታ ግዳጆችን በድል ተወጥታለች።
ጠላት ለአመታት ያዋጋኛል ብሎ እንዳዘጋጀው በወታደራዊ ጠበብቶቹ በግንባሩ መሪ ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ እና ሌሎች አመራሮች የተመሰከረለት ልዩ ቦታው አዲ ቀይህ የተባለው ቦታ ላይ ለ3 ቀናት በተደረገው ፍልሚያ በጀግንነት እየተዋጋች ሳለ ያልጠበቀች ገጠማት።
በዚህ ቦታ ላይ ጠላት ሙሉ ሀይሉን ተጠቅሞ መዋጋት በመጀመሩ እንደ ሌሎች ምሽጎች በቀላሉ መስበር ካለመቻሉም ባሻገር ፣ ጠላትን ለመደምሰስ የገባውን የወገን ጦር ለመቁረጥ መልሶ ማጥቃት በማድረጉ ፣ ወገን የሃይል ሚዛኑን ለማመጣጠንና ሌሎች ወታደራዊ ጥበቦችን ለመጠቀም ሲባል ከጠላት ከበባ ሰብረው እንዲወጡ ሲደረግ ፣ መ/ወ/ር ተስፋነሽ በጠላት ቀጣና ተቆርጣ ትቀራለች።
ወ/ር ተስፋነሽ ወገን አሸንፎ ሞሽጉን እንደሚሰብር ሙሉ እምነት ስለነበራት ፣ የታጠቀችውን ስናይፐር ጨምሮ መሬቱን ቆፍራ ራሷን ጉድጓድ ውስጥ ትቀብራለች።  አፈሩን በእጆቿ በላይዋ ላይ በመመለስ ከመሬቱ ጋር በሚገባ ትመሳሰላለች።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች ብዙ የጁንታው ታጣቂዎች በላይዋ ላይ እየተረማመዱ ከወዲያ ወዲህ ይመላለሱባታል።
መማረክን ከሞት በላይ የምትፈራውና ድሉን ሳታይ መሞት የማትፈልገው ጀግናዋ መ/ወ/ር ተስፋነሽ ፣ ያላት አማራጭ ሁሉንም ችላ ዝም ማለት ብቻ ነበር።
ነገር ግን ጁንታው ከአጠገቧ ላይ ዲሽቃውን ሲጠምደው ፣ አንዱ የዲሽቃው ወሳ እግር ከተቀበረችበት አቅራቢያ ላይ አረፈ።
በቃ ድሽቃው ቦታውን ሳይለቅ ከአቅራቢያዋ እየተኮሰ 3 ቀናት ተቆጠሩ።
በነዚህ ቀናት ራሷን እንደሙት ያለምንም እንቅስቃሴ ትንፋሿን አምቃ በከርሰ ምድር ሳለች ከፍተኛ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ ሰራዊታችን ሞሽጉን ሰብሮ ድል ማድረጉን የዲሽቃው ዎሳ እግርም እሷ ካለችበት ጉድጓድ አካባቢ መነሳቱን አወቀች ፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ራሷን ከቀበረችበት በማስነሳት አካባቢውን ስትመለከት ጀግኖች ጓዶቿ ጁንታውን አባረው በታውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረውታል።
እሷ ብታውቃቸውም እነሱ ግን ሙሉ ሰውነቷ ከአፈር ሰለተመሳሰለ አላወቋትም ነበርና ‘ እጅ ወደ ላይ ‘ የሚል ድምፅ ሰማች።
እሷም እጆቿን አንስታ ‘ ወገን ነኝ ‘ የሚል ድምፅ በደስታ ብዛት ተውጣ አሰማች። እነሱም ወደ ኋላ በመውሰድ ከ 3 ቀናት በኋላ እህልና ውሀ እንድትቀምስ አድርገው ተመልሳ ጁንታውን ለደምሰስ እየተፋለመች ትገኛለች።
Filed in: Amharic