ስለናንተ እኛ እናፍራለን…!!!
ሙሉዓለም ገ.መድኀን
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ኦነግ ከድርጅታዊ መዋቅርነት ተሻግሮ መንፈስ ሆኗል፡፡ መንፈሱ ታሪክን እንደ ፖለቲካ ርዕዮት ከማየት የሚጀምር ሲሆን፤ ታሪክ ላይ መቸንከር ዋና መገለጫው ነው፡፡ በእኩልነት የመቆም ፍርሃት ያለበት ኦነጋዊው መንፈስ በእኩል እድል ሳይሆን በእኩል ውጤትና ብልጫ አስተሳሰብ መመራትን ይፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን ለማየትና ለማግኘት የሚቸገረው ይህ ኃይል፣ ከ ቤተ-ኢትዮጵያ ይልቅ ኦሮሙማ መደበቂያ ምሽጉ ነው። ኢትዮጵያዊነትን በሌሎች የተጫነ አድርጎ የሚያቀርበው የአስተሳሰቡ ተሸካሚ ኃይል፣ መሠረት በሌለውና በተጋነነ ጥላቻ ሌላውን ለማጥቃት አልፎም ለመዋጥ ሲያደባ ውሎ ያድራል፡፡ ትላንትና ያልነበረውን ጥያቄ አሁን እየወለደ፣ ዛሬ የሌለውን ጥያቄ ለነገ እያማጠ እንደሚሄድ ከልምድ አይተነዋል፡፡
መንፈሱ የተጣባቸው የኦሮሞ ኃይሎች የፖለቲካ መርህ አልባነት፣ ይሉኝታ ቢስነትና የሞራል ዝቅጠት መገለጫቸው ሆኗል፡፡ ይህ በመንግሥታዊ መዋቅሩ እንደወረርሽኝ እየተስፋፋ ያለ አመለካከት በየመድረኩና በየሚዲያው ሲገለጥ ከርሟል፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ የታዘብነውን ነውር በአክቲቪስት ሽመልስ አረዳድ ‹የሴራ ፖለቲካ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ለሌላው ነውር የሆነው ለዚህ ኃይል ‹ሴራ› የሚል ስያሜ አለው፡፡ የመንፈሱ አውራሾች ከጀርባ ሆነው በጫኑት/በሚጭኑት አስተሳሰብ ሀገር በህልውና ፈተና ላይ ወድቃ እንኳ የአስተሳሰቡ ተሸካሚዎች ታውቆ ባደረው የመርህ አልባነት፣ ይሉኝታ ቢስነትና የሞራል ዝቅጠታቸው እንደቀጠሉ ነው፡፡
የሰሜን ዕዝ በከሃዲውና ጨፍጫፊው ትህነግ ከጀርባ መወጋቱን ተከትሎ በተጀመረው ጦርነት እንደ ሀገር ሳይሆን እንደጠባብ የፖለቲካ ቡድን ጥቅሙን እያሰላ ‹ከዚህ ጦርነት ምን እናተርፋለን› በሚል ሴራ ሲጎነጉን ሰንብቷል፡፡ ሀገር በህልውና ፈተና ላይ ወድቃ፣ የሀገሪቱ 70 ከመቶ መካናይዝድ የጦር መሳሪያ ተዘርፎ፤ 45 ከመቶ የሚሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ተከፍቶ፤ ‹ሁሉም ነገር ወደ ሕግ ማስከበር› በተባለበት ሰዓት የኦነግ አስተሳሰብ ተሸካሚው ቡድን ከጦርነቱ በኋላ ራያና ወልቃይትን ከአማራ ግዛትነት አላቆ በአማራ የግዛት ቁጥጥርና የሕዝብ ቅነሳ የሚያተኩረውን ሃሳዊውን የፌዴራል ሥርዓት ማስቀጠል ስለሚቻልበት ሁኔታ ነገር ያብሰለስል፣ ሴራ ይቀይስ፣ ኃይል ያሰባስብ፣… ነበር፡፡
ስለሁለቱም አካባቢዎች የቀደመ ማንነት የተዛባ የሚዲያ ዘገባ በማሰራት፣ በአካባቢዎቹ የተወለዱና ለነሱ ፍላጎት ተገዥ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ከአገር ውስጥና ከዲያስፖራው በማፈላለግ የገጽ ለገጽ ግንኙነት ለመፍጠር በመሞከር፣ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተጠኑና ተጨማሪ ቅራኔዎችን የሚፈለፍሉ አጀንዳዎችን በመልቀቅ እንዲሁም የሌሎች ክልል አመራሮችን በጉዳዩ ዙሪያ በመወትወት (Lobby) ኀይል ለማሰባሰብ ሲሞክር ሰንብቷል፡፡
ይህ ኃይል፣ በትህነግ አረመኔያዊ ድርጊቶች ወልቃይት እና ራያ ላይ ሲፈጸሙ የኖሩ መንግሥታዊ ፍጅቶችና የዘር ማጽዳት ወንጀሎችን አለባብሶ (ሆንብሎ አሳንሶ በማየት) የአማራን ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄና ሀገርን ከፍርሰት ጠርዝ የመታደግ ተጋድሎ ‹የርስት ማስመለስ› አስመስሎ አቀርቦታል፡፡ ማይካድራ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ አማሮች በማንነታቸው የተጨፈጨፉበትን አሳዛኝ ድርጊት ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ለሠራዊቱ ድጋፍ በክልሉ ከአገር ወዳድ የኦሮሞ ተወላጆች አሰባስቦ ስለላካቸው ሰንጋዎች ካሰራው የዜና ሽፋን ያነሰ ሽፋን መስጠቱ ከቡድኑ ባህሪ አኳያ ባይደንቀን እንኳ፣ የዶ/ር ሙሉ ነጋ ጊዜያዊ የትግራይ አስተዳደር ወልቃይትና ራያ ላይ እንዴት መንገሥ እንዳለበት ያለ አንዳች ይሉኝታ ቢስነት ሰሞነኛ አዋጅ እያጣቀሰ ለመምከር መሞከሩ፤ ለዚህ ኃይል በየትኛውም ቦታ የሚፈሰው የአማራ ደም የኦነጋዊ አስተሳሰቡ ጥም ማርኪያ እንደሆነ ያስረግጣል፡፡ ከሰላሳ ዓመት በላይ ብዙ ማይካድራዎችን ያየው የወልቃይት አማራ፣ ፍጹም ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ‹ከትግራይ የሚመጣ ጥሩ ጎረቤት እንጅ አስተዳደር ፈጽሞ አንቀበልም›፣ ‹ጥንትም አማራ፣ ዛሬም አማራ› በሚል አቋሙን እየገለጸ የኦነግ አስተሳሰብ ተሸካሚው ቡድን ወልቃይትንና ራያን በትግራይ አልያም በፌዴራል ስር እንዲተዳደሩ ለማድረግ ዕቅድ ‹ሀ› እና ‹ለ› ብሎ ግብ አስቀምጦ በመስራት ላይ ነው፡፡
ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያው የግለሰብ አስተያየት መስሎ የቀረበው ‹የርስት› ጉዳይ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ‹በመርህ› ስም እስከ ማንሳት ተደርሷል፡፡ ባሰበው ልክ ኃይል ማሰባሰብ ባይሳካለትም በትህነግ እግር ቤኒሻንጉል ላይ እጁን ያስረዘመ በመሆኑ በመርህ ስም ከአሶሳ የዓላማውን ተጋሪ ፈልጎ አላጣም፡፡ የመተከል አማራ የመከራ ምንጭ የሆነው ይህ ጥምረት፣ የወልቃይትና የራያ ሕዝብ ወደ እናት ግዛታቸው መመለሳቸውን ለማደናቀፍ የማያውቅበትን የመርህ ፖለቲካ መሟገቻ አድርጎ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡ ወሰን የማያውቀውና የኬኛ ፖለቲካ መሀንዲስ የሆነው ቡድን ከሕገ-መንግሥቱ መጽደቅ በፊት በጉልበት የተነጠቀን ግዛት ለማስመለስ ያልኖረበትንና የማያውቀውን መርህ መሟገቻ አድርጓል፡፡ የአስተሳሰቡ አናጺ የሆነው ሌንጮ ለታ በአባልነት ያለበትን ‹የወሰን አስተዳደርና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን›ን አማላጅ አድርጎ አቅርቧል፡፡
አገሪቱ ከምትችለው በላይ በመፈለግ የሚታወቀው ይህ ኃይል መርህን ፈጽሞ አያውቀውም፡፡ ምሎ በሚገዘትበት ሕገመንግሥት እንኳ አዲስ አበባ የፌዴራሉ እንጅ የኦሮሚያ መቀመጫ አይደለችም፡፡ ከተፈጥሮ ሃብት ጋር ተያይዞ ስለ ልዩ ጥቅም ከማንሳት በስተቀር ሕብረ-ብሄራዊቷን አዲስ አበባ፣ ኦሮማይዝድ ለማድረግ የሚፈቅድ አንድም የታሪክ፣ የህግና የሞራል መከራከሪያ መሠረት የለም፡፡ ይህ ኃይል ግን አዲስ አበባን የኦሮሚያ እምብርት ብሎ ከመግለጽ አልፎ ኦሮሞ የሆነች አዲስ አበባ ለመፍጠር በግልጽ ሕገ-መንግሥታዊ ጥሰት ሲፈጽም መርህ አልባነቱ አልታየውም፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ድሬዳዋን እንደከተማ አስተዳደር የሚገልጻት ቢሆንም ባልተጻፈ ሕግ 40% ለኦሮሞ፣ 40% ለሶማሌ፣ 20% ‹‹ሌሎች›› በሚል መመራቷ ከተማዋ ላይ ለሚስተዋሉ ሥርዓት ወለድ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ይህ መርህም ይሉኝታም የለሽ ቡድን ቀዳሚ ተጠያቂ ነው፡፡ ሐረርን ለመዋጥ ከግማሽ በላይ ርቀት የተጓዘው ቡድን ስለ ሀቀኛ ፌዴራሊዝም ሊያወራ ሲሞክር ስለ እነርሱ እኛ እናፍራለን!!
በዝህች አገር ለአገው፣ አዊ፣ ኦሮሞ፣ አርጎባ የራስ አስተዳደር ፈቅዶ ሀቀኛ ፌዴራሊዝምን የሚተገብረው አማራ ክልል ብቻ ነው፡፡ በኦሮሚያ ያሉት የዛይ፣ የትግረ ወርጂ፣ የጋሮ ብሔረሰቦች እና በአስር ሚሊዮን የሚቆጠር አማራ የራስ አስተዳደር መብት የነፈገ አመራር ስለ ሀቀኛ ፌዴራሊዝም ሊያወራ ሲሞክር ኦነጋዊውን የአስተሳሰብ በሽታ የዕድገት ደረጃ እየነገረን ነው፡፡
ከሁሉም በላይ አስቂኙ ነገር በአማራ ብልጽግና አመራር ውስጥ የነሱን አዲሱ ለገሠዎች፣ የነሱን በረከቶች፣ የነሱን ህላዊዎች መፈለጋቸው ነው፡፡ ራሳቸውን እንደ ኦሮምኛ ተናጋሪ ‹ወያኔ› ቆጥረውት’ኮ ነውእነዚህ ሰዎች ዳግም የመወለድ ዕድል ቢያገኙ እንኳ አሁን ያለውን የአማራውን ፖለቲካ ለመረዳት ዕድል ያላቸው አይመስልም፡፡ አሁን ካልቸራል አማራ ነው ፖለቲካውን እየመራ ያለው! አሁን ታሪክ ሰሪ እንጅ ታሪክ የሚያበላሽ አመራርም ሆነ ወታደር የለንም፡፡ ከሕዝባዊ መስመር ውልፍት ማለት ምን አይነት ሕዝባዊ ቁጣ አልፎም ቅጣት እንደሚያስከትል አመራሩ ገብቶታል፡፡ ከሰሞኑ የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ አመራሮች ስብሰባ መረዳት የሚቻለው ነገር የአማራ አመራር በወልቃይትም ሆነ በራያ ጉዳይ አንድ ልብ መካሪ አንድ ቃል ነጋሪ መሆኑን ነው፡፡
አካታችና አሰባሳቢ የፖለቲካ አካሄድ የሚፈልጉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ቢኖሩም የኦነግ መንፈስ ተጠቂ የሆኑ አመራሮች የያዙት መንገድ ለተከበረው የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ለመላ የኢትዮጵያውያን አደጋ ያዘለ ሆኖ ይታያል፡፡
የኦነግ አስተሳሰብ ተሸካሚው ኃይል፣ በቀጣይ ወልቃይትና ራያ ላይ ስፖንሰርድ ፓርቲ እስከማቋቋም የሚደርስ የማታገያ ስልት የቀየሰ ቢሆንም በቆፈረው ጉድጓድ ራሱ እንደሚገባበት ስንናገር የትህነግን ወድቀት እንደ ግርጌ ታሪክ ማጣቀሻ በማስታወስ ነው፡፡
አማራ የሚፈልጋት ኢትዮጵያ፤ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ እና በህግ-ገዥነት የተመሠረተ ዴሞክራሲ የሰፈነባት ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላት አገር ተገንብታ ማየት ነው፡፡ ፖለቲካ የሕዝብን ስትራቴጅክ ጥቅም ለይቶ መታገል ነውና ይህን ቀናዒ ፍላጎቱን በመደገፍ ሶማሌው፣ አፋሩ፣ ሲዳማው፣ ጉራጌው፣ ጋሞው፣… ከኦነጋዊ አስተሳሰብ ተሸካሚነት ነጻ የሆኑ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አብረውት ይሰለፋሉ፡፡ ግፍን የሚቃወም ሁሉ ከአማራ ጋር አብሮ ይሰለፋል!
***
በቁማር የፈረሰ ትዳር እንጅ የተገነባ ሀገር የለም!!
ወልቃይትና ራያ የተዘጋ ፋይል ነው!!