>
5:13 pm - Saturday April 19, 1152

ደስታችን ገደብ ይኑረው፤ ጦርነቱ አሁንም አልተገባደደም! (ይነጋል በላቸው)

ደስታችን ገደብ ይኑረው፤ ጦርነቱ አሁንም አልተገባደደም!

ይነጋል በላቸው


      ሕወሓትን ማጥፋት እንደዚህ ቀላል የሆነበትን ምክንያት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ወያኔ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ረጂም ዘመን የገነባው የጦር ኃይልና የመሣሪያ ጋጋታ እንዲሁም ምሽግና የመሬት ውስጥ ለውስጥ ዋሻ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንኩቶ የሆነበትን ምክንያት መርምሮ ማወቅ ከተደጋጋሚ ውድቀትና ሽንፈት ይታደጋል፡፡ አሸናፊው እውነትና ወኔ እንዲሁም ጊዜ እንጂ የመሣሪያና የወታደር ብዛት እንዳልሆነ ማወቅ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ እንደ አንድ አንጋፋ ዜጋ የሚሰማኝን ከአሁን በፊትም ሆነ አሁን እናገራለሁ፡፡ እኔና መሰሎቼ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ አስቀድመን ተናግረን በኋላ ላይ በተግባር የተከሰተውን “የትንቢት” ቃል ሁሉ አንድ በአንድ ከነተጻፈበት ዓመት ለትውስታ ያህል ጊዜው ሲደርስ መዘከራችን አይቀርም – ለዚያ ይበለን፡፡

ሰሞነኛ ወሬዎች ብዙ ናቸው – የቱ ተነስቶ የቱ እንደሚጣል ማወቅ እስኪቸግረን ድረስ በሀገራችን ብዙ ነገር በየቀኑ በሚባል ሁኔታ እየተከሰተ አግራሞታችንን ሲያንረው ይታያል፡ ሁሉን መናገር ያስቸግራል፤ ከተለያዩ ምክንያቶች አንጻርም ሁሉንም ነገር ዘርግፎ መናገርም እንደዚሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ሊነገሩ ከሚችሉ ውስጥ አንኳር አንኳሮችን መጥቀስ መጥፎ አይደለም፡፡

ወያኔ በፖለቲካም በጦርነትም ተሸንፏል፡፡ የተሸነፈ ኃይል መንፈራገጡ አይቀርምና በተለያዩ ግልጽና ድብቅ ሥፍራዎች የወያኔው ርዝራዘዦች ለተወሰነ ጊዜ መስዋዕትነትን ማስከፈላቸው አይቀርም፡፡ ወደ ሱዳን የሄደ ኃይላቸውም ከውጪ ጠላቶቻችን ሁሉን አቀፍ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ድጋፍና ዕርዳታ በመታገዝ ችግር መፍጠራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የማይቀር ትንሣኤ ግን ሊያደናቅፍ የሚችል ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ ይህ ተብሎለት ተብሎለት ያለቀ ወርቃማ ዘመን ሊብት መሆኑ ደግሞ በጣም ግልጽ ነው – አንድዬ የተመሰገነ ይሁን ከዋሻው ጫፍ ደርሰናል፡፡ የብርሃን ጭላንጭሉም መታየት ጀምሯል፡፡ 

እነ ታዬ ደንደኣ ቢጠነቀቁ ይሻላቸዋል፡፡ በሽሮና በጎመን ጥጋብ የሚደነፉ ሁሉ አደብ ቢገዙ የራሳቸውን ታሪክ ከማበላሸት ይቆጠባሉ፤ ደግሞም ለማያውቃቸው ይታጠኑ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አንዱ ነገድ ተለይቶ አንድን ጦርነት ያሸነፈበት አጋጣሚ አልተመዘገበም፤ ሁሉም በኅብረት ሆኖ ነው የውጪውንም ሆነ የሀገር ውስጡን የከሃዲዎች ጦርነት ድባቅ ሲመታ የኖረው፡፡ ጀግንነትና ፍርሀት ደግሞ ግለሰብኣዊ እንጂ ቡድናዊና ነገዳዊ ወይም ጎሣዊ የኮታ ቅርጫ የለውምና ከዚህ ዓይነት የተሳሳተ ግንዛቤ በአፋጣኝ እንውጣ፡፡ እርግጥ ነው – ብዙ የተበደለና የተገፋ ወገን ብሶት የሚወልደው ብርታትና ኃይል ስለሚኖረው የተለዬ በሚመስል ጀግንነትና ወኔ ጠላቱን የማንበርከክ ልማድ በየትም ሀገር የነበረና ያለ በመሆኑ ይህን እውነት ልብ ማለት ክፋት የለውም፡፡ ለማንኛውም ጎሣና ነገዱ ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵዊነትን የያዘ ኃይል አሸናፊ ስለመሆኑ ታሪካችን ኅያው ምሥክር ነውና ወፍ ዘራሾች አንደበታቸውንም ብዕራቸውንም አደብ ቢያስገዙ የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች ራሳቸው ናቸው – ለምሣሌ በሁሉም ተሣትፎ የተሸነፈውን ወያኔ “በኛ የአመራርና የውጊያ ብቃት ነው የተሸነፈው” በሚል ዕብሪት አገር ይያዝልኝ ማለት ትልቅ ነውርና የጮርቃነት ውጤት ነው – የታሪክና የድል ሽሚያ ውስጥ ገብቶ መነታረክ ዓላማን መዘንጋትና ለቀጣይ ወያኔነት ራስን እንደማዘጋጀት የሚቆጠር ግብዝነት ነው፡፡ አክራሪዎች የዱባ ጥጋብ ካለስንቅ ማዘመቱን ተረድተው ረጋ ይበሉ፡፡ ሀብትና ገንዘቡንም፣ ሥልጣኑንም፣ መሬቱንም … ሁሉንም ጠቅልለው መያዛቸውን ይግፉበት (መቼስ ማልጎደኔ!) – እንደወያኔ ግን ግድያና እሥሩን ይተውት፤ በፍጹም አይጠቅማቸውም፡፡ አላበሳቸው ያሰሯቸውን የኅሊና እስረኞችም በአስቸኳይ ይፍቱ – ዕድሜያቸውን ክፉኛ የሚያሳጥር ጽላሎት በዲያቢሎሣዊው አክሊላቸው ላይ ወድቆ ይታየኛልና ንጹሓንን ማሰርና መግደል እንደማይጠቅማቸው የምትቀርቧቸው ምከሯቸው፡፡ ወያኔን መኮረጅ የተማሪውን ደብተር ስታበላሽ የነበረችውንና ተማሪው በደንደሱ በኩል አንገቱን ገዝግዞ ያስቀመጠውን ቢላዎ አንስታ በስለቱ በኩል ማንቁርቷን በጥሳ እራሷን እንደገደለችው ሞኝ ጦጣ መሆን ነው፡፡ ዛሬ ቤተ መንግሥቱ በኦነግ/ኦህዲድ ቁጥጥር ሥር ሆኖ አክራሪ ኦሮሞ በኦነጋዊ የኬኛ ፖለቲካው ቢፈነጭበትም ይህ ሁኔታ እንዳለ ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል – ተጠየቁ እኮ ቀላል ነው፡- የደርግን መጨረሻ ማስታወስ ነው፤ የወያኔን መጨረሻ ማየት ነው፤ በሌሎች የዓለም ሀገራት ያሉና የነበሩ አምባገነኖችን የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ማስታወስ ነው – የኅዋ ሣይንስ ምርምርን የሚጠይቅ አይደለም ነገሩ፡፡ ከዚህ ከዚህ አለመማር ድፍን ቅልነት ነው፡፡ የሆድ ዘመን እየጨለመበት፣ የኅሊና ዘመን እየፈካና እየጎመራ የሚሄድበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ሆድ ውስጥ ወርዶ የተሸጎጠው ኅሊና ወደመደበኛ ሥፍራው ወደ ጭንቅላት መውጣቱ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መቼም ቢሆን አይቀርም፡፡ ከሁኔታዎች መገንዘብ እንደምንችለው ይህ የማይቀር ሂደት የጀመረም ይመስላል፡፡ አሽከር ሲያመር ገድሎ ይጠፋል፤ ውሻ ሆድ ብሶት ጌታውን ሲከዳ ቢችል ጌታውን ነክሶ ከግቢ ይጠፋል፡፡ በቅሎ ሲመራት ጌታዋን ጥላ በእግሯ ትረመርመውና ትገድለዋለች፤ ሆድ ለኅሊና ቦታውን የሚለቅበት ጊዜ አለ፤ አዲስ ነገር እየተናገርኩ አይደለም፡፡ እናም መቀናጆውን ብአዴንን የከዳው ኦህዲድ ጌታውንና ጓደኛውን እንደከዳ ሁሉ ሌላ ታሪክ ሊፈጠር እንደሚችልም መዘንጋት አይገባም፡፡ ጊዜ መስታወት ነው፤ ገና ብዙ ነገር እናያለን፡፡

ስለዚህ በተረኝነት ስካር የምትናውዙ አክራሪ ኦሮሞዎች ይህን አቅለቢስ መንታላ(busiest) ልጅ እየተጠቀማችሁ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናከስ አትፍጨርጨሩ፤ ልጁ እርግጥ ነው ላይ ላዩን ሲታይ ደህና ይመስላል፤ በዚህም ሳቢያ “የተመረጡትን” ሳይቀር አነሁልሏል – ውስጡ ግን ልዝብ ሰይጣን መሆኑ በጓደኞቹ ማንነት መታወቁ አልቀረም (የሽመልስ አብዲሣ የዓላማና የፍላጎት ባልደረባ ሆኖ ኢትዮጵያን ይወዳል ቢባል በትንሹ ድንቁርና ነው፤ ብዙዎችን በፍቅሩ የሚያጃጅልበት አንዳች ምትሃታዊ ነገር ሳይኖረው አይቀርም (ይባልማል))፡፡ 

ለማንኛውም የአሁን ተረኞች ሆይ! ኢትዮጵያ የትግሬ፣ የኦሮሞና የአማራ ብቻ እንዳልሆነች ወዳችሁ ሣይሆን ተገዳችሁ በቅርብ የምትረዱበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሰ ሥልጡን ጦርና ለብዙዎች ዓመታት የሚያዋጋ ስንቅና ትጥቅ እንዳለው የሚገመተው ሕወሓት በቀናት ፍልሚያ የማሽላ እንጀራ ሆኖ መፍረክረኩ ልቦና ላለው ሰው ትልቅ ትምህርት በሆነው ነበር፡፡ ግን ትዕቢትና ዕብሪት ሁለመናን ያሣውራሉና ብዙዎች ማሰቢያቸውን  ላልባሌ ፍላጎታቸው አዋሉት፡፡ በዚያም ምክንያት ይሄውና አቢይን የተማመነው አክራሪ የኦሮሞ ኃይል በቤንሻንጉልና በሌሎች በርካታ አካባቢዎች አማራን ማረዱን ቀጥሏል፡፡ በተለይ ሽመልስ አብዲሣ የተባለው ፀረ-አማራ ግለሰብ አማራን ያሳረደውን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፕሬዝደንት ጠርቶ ኬክ ሲያስቆርስ ማየት የዘመኑ ታላቅ የትራጂ-ኮሜዲ ተውኔት ነው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በአቢይ አስተዳደር ሥር ነው፡፡ የአቢይንና እርሱ የሚወክለውን የኦነግ/ኦህዲድን መሠረታዊ ፍላጎትና ዓላማ ቁልጭ አድርጎ የሚያሣይ ድርጊት ነው ይህ በዚህ ኅብረትንና አንድነትን በሚሻ አደገኛ ወቅት በድፍረት የተከናወነ የኬክ ቆረሣ ድራማ፡፡  ያሳዝናል፡፡ አማራ ብዙ የቤት ሥራ እንዳለበት አመላካች የሆኑ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መርሣት ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ጥጋብ መጥፎ መሆኑን አሁን ይበልጥ ተረዳሁ፡፡ ጥጋብ ጊዜን አይመርጥም፤ ጥጋብ ዐይንንና ጆሮን ይጋርዳል፡፡ ጥጋብ ልብን ይደፍናል፡፡ “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” መባሉም ለዚህ መሆን አለበት፡፡

ጦርነቱ እንደተጀመረ እንጂ እንዳላለቀ በርዕሴ ጠቁሜያለሁ፡፡ አዎ፣ ከወያኔ ጋር የተጀመረው ጦርነት ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡ የወያኔ አባላት የሆኑ ሁሉ “ምነው ወያኔ አርገህ ፈጠርከኝ!” በሚል ፈጣሪያቸውን በጠማማ አንጎላቸው ፊት የሚከሱበት ዘመን በቅርብ ይመጣል፡፡ ወያኔዎች የሠሩት ግፍና በደል እንዲህ በቀላሉ ታጥቦ የሚጸዳ አይደለምና ብዙ የደም ጎርፍ ይጠብቀናል፡፡ በቀላል ደስታ ተውጠው በትናንሽ ድሎች ጥይታቸውንና ደስታቸውን የሚያባክኑ አማሮችን ሃይ እንድትሏቸው በዚህ አጋጣሚ አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ደስታን አላግባብ መደሰት ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነም እየሰማን ነው፡፡ ዒላማውን የሳተ ጥይት ሰውን እየገደለ፣ በመቶዎች ብር የሚገዛ ጥይትም አለመላው እየከሰረ እንደሆነ ይነገራልና በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ዘመድኩን በቀለን የምታገኙ ሰዎች ይህን መልእክቴን እባካችሁን ለርሱ አድርሱልኝ፡፡

በፌዴራል ተብዬው መንግሥት ውስጥ ያላችሁ አፋዳሾችና አክቲቪስት ነን ባዮች ሁላ ወደየኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ደግሞም አታስቁን፡፡ ቢቻል በምናምን እየመረቀናችሁ የሚሰጣችሁን ሁሉ በሚዲያችሁ አታውጡ፡፡ ሆዳምነታችሁንና ቅጥረኝነታችሁን ከማጋለጡም በተጨማሪ አመኔታን ያሳጣችኋል፡፡ “ሳያጣሩ ወሬ፣ ሳይገድሉ ጎፈሬ” ይባላልና እባካችሁ ለማጣራት ሞክሩ፡፡ ሰሞኑን ከታዘብኩት አስቂኝ መረጃ አንደኛው ለምሣሌ ወያኔዎች ለነኢትዮ360 እና ርዕዮት ሚዲያ በየወሩ ብዙ ዶላር እንደሚከፍሉ የወጣው መሠረተ ቢስ መረጃ ነው፡፡ የሀሰት ፍብረካ ልክ ሊኖረው ይገባል፤ አለዚያ ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት አመኔታን ለሚያሳጣ ቋሚ ትዝብት ይዳርጋል፡፡ 

እውነት ነው – በነዚህ ሚዲያዎች የሚሠሩ ሰዎች ሰው ናቸውና ሊሳሳቱ ይችላሉ፤ ማንም ፍጹም የለምና፡፡ ሽህ ጊዜ ቢሳሳቱ ግን ለነዚህ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ወያኔ ቀለብ ይሠፍርላቸዋል ብሎ መዘገብ ሕዝብን መናቅ ነው – አንድ ሰው ካላበደ በቀር በቦምብ ለሚያደባየው ሰው ቀለብ አይቆርጥም፡፡ እንደዚህ ያሉ ማጅራት መቺዎች ያሉበት መንግሥት ደግሞ እንኳንስ ሀገርንና ሕዝብን ሊያሻግሩ ይቅርና እነሱም ከወያኔ የማይሻሉ ተራ አሉቧልተኞችና ሲመቻቸውም ነፍሰ ገዳዮች ናቸው – እያደረጉ ያሉትም ይህንኑ ነው፡፡ ንጹሓንን የሚያስርና የሚገድል “አሻጋሪ” የሰበሰባቸው አክቲቪስቶች ብዙ ተዓምር እያሳዩን ነው፡፡ ነገሩ ያለቃ ገ/ሃናን ተረት ያስታውሳል፡- በቤታቸው ያንገሸገሻቸውን የጎመን ይሁን የሽሮ ወጥ ጠልተው ወደጓደኛቸው ቤት ቢሄዱ እዚያም ተመሳሳይ ወጥ ጠበቃቸውና “በየት ዞረህ ቀደምኝ” አሉ ይባላል፡፡ የአቢይ አካሄድ የገጸ ባሕርያት ወይ የባለታሪኮች ለውጥ እንጂ የድርጊት ለውጥ የለውም፡፡

ለማንኛውም በአሁኑ ወቅት ከነስህተታቸውም ቢሆን ለኢትዮጵያ ከቆሙ የግል ሚዲያዎች መካከል አንዱ ኢትዮ360 መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ባልመሰክር እኔም ወያኔ ማነው ኦነግ/ኦህዲድ መሆኔ ነውና ይሄውና መሰከርኩ – መረጃ ቲቪንም ጨምሩልኝ፡፡ ግን ግን በጥሩ ሥራ መኩራት እንዳለ ሁሉ በስህተትም መጸጸትንና ይቅርታን መጠየቅን ማወቅ፣ በከንቱ መታበይንም ማራቅ መልካም መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ትኅትናን እንላበስ፤ መታበይን እንናቅ፡፡ ከከንቱ ውዳሤ ራሳችንን እናርቅ፡፡ የሰይጣን መግቢያ ቀዳዳዎችን ሁሉ በተቻለን መጠን እንድፈን፡፡ 

በመጨረሻም ፈጣሪ ሳይደግስ አይጣላምና መምህር ዘመድኩን በቀለንና ስማቸውንና ግብራቸውን  እዚህ ዘርዝሬ የማልጨርሰው ወገኖቼን በዚህን ክፉ ዘመን እውነቱን ይዘው እንዲሟገቱና ለተገፉ ብዙኃን አለኝታ ሆነው ሌት ተቀን እንዲደክሙልን እግዚአብሔር ስለሰጠን ስሙ ለዘላለም የተመሰገነ ይሁን፡፡ ይህ ብላቴና በትናንትናው የኅዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም የመረጃ ቲቪ ዝግጅቱ ላይ ያቀረበውን ሃተታ ማዳመጥ እጅግ ጠቃሚ ነውና እባካችሁን ጎብኙት፡፡ ዘመዴን መሰሎችን ያብዛልን፡፡ ጠላቶቻችን ምንም ዓይነት ይሉኝታና ሀፍረት የሌላቸው የፍየል ዐይን በጨው ቀቅለው የበሉ እንደመሆናቸው እነሱን ለመታገል አንዳችም ዳተኝነትና ይሉኝታ እንደማያስፈልግ ከዘመዴ መማር ይቻላልና እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርከው፤ ልጅም ይውጣለት፡፡ ዜጋ ማለት እንዲህ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሃ አንበጣ እየበላ የመንግሥተ ሰማይን መቅረብ ይሰብክ ነበር …

መልካም ዘመን ለሀገራችን!

Filed in: Amharic