>

ብልፅግናዎች ሆይ...!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ብልፅግናዎች ሆይ…!!!

ጌታቸው ሽፈራው

* ….ኢትዮጵያ በቅርቡ ጫፉ የተሳለ ብቻ ሳይሆን ጫፉ  የዞረ ጉጠትን ከውስጧ እያስወጣች ነው። የቆሰለች ሀገር ነች። የእናንተን ድክመትና የማዋቅራችሁ  ክፋት ተጨምሮበት የአንድ ሙዚቀኛ ሞት የረበሻት ሀገር ነች። ስትቀልቡት የነበረ ጥጋበኛ ተከበብኩ ስላለ ልትቃጠል ደርሳ የነበረች ሀገር ናት። የእናንተ አመራሮች ታዲያ ከዛ ሳይማሩ ማዶና ማዶ ሆነው ለመወራወር ቦታ እየመረጡ ነው….!
 
ለመጀመርያ ጊዜ ብልፅግናዎችን ልመክር ነው። አንድ ጀልባ ላይ ተሳፍረን፣ የጀልባውን መሪ ይዘው ክፉኛ እንጥሩብ እየዘለሉ   መርከቧን ወደሚያሰጥም ማዕበል እየወሰዱን ቢሆን ነው ምክሬ። ቤት ውስጥ ሆነው በውስጥ ቆልፈው ቤቱ ውስጥ ያለ ውድ ነገር የማይገባው ፍጥረት ሊያደርገው እንደሚችለው ሁሉ ሊያጠፉት፣ ሲብስም ቤቱን ውስጥ ሆነው በእሳት ሊያያይዙት በሚያስመስል ክፉኛ እብደት ውስጥ በመሆናቸው ነው ምክሬ!
1)  የፓርቲ ዲስፕሊን የሚባል አለ። በብልፅግናም ይሄ ቀርቷል ብዬ አላምንም። ይሁንና ሰሞኑን ራስን ለመሸጥም ሆነ ለሌላ አላማ ማዶና ለማዶ  ሆኖ  መወራወሪያ ፊሽካው በፌስቡክ ተጀምሯል። ይሄ ችግር ባልገጠመው ሀገር ቢሆን ኖሮ እንደማይፈልጋችሁ አካል አጋግለን በአፍጢማችሁ ለመድፋት ይጠቅመን ነበር። የኢትዮጵያን አንድነት ባይፈታተን፣ በሕዝብና ሕዝብ መካከል ችግር ባይፈጥር ለምንቃወማችሁ እጅግ ምርጥ አጋጣሚ ነበር። ለተቃዋሚው አናክሰናሶ፣ ብዙ  ኃይል ሳንጨርስ እናዳክሞ ከማይገባችሁ ስልጣን ማባረር ጥሩ አማራጭ ነበር። ማጋጋል እንጅ መምከር አያስፈልገውም ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያ ላይ ነው ስልጣን ያያዛችሁት። ኢትዮጵያ በቅርቡ ጫፉ የተሳለ ብቻ ሳይሆን ጫፉ  የዞረ ጉጠትን ከውስጧ እያስወጣች ነው። የቆሰለች ሀገር ነች። የእናንተን ድክመትና የማዋቅራችሁ  ክፋት ተጨምሮበት የአንድ ሙዚቀኛ ሞት የረበሻት ሀገር ነች። ስትቀልቡት የነበረ ጥጋበኛ ተከበብኩ ስላለ ልትቃጠል ደርሳ የነበረች ሀገር ናት። የእናንተ አመራሮች ታዲያ ከዛ ሳይማሩ ማዶና ማዶ ሆነው ለመወራወር ቦታ እየመረጡ ነው። ድንጋይ የሚወረውሩት በርካታ ሕዝብ ከኋላ ይዘው እንጅ ብቻቸውን ሆነው አይደለም። ብቻን መግጠምማ የጀግንነት ነበር። የእናንተ ፈሪዎች የሚገጥሙት የሕዝብ ጥሻ ውስጥ ተደብቀው ነው። ለእኛም ጥጋበኞቻችሁ ሌላ ሳያነካኩ የፖለቲካ ሞትን ክልትው ቢሏት እንዴት መልካም ነበር። ሆኖም ሕዝብን ጋሻ አድርገው ነው ድንጋይ የሚወረውሩት፣ ኢትዮጵያ የምትባል የመስታውት ቤትን ተጠልለው ነው ካልገጠምን እያሉ የሚሸልሉት። ይህን ስለምንቃወማችሁ ብቻ ዝም ብለን አናየውም። እናንተ ሰክራችሁ ባይታወቃችሁ ውጭ ሆነን ጉዳችሁን ለማጋለጥ የምንፈልገው ሀገርና ሕዝብ ይዛችሁ ልትወድቁ ዘመም ዘመን የምትሉበት የክፋትና የጥፋት ጉድጓድ  ይታየናል። አንዳንዴ የጋራ ጉድ ይኖረናል። ቢያንስ ሀገርና ሕዝብ የሚባል የጋራ ንብረት አለን። እናም የፓርቲ ዲስፕሊን የሚባል አለ። አመራሮቻችሁ በይፋ ወጥተው ፌስቡክ ላይ ሲፅፉ እርስ በእርስ በውስጥ መስመር  ተላልከው፣ የሆነ አጀንዳ ለማስያዝ ፈልጋችሁ፣ ከሕዝብ የሆነ ተቀባይነትን ፈልጋችሁ ይሆናል። አልፎ አልፎ ደግሞ በመካከላችሁ ችግር ሲፈጠር፣ ፌስቡክ ላይ መጥቶ በመፎግላት የሕዝብ አቋም በመያዜ ነው የተገፋሁት ማለት ይፈልጋል፣ የሕዝብን ድጋፍ ይዧል ተብሎ  እንዲፈራ ማድረግ ይፈልጋል። በየአደባባዩ ከሚፎገላ ጅላንፎ ካድሬያችሁ  የሕዝብን ደሕንነትና የሀገርን ቀጣይ እጣ ፋንታ ካልመረጣችሁ ስልጣን እጃቸው ላይ ወድቆ እንደምንም ተጨማልቀውበት ሀገር ካጠፉት ባለጊዜዎች አልተማራችሁም ማለት ነው። ሀገር ያጠፉ ባለጊዜዎች መሆንን ያህል መረገም ደግሞ የለም። ሀገር ጠፍታችሁ ጭምር ነው የምትጠፋው። በአመዷ ላይ የምትጭኑት የክብር አክሊል አይኖርም።
2) ማንም ቅኝ ገዥ አበላሽቶት የሄደ ሀገር አይደለም የያዛችሁት። ምንም ያህል ችግሮች ቢኖሩም በተቀየመ በነጋታው መልካም የሚመስል ስራ  ሰራን ብላችሁ ብትዋሹት  ይቅርታ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ድጋፍ የሚችር ሕዝብ ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ። ከጥንት ጀምሮ ያላትን ቢገላበጥ ወርቅ የሆነች ሀገር ነው በእጃችሁ ላይ ሳትታሰብ የወደቀችው። በሌላ በኩል ግን ስልጣን ላይ ባለ ቸልተኝነት፣ ጥጋብ፣ አላዋቂነት ወዳልሆነ አቅጣጫ ልትደርስ የምትችል፣ አላዋቂዎች የገዘገዟት ሀገርም ሆናለች ኢትዮጵያ። ሕመም ፀንቶባት፣ የጎረምሳ ድብደባና መጓተት እጃችሁ ላይ ፀጥ ሊያደርጋት የምትችል ታማሚም ጭምር አድርገዋታል። አድርጋችኋታል። መልካሟም፣ የገጠማት ክፉ ነገርም ከመቸም በላይ ስክነት፣ ቅንነት የሚያስፈልገው ነው። እንጣጥ እንጣጥ ተብሎ የሚፈታ  ችግር የላትም፣ በእቡይነት መፍትሄ አታገኝም። ስልጣን ያጠግባል፣ ያሰክራል፣ አይን ያውራል፣ ጆሮን ይደፍናል፣ አእምሮን ያውካል። መሳርያውንም፣ መሰሪነቱንም፣ ክፉንም ደጉንም መስርያንም በሙሉ በእጃችሁ ይዛችሁታል። ከሰማዩ አምላክ በታች ሕዝብን አምልኩን ብላችሁ መደለያም፣ መግደያም ማሳየት ትችላላችሁ። ስልጣን መጥፎ ነው።  ያለፉት የወደቁበትን ለማስታወስ አያስችላችሁም። ከባለፈው መማር ቢቻልማ ትህነግ ባልወደቀ ነበር። ትህነግ ከየትኛውም የክልል ኃይል የተሻለ የተደራጀ ኃይል ነበር። ከየትኛውም ኃይል ይልቅ ሕዝቡን በዕዝ ያስገባ፣ ሀብት የያዘ ኃይል ነበር። ግን ከወደቁት ብቻ ሳይሆን አወዳደቅን አልተማረምና እንደምናየው ሆነ። የቀደመው እቡይነቱ ነው። እቡይነት ደግሞ ይሰብራል። ትህነግ ሲሰበር የሰበረው ራሱን ብቻ አይደለም። አብዝቼ እቆምለታለሁ የሚለውን የትግራይን ሕዝብ ጎድቷል። እናንተ የያዛችሁት ግን ከዛ የከፋ ነው። ትግራይ እንደ ሀገር አትበተንም፣ ሀገር አልነበረችምና። የእናንተ እብደት ግን ኢራቅ እንደነበረው ሀገር ያፈርሳል፣ ሶማሊያ ላይ እንዳየነው ሀገር ይበትናል።
3) ኃላፊነት ለሚሰማው ስልጣን ተገኘ ተብሎ እንደፈለኩ ልሁን አይባልም። ቤተ እምነት ክፍቱን ተገኘ ተብሎ ልጆች ኳስ አይጫወቱበትም። ቢያንስ ቤተሰቦቻቸው አይፈቅዱላቸውም። ኢትዮጵያን የምታክል ሀገር ላይ ማንንም አምጥታችሁ ዝለልባት ስትሉ ነውርን ባታውቁት ነው። በርካታ የብልፅግና አመራር እንደኔው  የገጠርን ሕይወት የሚያውቅ ነው። ባያውቀው አስረዳዋለሁ። እረኞች እያለን እንሰሳቱን በሙሉ ለሚረብሽ  ጥጋበኛ ወይፈን መፍትሄ ነበረን።  ያለ ቅጥ እየዘለለ ክበዶቹን ይገፋል፣ ጥጆቹን ይረጋግጣል፣ ጠና ያሉትን ያከላትማል፣ አልበቃው ብሎ በረት ሰብሮ፣ ከበረት ዘልሎ ሌሎቹም በሌሊት ወጥተው ለጅብ እራት፣ የሌባ ሲሳይ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ሁሉ  እጋ ቢተርፉ እንኳ ገበሬው ሲደክምበት የከረመውን  የጓሮና ሌላ ሰብል እንዲወድም ምክንያት ይሆናል። ታዲያ ይህ ጥጋበኛ ወይፈን ችግር እንዳይፈጥር መጀመርያ በእረኛ በትር ቀንድ ቀንዱን ብለነው ሰከን  እንዲል እናደርገዋለን። አልሆን ካለ ከበረት ውጭ እንዲያድር አድርገን ሌሎቹ እንዳይረበሹ እናደርጋለን፣ በረት ሰብሮ ችግር እንዳይፈጥር እናደርጋለን።  ጅብ ቢበላው፣ ሌባ ቢወስደው የምንከስረው አንድ ጥጋበኛ ወይፈን ነው። በጄ ካለና ካላከላተመ ይታሰራል። ወራቱ የማይጎዳበት ከሆነ ደግሞ መጥገቢያውን ይቀጠቀጣል (ይኮላሽና) አርፎ ሰከን ብሎ ይኖራታል።  ወይፈኖቻችሁን ኢትዮጵያ ለምትባል በርካቶች ለሚኖሩባት ሰፋና ቆየት ስላለች ጥንታዊ  ክቡር በረት ብላችሁ አደብ አስገዙልን! በውስጧ ለሚገኙ በርካቶች አብሮ መኖር ሲባል ቀንዱን የሚባለውን ቀንዱን በሉት፣ በፖለቲካ መኮላሸት ያለበት የራሱ ጉዳይ።
4) ከድል በኋላ ግብ ግብ እንዳለ እናውቃለን። አሸናፊ ነኝ ያለ አንዱን አጥቅቶ ሲመጣ ለይደር የያዘው ላይ መዞሩ የተለመደ ፖለቲካ ነው። እነ መለስ ዜናዊ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግስት አቧራ የሚያስነሳ የውስጠ ፖለቲካ ግብ ግብ ውስጥ ገብተዋል። ከዛሬው አንፃር የእነሱ የቅንጦት ነበር። እነ መለስ የነበሩባትን ኢትዮጵያ እጅጉን ቢጎዷትም ቅሉ ድካሟ ግን አሁን ከፍቷል። የዛሬዋ ኢትዮጵያ እነ መለስ ዜናዊ ሲቧቀሱ ከነበሩበት ወቅት የባሰች ነች። ያኔ ስለ ኢትዮጵያ ሲታገል የነበረው ብዙው አሁን ወደራሱ ጠበብ ያለች መድረክ ተጠግቷል። ያኔ እነመለስ የራሳቸውን ፖለቲካ እንጅ ሕዝብን ከጀርባ አድርገው አልገጠሙም። ቢሆን እንኳ የሀገር ሕዝብ አልነበረም። የአሁኑ ወቅት የከፋ የሚሆነው ኢትዮጵያ ትህነግ የሚባል ነቀርሳን ቀዶ ጥገና ላይ መሆኗ ነው። ህክምና ላይ ነች። ትንሽ ስህተት ይገድላታል። ትንሽ ስክነት ያተርፋታል። ቀዶ ጥገና ላይ ያለች ሀገር ላይ በሕክምናው እሳተፋለሁ የሚልም ሆነ ለሕክምናው የሚውልን ቁሳቁስ የሚያመጣ አሊያም በአካባቢው ያለ ሁሉ አሉታዊም አወንታዊም ሚና ይጫወታል። የሰሞኑ የብልፅግና ካድሬ አያያዝ በሕክምና መሃል ያለችን ሀገር ሳትነቃ ባዛው እንድታሸልብ የሚያደርግ ሩህሩህነቱም፣ ሙያውም፣ ኃላፊነቱም የሌለው ነው።
ይህን ኃላፊነት የጎደለው፣ እንግጠም እያለ ሲዘልል የሚውል ካድሬውን አደብ ቢያስገዛልን መልካም ነው። ተናካሽ ውሻውን ቢያስር፣ የሚዘልል ወይፈኑን ቀንዱን ቢልልን ለኢትዮጵያ እፎይታ ነው።
Filed in: Amharic