ታልፈው ያልታለፉት የቤተ አማራው ፈተናዎች፣ እና አይታለፌው ጋርዮሻዊው ሀገራዊ ፈተናችን!
አሰፋ ሀይሉ
በኢትዮጵያችን በቀደምት ጊዜያት – በቤተ አማራው ሲተዳደሩ የቆዩ የየክፍላተ ሀገራቱ ብዙዎቹ ነባር ወሰኖች አንድ በአንድ እየተቆረሱና እየተሸነሸኑ – በግልጽ አደባባይም በስውርም፣ በአንዴም ቀስ በቀስም – ያለ ምንም ይሉኝታና ከልካይ – ተነጥቀዋል፣ ተወርሰዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ከቤተ አማራው ውጭ ነው ተብሎ ለሚታሰበው ኢትዮጵያዊ ዘውጌ ታድለዋል፣ የራሳቸውን ስምና የዘር ታርጋ ይዘው ከቤተ አማራው የአስተዳደር ወሰኖች ተፈልቅቀው በብሔር ብሔረሰብ ስም ተገንጥለው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡
ቤተ አማራው ይበዛባቸዋል ወይም በሀገር አምሳል የሁሉም መዳረሻዎች አድርጎ ፈጥሯቸዋል ተብለው የሚታሰቡና የሚጠረጠሩ ከተሞችና ሥፍራዎች ሁሉ ጊዜና አቅም በፈቀደው መጠን ሁሉ ልክ በጊዜ ሂደት የተገነባ ህብረብሔራዊነታቸው ተጠራርጎ እንዲጠፋ፣ በአንዱ ወይም በሌላው ብሔር እንዲዋጡ፣ በአንዱ ወይም በሌላው ዘውጌ ኃይል እንዲጠረነፉ፣ አሊያም በብሔር ጨረባ ተበሻቅጠው እንዳልነበር እንዲሆኑ ተደርገዋል!
ሌላ ቀርቶ ከቤተ አማራው አስተዳደር ወሰንነት በፀረ አማራው ኃይል መሪነት ተገፍተው የወጡትንና ከፍተኛ የየክፍላተ ሀገሩን ሕዝብ ቁጭትና ቁጣ በመቀስቀሳቸው ምክንያት አልረሳ ያሉትን በወሎና ጎንደር ክፍላተ ሀገራት ነባር የአስተዳደር ወሰኖች ላይ እንደተፈፀሙት ቅሚያዎች ያሉት ራሳቸውን የቻሉ ግፎች ሆነው ሳለ – ቅሚያዎቹን ለመቃውምና ለመፋለም ተቃውሞን ለማሰባሰቢያነት እንዲቀነቀኑ የተደረጉት አጀንዳዎች ራሳቸው – አንድም ከዘርና ከብሔር ዘውጌያዊ ትርክት ጋር እንዲቆራኙ፣ አሊያም ደሞ ጸረ አማራ ውጤት እንዲያመጡ በሩቁ ታልመው የተመተሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
የዚህ ቀመር ማጠንጠኛው ምናልባት አንድ ቀን – ዕድል ፊቷን አዙራብን ወይ ገዢነቱ ከቁጥጥራችን ውጪ ሆኖ በሆነ ጊዜ ላይ የንጥቂያው አስጠባቂ ሥርዓታችን ቢወድቅ እንኳ – እነዚያ የአስተዳደር ወሰኖችና ነዋሪዎች በጭራሽ ወደ ነበሩበት የየቤተ አማራው ክፍላተሀገራት አስተዳደሮች ተመልሰው እንዳይቀላቀሉ ለማድረግ – የቻልነውን ያህል ተግተን እንሠራለን የሚል እንደ እንግሊዝ ካሉ አስከፊ የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ይመነጭ እንደነበረው የወደፊት የጥፋት ፈንጂ የመቅበር ሥራ ነበር፡፡ ለዚያም ሲባል ያልተሠራ ደባ የለም፡፡
ለምሳሌ ከቤተ አማራው ዘውጌ ወይም ብሔር ማንነት ትርክት ጋር ባልተገናኘ ግልጽ መንገድ – ‹‹የጎንደር/በጌምድር የቀድሞ የአስተዳደር ወሰኖች በትግራዩ ኃይል አላግባብ ወደ ትግራይ ተደርገው ተካልለዋልና ይሄ ተጣርቶ ወደ ነበሩበት ይመለሱ›› የሚለው ትክክለኛው ህጋዊውና እውነተኛው ጥያቄ ወደጎን ተብሎ – ከቤተ አማራው ላይ በያካባቢው ለየተነጠቁት አስተዳደሮችና ወሰኖች በየልካቸውና በየፊናቸው የብሄር ስምና ታርጋ እየተሰፋላቸው – የቤተ አማራው የአስተዳደር ወሰን አላግባብ መነጠቅን የሚመለከተው ቀጥተኛ ፍትሃዊ ጥያቄ – በራሱ በነጣቂው በወያኔና አጋሮቹ በሚቀነቀነው የዘር ከረጢት አጀንዳ ውስጥ እንዲገባና ወደ ብሔር-ተኮር አጀንዳ እንዲቀየር – ቀን ተሌት ለዓመታት ተለፍቶ ተሠርቶበታል፡፡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ በጥናት የተተገበሩ የአካባቢዎቹን ዲሞግራፊ ለመቀየር የታለሙ የሰዎች ሰፈራዎችና ስደቶች ተከናውነዋል፡፡ በአንድ ሕዝብ ላይ የተነጣጠሩ የተቀናበሩ ዲሞግራፊክ፣ ኢኮኖሚክ፣ ፖለቲካልና ስነልቦናዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡
ይህ ሁሉ የቤተ አማራውን ህጋዊ ቀጥተኛ የአስተዳደር ጥያቄ ወደ ብሔር ማንነት ጥያቄ የተገባበት ደባ ውጤትም ውሎ አድሮ ፍሬ አፍርቶ እያየነው መሆኑ የሚገባን – እስካሁንም ድረስ – የእገሌ ማንነት አስመላሽ፣ የእገሌ የማንነት ጥያቄ፣ የእገሌ ህዝብ አማራ ነው፣ በእገሌ ሥፍራ ውስጥ ያለው አማራ እንዲህ ይሁን፣ በዚህ ይውጣ በዚህ ይግባ፣ እንዲህ ይመቻችለት፣ ወዘተ ወዘተ የሚል… ከተገነባው የዘውጌ ትርክት ያልወጣ – እና በብሔር ስም የሚቀነቀን – ብዙ የተቃውሞም አጀንዳ እየተለፈፈ መሆኑን ስናይ ጭምር ነው!
የቤተ አማራውን የአስተዳደር ወሰኖች እንደ ቅርጫ ሥጋ የመበጫጨቅና የመቀራመቱ የተጠና የጥላቻ፣ የማንአህሎኝነትና የበቀልም ተግባር የተፈጸመው በብሔር ስም መሆኑ ሲገርም – ያንን በመቃወም እንዲቀነቀኑ የተደረጉት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ደግሞ መልሰው – የወይልቃይት ጥያቄ፣ የራያ ጥያቄ፣ የሌላም የሌላም የትየለሌ ጥያቄ… እየተባሉ – በነጣቂው ዘረኛ ከረጢት አምሳል የተሰፉ የዘውጌ ልባሶች በየልካቸው ለብሰው እንዲቀነቀኑ መደረጋቸው እጅግ ገራሚ ነው፡፡
ይህም ዓላማው ፊት ለፊት ወጥቶ ያገጠጠ ባይሆንም፣ ፈጽሞ የተሰወረ ግን አይደለም፡፡ የቤተ አማራውን የአስተዳደር ወሰን አላግባብ የመቀራመት እውነተኛና ግልጽ ጥያቄ – የእገሌ ህዝብ ጥያቄ፣ የእገሌ ተወላጅ የማንነት ጥያቄ፣ የእገሌ ዘውጌ ተቃውሞ፣ ወዘተ ወዘተ እያስባሉ ቆይተው በመጨረሻ – እነዚያ በስማቸው ሲዘመርላቸው የቆዩትን ዘውጌዎች ከቤተ አማራው የተለየ የራሳቸው አስተዳደር ይኑራቸው ለማለት ታስበው – ‹‹ንጥቂያው እንደታሰበው ለዘመናት መዝለቁ ባይሳካ እንኳን አማራው መቼውኑም መልሶ አያገኛትም!›› የሚል፣ በራሳቸው አምሳል የተጠነሰሰና የተቦካ የወደፊት ‹‹ፕላን-ቢ›› ተንኮል መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው!
ለምሳሌ ወልቃይት ወልቃይት ሲባል ኖሯል፣ ዛሬ ወልቃይት አማራ ነው – ነው ወጉ፣ ነገ ደግሞ ቆይተው ወልቃይት ራሱን የቻለ ህዝብ ነው ስለዚህ ራሱን ያስተዳድር፣ ራያ ራሱን የቻለ ህዝብ ነው ስለዚህ ራሱን ያስተዳድር፣ ወዘተ እያሉ በለመዱት የዘውጌ ከረጢት ያንንም ይሄንንም እያስገቡ ለመቀጠል በተቃውሞ ስም ያቀበሉት የቀጣይ ንጥቂያ አጀንዳ ነው የማንነት ጥያቄው መፈክር፡፡ በነገራችን ላይ ይሄንን እኮ የአፋርንም አስተዳደር ለዘለዓለም የነበረ አስተዳደር እስኪመስል ድረስ ከወሎ ገንጥለው አሳይተውናል እኮ! ድብን አድርገው፡፡ ይሄ በአንድ አማካይ ዕድሜ ላይ ባለ ኢትዮጵያዊ ዕድሜ የተፈጸመ ስለሆነ፣ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ የሁሉንም ሥፍራና የአስተዳደር ወሰን እየጠሩ ከመሐል እስከ ድንበር መዘርዘሩ አዋቂን ማድከም፣ እና አሉ-ተባሉ መባባል፣ የነገር አመድ መቆስቆስ ብቻ ነው ትርፉ፡፡
/ወያኔዎችና ጭፍሮቻቸው የሚከተሉት ስትራቴጂ እኮ ልክ ነባሮቹ ቅኝ ገዢ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ሀገራችንን ለመቆራረስ ሲተገብሩት የነበሩትን ያንኑ አንድ ዓይነት መንገድ መሆኑ ሁሌ ይገርመኛል፡፡ ትናንት የኤርትራን ሸማቂዎች ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ሲያደራድሩ ሁሌ ለድርድር የሚያቀርቡት የኤርትራ ህዝብ ፕሌቢሳይት (ወይም ሪፈረንደም) አድርጎ ድምጽ ይስጥበትና ከኢትዮጵያ ጋር መሆን ከፈለገ ይሁን፣ ካልሆነ ይገንጠልና የራሱን ሀገር ይመስርት – የሚል ነበር፡፡ ይሄን የሚደግፉ ከዚህም ከዚያም ነበሩ ብዙ፡፡ መንጌ ግን እኔ በህይወት እያለሁ ይሄ ባገሬ አይተገበርም ባይ ነበረ፡፡ ለዚያ አቋሙም እሱም ሀገሩም ዋጋ ከፈለችና – ለህዝቦቹ ይመቻቸውም አይመቻቸውም – የኢትዮጵያ ጠላቶች የተመኙት ሆነላቸው፡፡
እንግሊዞቹ የእነሱን ሆንግ ኮንግ የተዋዋሉት ውል ሲያልቅ ዓመቱን ቆጥረው ለቻይና ያስረክባሉ፣ ፈረንሳዮቹና ሸሪኮቻቸው ግን ከኢትዮጵያ ጋር የገቡት ውል ያለቀባትን ጂቡቲን በ1977 ራሷን የቻለች ሀገር ያደረጓት በተመሳሳይ የህዝበ ውሳኔ መንገድ ነው፡፡ የእኛዎቹም የሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያ ብለው ሲስሉ የሚመጣባቸውን ቤተ አማራ ዋነኛ ጠላታቸው አድርገው መቆራረጥና ማሽመድመድ የፈለጉት፣ የተገበሩትምና ያቀዱትም በዚያው በቅኝ ገዢዎቹ ዓይነት መንገድ ነው፡፡ ገና ወደፊት የኦሮሚያ ተብዬዋን ሪፈረንደም ለተመሳሳይ ዓላማ ሲባል የሚያግዝ የውጭና የሀገር ውስጥ የኃይል አሰላለፍ ተፈጥሮ ካላየን በእውነቱ ፕላኔታችን ዑደቷን አቁማለች ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ጠላቶች ፍላጎት ተገንዝቦ፣ አንድ ሆኖ ከመቆም ይልቅ፣ በነጋ በጠባ የብሄር አጀንዳ እየፈለፈሉ እርስ በርስ መበላላትና መነካከሱን ሥራችን አድርገን እስከያዝነው ድረስ በአጠቃላይዋ በኢትዮጵያችንም ሆነ በአማራው ህዝብ ላይ የተሤረው ብዙ ነው፡፡ ፈጣሪ ልቦናውን፣ ጥበቡን፣ ብልሃቱን ይስጠንና ከክፉው ሁሉ ይጠብቀን ማለት ነው!/
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ – በቤተ አመራው ላይ በፕላን-ኤ ላይ የታቀደው ቅርጫ ሳይሆን ከቀረ በሚል፣ በተቻለው ሁሉ የፕላን-ቢ ደባም አብሮ ሲጎነጎን ኖሯል፡፡ የሌሎቹም አሁን በስም ሳንጠራ የምናልፋቸው ቅርጫው የተካሄደባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ደባና ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እኛ እንደፈለግነው ካልበላነው፣ እናንተም አታገኟትም፣ ሲያምራችሁ ይቀራታል – ነው ነገሩ፡፡ /በቅርቡ ራሱ በፈጠረው ዘረኛ ሥርዓት አጋፋሪዎች በጠብመንጃ ኃይል ተወግዶ በሽሽት ላይ የሚገኘው ዶ/ር ደብረጽዮን የተናገረው ‹‹መሬት አስመላሹም እንደጓጓ ይቀራታል! አይኖርባትም..!›› የሚል ዛቻም ሆነ ትንበያ ሲታይ… የሰውየውን ወቅታዊ ሁኔታ ያየ የተስፋ መቁረጥ ፉከራ መስሎት ይዘባበታል እንጂ… ዛቻው በቀላሉ የተገኘም፣ የወጣም፣ የሚጣጣልም አይመስለኝም፡፡ ያወጣትም ዛቻ የሰውየውና ሰውየው የሚመራው ኃይል ብቻ ሃሳብ አድርጎ የተመለከተው ካለ በበኩሌ የዋህ ነው የምለው፡፡ ያልተሻገርናቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡
ከትናንት እስከ ዛሬ – ይሄን የቆየ ወያኔያዊ የነጠቃና የቂም በቀል የማንነት አጀንዳ፣ በመደገፍም በመቃወምም ስም፣ ሆነ ብሎ አውቆ ከሚያቀነቅነው አካል ይልቅ፣ ምኑንም ሳያውቀው ወያኔን እንፋለማለን ባዮቹ ያቀረቡለትንና የሰጡትን በወያኔ የዘር ከረጢት የገባ መታገያ አጀንዳ እንደወረደ ተቀብሎ ከልቡ ተግቶ የሚያራግበው መንጋ እጅጉን ብዙ ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡ ለዚህ መንጋ ዛሬ ላይ ተነስተህ… እንዲህ መባሉ ስህተት ነው፣ ዋናው አጀንዳ ይሄ አይደለም፣ ያ ነው፣ እንዲህ ነው መባል ያለበት.. ብትለው – የወንፊት ቀዳዳ ታክል መስሚያ የለውም!
ግመልን በመርፌ ቀዳዳ እንደማሳለፍ ያህል የከበደ፣ መልሶ ወደ ኋላ ላጠንጥንህ ቢሉት በብዙው የሚያዳግት፣ ወደፊት ቅደም ቢሉት የሚጎተት፣ ገና ብዙ ብዙ መብላላት ያለበት ስስና ተሰባሪ የሥልጣን ሰታቴ ሥር እንደ ጉልቻዎች ተለያይተን እየተያየን የተጣድን ህዝቦች ነን፡፡ ይሄኛውን በዚህ መንገድ፣ ያኛውን ደግሞ በዚያ መንገድ ታክመዋለህ፣ ነገር ግን የችግሮቹን ሁሉ ፍሬ እያረገፈብን ያለው ዛፍ ያው አንድ ተመሳሳይ ዛፍ ነው፡፡ የብዙው የመበላላት ምንጭ የዘረኝነት ሥርዓቱ ነው፡፡ ያ እስካለ ድረስ አለባብሰው ቢያርሱ ነው፡፡ እየደጋገምን በአረም መወረሳችን አይቀርም፡፡ የአማራውን ንጥቂያ እቀለብሳለሁ ስትል፣ ሌላ አግጦ ይጠብቅሃል፡፡ ያን በዚያ መልክ በብሔር በተቃኘ መፍትሄ ፈታሁ ስትል ደግሞ አጠቃላዩ ሀገራዊ ነገር መጥቶ ፊትህ ድቅን ይላል፡፡
የዚህ ሀገር ችግር አማራ ተሆኖ ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ኦሮሞ ተሆኖ ብቻ አይፈታም፡፡ ትግሬ ተሆኖ፣ ወላይታ ወይም አደሬ ተሆኖ ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ የዚህ አገር ችግር በዘረኝነት ጥላ ውስጥ ተጠልሎ የሚፈታ አይደለም፡፡ እግር ተወርች ተብትቦ ካስቀረን ከዋናው የዘረኝነት ስንክሳር በጣጥሰን መውጣት ካልቻልን መቼም ከአዙሪታችን ልንወጣ አንችልም፡፡ እያንዳንዱ የየብቻ መዳኛችን ለአጠቃላዩ አውዳሚ ሥርዓት ተጨማሪ ዕድሜ ሰጪ ምግብ ነው፡፡ ለዚህ ነው – ዛሬ ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው የሚጠቅምና የሚያዛልቅ ነገር የመምጣቱ ጉዳይ – የመጨረሻ ውጤቱ ሲታይ – ምንም ሆኖ የሚቀረው፡፡
ዛሬ ላይ ያለንበት ፖለቲካ – ቀድሞ ከነበረበት ፈቅ ያላለ – አሁንም ዞሮ ዞሮ አንዱ ከሌላው በማይሻልበት፣ ሁሉም በየፊናው የየራሱ የተቡካካ የዘውጌ ጠባብነትንና ጋርዮሻዊ አስተሳሰብን የተላበሰ አቋም አንግቦ በሚገኝበት ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ እየዋኘ ያለ ፖለቲካ ነው፡፡ ዛሬም ላይ እንደ ትናንቱ ሁሉ የአድራጊነት የፈጣሪነት ሥልጣን እንዳለ ተጠቅልሎ በዘውጌ ፖለቲከኞች እጅ ቀጥሏል፡፡ አንዱ የዘውጌ ኃይል፣ ከሌላው ዘውጌያዊ ኃይል የተሻለ – ከዘረኝነት አስተሳሰብ የላቀ የሞራል ተክለሰውነት ለብሶ አይታይም፡፡ የተለየ ሀገራዊ ሰብዕና በሌለው የወረደ የጨረባ ተዝካር ውስጥ ሁሉም በየፊናው ህዝቡን በስሜት አሰልፎ እልም ብሎ ገብቶ ሲያበቃ፣ አንዱ አንዱን ከአንተ እሻላለሁ ብሎ ለመሞገት መንደፋደፍ – በአሁን ጊዜ እየታደምን ያለነው እጅ እግር የሌለው ሀገራዊ ትራጀዲያችን ነው፡፡
በበኩሌ የአማራው ዘረኛ ከኦሮሞው ዘረኛ የሚለይበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ የትግሬው ዘረኛ ከአደሬው ዘረኛ የሚለይበት አግባብ ይኖራል የሚል የተስተሀቀረ ቀመር የለኝም፡፡ ማንኛችንም ዘረኝነትን ከምንጩ ኢሞራላዊ አድርገን ካልተፀየፍን በቀር ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የጋርዮሹ ሥርዓት አቀንቃኞች መሆናችን ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ከዚህ.. ‹‹ከባልሽ ባሌ ይበልጣል›› እያባባለን ከሚኖር.. አስከፊ ጋርዮሻዊ አረንቋ ተረዳድተን እንውጣ.. ቢባል.. የረጋ ጆሮ ሰጥቶ፣ የራሱን ጎሰኛ የብሔር አድቫንቴጅ የሚመታበትን መላ ሳያውጠነጥን፣ እና ከልቡ አልትሩዪስት (ለራሱ ዘርማንዘር ሳያደላ፣ ለሀገርና ለህዝብ ብቻ ቅን አሳቢ በመሆን የተገኘ) ሀሳብ ሰንቆ፣ መልካሙን ዕድል ሁሉ ለአጠቃላዩ የሀገራችን ህዝብ ሊያደርገው ቆርጦ የተነሳም፣ የሚነሳም፣ ይህን መሰል ሃሳብ የሚሰማም፣ በዚህ መሰሉ ሀሳብ የሚሠማማም፣ የሚስማማም ሰው – በጋርዮሹ ሥርዓት ዘዋሪዎች ዘንድ ፈልጎ ለማግኘት ማሰብ – በከንቱ መማሰን ነው የሚል ምክንያታዊ አቋም አለኝ፡፡ ይህን ዓይነቱ ሀገራዊ ስብዕና – እንኳን ከጋርዮሹ ፈጣሪዎች ዘንድ፣ በሀገሩም ላይ የለም ዛሬ! ቢኖርም ከንፍሮ መሐል የተገኘ ጥሬ ሆኖ አብሮ በጎሰኛው ጋን ተጥዶ እየተንገበገበ ነው፡፡ ለመገኘትም፣ ጎልቶ ለመደመጥም ትንፋሹም፣ ዕድሉም አይኖረውም ፡፡
የዘረኝነትን አፈር ውሃ አቡክተው፣ የዘረኝነት ተራራ የተሰደረበትን የጋርዮሽ መሠረት ገንብተው፣ የዘውጌ ድር ሲያደሩና ሴራ ሲጠነስሱ ከኖሩ ጭንቅላቶች – ዛሬ ላይ ከዘርና ዘረኝነት አባዜ የራቀ ነገር እንዴት ተብሎ ነው የሚጠበቀው? ሴራ ብቻ ነው ያለው! የዘረኛና የዘረኛ ፉክክር ነው ያለው! አንዱ ዘረኛ ሌላውን ዘረኛ ቀብሮ ለመኖር ነው ህልሙ ሁሉ! እንደ ዱር እንስሳት እርስ በርስ ትነካከሳላችሁ ብለው አለያይተው፣ አፈራርተው፣ አጠራጥረው፣ ሲያጠላሉን የኖሩት አሁንም አብረውን አሉ፡፡ ዛሬ የተሸነፉ የመሠለው ካለ በእጅጉ ተሳስቷል፡፡ የዋሃን ሆነናል፡፡ ዘረኝነት ነግሶብን በመካከላችን አለ፡፡ ዘረኝነትን አንግሰን ተመችቶን በቲፎዞ ጎራ ለይተን ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው እያጨበጨብን ቅልጥ ባለ የዘረኝነት ፕሪምየር ሊግ ውስጥ እየኖርነው ነው፡፡ አንዱ ዘረኛ ወድቆ ሌሎች ዘረኞች ሲነግሱ የዘረኝነት ባላደራው የሞተ ይመስለናል እንጂ፣ የአንዱ ዘረኛ መውደቅ፣ ለብዙ ዘረኞች በር የሚከፍት የደስታቸው የድላቸው እና የዕድላቸው ጊዜ አሁን ነው፡፡
ትናንትናም የሚሰማ አልነበረም! ዛሬም የለም! ወደ ፊትም በልማድ እስረኝነት፣ በአድርባይነት፣ በእልህና በጥላቻ እየተደናበርንም እየተደናገርንም የገባንበትና፣ ከእርሱ ወጣ ብለን ሌላን ነገር ለማስተዋል እስካንችል ድረስ ሁለመናችንን የጋረደብን፣ ከውስጣችን ገብቶ የተዋሃደን፣ የጋርዮሽ አመላችን ጨርሶ እስኪለቀን ድረስ.. እንዲሁ ‹‹ግም ለግም አብረህ አዝግም›› ሆነን እንቀጥላታለን እንጂ – በዛሬው የብሔር አሳሞች ከበው የድርሻቸውን ለማንሳት በሚሻሙበት ሀገራዊ ገበታ ዙሪያ ታድመን – ከዘረኝነት በላይ ሆኖ – መገነጣጠሉ ለዶሮም አልበጃትምና አንድ የምንሆንበት መላ ይፈለግ ብሎ – እንደ ሀገር አስቦ ለሀገርና ስለሀገር የሚንቀሳቀስ ኃይል የለም! ትናንት ቢገኝ ኖሮ… ዛሬ ላይ የት በደረስን! ዛሬ ላይ ቢገኝ.. ነገ የት እንደርስ ነበር! ይሄ ኃይል ግን የለም!
በአንድ ወቅት አፍሪካን አንድ አደርጋለሁ ብላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሠረተች ሀገር – ዛሬ በማይሰሙ በማይለሙ ደነዝ ዘረኞች የተሞላች ሀገር ሆናለች! ኢትዮጵያ ዛሬ የትምህርት ካባ በደረቡ እልፍ ዘረኛ ፊደላውያን እጅና ጥርስ የገባች ሀገር ነች፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን የተማረው ሰው የመንገኞች መሪ ሆኖ በለው ግደለው ቁረጠው ፍለጠው በዚህ ውጣ በዚህ ግባ ሲልና ሲባባል እንጂ፣ ከመንጋው አፈንግጦ ከመንጋው የተለየን የተሻለን ጎዳና ሲመራና የተሻለ ሀገርን የሚያሻግር ራዕይን ሲያመላክት አልታየም! ሁሉም በየጎጡ ተሸጉጧል! ሁሉም ያው! ሁሉም ወደየትም በማያደርስ የጋርዮሽ እሰጣገባ ተጠምዶ፣ እዚያው እርገጭ እዚያው እመጭ ሆኖ የሚባክን ሆኗል!
ከዚህ ከተዘፈቅንበት የጋርዮሽ ሥርዓትና የጋርዮሽ ዘመን መበላላት፣ ከጋርዮሹም ጉዟችን የሚገላግለን መፍትሄ – ከዚህ አሁን ካለው የጋርዮሽ ሥርዓት፣ የሥርዓቱ የፊትም ሆነ የኋላ ሠልፈኞች አሊያም በጋርዮሹ ሥርዓት ለሥልጣን አፋቸውን እያረጠቡ ከሚቅለበለቡ ብዙሃን ተስፈኞች መጠበቅ – ከየዋህነትም አልፎ – ድንዛዜ፣ ድንቁርናና አዕምሮን መሳት ይባላል፡፡ አሁን ያለው የጋርዮሽ ሥርዓት፣ የጋርዮሽ ሥርዓቱ ተደማሪም ሆኑ ተጻራሪ፣ ተካፋይም ሆኑ ተቀናሽ አቀንቃኞች፣ እና የጋርዮሹ መንገኞች ባጠቃላይ ለዚህች ሀገር የተለየ ለውጥና ተስፋ የሚያመጡ አይደሉም፡፡
መቅሰፍትን ለሀገርህ ለወገንህ አትመኘውም፡፡ ግን እንደ ነብዩ ኢሣያስ ‹‹ፈጣሪ ሆይ እስከመቼ ነገሥታቱን ዝም ብለህ ትመለከታለህ? የሀጢያተኞችስ ግፍ ማብቂያው መቼ ነው? በቁጣህ አንድዳቸው! መቅሰፍትህን ላክባቸው!›› እያለ መቅሰፍትን እንደሚመኘው – እኛም ካታስትሮፊ ፖለቲክስ እየነዳን የምንገኝ – እና በተራችን በገዢዎቻችንና አጋፋሪዎቻቸው ላይ መቅሰፍትን የሚያስመኘን ጊዜ ላይ ብንገኝ አይፈረድብንም፡፡ ከሆነ ላልቀረ ምነው አንዴ እንደ መንጌ ዓይነቱን መቅሰፍት የሆነ፣ ሥርነቀል የሆነ፣ ይሄን የጋርዮሹን ነገር ዓለም ሁሉ ከሥሩ መንግሎ በጣጥሶ የሚጥልልን፣ የሆነ የመንጋውን ዘውገኞች ቀረጣጥፎ የሚበላ አንድ መንጉ መጥቶ፣ ጠራርጎ ባጠፋልንና በገላገለን! እንጂ ሌላስ መገላገያ ያለንም አይመስለኝ፡፡ ወይ ይሄ የኛ በዘረኝነት የተለከፈው የኛ ትውልድ አልፎ፣ ከጋርዮሹ መርዝ የተረፉ የወደፊቱ ነቄ ትውልዶች ቢነሱና ነገአችንን እንኳ ቢያተርፉልን – ብዬ እመኛለሁ እንደ ቅዠት አንዳንዴ! በዚህ አያያዛችን ከጋርዮሹ ዑደት መውጫም ሆነ መፈወሻ የሌለን፣ የጋርዮሽ ግዞተኞች፣ ባለንበት ረጋጮች፣ እንዘጭ እምቦጮች ሆነን መቅረታችን ነው፡፡ ያ ያሳስበኛል!
መፍትሄው ይህን የጋርዮሽ ሥርዓት፣ ከነአጠቃላይ ሰዎቹ፣ ከነምናምንቴው መንግሎ ለመጣል የሚነሳ የቆራጥ ትውልድ መምጣት ብቻ ነው! እስከዚያ እንዲሁ እየተቡካካንና አንዱ በአንዱ ላይ የስለት ጦር እየተወራወርን መኖር ብቻ ነው! ይህ ሥርዓት ታክሞ ከዳነ ከፊታችን ተዘርግቶ የሚጠብቀን የመደነቋቆር ዘመን በቀላሉ ማለቂያ የለውም! መደናቆር ብቻ ነው! ቢወቅጡት እምቦጭ ብቻ፡፡
ፈጣሪ ከገባንበት አስከፊ የዘረኝነት ህመም ይፈውሰን! ከዚህ የጉድ ዘመን ያውጣን ፈጣሪ አምላክ! ከተለከፍንበትና በወል ከታወርንበት የዘረኝነት ጦስ ጨርሶ ይማረን አንድዬ ፈጣሪ አምላክ! ዘመናችንን ከዘመነ ጋርዮሽ ቀንበር ይዋጅልን ሁሉን ቻዩ ፈጣሪ አምላካችን!
ሠላም ሠላም፣ ፍቅር ፍቅር፣ ሥርየት ሥርየት ሥርየት… ለመላ ሀገራችን፣ ለሕዝባችን ሁሉ ይሁን!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!