>
5:26 pm - Sunday September 15, 9191

መንግስት በትግራይ ክልል ለተከሰተው ችግር ልዩና አስቸኳይ ዕርዳታ ሊያደርግ ይገባል ! (ዘ ተስፋዬ)

መንግስት በትግራይ ክልል ለተከሰተው ችግር ልዩና አስቸኳይ ዕርዳታ ሊያደርግ ይገባል ! 

ዘ ተስፋዬ 


 

በህወሃት ከፍተኛ አመራር ውሳኔ፣ በትግራይ ልዩ ሃይልና በሰሜን እዝ ውስጥ በመለመሉዋቸው የእዙ አባላት አቀነባባሪነት ትግራይ ውስጥ ሰፍሮ፣ ሃገራዊ ሃላፊነቱን ይወጣ በነበረው የፌደራል ሰራዊቱ የሰሜን እዝ ላይ በአራት የተለያዩ ስፍራዎች ጥቅምት 24/2013 . ጥቃት መፈጸማቸው ይታወቃል። 

በዚህ ታሪክ ይቅር በማይለው የሀገር ክህደት ተግባር በርካታ የእዙን አመራሮችና ሌላ አባላትን ከመግደል ባሻገር ሺዎችን አግተው የእዙን ወታደራዊ ትጥቅ በመዝረፍ ለቀጣይ ጥቃት በመዘጋጀታቸው መሃከላዊ መንግስት ህግን ለማስከበርና ቀንደኛ አመራሮችን ይዞ ህግ ፊት ለማቅረብ በሚል ወታደራዊ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል። 

መንግስት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃቱ ከተጀመረ ማግስት ጀምሮ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በመሰረቱ ግቡን መቶ ህዳር 19/2013 መጠናቀቁንና የሚቀረው በሽሽት ላይ ያሉ የህወሃት አመራር አባላትን አሳዶ የመያዝ የፖሊስ ተግባር እንደሆነ ጠቅላይ ምኒስትሩ ተናግረው ነበር።

የወታደር ዘመቻ፣ ያውም የጦር አውሮፕላኖችና ከባድ መሳሪያዎች የተሳተፉበት ቀላል ሊሆን እንደማይችል፣ ውጊያው በሚካሄድበት ቀጠናም የሰላማዊውን ህዝብ የቀን ተቀን ኑሮ እንደሚያዛባ፣ ህዝብን ከቀዬው ሊያፈናቅልና ህይወትም ሊቀጥፍ እንደሚችል የታወቀ ነው፣ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ዘመቻም የሆነው ይሄው ነው።

በትግራይ ክልልበደህናውምጊዜ አስር በመቶ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ መሰረታዊ ኑሮውን የሚገፋው ከተራድኦ ድርጅቶች በሚያገኘው ድጎማ እንደነበር ሲታወቅ፣ ወታደራዊ ግጭቱ በመቀስቀሱ በሚልዮን ሊቆጠር የሚችል ህዝብ ኑሮው ሊናጋ እንደሚችልም መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም በኑሮ መናጋት በፍርሃት ወይንም በሌላ ምክንያት 40000 በላይ ዜጎችም ወደ ምድረ ሱዳን እንደተሰደዱ የሚታወቅ ነው።

ከልዩ ልዩ የዜና አውታሮችና በአንዳንድ ከተሞች ከሚገኙ የእርዳታ አስተባባሪ ድርጅቶች በሚሰማው፣ መሰረት የመሰረታዊ ፍጆታ ማለትም  ውሃ፣መብራት ስልክና የሃኪም ቤት ቁሳቁሶች ጭምር ትልቅ እጥረት ወይንም ሙሉ  ለሙሉ አለመኖር ህዝብን እንግልትና ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየከተተ ይገኛል

መንግስት በህግ የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች ተከታትሎ የመያዝ ሃላፊነት እንዳለበት ቢታወቅም፣ በተፈጠረው  የሰላም መናጋትና ችግር ምክንያትም የተዛባውን የህዝብ ኑሮ ወደነበረበት የተረጋጋ ሁኔታ መመለስ መንግስታዊ ግዴታው ነው። 

እርግጥ መንግስት ይሄን በሚመለከት አንዳንድ የመልሶ መገንባት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ቢገልጽም ፣በተግባር ግን ውሱን መሆኑን መቀሌ ያለው አይደር ሀኪም ቤት ገጠመው የተባለው የመድሃኒት የመብራትና ውሃ ችግር ማሳያ ሊሆን ይችላል። በዋና ከተማው እንዲህ ያለ ችግር እውን ከሆነ ደግሞ በአነስተኛ  ከተሞችና በገጠር አካባቢ የከፋ ችግር ሊኖር እንደሚችል ማሰብ ከባድ አይደለም።

 መንግስት ያለው አቅም ውሱን ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታዎች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ለመመለስ አዳጋች ቢሆንም እርዳታ ለመለገስ ፈቃደኛ የሆኑ የግብረ ሰናይ ድርጅቶችንም ሆነ መንግስታት በላቀ ቅልጥፍና አስተባብሮ አጣዳፊ እርምጃ መውሰድ ለነገ የሚባል ተግባር ግን ሊሆን አይችልም።

ክልሉ ከሰላም መደፍረስ በተጨማሪ በአካባቢው በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋና፣ (እህል በማጨጃ ወቅት የአንበጣ መንጋ ያደረሰበት ጉዳት) ሀገር አቀፉ ወረርሺኝ በመደራረባቸው ከሌላው የሀገራችን አካባቢ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው የግድ ይላል።

ወደ ሱዳን የተሰደዱ ወገኖቻችንን በሚመለከት መንግስት መልሶ ማስፈር ከባድ እንዳልሆነ ቢገልጽም፣ ሰው ቀየውን ለቆ ለመሰደድ ያበቁት ምክንያቶች ተቀርፈዋል ብሎ እስካላመነ ድረስ የመመለስ ፍላጎት ስለማይኖረው ባሉበት ሆነው ለጊዜው የሚረዱበትን መንገድ ከአስተናጋጇ ሃገርና ከዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር የማቀነባበር ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። 

ከሁሉም በላይ ግን በውጭ ለተሰደዱትም ሆነ በክልሉ ውስጥ ግጭቱን በመሸሽ ከቀዬአቸው ለተሰደዱ ወገኖች  አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በአጣዳፊ ማስፈን ይሄንንም ለማድረግ የሚደረገውን ጥረትና እንቅስቃሴ  በተጨባጭ እየተካሄደ ለመሆኑ፣ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር የዜና አውታሮች እንዲዘግቡ ማመቻቸት ችላ ማለት የሌለበት  የመንግስት ሃላፊነት ሊሆን ይገባል

ዘ ተስፋዬ 

Filed in: Amharic