>
5:13 pm - Monday April 19, 5706

ጃንሜዳ ላይ ጥያቄያችን ከጽዳት በላይ ነው...!!! (ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ማህበር)

ጃንሜዳ ላይ ጥያቄያችን ከጽዳት በላይ ነው…!!!

ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ማህበር

ትናንት ሕዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የአዲስ አበባ መስተዳድር ጃን ሜዳን የማጽዳት ሥራ ጀምሯል፡፡ አስቀድመን መንግሥት ቃሉን አክብሮ ወደ ተግባር መግባቱ የሚበረታታ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡ ይሁንና ግን ጃን ሜዳን ከገበያ ግርግር እና ከቆሻሻ አጽድቶ ለበዓለ ጥምቀት ማዘጋጀት ከከተማው ማዘጋጃ ቤቱ የምንጠብቀው ሦስተኛውና የመጨረሻው ጥያቄያችን መልስ መሆኑን የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑ ኦርቶዶክሳውያን እና መንግሥት እንዲያስታውሱት መጠቆም አንወዳለን፡፡ የጴጥሮሳውያን ኅብረት ጃን ሜዳን  አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሌሎች የሀገራችን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ባደረግናቸው ውይይቶች ሦስት የቤተ ክርስቲያናችን ጥያቄዎች እንዲመለሱ አቤት ስንል ቆይተናል፡፡
ኢትዮጵያችንን በዓለም መድረክ ከሚያስጠሯት ቅርሶቿ መካከል የሰማያዊ ሥርዐት ነጸብራቅ የሆነውና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዕደ ዮሐንስ በባሕረ ዮርዳኖስ መጠመቅን የምንዘክርበት በዓለ ጥምቀት አንዱ ነው፡፡ የጥምቀት ክብረ በዓል የዓለም ሕዝብ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል፡፡ ይሕን ጥንታዊና ሐዋርያዊ የማይዳሰስ መንፈሳዊ ሀብት ለዓለም ሕዝብ ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በብሔራዊ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምታከብርባቸው ቦታዎች አንዱና ከቀዳሚዎች መካከል የሆነው ጃን ሜዳ መሆኑ ዓለም ያወቀው ሐቅ ነው፡፡ ይሁንና በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንዲሉ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ስትጠቀምበትና ስታስተዳድረው የኖረችው የዚሕ ነባር ይዞታዋ የባለቤትነት ማረጋገጫ ከእውቅናዋ ውጪ  እና ከፈቃዷ ውጪ  ካርታ ተቆርጦ ለሌላ አካል የተሰጠ  መሆኑ በምሬት የሚነሣና የሕዝበ ክርስቲያኑን ልብ የሚሰብር ሐቅ ነው፡፡ በመሆኑም ጃን ሜዳን በተመለከተ ለመንግሥት በተደጋጋሚ ካቀረብናቸው ጥያቄዎች የመጀመሪያው ጥያቄ የቤተ ክርስቲያን የባለቤትነት መብት ታውቆ  ጥንታዊ ይዞታዋ ለሆነው ጃን ሜዳ የተቆረጠው እና ለሌላ ተላልፎ የተሰጠው አብዛኛው የማክበሪያ ቦታ   ተመልሶ ፣መብቷ ተከብሮ   የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጣት የሚል ነው፡፡
ለዚሕ ፍትሐዊ ጥያቄያችን ሥምረትም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ለአፈጻጸም የሚረዱ ውይይቶችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በውይይታችን ወቅት በደረስንበት ስምምነት መሠረትም ያለ አግባብ ቦታውን በባለቤትነት ይዞ እንዲያስተዳድር የተደረገው መንግሥታዊ አካል የሆነው የስፖርት ኮሚሽን የመጠቀም መብት ብቻ ተረጋግጦለት የባለቤትነት መብትን አስቀድሞ ያለ አግባብ ለተነጠቀችው ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ እንዲመለስ ተጠይቋል።በመሆኑም  የቦታውን ታሪካዊ የይዞታ ባለመብትነትን ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ቅርሥ የሆነው የጥምቀት በዓል ማክበሪያነትን ከግምት ውስጥ በመክተት ቤተ ክርስቲያን ባለቤት መሆኗን የሚያረጋግጥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መስጠት ቀጣዩ የመንግሥት ተግባራዊ እርምጃ እንዲሆን እየጠየቅን ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡
የጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂ ኅብረት ከጃን ሜዳ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለመንግሥት ያቀረበው ሁለተኛው ጥያቄ የጃን ሜዳ ባሕረ ጥምቀት ምን መምሰል እንደሚገባው የሚገልጽ ነው፡፡ ሚሊዮኖች ተገኝተው የሚከብሩት ዓለም አቀፋዊ የሆነው በዓለ ጥምቀት የሚከበርበት ጃን ሜዳ ለበዓሉ መንፈሳዊ ክብር፣ ለምእመናንና ምእመናት ደኅንነት፣ ለጎብኝዎች ምቾትና ደኅንነት በሚመጥን ደረጃ የተዘጋጀ ባሕረ ጥምቀት እንዳይደለ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ በመሆኑም “ባሕረ ጥምቀቱ ምን ገጽታ ሊኖረው ይገባል?” የሚል ምክክር በማድረግና ሙያተኞች ሐሳባቸውንና ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበት የቴክኒክ ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል፤ ቴክኒክ ቡድኑም የጥንታዊቷንና ሐዋርያዊቷን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ትውፊትና አስተምህሮ የጠበቀ ንድፍ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡
እንግዲህ ዛሬ የተጀመረው ገበያውን የማንሣትና ቦታውን አጽድቶ ለክብረ በዓሉ የማዘጋጀት ጉዳይ ከላይ ያነሣናቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች ቅጥያ መሆኑን መላው ሕዝበ ክርስቲያን ዐውቆ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎቻችንም በአግባቡ መልስ እንዲያገኙ ከጎናችን እንዲቆም በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
Filed in: Amharic