>
5:13 pm - Tuesday April 19, 5425

እኒህ ጉምቱ ሰዎችስ ለምን አማራውን አይጠሉትም...?!? (ጌታቸው ሽፈራው)

እኒህ ጉምቱ ሰዎችስ ለምን አማራውን አይጠሉትም…?!?

ጌታቸው ሽፈራው

 አልፎ አልፎ ዶ/ር አሰፋ የሚባሉ ባለሙያ ጋር ደውዬ እማራለሁ። እሳቸው ጋር ሳወራ ፌስቡክ ያስጠላኛል። ከ2004 ዓ/ም ጀምሬ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስት፣ አረንጓዴ ልማት…ሕገ መንግስታዊነት የሚባሉ የኢህአዴግ ድሪቶዎችን ሀሰት ስለመሆናቸው የፃፍኳቸው ነበሩ። ስለ ትህነግ ፋሽዝምም፣ ወንበዴ መንግስትነት እንዲሁ። ሰነድ አገላብጬ ከፃፍኳቸው ይልቅ ዶክተር አሰፋ በድንገት ጠይቄያቸው የሚነግሩኝ እጅግ ያስገርመኛል። በቅርቡ ብቅ ብቅ እያሉ ስላሉት የሶማሊና የአፋር ልሂቃን አንዳንድ ጉዳይ እያወራን ነበር።  የኦባንግ ሜቶ ብዙ ያስመሰከረው ነው። ዶክተር ኮንቴ ስለአማራ ሕዝብ በደል በይፋ የተናገሩትን፣ ሙስጦፌም በተደጋጋሚ ስለ ፍትሕ የሚያወራውን ጠቅሼ  “እነዚህ ፖለቲከኞች ለምን አማራን ሌላው ፖለቲከኛ እንደሚጠላው አልጠሉትም?” ብዬ ጠየኳቸው!
“እየውልህ ጌታቸው!” አሉኝ። “እኔ ተወልጄ ያደኩት ሀረር ነው። የሶማሊን ሕዝብ አውቀዋለሁ። በራሱ የሚተማመን ሕዝብ ነው።  ሌላ ሕዝብን አይጠላም። አሁን አልፎ አልፎ የምናያቸው  ከዚህ ስነ ልቦና የተቀዱ ይሆናሉ። ይህን ስልህ ግን በራሱ የማይተማመን፣ በጥላቻ  የታወረ የለም ማለት አይደለም።” ብለው የእኛውን ሳይሆን የማዶውን ሶማሊ ልሂቅ ችግር አወሩኝ።  በምሳሌነት የጠቀሱልኝ ኢትዮጵያን የወረረውን ቆይቶን ሶማሊያን በታትኖ ለምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጠንቅ የሆነው ዚያድባሬን ነው።  “ዚያድባሬ የጣሊያን ተላላኪ ነበር። ከተማ ነው ያደገው። ከተማ ውስጥ ለጣሊያን ሲላላክ በበታችነት ስሜት፣ ሌላውን በመጥላት ነው ያደገው። አሁን አልፎ አልፎ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉትና በራሳቸው የሚተማመኑት የሶማሊ ወጣቶች ቅኝ ግዛት ምን እንደሆነ አያውቁትም።  በተለይ የኢትዮጵያው ሶማሊ ሕዝብ ይህን ተላላኪነት አያውቀውም። የበታችነት አይሰማቸውም። የአማራ ጥላቻውም ሆነ የበታችነቱ የመጣው ከቅኝ ግዛት ባሕል ነው። ከተላላኪነት ነው።” ብለው አስረዱኝ።
በእርግጥ ይህ የበታችነት ሞቃዲሾ ብቻ አልቀረም። አማራን የሚያወግዙት፣ ኢትዮጵያን የሚጠሉት አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች የበታችነት የሚያሰቃያቸው፣ ጥላቻ የሚያናውዛቸው ከቅኝ ግዛት በቀዱት አስተሳሰብ ነው።  ለቅኝ ገዥዎች ሲላላኩ እነሱን እያመለኩ ነው። ቅኝ ገዥዎቹ የነገሯቸውን ይዘው ቅኝ ገዥዎች ሊያጠቃው የመጣውን ሕዝብ እየጠሉ ነው የፖለቲካ ትርክቱን ያስፋፉት። ቅኝ ገዥዎቹ ደግሞ ስለ አማራ “ገዥቷችኋል፣ ቀጥቅጧችኋል” እያሉ የበታች አድርጓቸው እንደኖረ ነው የነገሯቸው። ጣሊያን ሲመጣ የመጀመርያ ስራው አማራውን በሌላው ማስጠላት ነበር። በአማራ ላይ የሀሰት ትርክትን በስፋት የጀመረው ጣሊያን ነው። በመጀመርያው ወረራ ተሸንፎ ቢመለስም የኢትዮጵያን ሕዝብ ስሪትና አንጓ ለይቶ ሁለተኛ ጦርነት እስኪከፍትም በርካታ ሀሰቶችን አባዝቶ ለአሁኑ የኦነግና ትህነግ አይነት ክፉ አስተሳሰብ ለማስረፅ ብዙ ጥረት አድርጓል። የትህነግና የኦነግ ብሔርተኞች ማጣቀሻዎቻቸው የቅኝ ገዥዎቹ ፀረ አማራ፣ ፀረ ኢትዮጵያ ሰነዶች ናቸው። መሰረታቸው ቅኝ ገዥዎቹ ኢትዮጵያን ለመምታት ያራቧቸው የሀሰት ትርክቶች ናቸው። ቅኝ ገዥዎቹ ደግሞ እንደ አማራ ሕዝብ ኢላማ ያደረጉት አልነበረም። ቅኝ ገዥዎቹ ሲመለሱ ያን ክፉ ውርስ የዛሬዎቹ ተገንጣዮች ደርተውታል።ትህነግና ኦነግ ደግሞ ለብዙዎች አስታጥቀውታል።
ሕዝቡ ላይ አይሁን እንጅ የሶማሊም ሆነ አፋር ልሂቃን ላይ ይህ  አባዜ የለም ማለት አይደለም። ለአብነት ያህል ኦብነግ የዚህ ትርክት ተጠቂ ነው። ከዚያድባሬም፣ ከትህነግም፣ ከኦነግም ጋር አብሮ የኖረ ኃይል ነው። አፋርም ላይ መሰል ጉዳዮች ይኖራሉ። ግን ሕዝቡ ላይ አይደለም። የተወሰኑ ልሂቃን ላይ ነው። አሁን ብቅ ብቅ እያሉ ያሉት መካከል ደግሞ ይህ ክፉ በሽታ የለም። አማራን አይጠሉትም። የሚጠሉ የነበሩት ሳይቀሩ ከትህነግ ይልቅ የሕዝባቸውን ልዕልና እያዩ አደብ የገዙ ይኖራሉ። ያኔ በቅኝ ግዛት ዘመን ከክፉዎቹ ወራሪዎች የጥላቻውን አስተሳሰብ ስላልተጋቱ ነው። አብዛኛው ሕዝባቸው በከተማ አይኖርም። ከብት እያረባም፣ እያረሰም ከከተማ ራቅ ብሎ፣ የቅኝ ገዥ ዳረጎት እየተቀበለና እየተላላከ አልኖረም። የበታችነት ስሜትም፣ ጥላቻም የሌላቸው በዚህ ምክንያት ነው። በራሱ የሚተማመን ሌላውን አይጠላም።
ኦሮሚያና ትግራይን ጨምሮ ፀረ አማራነቱ በእጅጉ ተሰርቶበታል። ይህ ሕዝቡ ተላላኪ ስለነበር የመጣ  ችግር አይደለም። በርካታ ልሂቃኖች የቅኝ ገዥዎቹ ዳውላ ሆነው ሕዝብ ላይ ክፉ አስተሳሰብ እንዲጫን ስላደረጉ ነው። አማራንም ኢትዮጵያንም የሚያዩበት ፋሽስት ዳግመኛ ለመግዛት ያዘጋጀውን የሀሰት መረጃ ጦር በብዛት ስላከፋፈሉት ነው። ይህ ክፉ የቅኝ ግዛት ትርክት አማራን ብቻ አይጠላም። አማራን የሚጠላው ኢትዮጵያን ለማፍረስና ሕዝብን ለመቆጣጠር ነው። አሁንም ድረስ ፀረ ኢትዮጵያው አሜካላ የፋሽስት ምርጥ ዘር የሀሰት ትርክት ነው።  የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲስተካከል ካስፈለገ የትህነግና ኦነግ ብሔርተኞችና አጃቢዎቻቸው ከቅኝ ግዛቱ የሀሰት ትርክት መላቀቅ አለባቸው። ብቅ ብቅ እያሉ እንደሚገኙት የሶማሊና የአፋር ፖለቲከኞች በራሳቸው መተማመን አለባቸው። ጥላቻቸውን ማስወገድ አለባቸው። ብቅ ብቅ እያሉ እንደምናያቸው አንዳንድ የአፋርና የሶማሊ ልሂቃን በራሳቸው የሚተማመኑ እንጅ በበታችነት ስሜት አማራንም ኢትዮጵያንም የማይጠሉ ቢሆኑ ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ በሽታ ትታከማለች። አማራንም፣ ኢትዮጵያንም አይጠሉም ያልናቸው ልሂቃንም ነገ የማይታፈርባቸው እንዳይሆኑ በዚሁ አቋማቸው ቢቀጥሉ ለብዙዎቹ አርዓያ መሆን ይችላሉ።
የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አይጠቅምም። አማራንም ኢትዮጵያንም የሚጠላው፣ የበታችነት ስሜት የሚያናውዘው የቅኝ ግዛት የሀሰት ትርክትን ድሪቶ ለብሶ የቀረው ነው። ይህ ድሪቱ ሲወልቅ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያስቸገረው ተባይ ይራገፋል።
እስካሁን  ጠልታችሁ አላሳፈራችሁንም።  የቅኝ ግዛት አባዜን ከማያውቀው ሕዝብ እንጅ ከተገንጣዮቹ ስላልተዋሳችሁ አመስግነናል። ብትሳሳቱ ደግሞ ሕዝብ እንደአመጣጡ መተቸት ይጀምራል።
Filed in: Amharic